በዓለማችን ዋና የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የአየር ጠባይ ለውጥ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ነው። ለውጡ ላስከተለው ችግር መፍትሔ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎችንና መርሐ ግብሮችን በመንደፍ ከተለያዩ ፕሮግራሞች ጋር በማጣጣም እየሠራች ትገኛለች።
የግብርና ሚኒስቴር በዘርፉ ከሚያከና ውናቸው ተግባራት መካከል በተለይም በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥ አንዱ የትኩረት ማዕቀፍ በሆነው የህዝባዊ ሥራዎች ላይ በማካተት የአየር ጸባይ ለውጥን የሚከላከሉ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በተከናወኑ ሥራዎች መካከል ጋምቤላና አፋርን ሳይጨምር በሌሎቹ ክልሎች ላይ ባሉ 350 ወረዳዎች ውስጥ በልማታዊ ሴፍቲኔት የታቀፉ ሰዎችን ወደ ሥራው በማስገባት በከፍተኛ ሁኔታ ተራቁተው የነበሩ መሬቶች እንዲያገግሙና በአየር ፀባይ ለውጥ ላይም መጠነኛ የሆነ መሻሻልን እንዲያመጡ ተደርጓል።
ይሁንና የተከናወኑት ሥራዎች አገሪቱ እያራመደች ከምትገኘው «ለአየር ፀባይ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ» ጋር አቀናጅቶ በመሄድ ረገድ ከፍተኛ የሆነ የአፈጻጸም ውስንነት አለባቸው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በህዝባዊ ሥራዎች ማዕቀፍ ውስጥ የተካተቱ ተግባራት ከስትራቴጂው ጋር ተሰናስለው እንዲሄዱ የሚያስችል የአየር ለውጥን የሚቋቋም አሠራር የሚያሰርጽ ፕሮጀክት ቀርጾ ይፋ አድርጓል።
«የአየር ለውጥን የመቋቋም ስርፀት» የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ ዓላማውም «በዓለም አቀፍ አየር ፀባይ ለውጥ ጥምረት »(Global Climate Change Alliance)ና ለውጡን መቋቋም የሚያስችል አሠራር የሚያሰርጹ ዕቅዶችና ክንውኖችን በኢትዮጵያ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሀ ግብሩ ዘንድ እውን እንዲሆን የቴክኒካል ድጋፍ መስጠት ነው። በሌላ በኩልም ፕሮግራሙ በሚሸፍናቸው ወረዳዎች ላይ የሚገኙ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ የሚያስከትልባቸውን ተግዳሮቶች እንዳመጣጣቸው መቀልበስ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊው አቶ መለሰ መና እንደሚሉት የአየር ፀባይ ለውጥን የሚቋቋሙ ሥራዎችን መሥራት መሰረታዊ ከሆኑ ሥራዎች ሁሉ ቀዳሚ ነው፤ ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ጋር ሲዋሀድ ደግሞ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደማለት ይሆናል ይላሉ።
በአንድ በኩል የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ቤተሰቦች ምግብ በማቅረብ እንዲሁም ክፍያ በመክፈል እነርሱን መደገፍ የሚያስችል ሲሆን፤በሌላ በኩል ደግሞ ውሃን በማሰባሰብና አትክልቶችን በማልማት ጥቅም ላይ እንደሚውል ይናገራሉ። ክልሉም ከካፒታል በጀቱ 60 በመቶውን ውሃን ለማሰባሰብ ሥራ እያዋለ ነው ያሉት አቶ መለስ ይህ ማለት ደግሞ የግብርና ልማት ሥራዎችን መሰረት ከማስያዙም በላይ በቤተሰብ አካባቢ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር በመፍታት ከተረጂነት ወጥተው በአትክልት ልማት፣ በእንስሳት እርባታ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን በመሥራት አፈር እንዳይከላ የማድረግ እንዲሁም በአርሶ አደር ማሳም ሆነ ከማሳው ውጪ ቢተከሉ አካባቢውን ሊቀይሩ የሚችሉ ችግኞችን የማዘጋጀትና የመትከል በዚህም ለውጦች የማምጣት ሥራ በአግባቡ እየተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት። ጎን ለጎንም የአፈር ለምነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለምሳሌ ኖራ፣ ኮምፖስት ፣በርሚ ኮምፖስትና ሌሎችን በማዘጋጀትና በጥቅም ላይ በማዋል በአካባቢ ጥበቃ ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ በመሆኑም በሁለቱም ዘርፎች ላይ በክልሉ የሚሠራው ሥራ ትልቅ አርአያ እንደሚሆን አብራርተዋል።
ሴፍቲኔት ሳይመጣ በፊት የምግብ ዋስትና ችግር የነበረባቸው አርሶ አደሮች አሁን ላይ የወተት ላምና የእርሻ በሬ ከመግዛታቸውም በላይ አነስተኛ ንግዶች ላይ ተሰማርተው የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለቤተሰባቸው ተጨማሪ ገቢን በማስገኘት በኩልም ሰፊ ውጤት እንዳለ ያሳያል እንደ አቶ መለሰ ገለጻ።
ገጠር ላይ የሚሠሩ እንደ መንገድና የመስኖ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማሻሻል በኩል ከፍተኛ ሚናን ከመጫወታቸውም በላይ በጣም የተጋጋጡና የተጎዱ መሬቶችን በማልማት በኩል ለውጥ እየመጣ እንዳለ ተናግረዋል። ግብርና ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ይፋ ያደረገው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስርጸት ፕሮግራም ዋና ዓላማው ልማታዊ ሴፍቲኔትን መደገፍና አቅም እንዲኖረው ማድረግ እንደመሆኑ ክልሉ በተቀመጠው አቅጣጫና የሴፍቲኔት ፕሮግራሙን በሚያሳደግ መልኩ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል።
ከሀረሪ ክልል ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ሻወል በቀለ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ ሴፍቲኔት ትልቁ ጉልበት ነው፤ በዚህም የተራቆቱ መሬቶችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ እየተጠቀምንበት ነው ይላሉ። እንደ አጠቃላይም ሴፍቲኔት ፕሮግራም 22 ሺ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም አቅመ ደካሞችና ቀጥተኛ ተረጂዎች ሲኖሩ አብዛኞቹ ግን የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤን አጣምረው በመሥራት የሚጠቀሙ መሆናቸውንና በከፍተኛ ሁኔታ የተራቆቱ መሬቶች በአሁኑ ወቅት በማገገም ላይ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።
ክልሉ አብዛኛውን ጊዜ በድርቅ የሚጠቃ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ፕሮግራሙን ማስኬዱ ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው በአሁኑ ወቅት በተደጋጋሚ በድርቅ የመጠቃት መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱንና በቀጣይም በተለይም የግብርና ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው የአየር ለውጥን መቋቋሚያ ስርጸት ፕሮግራም እንደ ቀድሞው ጊዜ ከሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ጋር በማዋሀድ ለመሥራት መታቀዱንም አስረድተዋል።
ባለፉት ጊዜያት በክልል የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶች ሥራውን በባለቤትነት ይዞ የሚያንቀሳቅስ አመራር እንዳይኖር አድርጎ ነበር፤ በቀጣይ ግን በተለይም ይህንን አዲስ ፕሮግራም በመረዳትና በመውሰድ ቀድሞ ይሠራ ከነበረው የአየር ንብረት ጥበቃና ከሴፍቲኔት ጋር በማቀናጀት ዘለቄታዊና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።
በትግራይ ክልል የማህበረሰብ ሥራዎች አስተባባሪው አቶ አረፈ ኪሮስ እንዳሉት የክልሉ የመሬት አቀማመጥ ከ60 በመቶ በላይ ወጣ ገባ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የአፈር መሸርሸር አለ ከዚህም የተነሳ ሰፊ ድርቅ በየጊዜው ይከሰታል፤ በርካቶችም ተጎጂ ይሆናሉ፤ በመሆኑም ሴፍቲኔት ፕሮግራም ወደ ሥራ ሲገባ ግን የአፈር መከላትን በመከላከልና ህብረተሰቡ ዘላቂ የሆነ የምግብ ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ መቻሉን ይናገራሉ።
ክልሉ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት በጀመረው የሴፍቲኔት ፕሮግራም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር አስተሳስሮ መሥራት በመጀመሩ ሰፊ የእርከን፣ የቦረቦር እንዲሁም አነስተኛ የመስኖ ውሃን መያዝ የተቻለ ከመሆኑም በላይ በህብረተሰብና በቤተሰብ ደረጃ የመስኖ ልማትን መጠቀም ያስጀመረ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ትምህርት ቤት የጤና ተቋማትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በመሥራት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ እነዚህ ሥራዎች በጥምረት መሠራታቸው ህብረተሰቡን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ያሸጋገሩ አካባቢውንም ከ50 በመቶ በላይ የአፈር ለምነቱ የተጠበቀና የክልሉን የደን ሽፋን እንዲጨምር ያደረገ ሆኗል። ከዚህ ቀደም ክልሉ ላይ በየአምስት ዓመቱ የሚከሰት ድርቅ ነበር አሁን ግን የተፈጥሮ ሀብቱ በመጠበቁ ችግሩ የቀነሰ ከመሆኑም በላይ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥም መቻሉን ይናገራሉ፤ በቀጣይም ይህንን ተሞክሮ በመያዝ ሁሉም ሥራዎች በእቅድ ተቀርጸውና ከአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስርጸት ጋር በማቀናጀት ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተፈራ ታደሰ ባለፉት 17 ዓመታት በዘርፉ የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም የልማቱን ሥራ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር አጣጥሞ መሥራት ግን ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስርጸት ፕሮግራም ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ወደ ሥራ የሚገባና በአገሪቱ ከሁለት ከልሎች ውጪ በሁሉም ክልሎች ባሉ 350 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ሲደረግ የህብረተሰቡን ኑሮ በመቀየርና የአካባቢውን ጉዳት በመቀነስ በኩልም ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አብራርተዋል። አገሪቱ የተጎዱ መሬቶችን መልሶ በማልማት በኩል ሰፊ ልምድ አላት ያሉት ዳይሬክተሩ ፕሮጀክቱ ደግሞ እስከ አሁን የተሠሩትን በማጠናከር በቀጣይም ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት ሰፊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
እፀገነት አክሊሉ