ጦርነት ሰዎችን ለከፍተኛ ሥነ ልቡናዊና አካላዊ ስቃይ የሚዳርግ መሆኑ ነጋሪ አያሻውም። በተለይም በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ተዘርዝሮ የማያልቅ እንደሆነም እንዲሁ። ዘላለማዊ ጠባሳን የሚጥልና ቀና ብለው እንዳይሄዱ የሚያደርግም ነው። ለዚህ ደግሞ ጾታዊ ጥቃት ብቻ ማሳያ ነው። ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ይዞ ይመጣባቸዋል። ጉዳዩን ለማንሳት ያስገደደን ደግሞ የዛሬ አመት ገደማ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በተደረገ ጦርነት የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች በሴቶች ላይ የደረሰው ስቃይና መከራ ነው። በዚሁ ጦርነት ብዙ ጠባሳ ከጣለባቸው ከተሞች አንዷ ደሴ በመሆኗ በዚህች ከተማ ሴቶች ምን አይነት ፈተና እንዳሳለፉ አንድ ባለታሪክን መነሻ በማድረግ ልናወጋችሁ ስለፈለግን ነው።
አንድ ዓመት ከመንፈቅ ባስቆጠረው ጦርነት ብዙ ነገሮች እንደአገር ተከስተዋል። ብዙዎችን የሕይወት ምስቅልቅል ውስጥ ከቷቸዋል። ተረጋግተው እንዳይቀመጡም አድርጓቸዋል። ከዚያ የትም አንሄድም ብለው ለመቀመጥ የሞከሩት ደግሞ በረሃብ ተጠብሰዋል። ለልጆቻቸው የሚያቀምሱት አጥተዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬ የሴቶች አምድ እንግዳ ያደረግናት ወይዘሮ ስመኝ በቀለ አንዷ ነች። ጦርነቱ ከሴቶች ጋር በተያያዘ ያስከተለውን ችግር ራሷን አብነት አድርጋ አጫውታናለች።
ስመኝ እንደምትለው፤ ጦርነት ወንድ ሴት ላይል ይችላል። ምክንያቱም ሁሉንም ያጠፋል፤ ያሰቃያል። ከአቅምና ከተፈጥሮ አንጻር ሲታይ ግን ሴቶች ላይ የበለጠ በትሩ ይጠነክራል። ከዚህ አንጻር ጦርነት በደሴ ከተማ ብቻ በሴቶች ላይ የፈጠረው ቁስል በቀላሉ የሚሽር አይደለም። ሴቶች የቤት ውስጥ ኃላፊ እንደመሆናቸው በጦርነት ወቅትም ቢሆን ቤተሰቦቻቸውን አብስሎ የማብላት ባህላዊ እዳ የተጣለው በእነርሱ ጫንቃ ላይ ነው። ብቻቸውን ሆነው ብዙ ተግባራትን ያከናውናሉ። የቤተሰቡ ቁጥር ሲሰፋ ደግሞ ድካማቸውም የዚያኑ ያህል ይከብዳል፤ ውሃ መቅዳት፣ እህል ማስፈጨት፣ ማገዶ መስበር፣ ልብስ ማጠብ፣ የቤት ንጽህናን መጠበቅ፣ ልጅ ማሳደግ፣ በአመዛኙ በሴቶች ሚከናወኑ ተግባራት ናቸው፤ በጦርነት ወቅት እነዚህን ተግባራት ማከናወን አንድ ፈተና ቢሆንም ጦርነቱ በርካታ ነገሮችን ማውደሙን ተከትሎ የሚፈጠረው የመሰረታዊ ፍላጎቶች እጥረት ሌላው ፈተና ነው።
በደሴና አካባቢዋ ጦርነት በነበረበት ወቅት ችግር ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ የመብራት አለመኖር ነው። እህሉ እንደምንም ብሎ ቢገኝ እንኳን ማስፈጨት አይቻልም። ለማብሰል ደግሞ እንጨት መስበር ወይም መግዛት ግዴታ ነው። ይህንን ለማድረግም እድል አይኖርም። ስለዚህን ወቅት ታዲያ ቤት ያለው ሰው በሙሉ በረሃብ አለንጋ ይገረፋል፤ ስለዚህ ሴቶች በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆነው ቤተሰቦቻቸውን ለማቅመስ መታተራቸው አይቀርም።
ሌላው ብርሃን የማግኘት ጉዳይ ሲሆን፤ ይህንን ለመሸፈንም ሻማ አለያም ክብሪት መግዛት ያስፈልጋል። በጦርነት ወቅት ሱቆች አገልግሎት ስለማይሰጡ አንድ ክብሪት በ20 ብር እስከመሸጥ ደርሶ ስለነበር ሕይወት በይበልጥም በሴቶች ላይ አስቸጋሪ ሆኖ እንደነበር ታስታውሳለች።
ደሴ ላይ ሌላው አስቸጋሪ የጦርነት ገጽታ የውሃ እጦት ሲሆን፤ ለመጠጥ የሚሆን ውሃ ለማግኘት እስከ 50 ብር ድረስ አውጥቶ መግዛትን ይጠይቅ ነበር፤ እሱም ከተገኘ። ይህ ደግሞ ለሴቶች ምን ያህል ከባድ እንደነበር መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም ሴት ልጅ ንጽህናዋን ለመጠበቅ ከሌላው በበለጠ ውሃ ያስፈልጋታል። ግን በነበረው ሁኔታ ይህን ማድረግ አዳጋች ነበር። ከእርሷ በላይ ለሌሎች የምታስበው እናት የምትገዛውን ውሃና ምግብ ጭምር ለሌላው እየሰጠች ስትሰቃይ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትዝታዋ መሆኑን ታነሳለች።
በጦርነቱ ሌላው ከባዱና ልትቋቋመው ያልቻለችው ነገር የጾታዊ ጥቃቱ ጉዳይ እንደነበር የምታነሳው ስመኝ፤ ስቃዩ ከባድ መሆኑን ታወሳለች። እርሷ በአካል ባታያቸውም ይህ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች በአካላዊም በስነልቦናም መጎዳታቸውን ትገነዘባለች። ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መጠቃታቸው ሳያንስ ማህበረሰቡ ስለሚጠቋቆምባቸው የልብ ስብራታቸውን በቀላሉ የሚጠግንላቸው አይሆንም። በዚህም ራሳቸውን የሚያጠፉ እንደነበሩም ሰምታለች።
ሌላው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ያለው ሁኔታ ሲሆን፤ ኑሮን ለመግፋት ተንቀሳቅሶ መሥራት ግድ ቢሆንም ከደረሰባቸው ስቃይና ጉዳት አንጻር እንደልብ ለመውጣት ተቸግረው እንደነበር ትናገራለች። አሁን እያደር ነገሮች እየተረጋጉ ሲሄዱ ሁኔታዎች ቢቀየሩም ጦርነቱ እንዳበቃ አካባቢ ግን በፍራቻ ብቻ ለርሃብ የተጋለጡ ጥቂቶች እንዳልነበሩ ታነሳለች። በዚያ ላይ ነጋዴው ጦርነት ተከሰተ በሚል ችግሮችን እየደረደረ በእቃዎች ላይ የማይገባ ዋጋን ይጨምራል። ሰላም ነው ቢባል እንኳን በአለማመን ውስጥ ያለንና ያልሰራን ሰው በዚህ መልኩ ማሰቃየት ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል። እናም የሴቶች ፈተና በዚህ መልኩ ቀጥሏል ትላለች።
ጦርነቱ ያሳረፈው ጠባሳ ቢኖርም በዚያ ውስጥ የሚሯሯጡና ኑሮን ለማሸነፍ የጣሩ ሴቶችም ጥቂቶች አልነበሩም የምትለው ስመኝ፤ የጦርነቱ አለንጋ ሳይበግራቸው ደፋ ቀና እያሉ ቤታቸውን የሞሉ፤ ልጆቻቸውን ያበረቱና ጠላት እንዲመከት መከታ የሆኑም ሴቶች ነበሩ። ቁስላቸው ባይድንም ሕይወት ይቀጥላልና ከፍራቻ ይልቅ በአለው መረጋጋት ውስጥ መሥራትን የመረጡም ጠንካራ የወደፊት ተስፋ አብሳሪ ሴቶች እንደነበሩ በዚያ ጦርነት ውስጥ እንደታዩም ታወሳለች።
እርሷም ብትሆን ጦርነቱ አበቃ፤ አሸባሪው ሕወሓት ደሴን ለቀቀ ሲባል ጀምራ የእለት ጉርሷንና የቤተሰቧን ጉሮሮ ለመሙላት 11 ሰዓት ወጥታ ምሽቱ ድረስ መሥራትን እንደጀመረች ታነሳለች። ምክንያቱም በአለው ሰላም ውስጥ ሆኖ ራስን መለወጥ ካልተቻለ ጦርነት ኖረም አልኖረም ህይወት ፈተና መሆኑ አይቀሬ መሆኑን ስለምታምን ነው። ከጦርነት ስሜት ወጥቶ አለመስራት ሌላኛውን የድህነት ጦርነትን በራስ ላይ መክፈት እንደሆነም ስለምታውቅ ነው።
ወሎ አማራው ከኦሮሞው ጋር ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ ጋር ተዋዶ እንጂ ተጣልቶ የማያውቅባት ምድር ናት። አሻግሮ የሚያሻግርም ሕዝብ ባለቤት ናት። እናም ዛሬ ይህ ቢገጥመንም ነገ የተሻለ ይኖራልና ከመቆዘም ይልቅ መሥራት ላይ ልዩ ትኩረታችንን ልናደርግ ይገባናል ትላለችም። ለዚህ ደግሞ ህመማቸውን እየቻሉ ቀደም ሲል የጀመሩትን ሥራቸውን አጠናክረው የቀጠሉትን ሴቶች አብነት እናድናደርጋቸው ስትልም ትናገራለች።
ከጦርነት በኋላ ወለዬዎች ምንም እንደማይበግራቸው ያየሁት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጭምር ከሕመማቸው በጥቂቱ እንዳገገሙ ወደ ሥራ መግባታቸው ነው። የቻሉትን ያህል እየተፍጨረጨሩ መሆናቸው ደግሞ ያስመሰግናቸዋልም ትላለች።
እርሷም ወደ አረብ አገር የሄደችው ያለ አባት ያሳደጓትን እናቷን ለማገዝ ነበር። በዚያ ግን ብዙ የሚያስተምሯትን ነገር አይታለች። አንዱ በችግር ውስጥ ሆኖ እንዴት መስራት እንደሚቻል ነው። ከጦርነት በኋላም ቀጥታ ወደ ሥራ ለመግባቷ መሰረት ሆኗታልና የሰው አገር ልምዷ እናቷ በአካባቢው ዘንድ የሚታወቀውና ደሴ የገባ ሰው ሳይሸምተው የማይወጣውን የወሎ ጭስ እየነገዱ ያሳዩዋትን ሥራ አጠናክራ እንድትቀጥልም ይህ ልምዷ አግዟታልና ታመሰግነዋለች።
ሥራው ዝቅተኛ ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም ማንም ተርቦበት ግን አያውቅም። ማንም ቢሆን አይታረዝበትም። ይልቁንም ለሌሎች ሰዎች ጭምር ተርፎ ሲደጎምበት ይታያል። ለዚህ ደግሞ ዋና መንስኤው በመረዳዳት ውስጥ አብሮ ከፍ ማለት እንዳለ ታውቆ መሰራቱ ነው። አሁንም ይህንን የመረዳዳት ባህል አንግበው ጦርነቱ የጣለውን ጠባሳ ማከም እንደሚገባ ትናገራለች።
እናቷን በሞት እንደተነጠቀች ስትሰማ ወደ አገሯ የተመለሰችው ስመኝ፤ ከአረብ አገር ስትመለስ ብዙም ገንዘብ አልነበራትም። የእርሷ ታናናሾችም አሉ። ስለዚህም እነርሱንም ሆነ ራሷን ለመደጎም መስራት እንዳለባት በማመን የእናቷን ሥራ አስቀጠለች። የእርሳቸውን መደብ በመረከብም ነው ጉልት ላይ ቁጭ ብላ የምትነግደው። በዚህ ሥራ የፈለገችው ግብ ላይ እንደምትደርስ እምነቱ አላት። ምክንያቱም ኢትዮጵያን፤ ወሎን የምታውቃት በመረዳዳትና አብሮ በመሻገር ነው። ስለሆነም ይህ ጊዜ ያልፋልና እርስ በእርስ መተካከሙ ላይ መበርታት እንደሚገባም ታስረዳለች።
ነጻነት ኖሮ በአገር ላይ ዝቅ ብሎ መስራት ከተቻለ መቼም ቢሆን ከፍ ማለት አይቀርም የምትለው ስመኝ፤ ጦርነቱ ያደቀቀውን ሀብታችንን ዳግም ለመመለስ ከሁሉም በላይ መሥራት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። መቆዘሙ መቼም ሊያነሳን አይችልም። የእኛን ማንነት የማይመጥኑ ብዙ ነገሮችን አይተን ይሆናል። ነገር ግን እነርሱንም መመለስ የምንችለው ሰርተን ብቻ ስንለወጥ ነውና ይህንን እልህ አስጨራሽ ፈተና በሥራ ማሸነፍ ይገባናልም ባይ ነች።
‹‹አሁን በአገራችን ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። እንዳለፈው የመተባበርና የመተጋገዝ ባህሉ እየቀነሰ መጥቷል። ነጋዴው ትርፉን እንጂ ሰውን እያሰበ አይደለም። በብሔር መከፋፈሉና የእኔ ታላቅ ነው ባዩም በዝቷል። የተቸገሩትን ማየቱም እንብዛም ነው።›› የምትለው ስመኝ፤ የራስ የተባሉት ሰዎች (ነጋዴዎች) ሕወሓትን አይዞህ የሚል ወኔን ሰጥተውታል። ዜጎች በኑሮ ውድነቱ እንዲታመሱ በማድረግም ለኑሮ ውድነቱ በር ከፍተዋል። ሆኖም አሁን ሊበቃቸው ይገባል። ለዛሬ ህዝቡን የአለአግባብ መዝብረው ያገኙት ኃብት ነገ ይብሉት አይብሉት እርግጠኞች አይደሉም።
ወሎ ማንም የተቸገረ ሰው መጥቶ ጠግቦ የሚመለስባት ምድር እንጂ። ይህንን ደግሞ ከጦርነቱ በኋላም መድገም ያስፈልጋል። አንዳንድ የውሸት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ ሰዎችን መቀበልን መተው አለብን። በፍራቻ ሕዝቡን ከማሸበር ይልቅ እንዲሰራ ማበረታታት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስም ይገባል። የዚህን ጊዜ ጦረኞችን ድል እንነሳቸዋለን። ይህንን ለማድረግ ቁርጠኛ እንሁንም ስትል ትመክራለች።
ወሎ እንግዳ ተቀባይ አገር ነው። ሴቶች ደግሞ ለዚህ ግንባር ቀደም ናቸው። መቀነታቸውን ፈተው፤ ቤት ያፈራውን አራግፈው እንግዳ ይቀበላሉ። ጦርነት ቤታቸውን ቢያራቁተውም ዛሬም የወለዬዎች እንግዳ ተቀባይነት አልነጠፈም።
አሁን ላይ የልብ ስብራቱ የአንድ አካል ብቻ አይደለም እንደአጠቃላይ ጦርነት በተካሄደባቸው ቦታዎች ሁሉ ያለ ነው። እናም ያንን ለማከም በልቶ ማደር ላይ በቅድሚያ መሥራት ያስፈልጋልና የቀደመውን የገበያ ድምቀት መመለስ ላይ መረባረብ አለብን። ተረጋግቶ የሚሰራ ማህበረሰብ እንዲኖርም ሕወሓት የሚፈልገውን የሽብር ወሬ ማራገብ የለብንም። ምክንያቱም ይህ ለእርሱ እንጂ ለእኛ ምግብ አይሆነንም ብላለች።
ጦርነቱን ከእነጣለው ጠባሳ መመከት የሚቻለው በአንድ ነገር ብቻ እንደሆነ የምትጠቁመው ስመኝ፤ በአንድነታችን ጠንክረን ችግራችንን በጋራ ስንፈታው ብቻ ነው። በተለይም ያልባሰበት ወደ ባሰበት ማየት ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በጦርነቱ ቤተሰብ ያልሞተበት፤ ያልተሰቃየበትና ያልታመመበት አለ ለማለት ያስቸግራል። ይህንን ማዳንና ወደቀደመ ማንነት መመለስ የሚቻለው ጉዳቱ የአንዱ ብቻ ነው ብሎ ባለመውሰድ ነው። የወንድሜ ሕመም የእኔም ነው ማለት ይገባል። የተጎዳን የተጎዳ ነውና ማከም የሚችለው ይህንን እናድርግ ምክሯ ነው።
ጦርነቱና ሴቶችን በተመለከተ የሴቶች መብት ተሟጋች፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ከለላ፤ የምክርና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት የሚታወቀው የሴቶች ማረፊያ እና ልማት ማህበር መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የሕግ ባለሙያዋ ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር በአንድ ወቅት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያሉትን እናንሳና ሀሳባችንን እናሳርግ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነት ሳቢያ የጥቃቱ ሰለባዎች ቁጥር ጨምሯል ወይም ቀንሷል ለማለት የተጠና የለም። ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ በጓዳ ይቀር የነበረው ችግር አደባባይ እየወጣ በመሆኑ መጨመሩን ያሳየናል። ሌላው ጦርነት ባለበት አካባቢ ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት የመጋለጥ ምጣኔ እንደጨመረ የሚያሳየው ደግሞ በየሆስፒታሉ የሚታየው የተጎዱ ሴቶች ብዛት ነው። የሚያደርሰው ጥቃት ከጦር መሣሪያ ከባድ ምት እንደማይተናነስ አይተናል ይላሉ።
የሴቶችን ጥቃት ግጭት ፈጣሪዎች ሳይቀሩ ይጠቀሙበታል የሚሉት የሕግ ባለሙያዋ፤ የጥቃቱ ነገር ገና በጣም ብዙ ሥራ እንደሚፈልግ ያነሳሉ። ለዚህም ማህበራቸው በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ይናገራሉ። ለዚህም እንደማሳያ የጠቀሱት ለሦስት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው መጎብኘታቸውንና አቅም በፈቀደ አስፈላጊውን የምክር እና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ነው።
ደሴ እና ወልደያ በሚገኙት በአቋቋሟቸው ማረፊያ ቤቶች ከአንድ ሺህ በላይ ሴቶችን ማገዝ እንደቻሉም ያስረዳሉ። ይህ ጦርነት በጣም አስከፊና ሰውን ለመርዳት እንኳን ያልተቻለበት ነው። እናም ያለማህበረሰቡ እገዛ ብዙዎች መዳን አይችሉምና ማህበረሰቡ በትንሹ እንኳን ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችን መንከባከብ መቻል አለበት። እኛም ምክራቸውን እውን አድርገን አገራችንን እናሻግራት በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014