ታላቁ ሩጫ የታላቋ ኢትዮጵያ መገለጫ!

ኢትዮጵያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በትውልድ ቅብብሎሽ በምታፈራቸው ከዋክብት አትሌቶቿ አማካኝነት ዓለም ‹‹የሯጮች ምድር›› ብሎ የክብር ካባ ደርቦላታል፡፡ ይሁን እንጂ አትሌቶቿ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ መድረኮች የነገሡትን ያህል ትልልቅ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በሯጮቹ ምድር ለማስተናገድ ሳትታደል ቆይታለች፡፡

ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በሁሉም ረገድ እያደገ የመጣው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዐይነ ግቡ ሆኖ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን ማግኘቱን ቀጥላል፡፡ በቅርቡም ለጎዳና ላይ ውድድሮች እውቅናና ደረጃ የሚሰጠው የዓለም አትሌቲክስ ‹‹ሌብል›› በሚል ስያሜ ደረጃ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ውድድር አድርጎታል፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጎዳና 10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መካሄድ ከጀመረ እነሆ 24 ዓመታትን አስቆጥሯል:: በእነዚህ ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተሳታፊዎች በማፍራት ከትልልቅ ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ተርታ መሰለፍም ችሏል፡፡ ውድድሩ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ ከውድድር ባሻገር በርካታ በጎ ምግባሮችን በማድረግ ለበርካታ ወገኖች አለኝታነቱን አሳይቷል:: ፖሊዮን ጨርሰን እናጥፋ የሕፃናት ሩጫ እና ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በችግር ውስጥ ያሉ በርካታ ሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ አድርጓል። ዛሬ ለ24ኛ ጊዜ ሲካሄድም ‹‹የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ሕጻናት›› በሚል መሪ ሃሳብ ሌላ በጎ ዓላማ ሰንቆ ነው፡፡ 50 ሺ ሰው ሲያሳትፍም የሉሲ (ድንቅነሽ)ን ሃምሳኛ ዓመት በማሰብና ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለዓለም ለማሳየት ጭምር ነው፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በአፍሪካ ከሚካሄዱ የጎዳና ውድድሮች ሁሉ ቀዳሚና ትልቅ መድረክ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ማስጠራት የቻሉ ኮከቦችን በማፍራት ተጠቃሽ ነው። ዛሬ ላይ በተሳታፊ ቁጥርና በዓለም ከሚገኙት ታላላቅ የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ ነው።

ዘመናትን ለተሻገረው የኢትዮጵያና አትሌቲክስ ጠንካራ ትስስር ታላቁ ሩጫ ያስመዘገበው ስኬት በቂ ባይባልም በዚህ ስኬቱ ማግስት ለኢትዮጵያ ስፖርት ቱሪዝም ፈር ቀዳጅ ሆኖ ለመቀጠልና ይበልጥ ለመጠናከር ትልቅ አቅም የሚሆን ነው፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሁን ላይ በርካታ ሺህ ኢትዮጵያውያን የሚናፍቁት፣ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት ዓመቱን ጠብቀው በመምጣት በኅብረ ቀለማት ያሸበረቀው ውድድር አካል ለመሆን የሚመኙት ሆኗል፡፡ ትልቅ ስም ካላቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንስቶ የረጅም ርቀት ውድድሮች ከዋክብት የሆኑ የዩጋንዳ እና ኬንያ አትሌቶች የዚህ ታላቅ ውድድር ተፎካካሪ መሆናቸውም እየተለመደ መጥቷል። ይህን አጠናክሮ ማስቀጠልና በዓለም አትሌቲክስ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጪ ሀገር ተሳታፊዎችና ጎብኚዎችን እየሳበ ይገኛል፡፡ እንግሊዝ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሙያተኞች ኤኤአ 2015 ላይ ያደረጉት ጥናት በታላቁ ሩጫ ለመሳተፍ የመጡ የውጪ ዜጎች ቁጥር ሰባት መቶ ነበር፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚያስረዳው ከሆነ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሁለት ሚሊዮን ዶላር ያህል አውጥተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁ ተጠቃሚ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔ ታ ጨምራል፡፡

እንደ ታላቁ ሩጫ አይነት የጎዳና ላይ ውድድሮች ከስፖርታዊ ኩነት ባለፈ መልከ ብዙ ፋይዳዎች እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ይህን ፋይዳ ቀድመው የተገነዘቡና ጠንክረው የሠሩ በርካታ ሀገራት ከቱሪዝምና ከጤና ጋር በተያያዘ ብዙ በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርን የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ በኩል ያለውን አበርክቶ ከፍ ከማድረግ በዘለለ በስፖርት ቱሪዝም የበለጠ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ከምንም በላይ ታላቁ ሩጫ ጎሣና ቀለም፣ ፆታና ዕድሜ ሳይለይ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ የሚያሰባስብ ሠላምና ፍቅር ጎልቶ የሚታይበት የኢትዮጵያን መገለጫ መድረክ ነውና ከፍ ልናደርገው ይገባል!

አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You