የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ በግጭት አዙሪት ውስጥ አልፈዋል። አሁንም ከዚህ ችግር ሙሉ ለሙሉ አልተላቀቁም፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ያላቸውን ከማጣት እና ሕዝቦቻቸውን ለከፋ ችግር እና መከራ ከመዳረግ ያለፈ ያተረፉት አንዳች ነገር የለም። በድህነታቸው ላይ ድህነትን ፣ በኋላ ቀርነታቸው ላይ ኋላ ቀርነት በመጨመር ትናንቶችን ናፋቂ አድርጓቸዋል።
የነበሩ የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦች የወለዷቸው የመለያየት ዝማሬዎች፤ አምባገነን መሪዎች የፈጠሯቸው የመስፋፋት እሳቤዎች፤ አካባቢው ካለው ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አኳያ ስትራቴጂክ ጥቅም አለኝ የሚሉ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት … ወዘተ በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንዳይሰፍን ፈተና ሆኖ ቆይቷል።
በተለይም በየወቅቱ ወደ ስልጣን የሚመጡ የአካባቢው ሀገራት መንግሥታት የቀጣናውን ሕዝቦች የሰላም እና የልማት ፍላጎት ተረድተው፤ ለዚህ የሚሆን አካባቢዊ የትብብር ህብረት ፈጥረው ከመንቀሳቀስ ይልቅ፤ ከትናንት የተዛቡ ትርክቶች በመነሳት ልዩነቶችን አስፍቶ ወደ ግጭት የሚወስዱ መንገዶችን ሲከተሉ ቆይተዋል።
በዚህም አካባቢው ለረጅም ዓመታት ሰላም አጥቶ ቆይቷል፤ ከዚህም በከፋ መልኩ ዓለም አቀፍ የሽብርተኛ ቡድኖች እና ጽንፈኛ ኃይሎች መናኸሪያ ሆኗል። ችግሩ ከአካባቢው ሀገራት አልፎ ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነበትም ሁኔታ ተፈጥሯል። ስጋቱን ለመቀልበስ የተደረጉ ጥረቶችም ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል።
በርግጥ የአካባቢው ሀገራት ካላቸው የተፈጥሮ ጸጋ እና ታሪካዊ የወንድማማችነት ጉርብትና አኳያ፤ ፍትሐዊ ለሆነ ተጠቃሚነት፣ አቅሞቻቸውን በጋራ አልምተው፤ ተጽእኖ ፈጣሪ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ አቅም ሆነው የሚወጡበት ዕድል ከፍ ያለ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።
በተለይም የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ጥሎት የሄደውን ፣ የመለያየት ትርክት እና ትርክቱ የፈጠረውን አለመተማመን በማስወገድ ፣ በአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች መካከል የነበረውን እና ያለውን ወንድማማችነት በማደስ ፣ አካባቢውን የተሻለ የልማት ኮሪደር ማድረግ ይቻላል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ላይ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ሰላምን በመፍጠር ቀጣይነት ያለው አካባቢያዊ ልማት ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረትም ይህንኑ እውነታ ታሳቢ ያደረገና ለአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የሰላም እና የልማት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አዲስ የትብብር ምዕራፍ ነው።
በሕዝቦች መካከል አለመተማመንን በማስወገድ ፍትሐዊ እና ዘላቂ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ጉርብትና መፍጠር የሚያስችል፣ከሴራ እና ከመደነቃቀፍ ወጥቶ ፣በበጎ ህሊና ወደ መደጋገፍ፣ አብሮ ቆሞ ወደ መራመድ የሚወስድ ዘመኑን የሚዋጅ ፣ ከትናንት የሚያሻግር አስተሳሰብን መሰረት ያደረገም ነው።
ይህንን መልካም/ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ ተረድቶ ፤ ለአካባቢው ሕዝቦች የጋራ እጣ ፈንታ አብሮ ከመጓዝ ይልቅ፤ ማንንም አትራፊ ሊያደርጉ በማይችሉ የትናንት የጥፋት እሳቤዎች መነዳት የታሪክ ተጠያቂነትን ከማስከተል ባለፈ፤ በአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የሰላም እና የልማት ፍላጎት በተቃርኖ መቆም ነው።
ዓለም ለትብብር እና ፍትሐዊ ለሆነ የጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ ዋጋ ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ባለበት በዚህ ዘመን፤ የሀገር እና የሕዝብ ውክልና ይዞ የራስን የፖለቲካ ፍላጎት እና ፍላጎቱ የወለደውን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጥረት ሀገር እና ሕዝብን በአደባባይ መካድ ሲሆን ትልቅ ጸጸትን የሚያስከትልም ነው።
ከዚህ አኳያ በቀጣናው ያሉ ሀገራት መንግሥታት አካባቢውን ከግጭት አዙሪት በመታደግ ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት በማስፈን፤ የሀገራቱን ሕዝቦች የሰላም እና የልማት ጥያቄ ለመመለስ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የተጀመረውን መነሳሳት በአግባቡ ተረድተው ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም