አዲስ አበባ:- የንግድ ሥርዓቱ በውድድር ላይ የተመሰረተና የዘርፉ አንቀሳቃሾችም በተጠያቂነት መንፈስ እንዲሠሩ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የንግድ ውድድርና ሸማቾችች ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ ትናንት ለሸማቹና ለንግዱ ማኅበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በሰጠበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሚካኤል ተክሉ እንዳሉት፤ መንግሥት የንግድ ሥርዓቱን በውድድር እንዲሁም በጥራት ላይ የተመሰረተ እዲሆንና አምራቾችም ሆኑ ነጋዴዎች በተጠያቂነት መንፈስ ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ እየተሠራ ነው ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ለንግዱ ዘርፍ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር መስፈን መንግሥት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከማድረጉ በላይ ባለሀብቶቹ ጠንካራ ውድድር ባለበት ገበያ ላይ ገብተው አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
ፀረ ወድድር የሆኑ የንግድ ተግባራት የሚፈፀሙበት፣ የሸማቹን መብትና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ጥራት የጎደላቸው ምርቶች ለገበያ የሚቀርቡበት፣ ለምርቶችና አገልግሎቶች የተጋነነ ዋጋ የሚጠየቅበት፣ አቅርቦትና ፍላጎት እንዳይጣጣም የሚሠራበት በአጠቃላይ ገበያው በተወሰኑ አካላት ቁጥጥር ሥር የሚወድቅበትና ተወዳዳሪ ነጋዴዎች ከጨዋታ ውጭ የሚሆኑበት ሁኔታ እየተስተዋለ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
እነዚህን ችግሮች ለማስወገድና ዘርፉ በቀጣይ በኢኮኖሚው ላይ ሰፊ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አዋጅ ቁጥር 813/2006 ተቋቁሟል፤ በዚህ አዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረትም የተለያዩ ችግር ፈቺ እንቀስቃሴዎችን እያደረገም እንዳለና ለነጋዴው እንዲሁም ለሸማቹ ይህንን መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀት እንደሚገኝበት ጠቁመዋል።
በንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለሥልጣን ምርመራና ክስ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌትነት አሸናፊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ፣ አባል ለመሆን ዋጋንና ጥራትን መሰረት አድርጎ መወዳደር እንደሚያስፈልግ፣ ይህም የተቋሙ አባል ስንሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ጠንካራ የንግዱ ማህበረሰብ በጥራትና በተሻለ ዋጋ ከሚያቀርቡ የንግድ ድርጅቶች ጋር መፎካከር እንደሚቻል አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ ጠንካራ የንግድ ውድድርን ለማሸነፍ መንግሥት ከአሁኑ ሕግና ፖሊሲ እየቀረፀ መሄድ እንዳለበት፤ ኢንዱስትሪዎችም የመንግሥትን ሕግና ፖሊሲ ከመጠበቅ ባሻገር ራሳቸውን በመቆጣጠር ፉክክራቸውን በዋጋ፣ በጥራትና በአማራጭ ላይ ብቻ አድርጎ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አብራርትዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
እፀገነት አክሊሉ