የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት /ኢጋድ/ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚገኙ ስምንት ሀገራትን ማለትም ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ሱዳንን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ኬንያን ሶማሊያንና ኡጋንዳን የሚያጠቃልል የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ድርጅት ነው። የቀጣናው ሀገራት የሚገኙበት የአፍሪካ ቀንድ ታዲያ በተደጋጋሚ በድርቅ ሲጠቃና ያልተጠበቀ ዝናብ ሲከሰትበት ይታያል።
በተለይ ደግሞ ድርቁ በቀጣናው ከአመት አመት በከፋ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ጎርፍ፣ የበረሃነት መስፋፋት፣ የመሬት መሸርሸር፣ የበርሃ አንበጣ፣ ኮቪድ-19፣ ግጭቶች፣ የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም ችግሮች ድርቁን አባብሰውታል።
በድርቁ በእጅጉ የተመታው አካባቢ 70 ከመቶ ያህሉን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚሸፍን ሲሆን በአመቱ ከ600 ሚሊ ሊትር ያነሰ የዝናብ መጠን የሚያገኝና ደረቅና ከፊል ደረቅ ተብሎ የሚታወቅ ነው። ይህ ስነ ምህዳራዊ ሁኔታም በቀጣናው የሚኖሩ በርካታ ዜጎችን ለምግብና ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዳርጓል። መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ጫናም አሳድሯል። በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
በቀጣናው በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከልና ይህንኑ ተከትሎ የሚመጣውን አካባቢያዊ ጉዳት ለመቀነስ ብሎም በዚሁ ቀውስ ዙሪያ ለመወያየት የቀጣናው አባል ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እ.ኤ.አ መስከረም 2011 ናይሮቢ ላይ ጉባኤ አካሂደዋል። በዚሁ ጉባኤም አባል ሀገራቱ የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ ልማት ኢኒሺዬቲቭ ውሳኔ አሳልፈዋል። አባል ሀገራቱም በዓመት ሁለት ጊዜ እየተሰባሰቡ በዚህ ረገድ የተከናወኑ ስራዎችን ይገመግማሉ።
አቶ እድሜዓለም ሽታዬ በኢጋድ የኢትዮጵያ የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ ልማት ኢኒሺዬቲቭ አስተባባሪ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት የኢጋድ የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ ልማት ኢኒሺዬቲቭ (IGAD Drought Disaster Resilience and Sustainability Initiative (IDDRSI) ዋነኛ አላማ በኢጋድ አባል ሀገራት የሚከሰተውን የድርቅ ጉዳት ለመከላከል የሚያስችሉ ማእቀፎችን ተግባራዊ ማድረግ ነው። በነዚህ ማእቀፎች ውስጥም ወደ ስምንት የሚሆኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2011 ድረስ ባሉት አመታት ውስጥ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቷል። በዚህ ድርቅ ወደ 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ጉዳት ደርሶበታል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሀብትም ሞቷል። ከዚህ በመነሳትም የኢጋድ አባል ሀገራት በተቀናጀ መልኩ ለመስራት እንዲቻል የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ ልማት ኢኒሺዬቲቭን በማዘጋጀት በዚሁ ላይ በመመርኮዝ አባል ሀገራት የራሳቸውን የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ ልማት ኢኒሺዬቲቭ ማእቀፍ እንዲያዘጋጁ ተደርጓል።
ከዚህም አንፃር ኢትዮጵያ የራሷን ‹‹ካንትሪ ፕሮግራሚንግ ፔፐር›› የሚባል ሰነድ አዘጋጅታና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ ፕሮጀክቶችን ቀርፃ ከልማት አጋር ድርጅቶች
ጋር በመተባበር በሚገኘው ድጋፍና ብድር የድርቅ መቋቋሚያ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች። በዚህም የድርቅ መቋቋሚያ አቅምን ድርቅ በሚያይልባቸው አካባቢዎች ላይ በተለይ ደረቃማ በሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች፣ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች፣ በዋናነት በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር በሚኖሩባቸው የሀገሪቱ ቆላማ ክፍሎች ተግባራዊ እየተረገ ነው።
በተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠባበቅ፤ ይህም ሲባል የግጦሽ መሬትን የማልማት፣ የመጠበቅና የመንከባከብ፣ የውሃ መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት የገበያ ትስስርን መፍጠር፣ የገበያ መሰረተ ልማት አውታሮችን መዘርጋት፣ መረጃ ለአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ እንዲደርስ ማድረግና ባኗኗር ዘዴው ላይ ተመርኩዞ የኑሮ ዋስትናውን ማረጋገጥና በተለይ ደግሞ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ለማከናወን ተሞክሯል።
በዚህ የተወሰኑ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በተደረጉባቸው አካባቢዎች በቤተሰብ ደረጃ በተለይ በሱማሌና አፋር ክልሎች፣ በኦሮሚያ ቦረና ዞን፣ በደቡብ የደቡብ ኦሞ ዞኖች በተሰሩ ስራዎች መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን ማየት ተችሏል። ስራዎቹ በቤተሰብ ደረጃም አርብቶ አደሩ ድርቅ
የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በመጠኑም ቢሆን አስተዋፅኦ አድርጓል። ነገር ግን ይህ በቂ ነው ማለት አይደለም። የድርቅ መቋቋም አቅምን ለመገንባት ዘለግ ያለ ጊዜ የሚወስድ የተቀናጀ የልማት ስራ ይጠይቃል።
ከዚህ አንፃር ለአብነት እ.ኤ.አ በ2021 እና 2022 ሶማሊያና በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ድርቅ ላይ በተሰሩ የልማት ስራዎች በተለይ የውሃ ግድቦችና ኩሬ ስራዎች እጅግ በርካታ የእንስሳት ሀብት በድርቅ እንዳይጎዳ ለመከላከል ተችሏል። የግጦሽ ልማትንም በተመለከተ ከዚህ ቀደም የግጦሽ ሳር ወደቆላማ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሌሎች የሀገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች መምጣቱ ቀርቶ አርብቶ አደሮቹ በግጦሽ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲችሉ ስራው አስተዋፅኦ አድርጓል።
ለአብነትም የሱማሌ ክልል ለአፋር ክልል የግጦሽ ሳር ሰጥቷል። የደቡብ ክልል ከፊል ቆላማው ክፍል ለኦሮሚያ ክልል ቆላማ ክፍል ሰጥቷል። በተመሳሳይ እዛው ኦሮሚያ ክልል ከአንዱ ወረዳ ወደሌላው ወረዳ የግጦሽ ሳር በማንቀሳቀስ በእንስሳት ሃብት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ተችሏል።
የድርቅ ጉዳትን በአጭር ጊዜ መከላከል አይቻልም። በኢጋድ የተነደፈው የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ ልማት ኢኒሺዬቲቭ ማዕቀፍም እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ ለአስራ አምስት አመታት በየሦስት አመታቱ ምእራፍ ተከፋፍሎ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ሆኖም ይህ ማእቀፍ ድርቅን ለመከላከል እያገዘ ያለ ቢሆንም በቂ ነው ተብሎ አይታሰብም። በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮጀክቶቹ የሚከናወኑባቸው ቦታዎች ውስንና ሁሉንም የአርብቶ አደር ቦታዎች ስለማይሸፍኑ ተጨማሪ ሃብት ያስፈልጋል። የመንግስትና የልማት አጋር ድርጅቶችንም ድጋፍ ይጠይቃል።
በቅንጅትና በተባበረ መልኩ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ግን በቀጣዮቹ አስርና አስራ አምስት አመታት በቤተሰብ ደረጃ በተለይ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2014