በአገራችን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት የተከሰተው ድርቅ በርካታ የክልሎቹን ዞኖች ለጉዳት በመዳረግ በሰውና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። የየክልሎቹ መንግሥታትና የተለያዩ ወገኖች ያደረጉትን ርብርብ ተከትሎ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ሞት ባይኖርም፣ ሰዎችን እስከ ማፈናቀል የደረሰና ለተረጂነት የዳረገም ሆኗል።
በከብት ሀብት በኩል ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ከየክልሎቹ የወጡ መረጃዎችን ዋቢ ያደረጉ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሱ ከብቶች አልቀዋል፤ በተቀሩት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ድርቁ በተለይ በክልሉ ቦረና ዞን የሚገኙትና የቦረና ከብቶች በመባል የሚታወቁትን በእጅጉ ጎድቷል። የቦረና ከብቶች ዝርያ እንደ አገር በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈለጉ ናቸው። የከብቶቹ ቁመናም የተለየና በብዙዎች አእምሮ ውስጥ አይነ ገቡ ናቸው። በአገር ውስጥ ገበያም ቢሆን የእዚህ አካባቢ ከብቶች ለምርጫ ሲቀርቡ ይሰማል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ አርብቶ አደር ሲሆን፣ የቀንድ ከብቶቹ የኢኮኖሚ መሠረቱ በመሆናቸው ከአብራክ ክፋይ ልጆቹ ባልተናነሰ ለከብቶቹ ልዩ ፍቅር አለው። ዞኑ ዝናብ አጠር በመሆኑ ከብቶቹን ይዞ ግጦሽና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀሳል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በዝናብ አጠር አካባቢነቱ ላይ ሌላ ችግር አስከትሎበታል። በድርቅ ተጠቅቷል። በድርቅ በመጠቃቱ የተነሳ የትም ሄደ የት ለከብቶቹ የሚሆን ውሃም ሆነ ግጦሽ ማግኘት አልቻለም። ይህ የሆነው ደግሞ የዝናብ እጦቱ ለአንድ ወቅት ብቻ የተከሰተ አለመሆኑ ላይ ነው። ለተከታታይ አመታት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመጣሉ አካባቢው በድርቅ ተጠቅቷል። ድርቁ በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት ከፍቶ ከብት አርቢውን ማኅበረሰብ በእጅጉ ጎድቶታል። አርብቶ አደሩ በርካታ ከብቶቹን አጥቷል፤ የተረፉትም ቢሆኑ ክፉኛ ተጎድተዋል። የሰብል ምርት ፊቱንም ቢሆን ብዙም የሚታሰብ አይደለም።
ችግሩ በመክፋቱ የተነሳም በርካታ አርብቶ አደሮች ከቄያቸው ተፈናቅለው መጠለያ ገብተዋል፤ እርዳታ ተቀባይ ለመሆንም ተዳርገዋል። በመግቢያችን ቦረናን ለአብነት አነሳን እንጂ የክልሉ ምዕራብና ምሥራቅ ጉጂ ዞኖች፣ባሌ፣ ምሥራቅ ባሌ፣ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በከፊል ምሥራቅ ሸዋ በድርቁ በእጅጉ መጎዳታቸውን ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የክልሉ መንግሥት ሙሉ አቅሙን ተጎጂዎችን ለመታደጉ ሥራ አውሏል፤ ክልሎች መኖ ከማቅረብ አንስቶ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል። ድጋፍና ክትትሉ አሁንም አልተቋረጠም።
እየተደረገ ያለው ድጋፍ ችግሩን በምን ያህል እያቃለለው እንደሆነ፣ ስለድጋፉ ቀጣይነት፣ አሁን የምንገኝበት የክረምት ወቅት ደግሞ ለግጦሽ ሳር ምቹ ሁኔታ ስለሚኖረው አስተዋጽኦ እና ዝናቡን ተከትሎ የታዩ መሻሻሎች ስለመኖራቸውና ዝናቡን ለመጠቀም ያለውን ዝግጁነትና እየተከናወነ ስላለው ተግባር በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት መኖ ልማት አጠቃቀም ባለሙያዎች ከሆኑት ከአቶ ደመቀ መዝሙር እና አቶ አበራ ከተማ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ባለሙያዎቹ እንዳስረዱት፤ አካባቢዎቹ ከእርሻ ሥራ ይልቅ በከብት እርባታ ነው የሚታወቁት።በመሆኑም የማኅበረሰቡ ኑሮ የተመሠረተው ከብት በማርባት ነው። በተለይም ቆላማው የክልሉ አካባቢዎች ከብት አርቢዎች በስፋት የሚገኙባቸው ናቸው። በአብዛኛው ቦረና፣ ምዕራብና ምሥራቅ ጉጂ። ቦረና ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በከብት እርባታ የሚታወቁ ናቸው። አካባቢዎቹ ላይ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት በመኖሩ ዝናብ አጠር ተብለው የተለዩ ናቸው።
አቶ ደመቀ እንዳስረዱት፤ በዝናብ አጠር ከተለዩትና ችግሩ ጎልቶ ከታየባቸው የክልሉ ስምንቱ ዞኖች መካከል ጉዳቱ ጎልቶ የታየባቸው ቦረናና ምሥራቅ ጉጂ በከፊል፣ምዕራብ ጉጂ፣ምሥራቅ ሐረርጌና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅ ሸዋ በከፊል ናቸው። የዝናብ እጥረቱ በእንስሳቱ ላይ ያስከተለው የሞት ጉዳት ሙሉ ለሙሉና በከፊል በሚባል ደረጃ ይገለጻል።አካባቢዎቹ ዝናብ አጠር በመሆናቸው ከብት አርቢው ማህበረሰብ ለእንስሶቹ የግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር ባህሉም ልምዱም አለው።
በዚህ አመት ያጋጠመው የዝናብ እጥረት ግን ከአቅማቸው በላይ ሆኖበታል። በመጠኑም ቢሆን ማትረፍ የቻሉት የቆየውን ልምዳቸውን በመጠቀም እንስሶቻቸውን ይዘው ከመኖሪያ ቀዬያቸው ለቀው የግጦሽ ሳርና ውሃ ለማግኘት በመሄድ ባደረጉት ጥረት ነው።ለአብነትም ምሥራቅ ባሌ ላይ የነበሩት ከፍ ወዳለ ስፍራ ወደሚገኙት ባሌና ሐረርጌ፣ የቦረና አካባቢዎች ደግሞ የደቡብ ክልሉ ኮንሶ አካባቢ በመሄድ ከብቶቻቸውን ከእልቂት ለማትረፍ የሚችሉትን አድርገዋል። እንዲህ ያለውን መንገድ ያልተጠቀሙት ናቸው በጣም የተጎዱት።
የዝናብ እጥረት መከሰት ከደን መመናመን ጋር የሚያያዝበት አጋጣሚ በመኖሩ እንዲህ ያለው ሁኔታ አካባቢው ላይ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ ላለመጣሉ ምክንያት ሆኖ እንደሆን አቶ ደመቀ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በአካባቢዎቹ የሰብል እርሻ ሥራ የተለመደ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ደን መንጥሮ ለእርሻ የማዋል ባህል የለም ይላሉ። በመሆኑም ችግሩ ከደን መመናመን ጋር የተያያዘ አይደለም፤ ከምሥራቅ አፍሪካ የሰሀራ በረሃ ወላፈን ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ተጋላጭነት ነው ሁኔታውን አስከፊ ያደረገው ሲሉ ያብራራሉ።
በዝናብ እጥረት ምክንያት በተከሰተው ድርቅ በአካባቢዎቹ የደረሰውን ጉዳት የሚከታተል ከተለያዩ ክፍሎች የተውጣጣ አባላት የተካተቱበት የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደመቀ፣ ሙሉ መረጃውን ማቅረብ ባይቻልም ጉዳቱ አካባቢን ለቆ እስከ መሄድ ደረጃ የደረሰ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ፤ መንግሥትም በአካባቢዎቹ የደረሰውን ጉዳት እንደተገነዘበ ተጋላጭ በሆኑት አካባቢዎች ለመድረስ ጥረት አድርጓል። በተለይ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ በተጎዱት አካባቢዎች ላይ ርብርብ አድርጓል። ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቀልበስ ባይቻልም ለመቀነስ ተከታታይ ሥራዎችን ሠርቷል። የችግሩ ስፋትና የመንግሥት አቅም ውስን መሆን ድጋፉን ፈታኝ አድርጎታል።
በዚህ ወቅት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የመኸር የግብርና ሥራ የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው፣ የግብርና ምርቶች ተረፈ ምርት በግዥ እንኳ ለማግኘት ተግዳሮት ማጋጠሙን ይገልጻሉ፤ ተረፈ ምርቱን ለማግኘትም ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፤ ይህም ሆኖ ጥረቱ አልተቋረጠም ሲሉ ያብራራሉ። ረጂ አካላት፣ አርሶ አደሩና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በድጋፉ ከፍተኛ ርብርብ ባያደርጉ ችግሩን በመንግሥት አቅም ብቻ ለመፍታት አስቸጋሪ እንደነበር ተናግረዋል።
የከብት መኖ ወደ ተጎጂ አካባቢዎች ይጓጓዝ የነበረው ከመሀል አገር ከሱሉልታና ከባሌ አካባቢዎች ነበር። መኖ ሲቀርብ፣ ለመጠጥ የሚሆን ውሃ አቅርቦት ችግር ያጋጥማል። ውሃ በቦቴ በማጓጓዝ ለሁሉም ለማዳረስ ደግሞ አስቸጋሪ ነበር። ወራጅ ወንዝ በአካባቢዎቹ አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ ፈታኝ አድርጎታል።
ቦረና ዞን 13 ወረዳዎች አሉት። ወረዳዎቹን አቋርጦ የሚያልፍ ወንዝ ግን የለም።አማራጩ የግጦሽ ሳርና ውሃ ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች እንስሳቱን ይዞ መሄድ ነው።በተፈጥሮ ያጋጠመን ችግር ለመቋቋም የማይቻል በመሆኑ የነበረው አመራጭ አቅም የፈቀደውን ድጋፍ ማድረግ ነው። በዚህ መልኩ ሥራዎች ባይሠሩ ኖሮ ለተረፉት እንስሳት ተደራሽ መሆን አይቻልም ነበር።
የአካባቢው ችግር ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እየተደረገ ባለው ድጋፍ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ችግሩ ከአቅም በላይ ቢሆንም የክልሉ መንግሥት በመኖ ልማቱ የሚችለውን በማድረግ ድጋፉን አጠናክሯል።
አቶ ደመቀ እንዳስረዱት፤ ክልሉ በየአካባቢዎቹ የመኖ ልማት ሥራ በማከናወን ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በክልሉ መንግሥት ‹‹ላይቭስቶክ ፊድ ኢኒሼቲቭ ኦፍ ኦሮሚያ ሪጅን›› የሚል ፕሮግራም ተቀርጾ መጠነ ሰፊ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።በእስካሁኑ እንቅስቃሴም በቦረና ዞን ኤልወያ በተባለ ወረዳ ውስጥ የምንጣሮ ሥራ ተከናውኖ 60ሺ ሄክታር መሬት ላይ ለከብቶች መኖ የሚውል ልማት ማከናወን ተችሏል። ልማቱ የተከናወነው በወል መሬት ላይ ሲሆን ከዚሁ ሄክታር ላይ አንድ ዙር የለማ መኖ ተሰብስቧል።
በተጨማሪ በወረዳው ሰገን በተባለ ቀበሌ ላይ ደግሞ በ198 ሄክታር መሬት ላይ ልማቱ የተከናወነ ሲሆን፣ 30 ሄክታር በመስኖ፣ ቀሪው 168 ሄክታር በዝናብ ነው የለማው። በባሌ ዞን ደሎመና ወረዳ ውስጥ በወል መሬት ላይ 43ሺ ሄክታር በዝናብ በመልማት ላይ ይገኛል። 120 ሄክታር ደግሞ በመስኖ ለምቶ ምርት ተገኝቷል።
ጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ ውስጥ ሦስት ሺ 440 ሄክታር በወል መሬት ላይ፣ 66ሄክታር ደግሞ በገበሬ ማሳ ላይ በዝናብ እየለማ ይገኛል። በአርሲ ዞን በስድስት ወረዳዎች ውስጥ 125ነጥብ ሦስት ሄክታር ላይ ለምቶ ጥቅም ላይ ውሏል። በምዕራብ አርሲ ዞንም የመንግሥት ይዞታ በሆነው ሦስት መቶ ሄክታር ላይ እየለማ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በ40 ሄክታሩ ላይ የዘር ብዜት ልማት እየተከናወነ ይገኛል። በቀሪው 260 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ መኖ እየለማ ነው። በጥቅሉ በተቀረፀው ፕሮግራም ወይንም በኢኒሼቲቩ 107ሺ249 ነጥብ 3 ሄክታር የእንስሳት መኖ ልማት ተከናውኗል።
በዝናብ እጥረቱ በተከሰተው ድርቅ የተጎዱትን እንስሳት ለመታደግ በዚህ መልኩ እየተደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎን የዚህ የክረምት ወቅት የግጦሽ ሳር እንዲገኝ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰን ይህን ተከትሎ የታየ መሻሻል ታይቶ ስለመሆኑም አቶ ደመቀን ጠየቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ ይህ የክረምት ወቅት አካባቢውን የሚሸፍን አይደለም ብለዋል። በድንበር አካባቢ ከሚገኝ እርጥበት በስተቀር አካባቢው ላይ በመስከረምና ጥር ወራት አነስተኛ ዝናብ እንደሚጠበቅ፣ ሚያዝያና ግንቦት ወራት ደግሞ በተሻለ ዝናብ እንደሚያገኙ ነው ያመለከቱት።
አሁን ባለው ሁኔታም በነዚህ በተጠቀሱት ወራት ካልሆነ የተፈጥሮ ጉዳይ በመሆኑ በክረምቱ የግጦሽ ሳር ለማግኘት ተስፋ የሚደረግ ነገር እንደሌለም ተናግረዋል። ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ አጥጋቢ ባይሆንም ጥቂት ዝናብ ጥሎ በመጠኑም ቢሆን በአካባቢው እርጥበት ታይቶ እንደነበር አስታውሰው፣ ለዚህም ነው መንግሥት አማራጭ ለሌላቸው በተለያየ ድጋፍ ተደራሽ እየሆነ ያለው ሲሉ አብራርተዋል።
የቢሮው የእንስሳት መኖ ልማት አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አበራ ከተማ በበኩላቸው እየተደረገ ካለው ድጋፍ በተጨማሪ ከብቶቹ በራሳቸው ከአየር ንብረቱ ጋር ተላምዶ በመኖር ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ በመጠኑም ቢሆን ከብቶቹን ለማዳን የተደረገውን እንቅስቃሴ እንዳገዘው ተናግረዋል። ችግሩ ሰፊ አካባቢዎችን የሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ድጋፉ በሚፈለገው ልክ አጥጋቢ ነው ለማለት እንደሚያስቸግርም ጠቁመዋል።
ርብርቡ ባይኖር ጥቂቶችንም ማትረፍ እንደማይቻልም ጠቅሰው፣ በደርቁ ምክንያት ከብቶች ማለቃቸው ጉዳቱ ለአርብቶ አደሩና ለክልሉ ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ እንደሆነም አመልክተዋል።
እንደ አቶ አበራ ገለጻ፤ የቦረና አካባቢ ከብቶች ዝርያ በጣም ተፈላጊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በወተትና በስጋ ምርታቸው የታወቁና እውቅናቸውም እስከ ኬንያ ታንዛኒያ የዘለቀ ነው። ከብት በማርባት ለገበያ ማቅረብ የሚፈልጉ አካላትም የቦረና አካባቢን ይመርጣሉ። የዝናብ እጥረቱ ባስከተለው ድርቅ የአካባቢው ከብቶች መጎዳታቸውና እልቂቱም ሰፋ ያለ መሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጫናው ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ በአገር ደረጃም ሊገለጽ የሚችል ነው።
በክልሉ መንግሥት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ይሸፍናል የሚል እምነትም አይጣልም ያሉት አቶ አበራ፣ ተፈጥሮ ካላገዘ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል። በአካባቢው ዝናብ በሚጠበቅባቸው ወቅቶች ዝናብ ከጣለ ችግሩ ይቃለላል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።
ችግሩ የገዘፈ ስለመሆኑ መገናኛ ብዙኃንም በተለያዩ ጊዜያት ይዘዋቸው በወጡ ዘገባዎች ጠቁመዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶችን ገድሏል፤ የሰው ሕይወት ባያጠፋም ለመፈናቀል ዳርጓል። ከብቶቹን ወደ አጎራባች የክልሉ ዞኖችና ወደ ደቡብ ክልል አካባቢዎች በማሸሽ ከእልቂት መታደግ ባይቻል ኖሩ የከብቶቹ እልቂት በእጅጉ ከፍተኛ ሊሆን በቻለ ነበር።
በተፈጥሮ ጫና ውስጥ የወደቁትን ስምንቱ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ለመታደግ ጥረቶቹ መጠናከራቸው ተገቢ ነው። ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ የክልሉ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግሥቱ ለጋሾችና በተለይም በእንሳስት ሀብት ላይ የሚሠሩ አካላት ኃላፊነትም ጭምር ነው እንላለን።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014