‹‹አስራት፣ስጦታውና ጓደኞቹ ሽርክና›› በማእድን ልማት የተሰማራ አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።በአማራ ክልል ወገልጤና ወረዳ በማዕድን ልማት በማህበር ተደራጅተው በሥራ ላይ ከሚገኙት ማህበራት መካከል አንዱ ነው፤ የተመሰረተው በ1999ዓ.ም ነው፡፡
አባላቱ ወደ ልማቱ ሲገቡ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናው የተሰጠን በማዕድን ቁፋሮ ወቅት በሰው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እንድናደርግ፣ ግብይቱን በደረሰኝ እንድናከናውን፣ አምራቹ ወይንም አልሚው የቁጠባ ባህል እንዲያዳብርና ኑሮውን እንዲያሻሽል፣ የአካባቢው ሀብት ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር በሚል መሰጠቱን የሽርክናው አባል አቶ አስራት ሲሳይ ይናገራሉ፡፡
አቶ አስራት ስልጠናው ግን መረጃ ከመስጠት ባለፈ ጠንከር ያለ የሙያ ክህሎት የሚያስጨብጥ አልነበረም ሲሉ ይጠቁማሉ።ስልጠናው መረጃ ከመስጠት ባለፈ የሙያ ክህሎትን የሚያስጨብጥ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ።
ከአምራቹ ይልቅ ጥሬ ዕቃውን ከአምራቹ ገዝተው እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡት በተሻለ ስልጠና እንደሚያገኙ የሚናገሩት አቶ አስራት፣ በእርሳቸው እምነት ግን እንደየሥራ ድርሻቸው ሁለቱም አካላት በስልጠና ክህሎት መብቃት አለባቸው።እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡት አካላት ጥሩ ሊሰሩ የሚችሉት አምራቹ ምርቱን በጥራት ሊያቀርብላቸው ሲችሉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከመሬት ቆፍሮ ማዕድን በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማራው ወይንም አምራቹ የተለያየ ስልጠና እና የመስሪያ መሳሪያ ድጋፍ ያስፈልገዋል ሲሉ ያመለክታሉ።
እንደ አቶ አስራት ማብራሪያ፤ በቁፋሮ ወቅት ማዕድኑ በጥንቃቄ ከመሬት ውስጥ ካልወጣ ለምርት መቀነስና ለጥራት መቀነስ ምክንያት ይሆናል።ገበያ ላይም የሚፈለገውን ያህል ገቢ ለማግኘት ተጽእኖ ያሳድራል።በመሆኑም በክህሎት እንዲሰራ አምራቹን ማብቃት ያስፈልጋል፡፡
ለልማቱ ሥራ የሚያስፈልጉ እንደ አፈር ማስወገጃ፣ ባትሪና ማቀዝቀዣ የመሳሰሉት ደግሞ በድጋፍ ቢሟሉ የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻላል።መንግሥት የሥራ መሳሪያዎችን ገዝቶ ማቅረብ ባይችል እንኳ በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርቦት እንዲኖር ቢያደርግ አንድ ድጋፍ ነው ይላሉ። ማህበሩ ለሚመለከተው አካል በተለይም ማህበሩ ለሚገኝበት ወገልጤና ወረዳ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘቱንም ይናገራሉ።አምራቹ ለቁፋሮ ሥራ እየተጠቀመባቸው ካሉ መሳሪያዎች አንዱ ዶማ ሲሆን፣ ይህንንም ከነጋዴ አራት መቶ ብርና ከዚያ በላይ በሆነ ዋጋ ነው የሚገዙት።አንካሳ የተባለው የአፈር መዛቂያ መሳሪያም አምስት መቶ ብርና ከዚያ በላይ በሆነ ዋጋ ነው የሚገዛው፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአይን ላይ ጉዳት እንዳይደርስም መከላከያ መነጽር ያስፈልጋል።ጉድጓዱ ጥልቀት ሲኖረው ብርሃን ስለሚያስፈልግ ባትሪ ይጠቀማሉ።የአንድ የባትሪ ድንጋይ ዋጋ እስከ ስምንት ብር በመድረሱ ወጭው ከፍተኛ ሆኖባቸዋል።ወጭውን ለመቀነስ በቻርጅ የሚሰራ ባትሪ ያስፈልጋል።ማዕድኑ እስኪገኝ ረዘም ያለ ኪሎ ሜትር ድረስ መቆፈርን ይጠይቃል፤ በዚህ ወቅት ሙቀት ይጨምራል።ሙቀቱ ደግሞ ለራስ ምታትና ለተለያየ የጤና ችግር ስለሚያጋልጥ ማቀዝቀዣ መሳሪያ ያስፈልጋል።ይሄን መሳሪያ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በአካባቢው አምራችም ሆነ በማህበራቸው እውቀቱ ስለሌለ እየተጠቀሙ አይደለም።በሙቀቱ መታፈን ስለሚያጋጥማና ለአደጋም ስለሚያጋልጥ የግብአቱ አቅርቦት አስፈላጊ ነው፡፡
የማዕድን መቁረጫ መሳሪያም እንዲሁ እስከ አምስት ሺ ብር ዋጋ የሚያወጣ በመሆኑ ወጭው አቅምን ይፈትናል።አሁን ባለው የማዕድን ልማት አምራቹ በልማድ ነው እየሰራ የሚገኘው።በቁፋሮ ወቅት ጥንቃቄ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም ከጉዳት የሚታደገው አይነት አይደለም።የተለየ አልባሳትም አይጠቀምም፡፡
ለማዕድን ልማቱ በሚያስፈልጉ እነዚህን መሳሪያዎች በመጠቀም ረዘም ላለ ጊዜ የሰሩ እንደመሆናቸው ለአቶ አስራት ጥያቄ አቅርበንላቸው በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ የማዕድን ቁፋሮ ሥራው በሰአትና በቀን አይገደብም።በለስ ከቀናው ጥልቀት ያለው ጉድጓድና ረዘም ያለ ኪሎ ሜትር መቆፈር ሳይስፈልገው ማዕድኑን ሊያገኝ ይችላል።አንዳንዴ ደግሞ ሶስት ቀናትና ከዚያ በላይም ጊዜ ሊወስድ ይችላል።ይሄን ያህል ጊዜ ወስዶም የማይገኝበት አጋጣሚ ይፈጠራል። መወሰን አይቻልም፡፡
የዚህ አንዱ ክፍተት የማዕድን ቁፋሮው የሚካሄደው በጥናት ተለይቶ አለመሆኑ ላይ ነው፤ ቁፋሮው ሳይንሳዊ አይደለም፤ አልሚው በተለምዶ ማእድኑ ይገኝበታል ብሎ በሚገምተው አካባቢ የሚከናወን በመሆኑ ነው።ከልማዳዊ አሰራር በወጣ ልማቱ እንዲከናወን ከክልሉ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በ2012ዓ.ም ላይ ቢወያዩም ለውጥ አልተገኘም ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ፍለጋው በሳይንስ የተደገፈ ቢሆን የሚገኘው ማዕድን ቀድሞ ስለሚታወቅ በዶማ ተከስክሶ መጠኑ ሳያንስና ጥራቱ ሳይጓደል ከመሬት ማውጣት ይቻል ነበር።ይህ ባለመሆኑ በተለመደው አሰራር ማዕድን አምራቹ በልምድ ከሚያውቀው በመነሳት ማዕድኑ የሚገኝበትን ቦታ በማመላከት ፈቃድ ሲያገኙ ነው ቦታው ተከልሎ ሲሰጣቸው ልማቱን የሚያከናውኑት። የማዕድን ልማቱ በክህሎትና በሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ቢታገዝ የአምራቹን ድካም ይቀንሳል። በመላ በመቆፈር የሚባክነውን ማዕድን መታደግ ይቻላል፡፡
በልማቱ በቆዩባቸው ጊዜያት በአደጋም ሆነ በመልካም ጎን የሚያነሱት ካለ? እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ማዕድን አግኝተው የተደሰቱበትን አጋጣሚ እንዲያስታውሱኝ ላቀረብኩላቸው ጥያቄም በምላሻቸው በቁፋሮ ወቅት ናዳ አጋጥሞ የተጎዱ አምራቾች እንዳሉ ገለጹልኝ።በተለያየ ተግዳሮት ውስጥ ሆነው ልማቱን ቢያከናውኑም የልፋታቸውን ያህል ጥቅም ባያገኙም አንድ ወቅት ላይ በአንድ ጊዜ ቁፋሮ እስከ 80 ግራም አግኝተው መጥረብና ሌላም ተጨማሪ ሥራ ሳያስፈልገው አንድ መቶሺ ብር ሸጠው የተጠቀሙበትን ጊዜ እንደማይዘነጉት ነገሩኝ፡፡
እነ አቶ አስራት በተረፈ ግን እንደ ማዕድኑ አይነት በግራም ከአንድ ሺ አምስት መቶ ብር አንስቶ ያገኛሉ።በቁፋሮ ወቅት በዶማ እየተፈረካከሰ ልፋታቸውን ከንቱ እያደረገባቸው የሚያዝኑበት ጊዜ የበዛ እንደሆነም አስታውሰዋል።የማዕድን ልማቱ ኑሮአቸውን ስለሚደጉምላቸው ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥም ሆነው እየሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ 190 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ከልማቱ የሚያገኙት ትርፍም ለአባላቱ ይከፋፈላል ያሉት አቶ አስራት፣ ኑሮውን የመለወጥ ጥረት እንደ ግለሰቡ የሚወሰን መሆኑን ሁሉንም ወክሎ መናገር እንደማይቻል ይናገራሉ።እሳቸው በግላቸው ግን ከተማ ውስጥ መኖሪያ ቤት ገንብተዋል።
አቶ አስራት እንደሚሉት፤ ግብይቱ ላይም ሀሳባቸውን ሰጥተውናል። ግብይቱን ከህገወጥ ተግባር ለመከላከል የመቆጣጠሪያ ኬላ ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ የተደራጀ ነገር ባለመኖሩ ህገ ወጥነትን መከላከል ተችሏል የሚል እምነት የላቸውም።ሀብቱ በደላላ እጅ ላይ ወድቋል። ደላላው ሳይደክም ሀብት እያካበተ መሆኑን በአይናችን እያየን ነው ይላሉ። በተለይም ደላንታ ወረዳ ላይ በስፋት እየተመረተ ያለው የኦፓል ማዕድን ሀብት በዚህ መልኩ መመዝበሩን ይገልጻሉ።
ትግራይ ክልል ላይ ኬላ በመቋቋሙ በክልሉ የሚለማው የሳፋየር ማዕድን ሀብት ለህገወጥ ገበያ የተጋለጠ እንዳልነበርም አስታውሰዋል።ይህም ሁኔታ በቁጥጥርና ክትትል ግብይቱ በሚከናወንበት የኦፓል ማዕድን ሀብትና ሳፋየር ማዕድን ሀብት መካከል የዋጋ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ሲሉ ያብራራሉ።
የሳፋየር ማዕድን በውድ ዋጋ ነው ለገበያ የሚቀርበው። ኦፓል ደግሞ ዋጋው ይቀንሳል።የማምረት ሥራው እኩል ልፋትና ድካም እየጠየቀ ነገር ግን በቁጥጥርና ክትትል ማነስ ምክንያት አምራቹ እኩል ተጠቃሚ መሆን አልቻለም ይላሉ አስራት።
ከፌዴራልና ከክልል የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተለያየ ጊዜ መድረኮች ሲዘጋጁ ክትትልና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ህገወጥነትን የመከላከል ሥራ መስራት እንዳለበት መጠቆሙንም አስታውሰዋል።እልባት ሳያገኝ አካባቢው የጦርነት ቀጣና ውስጥ መግባቱን ይገልጻሉ።የጦርነቱ መከሰት ደግሞ ጥያቄው ምላሽ ሳያገኝ እንዲዘገይ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን ጽህፈት ቤት የማዕድን ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ጀማል እንድሪስን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ እስካሁን ባለው ተሞክሮ ስልጠና የሚመቻቸው እሴት ጨምረው ለገበያ ለሚያቀርቡ ነው።እሴት ጨምረው ለገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኙት በዘርፉ የሰለጠኑና ምሩቅ ቢሆኑ ይመረጣል።በሥራቸው የሚይዟቸው ሙያተኞችም ስለሚኖሩ ተጨማሪ የሙያ ስልጠና ድጋፍ ቢደረግላቸው የበለጠ ውጤታማ ያደርጋቸዋል። ማዕድኑን በተለያየ ዘዴ በማስጌጥ ገበያን እንዲስብ የሚያስፈልግ በመሆኑ ክህሎታቸውን ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡
ከዚህ አንጻር ማዕድኑን ከመሬት ለማውጣት የተለየ ክህሎት ያስፈልጋል ተብሎ አይታሰብም።እስካሁን ባለው አሰራር የማዕድን አምራቾች በእነርሱ እውቀት ላይ ተመስርተው ነው እየሰሩ የሚገኙት።ስራው ክህሎት የሚጠይቅ አይደለም በሚል እምነት በተደራጀ ሁኔታ ለአምራቾች ስልጠና የሚውል በጀት ተመድቦም ሆነ በዕቅድ ተይዞ አልተሰራበትም።እሴት ጨምረው ለሚሰሩትም ቢሆን በበጀት እጥረትና በተለያየ ምክንያት በሚፈለገው ልክ ስልጠናውን እንዲያገኙ እየተደረገ እንዳልሆነ አቶ ጀማል ተናግረዋል፡፡
አምራቾቹ በስልጠና ባይታገዙ እንኳን በመላምት ማዕድኑን ለማውጣት ጥረት ከሚያደርጉ ድካማቸውን ለመቀነስ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚታገዙበት ሁኔታ መመቻቸት የለበትም ወይ ለሚለው ጥያቄ አቶ ጀማል በሰጡት ምላሽ፤ ጽህፈት ቤቱ በአወቃቀርም ገና የተደራጀ ባለመሆኑ እንዲህ ያሉ አሰራሮችን ለማስተካከል አልተቻለም።ለቁፋሮ ሥራ የሚውሉ የሥራ መሳሪያዎችና አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች የሚቀርቡበትን ሁኔታ ለማስተሳሰር እንኳን አልተቻለም ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር የጀመረው ድጎማ ነበር፡፡በአጥጋቢ ሁኔታ ሳይከናወን ተቋርጧል።የክልሉ መንግሥትም በአቅም ውስኑነት ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም። አምራቾቹ በራሳቸው አቅም በግዥ ነው እየተጠቀሙ የሚገኙት። ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታም ለዘርፉ ትኩረት እንዳይሰጥ ምክንያት መሆኑን አቶ ጀማል ይጠቁማሉ፡፡ከችግሩ በፊትም ቢሆን ዘርፉ ትኩረት አግኝቷል የሚል እምነት የላቸውም፡፡
በባህላዊ መንገድም ቢሆን የተሻለ ግንዛቤ ባላቸው እየተከናወነ እንዳልሆነና እየባከነ መሆኑን በተለያየ ጊዜ በሚከናወን የአፈፃፀም ግምገማ መድረኮች ላይ እንደሚነሳም አስታውሰዋል።በዚህ ረገድ ለቀጣይ አመትም ቢሆን በተለየ ሁኔታ የተቀመጠ ነገር አለመኖሩንም ነው ያመለከቱት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ምድር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጉ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ በማዕድን አልሚዎች ላይ የሚስተዋለው ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣በሌሎች ሀገሮች ላይም ያጋጥማል። በማዕድን ቁፋሮ ወይንም ልማት ሥራ ላይ ሥራዎቹ መለየት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ እንደወርቅ ማዕድኖች ላይ በመካከለኛና በትላልቅ ኩባንያዎች በዘመናዊ መሳሪያ ታግዘው የሚሰሩት በጥናትና ምርምር መደገፍ ይኖርባቸዋል።
የተቀሩት በባህላዊ መንገድ የሚከናወኑትን ከፍተኛ በጀት መድቦ ስልጠና በመስጠት እንዲሰሩ ለማድረግ አቅም ላይኖር ይችላል። ደግሞም የሚገኘው የሀብት መጠንና የሚደረገው ድጋፍ ካልተመጣጠነ ጉዳቱ ያመዝናል። ባህላዊው የአመራረት ዘዴ ከነስሙም የጉልበት ሥራ ነው የሚባለው። ማዕድኑ ሲገኝ ይገኛል፤ ሳይገኝም እንደገና ይሞከራል። ለዚህም ነው ከፍተኛ ክህሎት አያስፈልጋቸውም የሚባለው ሲሉ ያብራራሉ።
ስራው በአደረጃጀት፣በተከታታይ ክትትልና ድጋፍ መታገዝ እንዳለበትም ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ያስገነዝባሉ። ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንዲቻል ጥሩ የሆነ ፖሊሲ መቅረጽ ይጠበቃል።በዚህ ላይ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችም ስለሚኖሩ ከነዚህ ተቋማት ጋር መስራት ያስፈልጋል። ግንዛቤም እንዲኖራቸው ቢደረግ አምራቾቹ ሥራቸው ልፋት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ያግዛቸዋል። ባህላዊ የማዕድን አምራቾች በማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ መንግሥት እያከናወነ ያለው ተግባርም ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ያብራራሉ፡፡
በባህላዊ መንገድ የሚከናወን ማዕድን የማውጣት ሥራ በዘመናዊ መንገድ አቀላጥፎ ለመሥራት እንዲያስችልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩልም የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲሰሩ በማዕድን ሚኒስቴርና በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ መካከል የካቲት 25ቀን 2014ዓም የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለይም የማዕድን ሀብቱ በስፋት በሚገኝባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች)ጋር አብሮ ለመሥራት እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑ መገለጹም ይታወሳል። አላማው የትምህርት ተቋማቱ በማዕድን ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የትምህርት ክፍሎችን (ዲፓርትመንቶች) በመክፈት ሙያተኞችን እንዲያፈሩ ማስቻል፣በሌላ በኩል ደግሞ በጥናትና ምርምርም አበርክቶ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። በዚሁ መሠረት የትምህርት ተቋማቱ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር የሚሰሩበት ሥርአት ተዘርግቷል።በአሁኑ ጊዜም ቁጥራቸው ወደ 45 የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡
ለግንባታ የሚውለው ማርብል የተባለው ግብአት ላይ ስልጠና ለመስጠት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ማዕከል ለማቋቋምም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ከዚህ ቀደም ከሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች በባህላዊ መንገድ ማእድን የሚያመርቱ ወገኖች አቅም በማጎልበት ይበልጥ ምርታማ እንዲሆኑ አመራረታቸውም ለጉዳት የማይዳርጋቸው እንዲሆን ለማድረግ እንደመሆኑ በቀጣይ በዘርፉ ለውጥ እንደሚያሰገኙ ተስፋ ይደረጋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2022