“ደራርቱ ሀገር መሆኗን አሁን ያወቀ ሰው ዘግይቷል። ለዚያውም ድንቅ ሀገር ናት። ዝናዋ ሰማይ ነክቶ፣ስሟ ዓለምን በናኘ ጊዜ እንኳ ደራርቱ በትህትና መሬት የነካ ልብ ያላት አትሌት ነበረች።…ሀገር ማለት ሰፊ ልብ ያላት ዓመለ ሸጋውን ብቻ ሳይሆን፣ዓመለ ቢሱንም አቅፋና ደግፋ የምትይዝ ማለት ነው።
ደራርቱ፣ብሔርና ሃይማኖት ለይታ አትወድም፣ሰው መሆንህን አይታ እንጂ !..ታዲያስ ደራርቱን የምታህል መልካም ሀገር የተሸክመችው ኢትዮጵያስ እድለኛ አይደለች?…እሾሆችን የምትታገስ አበባ ስላለቻት?…ለካ “ደራርቱ”ማለት አበባ ነው?..”
ይህ ንግግር የተገኘው ከዝነኛዋ ተዋናይ አርቲስት ሀረገወይን አሰፋ የፌስቡክ ግድግዳ ነው፡፡ሀረገወይን ራስዋ ደግሞ የዚህ ንግግር ባለቤት ሌላኛው አንጋፋ አርቲስት ደረጄ በላይነህ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ የሆነ ሆኖ ሁለቱ አርቲስቶች ለደራርቱ ባላቸው እይታ ተስማምተዋልና ያሉትን ብለዋል፡፡
ይህ ሀሳብ ግን የሁለቱ ከያኒያን ብቻ አይደለም ፤ የብዙ ኢትዮጵያውያንም እንጂ፡፡ደራርቱ ግለሰብ ሆና ሀገር የሆነች ሴት መሆኗን ፤ ዝናዋ ትህትናዋን እንዳላሳጣት ፤ ስልጣንም ሰብአዊነቷን እንዳልሰወረባት በተደጋጋሚ ታይቷል፤ ዘንድሮ ደግሞ ሊከለል በማይችል ሁኔታ ፍንትው ብሎ ተገልጿል፡፡
የዘንድሮው ውድድር ኢትዮጵያ በአለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከፍተኛ የሚባለውን ውጤት ያስመዘገበችበት ውድድር ነበር፡፡ ለዚህ ስኬትም ብዙ ተጠቃሾች አሉ፡፡ ከነዚህ መሀከል ግን ዋነኛዋ ደራርቱ ናት፡፡ ምክንያቱም የደራርቱ እናታዊ አመራር በአሸናፊዎቹ ላይ የነበረው ተጽእኖ በግልጽ የሚታይ ስለነበር ነው፡፡
ሁሉም ድል ያስመዘገቡ አትሌቶች ከፈጣሪያቸው ፤ ከቤተሰቦቻቸው ፤ ከማኔጀሮቻቸው እና ከአሰልጣኞቻቸው በመቀጠል ዋና ምስጋና የሚያቀርቡት ለደራርቱ ነው፡፡ ምስጋናው የተለመደ አይደል ወይ ምን ያስደንቃል የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ነገር ግን አትሌቶቹ ያመሰገኑበት ምክንያትን ካየን የምስጋናውን ልዩነት እንረዳለን፡፡
ምስጋናው ደራርቱን እንደ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ወይም እንደ ባለስልጣን ከማየት የመጣ ሳይሆን ደራርቱን እንደ እናት ፤ እንደ እህት ፤ እንደ ቅርብ ጓደኛ ፤ እንደ አማካሪ ከማየት የሚመነጭ ነው፡፡እንደዚህ ሲሆን ደግሞ ይለያል፡፡
እኛ ሀገር ሰዎች ስልጣን ሲይዙ ሰውነታቸውን ይረሱታል፡፡አለቅነታቸው ይጫናቸዋል፡፡የተቀመጡበትን ወንበር ለመሙላት የሚያደርጉት ጥረት አምባገነን ያደርጋቸዋል፡፡ማንም የማይቀርባቸው አስፈሪ ፍጥረታት ይሆናሉ፡፡በዚህም የተነሳ የእነሱን ስኬት ከሚፈልገው ሰው ይልቅ ውድቀታቸውን የሚመኘው ይበልጣል፡፡ እንኳን እንደ ወዳጅ እንደ ሰው እንኳን የሚያያቸው እንኳ ይጠፋል፡፡
በዚህም የተነሳ የእነሱ ስብእና ውድቀት ለተቋማዊ ውድቀት መንስኤ ይሆናል፡፡ ደራርቱአዊነት የሚያስ ፈልገው እዚህ ጋር ነው፡፡ሰውነትን ቅድሚያ መስጠት ፤ እናታዊነት፤ እህታዊነት ፤ ጓደኛዊነትን ቅድሚያ መስጠት፡ ፡እናታዊ አቀራረብ የትኛውንም ሳይንሳዊ ስሌት ይረታል፡ ፡በሳይንሱ መሰረት ሊሸነፉ የሚችሉ አትሌቶች በደራርቱ እናታዊ አቀራረብ ግን ወደ አሸናፊነት መጥተዋል፡፡እንደ ኢትዮጵያ ላለች በብዙ ነገሮች ላይ የአቅም እጥረት ላለባት ሀገር ያለው አማራጭ የደራርቱ አካሄድ ነው፡፡
እኛ ለአትሌቶቻችን በጣም የተራቀቀ ሳይንሳዊ ስልጠና ፤ ሳይንሳዊ ትንተና ፤ ሳይንሳዊ አመጋገብ እና መሰል ነገሮች መስጠት አንችልም፡፡ ሳይንስን የሚልቅ እናታዊ እና አባታዊ ፍቅርን በመስጠት ግን የሰዎችን አቅም መገንባት እንችላለን፡፡ደራርቱ ያደረገችውም ይሄን ነው፡፡
በሌላ መልኩ ደራርቱ አጀንዳ ሳታደበላልቅ የምታስኬድበት መንገድም አስገራሚ ነው፡፡ይህ ውድድር የተካሄደው ሀገራችን ብዙ ችግር ውስጥ ገብታ እየዳከረች ባለችበት ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም ሰው የያዘው የሆነ አይነት የሀዘን ጓዝ አለ፡፡ አትሌቶችም የህዝቡ አካል ናቸውና ተመሳሳይ ስሜት እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው፡፡በተለይም ቤተሰቦቻቸው ትግራይ ውስጥ የሚገኙ አትሌቶችን በምን አይነት ስነ ልቡናዊ ተግዳሮት እና ፖለቲካዊ ጫና ውስጥ ሆነው እንደሚወዳደሩ ግልጽ ነው፡፡
የማንን ባንዲራ መያዝ እንዳለባቸው እና ካሸነፉ ምን ማለት እንዳለባቸው በተለያየ መልኩ ከተለያዩ ቡድኖች እንደሚነገራቸው ግልጽ ነው፡፡ታዲያ ደራርቱ እንዲህ አይነቱን የአጀንዳ መደበላለቅ ሳታስተናግድ እና ልጆቹንም አላስፈላጊ ጫና ውስጥ ሳትከት ወቅታዊ ስሜታቸው እንዳለ ሆኖ አጀንዳ ሳይደበላለቅ የጋራ በሆነው አጀንዳ ላይ እንዲበረቱ ማድረግ ችላለች፡፡
ይህ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው ግለሰባዊ መከፋት ቢኖርበት ያንን መከፋት ጭራሽ አባብሶ ያን ሰው ጽንፈኛ የሚያደርግ እንጂ አባብሎ እና አሳምኖ ወደ የጋራ ጥቅማችን የሚያመጣ አመራር ማግኘት ከባድ እየሆነ ነው፡፡ደራርቱ ግን በእናታዊ ባህሪዋ ሁሉን እንደ አመሉ ይዛ ፤ አንዳንዴ እያለቀሰች ፤ አንዳንዴ እየሳቀች ፤ አንዳንዴ እያቀፈች ፤ ሌላ ጊዜ ጫማ እየፈታች ለውጤት አብቅታለች፡፡
እንዲያውም አትሌቶቹን አባብሎ እና አስታምሞ እንዲከርሙ ከማድረግ ባለፈ ይህ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያስፈልገው በማሳመን ሁሉም የአቅሙን የመጨረሻ መጠን እንዲጠቀም ማድረግ ችላለች፡፡ይህ ደራርቱአዊ ውጤታማ መንገድ ነውና እንደ መልካም ተሞክሮ ሊቀመር እና ሊስፋፋ ይገባል፡፡
ሌላኛው አስገራሚ ነገር ደራርቱ ለስኬት የምታደርገው ያልተቆጠበ ጥረት እና ደስታዋን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የምትደስበት ሁኔታ አስገራሚ ነው፡፡በዚህ ውድድር ላይ እንዳየነው ደራርቱ ልጆቿን ለማበረታታት መሪ ሊያደርገው ከሚገባው በላይ አድርጋለች፡፡ የቆጠበችው ነገር የለም፡፡ያደረገችውን ያረገችው አደረገች ለመባል እና ከተጠያቂነት ለመዳን ሳይሆን ውጤቱ አስፈላጊ ነው ብላ ስላመነች ነው፡፡
ይሄ አንድ ትልቅ ነገር ነው፡፡በሌላ መልኩ ድሉ ሲገኝ የምትደሰትበት መንገድ እንደ መሪ ወይም እንደ አንድ አንጋፋ አትሌት ሳይሆን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ይህም ትልቅ ትምህርት ነው፡፡የህዝብን ስሜት ማወቅ እና መጋራት ሲቻል ነው ለህዝብ መድከም የሚቻለው፡፡መሪ ከህዝብ ለየት እና ከፍ ብሎ መታየት ያለበት በስትራቴጂያዊ አስተሳሰቡ እና በትህትናው እንጂ ከሰው ጋር ሆኖ ባለመደሰት አይደለም፡፡
ደራርቱ ግን በቴሌቪዥን ስናያት ከኛ መሀከል አንዷ ትመስል ስለነበር ደስታዋን ስንጋራ ፤ ደስታችንን ስትጋራ አብረን ከርመናል፡፡ አሁንም ቢሆን በደራርቱ ማንነት፣ የአትሌቲክስ ህይወት ፣ የአስተዳደር መንገድ እና መሰል ነገሮች ላይ መጽሀፍ ሊጻፍ ፣ ጥናት ሊጠና ፣ ተሞክሮ ሊቀመር እና ሊስፋፋ ይገባል፡፡እንደሚጠቅመን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም