የተወደዳችሁ የ”አዲስ ዘመን”ቤተሰቦችና አንባ ቢዎች ፤ በቅድሚያ አትሌቶቻችን በ18ኛው የኦሪገን የአለም ሻምፒዮን ባስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል እንኳን ደስ አላችሁ ! እንኳን ደስ አለን ! ማለት እፈልጋለሁ ። የምንጊዜም ጀግናችን፣ ብሔራዊ ምልክታችንና ኩራታችን አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ አትሌቶቻችን በአሜሪካ ኦሪገን ዩጅን በ18ኛው የአለም ሻምፒዮን የተቀዳጁትን አንጸባራቂ ድል፤”ከሜዳሊያ በላይ ነው ።”ሲል ገልጾታል። እውነት ነው ከሜዳሊያ በላይ ነው። ለ30 አመታት መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ የተዘራውን ልዩነት፣ ጥላቻና መጠራጠር ለብቻው ሙሉ በሙሉ ባያረክሰውም በጅምር ላለው ጥረት ተደማሪ አቅም ይሆናል።
በሀሰተኛ ትርክት ልፋፌ ነቢብ በወገኖቻችን ላይ በተደጋጋሚ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከፈጠረብን ሀዘን ሙሉ በሙሉ ባያወጣንም በመጠኑም ቢሆን መጽናኛ ስለሚሆነን ከሜዳሊያ በላይ ነው። እንዲሁም በዚህ ቅስም ሰባሪ፣ ክፉና ፈታኝ ሰዓት የተገኘ ታላቅና አንጸባራቂ ድል መሆኑ ከቀደሙትም ከሚከተሉትም ልዩ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ። ከመቼውም ጊዜ በላይ ያለንበት ሁኔታ እንዲህ ያሉ መጽናኛዎችን እና የጠለሸውን ገጽታችንን መልሶ መገንቢያ ወረቶችን አብዝቶ በብርቱ ይሻልና። ከዚህ አንጸባራቂ ድል ጀርባ ያሉ አሰልጣኞች፣ የህክምና ባለሙያዎችና ቤተሰቦች የማይተካ ሚና እንዳለ ሆኖ የአትሌት ኮማንደር ደራርቱ ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነው አመራሯ በአትሌቶች መካከል የፈጠረችው አንድነትና እንደ ቡድን በመስራት አገርን እንዲያስቀድሙ ለተጫወተችው የማይተካ ሚና በልኩ እውቅና ሊቸራት ይገባል።
ከ1970ዎቹ እስከ 80ዎቹ መጀመሪያ እነ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ብርሃኑ ግርማ፣ ከበደ ባልቻና መሐመድ ከድር በአለም የአትሌቲክስ መንደር ማንንም ጣልጋ ሳያስገቡ ከአንድ እስከ ሶስት በመግባት ያሸንፉ ስለነበር ” አረንጓዴው ጎርፍ ” የሚለውን ቅጽል ሊቀዳጁ ችለዋል፡፡ ያው እንደሚታወቀው የአትሌቶቻችን ማልያ አረንጓዴ ስለሆነ ነው ተከታትለው ሲያሸንፉ አረንጓዴው ጎርፍ የሚባሉት። ይህ የመጀመሪያው አረንጓዴ ጎርፍ ነው። በ2005 ዓ.ም በፊንላንድ ሄልሲንኪ በተካሄደው 10ኛው የአለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከሩሲያ በመቀጠል በ3 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ2 ነሐስ ከዓለም ሦስተኛ ሆና ከማጠናቀቋ ባሻገር፤ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት ሁለተኛውን አረንጓዴ ጎርፍ ለአለም አሳይተዋል። በ5000 ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ መሠረት ደፋር የብር፣ እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ ሜዳሊዎችን ሲያጠልቁ መሠለች መልካሙ ደግሞ 4ኛ በመውጣት አለምን ለ2ኛ ጊዜ እውነትም አረንጓዴው ጎርፍ አስብለውታል።
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ10000 ሜትር እንደገና ወርቅ ባጠለቅችበት፤ ቀነኒሳ በቀለና ስለሺ ስህን በ10000 ሜትር ወንዶች ተከታትለው በመግባት የወርቅና የብር ሜዳሊያ አጥለቅልቀዋል። እኔ ሳልሳዊ ያልሁት 3ኛው የአረንጓዴ ጎርፍ ደግሞ ሰሞኑን በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን ለተከታታይ 10 ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው እሁድ ለሰኞ አጥቢያ በተጠናቀቀው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ ጀግኖች አትሌቶቻችን በመሮጫ መምና ዩጅን ጎዳናዎች ላይ እንደገና አረንጓዴ የብራ (ዝናብ የሌለበት) ጎርፍ ሆነዋል። ታላላቅ የዓለም መገናኛ ብዙኃንም በአረንጓዴው መለያቸው መላውን ዓለም ያስደመሙት ኢትዮጵያውያኑ እውነትም አረንጓዴው ጎርፍ እንጂ ሌላ ቃልም ሆነ ቅጽል እንደማይገልጻቸው ዘግበዋል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን በጉጉት በጥፍራቸው ቆመው ሲጠብቁት የነበረው የወንዶች 5000 እና 10000 ውጤት ለምን እንዳልተሳካ በግልጽ ተነጋግሮ ማስተካከያ ማድረግ ያሻል።
ከአሜሪካ ቀጥሎ በ4 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ2 ነሐስ በ10 ሜዳሊያ ከአለም 177 አገራትን አስከትላ 2ኛ መሆኗና ሰንደቃችን በአለም አደባባይ በተደጋጋሚ ከፍ ብሎ መውለብለቡ፤ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ግብጽ፣ ሕወሓት፣ የምዕራባውያን ሚዲያ፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ተብዬዎች ተቀናጅተውና ተናበው በከፈቱብን የጸረ ኢትዮጵያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና በአናቱ የእኛ የዲፕሎማሲና የሕዝብ ግንኙነት ድክመት ተጨምሮበት ክፉኛ የጠለሸውን ገጽታችንን ለማሻሻል ያግዛል። ይሄን ተከትሎ ደግሞ ቱሪዝሙን ያነቃቃዋል። ስፖርትን ባጠቃላይ ከአገራችን አውድ አውጥተን ብንመለከተውም ተመሳሳይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ነው ያለው።
“ስፖርት አለምን የመቀየር ጉልበት አለው። ሕዝብን ለአንድነት የማነሳሳት ኃይል አለው። ከሌላ ከምንም ነገር በላይ ሕዝብን አንድ የማድረግ ብርቱ ጉልበት አለው። ወጣቱን በሚገባው ቋንቋ ያነጋገራል። ስፖርት ተስፋ በተቆረጠበት ተስፋን ያለመልማል። ከመንግስት በላይ ዘረኝነት የመታገል ኃይል አለው። በማንኛውም አይነት መድልዎና ልዩነት ፊት ላይ የመሳለቅ ጉልበት አለው።” የመጀመሪያው የነጻዋ ደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ/ማዲባ/የስፖርትን ኃያልነት በዚህ ደረጃ ከስፖርትነት በላይ አግዝፎ የገለጸው በስማ በለው አይደለም። በተግባር በህይወቱ ኑሮትና ተገልጦ አይቶት እንጂ።
በወጣትነቱ በአፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ ቦክሰኛ እያለ የስፖርትን ኃያልነት ተገንዝቧል ። ፕሬዚዳንት ከሆነ በኋላ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በ1995 ዓ.ም አገሩ የምንጊዜም ተቀናቃኟን ኒውዚላንድን አሸንፋ የራግቢን የአለም ዋንጫ ስታነሳ በደቡብ አፍሪካውያን መካከል የፈጠረውን የአንድነትና የመቀራረብ ስሜት በቅርብ ተረድቶታል ። በ2010 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን የአለም የእግር ኳስ ጨዋታን ስታስተናገድ ዜጎች ነጭ ጥቁር ሳይሉ እንዴት በአንድነትና በአብሮነት ቆመው እንደ ነበር በአይኑ ስላየ ነው ስፖርት ከስፖርትነት በላይ መሆኑን በተደጋጋሚ በአደባባይና በሸንጎ ይመሰክር የነበረው። ስለሰሞነኛው የአለም የአትሌቲክስ አንጸባራቂ ድል ትርጉምና አንድምታ ላይ ይሄን ያህል ካልሁኝ አይቀር በቢቢሲ የአማርኛው መስኮት በአለም ሻምፒዮን የአገራችንን የኋላ ታሪክ አሻግሬ ላማትር።
ኢትዮጵያና ሜዳሊያ የተገናኙት ገና ከጅምሩ ፊንላንድ ሄልሲንኪ በተደረገው የመጀመሪያው የአለም ሻምፒዮና ውድድር ነበር። በዚህ የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ከበደ ባልቻ ነው ። ከበደ በማራቶን ውድድር ሁለተኛ ወጥቶ የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ ችቦውን አቀጣጠለ ። በጣሊያኗ ከተማ ሮም በተካሄደው ሁለተኛው ውድድር ግን ኢትዮጵያ አልተሳተፈችም። በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያ በመሰብሰብ አሜሪካንን የሚስተካከላት የለም።
ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ደግሞ ጎረቤት አገር ኬንያ ናት። ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር እስካሁን ባከማቻቸው ሜዳሊያዎች ከዓለም ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀም ጣለች። የ2022 የኦሪገን ሻምፒዮናን ጨምሮ ኢትዮጵያ 95 ሜዳሊያዎች አሏት። 33 የወርቅ ፣ 34 የብር እንዲሁም የ28 የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሰባስባለች። አትሌት ከበደ ባልቻ በማራቶን መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የብር ሜዳሊያ ያስገኘ አፍሪካዊ መሆኑን ቢቢሲ ያወሳል።
በፈር ቀዳጁ የሄልሲንኪ ውድድር ኢትዮጵያ በከበደ ባልቻ ነሐስ ሜዳሊያ አሸንፋ ከዓለም 15ኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ ፤ በዚህ ውድድር የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት የቻለች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ናት ። በወቅቱ ምሥራቅ ጀመርን 19 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 1ኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ የውድድሩ ኃያል አገር አሜሪካ ደግሞ 2ኛ ሆና ትከተላለች ። በጣልያኗ ሮም በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና “የአትሌቲክስ ቡድን እየመራ የሚጓዝ አሠልጣኝ ባለመገኘቱ ኢትዮጵያ አልተሳተፈችም።”ሲል ቢቢሲ ምንጭ ጠቅሶ ያስታውሳል ።
ኢትዮጵያ በዚህ ታላቅ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መድረክ የመጀመሪያውን ወርቅ ያገኘችው በአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ አማካይነት ነው ። ኃይሌ የጀርመኗ ስቱትጋርት ባዘጋጀችው አራተኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ10000 ሜትር ለአገሩ ወርቅ ማምጣት ችሏል ። በ5000 ሜትር ተወዳድሮ የነሐስ ሜዳሊያ ለአገሩ በማምጣት ባለ ድርብ ድል ሆነ ። አትሌት ፊጣ ባይሳ ደግሞ ሌላ ነሐስ አክሎ ኢትዮጵያ በሦስት ሜዳሊያ አሸብርቃ ተመለሰች። ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መድረክ በስዊድኗ ጉተምበርግ ከተማ እስከተሰናዳው ውድድር ድረስ ከአፍሪካ አንደኛ በመሆን አጠናቃለች። በጉተምበርግ በተካሄደው ውድድር ግን አንደኝነቱን ለኬንያ አስረከበች ።
በዚህ ውድድር ኬንያ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጨምራ ስድስት ሜዳሊያ በመሰብሰብ ስሟን ከፍ አደረገች ። በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያና ኬንያ ከጉተምበርጉ ፍልሚያ በኋላ ፉክክራቸው እየበረታ መጣ። በ2003 ዓ.ም በተካሄደው የፓሪሱ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 3 የወርቅ ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ ሜዳሊያ በማምጣት ከዓለም አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት መድረክ አይረሳም ። በፊንላንድ ሄልሲንኪ የተካሄደው 10ኛው ሻምፒዮና ግን ለኢትዮጵያ ልዩ ነበር ይላል ቢቢሲ። ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ከአሜሪካና ከሩሲያ በመቀጠል በ3 ወርቅ ፣ በ4 ብርና በ2 ነሐስ ሜዳልያዎች በመንቆጥቆጥ ከዓለም 3ኛ ሆና አጠናቀቀች ።
ይህ የሄልሲንኪው ውድድር ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ሁለተኛው የ“አረንጓዴው ጎርፍ” ነው። ከሁለት ዓመት በኋላ ጃፓን ኦሳካ ባሰናዳችው ውድድር ድል ፊቱን ወደ ኬንያ አዞረ። ኬንያ በዚህ ሻምፒዮና 5 ወርቅን ጨምሮ 15 ሜዳሊያዎች ጠራረገች። ከዚያ በኋላ በነበሩት የበርሊን ፣ ዴጉ ፣ ሞስኮ ፣ ቤይጂንግ ፣ ሎንዶን ፣ ዶሃ ላይ በተካሄዱ ውድድሮች ኬንያ በሜዳሊያ ብዛት ኢትዮጵያን እየመራች ቆይታለች ።
አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና የተሳተፈችው በ1991 ዓ.ም ቶኪዮ በተዘጋጀው ውድድር ነው ። ምንም እንኳ ደራርቱ በተሳተፈተችበት የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ሜዳሊያ ባታመጣም በቀጣዩ ዓመት ባርሴሎና በተዘጋጀው ኦሊምፒክ ላይ ወርቅ ማጥለቅ ችላለች ። የአገሯን ስም በተለያዩ መድረኮች ያስጠራችው ደራርቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆና ከተመረጠች በኋላ ለውጥ ማምጣት ችላለች ። ነገር ግን ለደራርቱ ሁኔታዎች ሁሉ የተመቻቹ ነበሩ ማለት ከባድ ነው ።
ደራርቱ ፌዴሬሽኑን መምራት ከጀመረች ወዲህ ሁለት ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና ፤ አንድ ጊዜ በኦሊምፒክ መድረክ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ተሳትፋለች ። በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በተሰናደው የ2019 የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ ፣ አምስት ብርና አንድ ነሐስ ይዛ በድል ተመልሳለች ። በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች በሚታወቁበት የመካከለኛና ረዥም ርቀት ውድድር የተለመደውን ወርቅ ማስመዝገብ ባይችሉም ተስፋ ያላቸው አትሌቶች ታይተዋል ።
ኢትዮጵያ በመድረኩ በስምንት ሜዳሊያ አምስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቀቀች ። ከዚህ በኋላ በደራርቱ የተመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ታላቅ ወደ ሚባለው የኦሊምፒክ መድረክ ነው ያቀናው ። በ2022 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያገኘችው ሜዳሊያ ብዛት አራት ነው። ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ካመጣቻቸው ዝቅተኛ ከተባሉት የሚመደብ ነው ። ቀጥሎ ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፍ መድረክ ባለፈው መጋቢት የተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ፍልሚያ ነው። ይህ መድረክ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደምቀው የታዩበት ነበር ። ኢትዮጵያ በአራት ወርቅ ፣ በሦስት ብርና በሁለት የነሐስ አሜሪካንን አስከትላ ከዓለም ቁንጮ ሆና አጠናቃለች ።
በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄው የዘንድሮው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ አንጸባራቂ ድል ማስመዝገብ ችላለች ። በተለይ የኢትዮጵያ አትሌቶች የምንጊዜም ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ በምትታወቅባቸው ርቀቶች ሳይቀር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ብቅ ብቅ ማለታቸው በቀጣይ ከተሰራበት የተሻለ ውጤት ሊመዘገ ብበት እንደሚችል አመላክቷል ።
ኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ብቻ አይደለም የሚጋሩት ። ሜዳሊያ የሚታደልበት የአትሌቲክስ መድረክንም ጭምር እንጂ ይላል ቢቢሲ የሁለቱን አገራት ፉክክር ለማስ ታወስ። በተለይ በረዥም ርቀት የሩጫ ውድድር ሁለቱ አገራት በየመድረኩ አንገት ለአንገት ሲተናነቁ ማየት አዲስ አይደለም። ኃይሌና ፖል ቴርጋት በሚሊ ሜትር ተቀዳድመው ሲገቡ የነበረውን ትዕይንት ማን ይዘነጋል ። ቀነኒሳና ኪፕቾጌ በሁለት ሰከንድ ልዩነት የጨበጡት የማራቶን ክብረ ወሰንም እንዲሁም ተመዝገቦ የሚኖር ነው። ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በመካከለኛ ርቀት ማለትም በ5000ና በ10000 ሜትር ፤ የኬንያ ደግሞ በአጭርና በመካከለኛ የ800 ፣ የ1500 እና የ3000 ሜትር ርቀቶች ሲነግሱ ማየት የተለመደ ነው ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኬንያዊያን በመካከለኛ ርቀት ኢትዮጵያን ሲፋለሙ ተመልክተናል። ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደግሞ በ1500 እና 3000 ሜትር መሰናክል ውድድሮች ኬንያዊያንን መፈተን ይዘዋል። በ2019 የዶሃ ዓለም ሻምፒዮና በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ኬንያዊው ኪፕሩቶ ታዳጊው ኢትዮጵያዊ ለሜቻ ግርማን በሚሊ ሜትር ቀድሞ ወርቅ ያጠለቀበት ውድድር የሚዘነጋ አይደለም። በነገራችን ላይ ለሜቻ ግርማ በ3000 ሜትር መሰናክል ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያስገኘ የመጀመሪያው ወንድ አትሌት ነው ይለናል ቢቢሲ። አትሌት ሶፊያ አሰፋ በ2013 ሞስኮ ላይ ያገኘችው ነሐስ በርቀቱ ብቸኛው የኢትዮጵያ ሜዳሊያ ነው። በዘንድሮው የኦሪገን ዓለም ሻምፒዮና የታየውም ይህ ነው።
ለሜቻ ግርማ በርቀቱ ሁለተኛ ብሩን በተከታታይ አጥልቋል። ጉዳፍ ፀጋይ ደግሞ በ1500 ሜትር ለአገሯ ብር አስገኝታለች። ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕየጎን ለአገሯ ወርቅ አስገኝታለች። የኬንያ መገናኛ ብዙኃን በዘንድሮው የኦሪገን ውጤት ደስተኛ አለመሆናቸውን እየገለጡ ነው። ኬንያ ባለፈው የዓለም ሻምፒዮናም ሆነ በኦሊምፒክ መድረክ ከኢትዮጵያ ልቃ ብታጠናቅቅም በዓለም የቤት ውስጥ ውድድርና በአሜሪካው የዓለም ሻምፒዮና የተመዘገበው ውጤት አመርቂ ሆኖ አልተገኘም።
በአሜሪካዋ ኦሪገን ግዛት ሲካሄድ የሰነበተው18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለፈው እሁድ ተጠናቋል። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በወንዶች እና ሴቶች ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉ የውድድር ዘርፎች ተሳትፋለች። አራት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሁለት የነሃስ ሜዳልያዎችን በመቀዳጀት ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ሆና በድል አጠናቃለች። ኢትዮጵያ በኦሪገን ካሸነፈቻቸው 10 ሜዳሊያዎች ሰባቱ በሴት አትሌቶች የተገኙ ናቸው። ለእንስት አናብስቱ በዚህ አጋጣሚ ከመቀመጫዬ ተነስቼ ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌያለሁ። የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በፈረንጆቹ ከ1983 ጀምሮ በየሁለት ዓመት ልዩነት መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ5000 እና በ10000 ሜትር ውድድሮች ስመ ጥር ሆነውበታል።
ቀደም ሲል በ10 ሺህ ሜትር፣ በ5 ሺህ ሜትር እና በግማሽ ማራቶን፤ ሦስት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ በዚህ ታላቅ መድረክ አሸናፊነቷን አስጠብቃለች። ለተሰንበት ከውድድሩ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠችው አስተያየት “ህልሜ እውን ሆኗል። ይህ ድል ከዓለም ክብረወሰን በበለጠ ለእኔ ትልቅ ነው። በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች። አትሌት ጎይተቶም ገብረሥላሴም በሴቶች ማራቶን የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በመስበር አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በኦሪገን መድረክ ደግሞ በማራቶን ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። ከዚህ በፊት ማሬ ዲባባ በ2015 ቤይጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆና ነበር ።
ኢትዮጵያ ፤ በተለይ በፈረንጆቹ ከ1999 እስከ 2007 ባሉት ዓመታት በ10 ሺህ እና በ5 ሺህ ሜትር ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ውድድሩን በማሸነፍ በርካታ ሜዳሊያ አካብታለች። ጌጤ ዋሚ ፣ ደራርቱ ቱሉ ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ አልማዝ አያና እና ሌሎች በአትሌቲክሱ ዓለም አገራቸውና ያስጠሩ ሴት አትሌቶች ናቸው ።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም