ዛሬ መጠጥ ቤቱ ከወትሮ በተለየ መልኩ ደመቅ ብሏል። የጎሪጥ ከሚተያየው ይልቅ እየተቀላለደ እየጠጣ የሚያውካካው ጎልቷል። ከስንት ዘመን በኋላ አንድ አዲስ እንግዳ ከወደ ባህር ማዶ ያደረገውን ኑሮውን ትቶ ወደኢትዮጵያ መመለሱን አብስሯል።የተገኝ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሁሉንም አስደስቷል።እርሱ የኢትዮጵያን ምድር ከረገጠበት ቀን ጀምሮ ሰበብ አድርገው በየቀኑ እየተሰባሰቡ መጠጣቱን ተያይዘውታል።
ተሰማ መንግስቴ ወደ ግሮሰሪው ሲገባ ጭብጨባው ደመቀ። ከኋላው ዘውዴ መታፈሪያ ተከተለ።ሁሉም የበለጠ ሞቅ አድርገው አጨበጨቡ።ጊዜው ክረምት ቢሆንም ግሮሰሪዋ በሙቀቱ ተጨነቀች፤ በደስታው መሃል ሞቅታ የተሰማቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማውራት በመጀመራቸው እንግዳው ተገኝ ከመደሰት እና ከመዝናናት ይልቅ ወደ መጨነቅ ተሸጋገረ።ያው ከመልካም ወደ በጣም መልካም ብቻ ሳይሆን ከመልካም ወደ መጥፎ ስሜት መሸጋገርም ስሙ ሽግግር አይደል? እናም እንግዳው ተገኝ የጥንት ጓደኞቹ ሲዝናኑ ከመደሰት ይልቅ መጠን እንዳያልፉ ሰጋ።በተለይ አልፎ አልፎ የሚያወጡት ቃል አስጨነቀው።ሁኔታው ከመዝናናት ወደ አመረረ ጠብ እንዳይቀየር ፈራ።
ተገኝ፣ ከፍርሃቱ መለስ አለና በልቡ ‹‹በኢትዮጵያ መዝናናት አሁንም በሽ ነው›› አለ ለራሱ።አሜሪካ ውስጥ መዝናናት ማለት በስንት ጊዜ አንድ ጊዜ ለዚያውም ከአንድ እና ከሁለት ሰው ጋር ምናልባት ጊዜ የሚሰጥ ካለ በዓመት ግፋ ቢል በጣት ለሚቆጠሩ ቀናት መዝናናት ሊኖር ይችላል።ያ ብርቅ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ትናንትናም ዛሬም በየቀኑ ተሰብስቦ መዝናናቱና ማውካካቱ መበራከቱ አስገርሞታል።ነገሩ የአሜሪካ ስርዓቷ ራሱ ብዙ ጊዜን በመዝናናት ለማሳለፍ የሚያመች አይደለም።
ግሮሰሪውን የሞላው ቦርጫም እና ደረቱ ያበጠ ጎረምሳ በሙሉ፤ የልጅነታቸውን ጊዜ ከማውራት አልፈው ፖለቲካውን ወደ ማቡካት ውስጥ ገብተዋል።ድሮ ከሰው ጋር ለመገናኘት የብሔር ጉዳይ አይነሳም።ስለዚህ የድሮዎቹ ጓደኛሞች ከተለያዩ ብሔሮች ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ሃይማኖቶችም የተወጣጡ ናቸው።ቅድሚያ ደስታቸውን ያሟሟቀው የተገኝ ወደ አገር ቤት መመለስ ቢሆንም ሰሞኑን የአትሌቶቻችን ድል ታክሎበት ሁሉም ተፍነክንኮ ነበር።
ሁሉም ያለልዩነት የተሰማቸውን ደስታ እየገለፁ እየተሳሳቁ ሲያውካኩ ቆይተው የደስታ ስሜት ለቀቅ እያደረጋቸው ወደ ፖለቲካ ወሬ ሲገቡ ግን ፅንፍ ይዘው መከራከር ጀመሩ።‹‹ነጋሪ የሌለው የታማ አይመስለው›› እንዲሉ አንዱ ሌላውን እየናቀ ይሔኛው ብሔርማ የኢትዮጵያ ጠላት ነው።ያኛው ብሔር ደግሞ ዓላማው ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።ይሔኛው ብሔር ጦርነት አይችልም።ይሔኛው ብሔር ጦርነት እና አሸናፊነት የግሉ ነው።እየተባባሉ መጨቃጨቅ ጀመሩ።ጓደኛሞቹ ተገኝን ሰብስበህ እንደጋበዝከን በተራችን እንጋብዝህ ብለው ጠርተው ስለጎተጎቱት ቢገኝም ከመደሰት ይልቅ በድርጊታቸው ጭንቀት ውስጥ ገብቷል።
ተገኝ ከ20 ዓመት በፊት አገር ለቆ ሲወጣ ከጓደኞቹ ጋር ይውሉ የነበረው ኳስ ሜዳ ላይ ሲጫወቱ ነበር።አሁን መብሰል ማደግ መጣና ዕድሜ በመግፋቱ የጓደኝነት ማሳለፊያ ቦታ እግር ኳስ ሜዳ ላይ ሳይሆን አንዲት ጠባብ ግሮሰሪ ውስጥ ተወተፈ።ይህ ከዕድሜ ጋር የመጣ ለውጥ ጤና ላይ ጉዳት በሚያስከትል መልኩ የተቀየረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ፅንፍ ይዞ የራሱን ብሔር እያሞገሰ ሌላውን እያንኳሰሰ ማቅራራቱ ሌላው ለተገኝ ጓደኞቹን አውርዶ እንዲያያቸው አስገደደው።
አጠር ብሎ ራሱ ገባ ያለው ቦርጫሙ ጌታቸው ከጓደኛሞቹ መካከል ከመቀመጫው ብድግ ብሎ አጨበጨበና ‹‹ሰንበሌጥ ለቤት ቀሚስ ለባለቤት›› እንደሚባለው ሁሉ ለሁሉም ባለቤት አለው።እንዲሁ ለአንዱ የሚገባውን ለሌላው መስጠት መዘዙ ብዙ ነው።ሥልጣን የሚገባው እና አገዛዙንም የሚችለው አንድ ብሔር ነው አለ።ይህ ብሔር ደግሞ ‹‹ እንቶኔ ›› ነው፤ ሲል አንዳንዶቹ በተቀመጡበት እግራቸውን አንስተው አንዳንዶቹ ደግሞ ቆመው እያውካኩ አጨበጨቡ።የተስተጋባው ጭብጨባ ገሚሱ በደስታ እና በድጋፍ ድምፅነት ሲሆን፤ ገሚሱ ደግሞ በብስጭት ነበር።
ሌላኛው ረዘም ብሎ ትከሻው የሰፋው ባለአፍንጫ ጎራዴው እርሱን ተከትሎ፣ ‹‹እኔ ደግሞ ልንገርህ ‹ለራሱ አብዷል አትርሳኝ ብሎ ተከትሎታል› እንደሚባለው እናንተ አንዱ ብሔር የራሱን ጉዳይ ሳይጨርስ ከኋላ እየተከተላችሁ ‹ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ› እያላችሁ ስታስጨንቁ ዋጋችሁን እያገኛችሁ ነው፡፡›› ሲል ሁሉም እየሳቀ ማውካካቱ ቀጠለ፡፡
ተሰማ መንግስቴ በበኩሉ፤ ብድግ ብሎ፣ ‹‹ ችግሩ እኮ አልገባችሁም፡፡›› አለ።‹‹እንግዲህ ሹመኛው ከገባህ አስረዳና›› አሉት። ‹‹ሰንበሌጥ ለቤት ቀሚስ ለባለቤት›› ባዩ ጌታቸው፣ ስልጣን የመላ ሕዝብ መሆኑን አያውቅም፤ ቢያውቅም አያምንም።ስልጣን የአንድ ብሔር አይደለም፤ የመላ ሕዝብ ነው።አንድ አካል መንግስት የሚሆነው በህዝብ ይሁንታ ብቻ ነው።አንድ ብሔር ስለፈቀደ እና ስላልፈቀደ አይደለም።አንድ ብሔር መፍቀድ አለበት ተብሎ ሊጠቀስ ከቻለም ብዛት ያለውን ሕዝብ የያዘው ብሔር መሆን አለበት።
ስለዚህ በሁሉም ብሔር ተፈቅዶ የተያዘ ስልጣንን ‹እከሌ› የተባለው ብሔር ካልያዘው ሊሳካለት አይችልም ብሎ ዓይነት ትዕቢት ብዙ አያስኬድም ሲል፤ ተገኝ በተሰማ መንግስቴ ሃሳብ መስማማቱን ለመግለፅ ጭንቅላቱን በአዎንታ መልክ ነቀነቀ።‹‹ሰንበሌጥ ለቤት ቀሚስ ለባለቤት›› ያለው ጎልማሳ ግን ብድግ ብሎ ከመናገር አልፎ ጠብ አማረው፤ ብድግ ሲል፤ ግራ እና ቀኝ የተቀመጡ ጓደኞቹ እጁን ይዘው አስቀመጡት።
ሌላኛው ተነሳ፤ ‹‹ግልፅ ግልፁን እንነጋገር፤ እኛ መቼም ፖለቲካው አይመለከተንም ብለን ወደ ንግዱ ዞረን እንጂ አብሮን የተማረው ለማልኝ የተባለው ገና ተማሪ እያለን የድሮ ካድሬ ትዝ አይላችሁም? የወረዳ ስልጣን ላይ ወጥቶ ሕዝብ ከማገልገል ይልቅ በተቃራኒው ዓለምን የተቆጣጠረ መስሎት በቀደም ሳየው ዓየር መቅዘፍ ጀምሯል።ሰዎች ሲያወሩም ከሥራው በላይ ጉራው መከራ ሆኗል።አብሮን ያለውን ተሰማ መንግስቴን የእዚህ ብሔር ተወላጅ ስለሆንክ ስልጣን አይሆንላችሁም አልከው ታዲያ ለማልኝ የእናንተ ብሔር ተወላጅ ሆኖ እንደአቅሙ ስልጣን አላጣም።ነገር ግን መቼ አስተካክሎ አስተዳደረ? እንኳን አገር ወረዳም በቅጡ ማስተዳደር አቅቶታል።ጉዳዩ ብቃት እንጂ ብሔር አይደለም።በብሔር ከማሰብ ይልቅ በብቃት ላይ ብቻ ብንነጋገር ይሻላል›› ሲል፤ ሌላኛው በበኩሉ ሃሳብህ ትክክል ነበር።ነገር ግን ችግሩ እኮ ስልጣን በብሔር እንጂ በብቃት ባለመሆኑ ነው።ይህንን ደግሞ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው በማለት የጌታቸውን ሃሳብ በመደገፍ ጉዳዩን አጀንዳ አደረገው።
ሌላኛው ቀጠለ፤ ‹‹ሰንበት ሲጠም ከአርብ እሮብ ይብሳል ይባላል።ጊዜው የኢትዮጵያ ሰንበት ነው።መልካም ጊዜ ነው ብሎ ተስፋ ያላደረገ አልነበረም።ነገር ግን እንዲያው አሁን እርስ በእርሳችን የከፋንበት ጊዜ ሆነ።ሁላችንም ራሳችንን ማሸነፍ አቅቶን በብሔር እና በሃይማኖት ላይ ተለጥፈን የጋራ ህልም አጣን።ይህ ሁሉ ቀድሞ የብሔር ነፃነት በሚል ተዛብቶ የተዘራው ዘር ተጣሞ ፍሬ በማፍራቱ ነው።አንዱ ሌላውን እያጥላላ አንዱ ሌላውን እያሳደደ የሚገድልበት ጊዜ ላይ ደረስን›› አለ።
ጌታቸው ተነሳ፤ ቀዝቀዝ ብሏል።አንድ ተረት እንድናገር ይፈቀድልኝ አለ።ሁሉም በጭብጨባ መፍቀዳቸውን አሳወቁ።ስካር ላይ ለመድረስ ትንሽ ቀርቶታል።በየመሃሉ ስቅ ይለዋል።ተረቱን ጀመረ።‹‹እረኛ ሆኖ የኖረው የባላገር ልጅ ዕድሜው ለእርሻ ደርሷል ተብሎ ከአባቱ ጋር ለማረስ በሬ ጠመደ።አባት በሬ እንዴት እንደሚጠመድ በደንብ ስላሳዩት እርሱም አባቱ እንዳሳዩት በሥነስርዓት ለመጥመድ አልተቸገረም።አስተራረሱንም አሰልጥነውት ኖሮ በደንብ አረሰ።ቀድሞም አልፎ አልፎ ይሠራው የነበረው ዘር የመዝራት ስራንም በብቃት ተወጣ።ከዘር በኋላ ስራውን የጨረሰ መሰለው።አባት ዕድሜያቸው ገፍቶ ደክሟቸዋልና ሲያርስ ቢመለከቱትም ከዛ በኋላ ያለው አያቅተውም ብለው ችላ ብለውታል።ማጨዱም ቢሆን በደቦ ይሠራል ብለው አልፈውታል፡፡
ልጁ እርሻውን መልሶ ሳያየው ሰነበተ።አባት የተዘራውን ለመጎብኘት ሲሔዱ ከእህሉ እኩል አረም በቅሎ አዩ።ልጃቸውን ጠርተው ጥያቄ አቀረቡለት።‹‹ምን ሆነህ ነው?›› አሉት።እኔ ያሰብኩት የተዘራው እንደሚበቅል ነው።አረሙም የሚነቀለው መጨረሻ ላይ ስለመሰለኝ ነው በማለት መልስ ሰጠ። አባት ‹‹ልጄ›› አሉ።‹‹አረም ሳይፈለግ አንደሚበቅለው ሁሉ ባለጋራም ሳይታሰብ ሊያጋጥም ይችላል።አረም እና ጠላት ሳይዘሩት በድንገት የሚበቅል መሆኑ መዘንጋት የለብህም።
በሕይወትህ ለሥራህ ውጤታማ የሚያደርግህን መንገድ ስትፈልግ በሔድክበት እንቅፋት እንደሚኖር አትዘንጋ።እንቅፋቱን ከስር ከስር አንሳ።እንቅፋት የአንተ ጠላት ነው።አረምም ተመሳሳይ ነው።ድካምህን ከንቱ የሚያደርግብህ ቀበኛሕ ነው።ስለዚህ እስኪያድግ እና ለመነቀል እስኪያስቸግር እህሉን እስኪውጠው ጊዜ አትስጠው።ከስር ከስር ንቀለው።ሳይታሰብ በቅሎ ስለሚያድር ከእርሻህ ላይ አይንህን አትንቀል።ጠላትም በተመሳሳይ መልኩ ሳይታሰብ የሚመጣ በመሆኑ ዘወትር ዙሪያህን አማትር፤ ጠላት እንዳይኖርህ አስተውለህ ተንቀሳቀስ፤ ጠላት ካለህም በመካከላችሁ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መላ ምት›› አሉት።የእኛ ችግር የዚህ ተረት ቢጤ ነው፡፡›› አለ።
ብዙዎቹ ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም።እናም ‹‹አልገባንም›› አሉት።እኛ ኢትዮጵያን ለመመስረት ብዙ መስዋዕትነት ከፍለናል።ስልጣን ይዘን ለብዙ ዘመናት ገዝተናል።ሆኖም ግን በአገዛዛችን ዘመን ተዘናግተን ብዙ ጠላት ሊኖረን እንደሚችል አላሰብንም።አባቶቻችንም ሲያስተምሩን ጨርሰው ስላላስረዱን አሁን ላይ ብዙ ጠላት አፍርተናል።ትልቁ ችግር ይሔ ነው።ቅድም ዋጋችሁን እያገኛችሁ ነው የተባልነው በዚሁ ምክንያት ነው ብሎ አረፈው።
ጀማል ተነሳና፣ ‹‹እና ስልጣን መያዝ ያለበት በኛ ብቻ ነው እያልከን ነው›› ሲለው ጌታቸው፣ ‹‹ እንክት!›› ሲል ምላሽ ሰጠ።ቀጠለና ‹‹እናንተ ንግዱ ይበቃችኋል፡፡›› ሲለው፤ ሁሉም ሳይደማመጥ መንጫጫት ጀመረ።የተገኝ ጓደኞች የሚወራወሩት ቃላት አንዱ ሌላውን እንዲቀየም፤ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እንዲመለከተው የሚያደርግ ይመስላል።ቀድሞ ተፋቅረው፣ ተስማምተውና ተባብረው በእኩልነት ይኖሩ የነበሩ ጓደኛሞች አሁን ግን ውስጥ ውስጣቸው በቅራኔ እየተሞላ መቆሳሰል ጀምረዋል።
ጌታቸው ተነሳ፤ ‹‹ንፁሃንን መፍጀት በፍፁም አያዋጣም።በእኛ ጥፋት ሌሎችን መጉዳት ያሳዝናል፤ ይሔ ያበሳጫል።ይሔ ብዙ ያስብላል።እኛ ስላልሞትን የሞተ ሰው የሌለ ከመሰለን ተሳስተናል፡፡›› አለ።
ተገኝ በበኩሉ፤ የሰው መሞት እርግጥ ያሳዝናል።ነገር ግን ፅንፍ ይዞ እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ሙጭጭ ማለት፤ ለራስ ብቻ በማሰብ የሌሎችን መብት መርገጥ ለማንም አያዋጣም።እንዲያውም ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል።ነገር ግን መባል ያለበት የሁሉም ሰው መብት ይከበር ነው አለ።
ጀማል በበኩሉ፤ ‹‹እኩልነት ይኑር ማለት ሁሉንም ያስማማል።ነገር ግን ለእኔ የተለየ መብት ይሰጠኝ፤ በዝባዥ ልሁን፤ ስልጣን የሚገባው ለእኔ ብቻ ነው ማለት ካለ ተበዝባዥም ተጨቋኝ ነኝ ሊል ብቻ ሳይሆን ጭቆናውን ከአናቱ ላይ ለማራገፍ ሊሞክር ስለሚችል መፍትሔው ማንም በዝባዥ ማንም ተበዝባዥ፤ ማንም ጨቋኝ ማንም ተጨቋኝ ሳይሆን ሁሉም በሕግ እኩል የሚሆንበት ሁኔታን ማመቻቸት ብቻ ነው።ለዚህ ሁሉም ሊታገል ይገባል።
የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብት በትክክል ሊከበር የሚችለው ብሔር ላይ ተንጠልጥሎ የአንዳንድ ስልጣን ወዳዶች እና የውጪ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ፍላጎት ለማሟላት ብሔር ስር ተወሽቆ መሆን የለበትም።ስለኛ ብሔር ብቻ ሳይሆን ስለሌሎችም የኢትዮጵያ ብሔሮች እንቆርቆር።ስለሞትም ሆነ ስለ ጉዳት ስናነሳ ብሔር ለይተን ሳይሆን የሰው ልጅ ለምን ይህ ድርጊት ይፈፀምበታል? ብለን መሆን አለበት።
ግማሹ አርሶ ዘርቶ አጭዶ ሲያዘጋጅ፤ ሌላው ጭኖ አጓጉዞ ለገበያ ሲያቀርብ ሌላው ደግሞ በሌላ በኩል የሚገባውን አገልግሎት ሰጥቶ ከተገልጋይ ተገቢውን ክፍያ ሲቀበል፤ ሰው በመስራቱ ብቻ እያገኘ ሲሔድ አንዱ ከአንዱ ጋር በሚገባው ልክ ሲተሳሰር ሁሉም ትክክል ይሆናል፡፡›› ብሎ ቁጭ ሲል፣ ጓደኛሞቹ ለጀማል አጨበጨቡ፡፡
ጭብጨባው ሲያበቃ ጌታቸው፣ ለጀማል ‹‹ከጦርነት እና ከስልጣን ሸሽታችሁ፤ ንግድ ላይ ዘመናችሁን አሳለፋችሁ።አሁን ደግሞ ከንግድ ዘርፍ ሲያባርሯችሁ ደህና ዲስኩረኛ ወጥቷችኋል።በቃ በቀጣይ ምርጫ ስልጣኑን ጀባ እንላችኋለን፡፡›› ሲል ጓደኛሞቹ በድጋሚ በጌታቸው በኩል ይሁኑ በጀማል በኩል ሚናቸው ሳይለይ እየሳቁ እና እያጨበጨቡ ደግፈናል ሲሉ አውካኩ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2014