የአገራችን ሰው «የዕለት ጉርሱን የአመት ልብሱን» ይላል ወግ ሲያወጋ። በዚህች ምሳሌያዊ አባባል ውስጥ የሚታየው አንድ ነገር ምን ያህል አነስተኛ ፍጆታ ተጠቃሚ እንደሆንን ነው። በኢትዮጵያውያን ቤት ውስጥ ብዙ ነገር መሰብሰብ የተለመደ አይደለም። የአቅም ማነስ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታችንም ባህላችንም መመጠንን ያበረታታል። በዚያው ልክ የገዛነውን ነገር ለረዥም ጊዜ የመጠቀም ልምድ አለን። በኢትዮጵያውያን ቤት ልብስም ሆነ ሌላ ዕቃ እንዲሁ ዝም ብሎ አይጣልም። ጠቀመም አልጠቀመም ለአመታት ይቆያል።
ይህ ከምዕራባውያን አኗኗር የተለየ ነው። የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም ተጠቃሚነትን ያበረታታል። ለኢኮኖሚው እና ለባለሀብቱ የሚያስፈልገው ያ ስለሆነ። ስለዚህ በሁሉም ነገር ላይ ብዛት ይበረታታል። እንደኛ ነገሮችን የሚለኩት በአመት አይደለም። በወቅት ነው። የበጋ ወቅት መጠቀሚያ፤ የክረምት ወቅት መጠቀሚያ፤ የመጸው ወቅት መጠቀሚያ፤ የጸደይ ወቅት መጠቀሚያ አላቸው። ልብስም ላይ ተመሳሳይ ነው። ለየወቅቱ የራሱ የሆነ ልብስ አለው። እኛ ጋር ልብስ በአመት አንዴ ነው። ያቺው ልብስ በጋ ትለበሳለች፤ ክረምት ሲመጣ ጋቢ ጣል ይደረግበታል። አከተመ።
አሁን አሁን ግን ከተሜነት ሲስፋፋ ልብስን በተመለከተም እንዲሁ ለውጦች እየመጡ ነው። ሰዎች ብዙ ልብስ መግዛት ጀምረዋል። ለመሆኑ ሰዎች ምን ያህል ልብስ ይጠቀማሉ የሚለውን በእኛ አገር ብዙም ጥናት ባይሠራበትም በሌሎች አገራት ግን ጥናት ተደርጎበት አንዳንድ መረጃዎች ተገኝተዋል።
ኮንሰምፕሽን ኤንድ ኢንቫይሮንመንት የተባለ ድረ ገጸ (How many clothes we own and how many clothes we wear) በሚል ርእስ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከሁለት አመት በፊት አንድ ጽሑፍ አቅርቦ ነበር። በጽሑፉም ጉዳዩን አስመልክቶ በተደረገ ጥናት ሰዎች ምን ያህል ልብስ ይኖራቸዋል የሚለውን ለማወቅ አዳጋች ቢሆንም በመጨረሻ የተገኘው ግኝት ግን ብዙዎቹ በልብስ ቁምሳጥናቸው ውስጥ ካላቸው ልብስ ከ50 በመቶ በላዩን እንደማይጠቀሙበት ያስቀምጣል።
የጀርመኑ ሞቪንጋ የተሰኘ ድርጅት በ20 አገራት በሚገኙ ከ18ሺ በላይ ቤተሰቦች ላይ ባደረገው ጥናት እንዳረጋገጠው ከሆነ ብዙዎች ያላቸውን ልብስ በአብዛኛው አይጠቀሙትም። በዚህ በኩል በጥናቱ ከተካተቱ አገራት ልብሳቸውን ባለመጠቀም ቀዳሚዎች ቤልጄማውያን ናቸው። የቤልጅየም ሰዎች ካላቸው ልብስ 12 በመቶውን ብቻ የሚለብሱት ሲሆን እነሱን የሚከተሉት ደግሞ አሜሪካውያን ናቸው።
ካላቸው ልብስ 18 በመቶውን ብቻ ነው የሚጠቀሙት። በጥናቱ ከተካተቱት አገራት የገዙትን ልብስ በአግባቡ ይጠቀማሉ የሚባሉት ሩሲያውያን እንኳን ካላቸው ልብስ የሚጠቀሙት 53 በመቶውን ነው። አስገራሚው ነገር ግን ብዙዎቹ ያላቸውን ልብስ በአግባቡ እየለበሱ እንደሆነ ነው የሚሰማቸው።
ሰዎች የገዙትን ልብስ የማይለብሱት ለምንድን ነው ሲባል መልሱ ብዙ ነው። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶቹ ልብሶች ለአንድ ጉዳይ ብቻ ተብለው የተገዙ በመሆናቸው የመረሳት ዕድላቸው ሰፊ ነው። ዋነኛው ምክንያት ግን ብዙ ሰዎች የገዙትን ልብስ ስለማይወዱት ነው። ብዙ ሰዎች በአነስተኛ ዋጋ ልብስ ሲያገኙ ለመግዛት የማያንገራግሩ ሲሆን ነገር ግን እነዚያ ልብሶች በዋጋ የመርከሳቸውን ያህል በጥራትም ዝቅ ያሉ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ ሊለበሱ አይችሉም። ይህም ባለ ልብሶቹ ልብሱን እንዲጠሉት ያደርጋቸዋል።
ብዙዎች የዋጋውን መቀነስ እንጂ የልብሱን ጥራት አስበውበት አያውቁም። ስለዚህም ትኩረታቸው ከዋጋው ተነስቶ ወደ ልብሱ ሲዞር የገዙት ልብስ ብዙም እንደማያምር ወይም እንደማይመች ይገነዘባሉ። ያኔ እዚያው የልብስ ሳጥናቸው ውስጥ ይተዉታል። እንዳይለብሱት አላማራቸውም ወይም አልሆናቸውም፤ እንዳይጥሉት ገንዘብ አውጥተውበታል፤ እንዲሁ ሳጥን እያሞቀ ይቀመጣል።
ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ብዙዎቹ ልብሶች የአንድ ሰሞን ፋሽን በመሆናቸው ፋሽኑ ካለፈ በኋላ እነዚያን ልብሶች መልበስ መሳቂያ ስለሚያደርግ ነው። በተለይም የፋሽን ኢንዱስትሪው ዋነኛ ሥራ አዳዲስ ዲዛይኖችን ማስተዋወቅ እና በተቻለ መጠን ብዙ ገንዘብ መሰብሰብ እንደመሆኑ መጠን አምና ክረምት ላይ የተለበሰው ፋሽን ዘንድሮ ላይ ኋላ ቀር ተብሎ ከሱ የተሻለ ልብስ ይመጣና የተገዛውን ልብስ ከጨዋታ ውጪ ያደርገዋል። እንዲያም ቢሆን ብዙ ሰው ፋሽኑ ያለፈበትን ልብስ አይጥለውም፤ እዚያው ያስቀምጠዋል። ሌሎች ደግሞ ልብስ ከገዙ በኋላ የሰውነት ቅርጽ ለውጥ ይከሰታል።
ከስተው የገዙት ልብስ ሲወፍሩ ጥቅም ያጣል፤ ወፍረው የገዙትም ሲከሱ እንደዚያው። ይሄኔ ግን ብዙዎቹ ወደ ፊት ስወፍር ወይ ስከሳ እለብሰዋለሁ ብለው ያስቀምጡታል። ሌሎች ደግሞ እንዲሁ የመግዛት ሱስ ስላለባቸው የሚገዙ ናቸው። ለምን እንደፈለጉት ሳያውቁ ይገዛሉ፤ ከዚያም ቤታቸው ሲገቡ ልብሱን ይረሱታል። በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ የልብስ አምራቾች እና ነጋዴዎች አደገኛ ፈሊጥ አለ።
በ50 ዶላር የሚሸጠውን ልብስ ያለምንም ምክንያት 80 ዶላር ነው ብለው ዋጋ ይተምኑበታል፤ ከዚያም የማጣሪያ ሽያጭ ነው ይሉና 80ውን ሰርዘው በ50 ዶላር ውሰዱ ይላሉ። ሸማቹ በርካሽ አገኘሁ ብሎ ልብሱን ይገዛል። የገዛበት ዋነኛ አላማ በርካሽ ስላገኘው እንጂ ልብሱን ስላስፈለገው አይደለም። እንዲህ እንዲህ እያለ ልብሱ ይከማቻል። ከዚህ ሁሉ ግን የሚለበሰው ጥቂቱ ነው።
አሁን አሁን ይህ ልማድ እኛም ጋር ገብቷል። ኢትዮጵያውያንም በተለይ ከተሜው ሸማች እየሆነ ነው። አሁን እንደ ድሮው ልብስ በአመት አይደለም የሚገዛው። ልብስ የሚገዛው በተገኘው አጋጣሚ ነው። ድሮ ድሮ አልባሳት የአዘቦት እና የበዓል ነበሩ። የክት ልብስ በአዘቦት ቀን አይለበስም ነበር። አሁን ግን ሁሉም ቀን የክት ልብስ የሚለበስበት ሆኗል። ሁሉም ቀን የየራሱ ፋሽን አለው። ስለዚህም ሰዎች ልብስ በብዛት ይሸምታሉ።
ነገር ግን ምን ያህሉ ይለበሳል የሚለው ነው ዋነኛው ጥያቄ። ይህን የሚያመለክት ጥናት አገራችን ውስጥ መኖሩን እርግጠኛ ባንሆንም በቀን በቀን ልብስ ይቀይራሉ የሚባሉ ሰዎች እንኳን ካላቸው ልብስ ብዙውን እንደማይጠቀሙበት ለማወቅ ብዙ ምርምር አያስፈልግም።
ማጠቃለያ የሚሆነው ሰዎችን ልብስ አትግዙ አይባልም፤ ነገር ግን የገዛችሁትን ልብስ ተጠቀሙበት ነው። ይህ ለኢኮኖሚውን ለከባቢውም ጠቃሚ ነው። የማትጠቀሙትን ልብስ ደግሞ ሰብስባችሁ አትያዙ፤ ለቸገረው ስጡ በተለይም በዚህ የክረምት ወቅት ሰዎች ልብስን ይፈልጋሉና ለግሱ ዋነኛ የማጠቃለያ መልዕክት ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014