የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ቀጥሏል፤ ኢኮኖሚውን የሚዘውረው ግብርናው ነው። ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሻገር ብዙ ጥረት ቢደረግም፣ ለእዚህም ግብርናውን ጭምር አንደመሣሪያ ለመጠቀም ቢሞከርም፣ ኢኮኖሚው ከግብርናው ጫንቃ ላይ ሊወርድ አልቻለም።
የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማሳደግ እንዲሁም ለገበያ ለማምረት ጭምር ብዙ ተሠርቷል፤ ይህን ተከትሎም ምርትና ምርታማነቱ እያደገ ቢመጣም፣ ካለው እምቅ አቅም፣ አገሪቱ ከሚያስፈልጋት የግብርና ምርት አኳያ ሲታይ ምርትና ምርታማነቱ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አለመሆኑ በመንግሥት ጭምር እየተገለጸ ይገኛል። ሊታረስ የሚችል ሰፊ መሬትና የሰው ኃይል የውሃ ሀብት እያለን ስንዴ ከውጭ አገር ስናስገባ የኖርበት ሁኔታም ለእዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ለእዚህ ደግሞ አንደ ችግር ከሚጠቀሱት መካከል ግብርናው የሚካሄደው በኋላ ቀር መንገድ መሆኑ ነው። በአገራችን ትራክተሮች በብዛት ይታዩ የነበሩት በመንግሥት እርሻዎች ብቻ ነበር፤ አንዳንድ ባለሀብቶች ወደ ግብርናው ዘርፍ መግባታቸውን ተከትሎ ትራክተሮች የሚታዩት በእነሱ ይዞታዎች ነበር። በግብርና ምርምር ተቋማትና በመሳሰሉት ብቻ ነበር ትራክተር የሚታየው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርሶ አደሮች ትራክተር እየተከራዩ መሥራት ጀምረው ነበር፤ በአቅራቢያው ትራክተር ያላቸው ባለሀብቶች እና ተቋማት ካሉ። እናም ትራክተር ብርቅ የሆነባት አገር ውስጥ ነው የኖርነው።
ግብርናውን ከኋላቀርነት የመታደጊያ አንዱ መንገድ በዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎች እርሻው እንዲካሄድ ማድረግ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ፋይናንስ ያስፈልጋል። መንግሥት ለግብዓትና ለመሳሰሉት ድጋፍ ቢያደርግም ግብርናውን በማዘመን በኩል ግን የፋይናንስ አቅርቦት እያደረገ አይደለም።
በአገራችን ባንኮች ለግብርናው ዘርፍ ብድር አያቀርቡም፤ የግብርና ባለሙያዎች፣ ኢኮኖሚስቶችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጭምር ይህን እውነታ ይጋሩታል። ይህን ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጭምር በተደጋጋሚ ገልጸውታል። ባንኮች ለሕንፃ ገንቢዎች እንጂ ለአርሶ አደሮች ብድር እያቀረቡ አለመሆኑን መናገራቸውን አስታውሳለሁ። የግብርና መሣሪያዎች ታክስ እየተከፈለባቸው ነው ከውጭ የሚገቡት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለውጦች እየታዩ ናቸው። የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲቻል ለግብርና ሜካናይዜሽን ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። አርሶ አደሩ የተለያዩ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ከጀመረ ቆይቷል፤ በግብርናው ዘርፍ እስከ አሁን ለታየው የምርትና ምርታማነት እድገትም ይህ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
አሁን ደግሞ አርሶ አደሩ በትራክተር ማረስ ውስጥ እየገባ ይገኛል። የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተፈቅዶ እየተሠራበት ነው። የግብርና ሚኒስትሩ ሰሞኑን አንደገለጹት፤ እስከ አሁን በተሠራው ሥራ ከ550 በላይ የሚሆኑ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ግዥ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። በቅርቡ የወጣ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ስምንት ሺ ትራክተሮች አርሶ አደሩ ቀዬ ገብተው የግብርናውን ሥራ እያሳለጡ ይገኛሉ።
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዚህ አመት ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 324 የሜካናይዜሽን ትራክተር ለአርሶአደሮች ተሰጥተዋል። በ2014 መጨረሻ ተጨማሪ 700 ትራክተሮች ለአርሶ አደሩ ይቀርባሉ። በቀጣይ አምስት አመታት ከ26 ሺህ ትራክተሮች በላይ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ታቅዶ እየሠራ ነው።
በኦሮሚያ ክልልም በርካታ አርሶ አደሮች ባለትራክተር የሆኑበት ሁኔታ ስለመፈጠሩ መገናኛ ብዙኃን ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች ሲተላለፉ ካቀረቧቸው ዘገባዎች ተረድተናል። በግብርናው ዘርፍ ባለሀብቶች በስፋት የሚንቀሳቀሱበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 34 ትራክተሮች በአርሶ አደሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ ሁኔታ እየተስፋፋ ካለው የኩታ ገጠም እርሻ ጋር ሲዳመር ቀጣዩ ጊዜ የግብርናው ዘርፍ እምርታ ይበልጥ የሚታይበት እንደሚሆን ያመለክታል። የግብርናው ምርትና ምርታማነት እድገት ጥያቄ ውስጥ አይገባም።
ምርትና ምርታማነቱ በእጅጉ የላቀና የአገሪቱን እና የዜጎችን የምግብ ዋስትና ችግር ከመፍታት አልፎ ለገበያ ማምረት ላይ የሚደርስ መሆን ይኖርበታል። እናም በዚህ የመኸር ወቅት በርካታ ትራክተሮች ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ የገቡ እንደመሆናቸው ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ይጠበቃል። ከፍ ተብሎ እንደተጠቀሰው በአሁኑ ወቅት የግብርና ዘርፍ ባለ 8 ሺ ትራክተሮች መሆን ችሏል። ይህን ያህል ትራክተር በዘርፉ መሰማራቱ ትልቅ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል እንድንጠብቅም ያደርገናል።
በየአመቱ በዚህ ልክ መጓዝ ከተቻለም ሰፋፊ ለውጦችን ማስመዝገብ ይቻላል። ለእዚህ ለውጥ እውን መሆን ግን ብዙ መሥራት ይጠበቃል። አሁን አርሶ አደሩ ቀዬ የገቡ ትራክተሮችን እንደ ዘር ማየት ይገባል እላለሁ፤ ለዚያውም እንደ ምርጥ ዘር። ምርጥ ዘር ብዙ ምርት ያሳፍሳልና በቀጣይ ከአሁኖቹ ትራክተሮች ተሞክሮ በመነሳት ሌሎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ትራክተሮች በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንደሚርመሰመሱ ይጠበቃል።
አርሶ አደሩ በግሉም ሆነ እየተሰባሰበ አልያም በኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በኩል ግብርናውን ከእጅ ወደ አፍ ከሆነው አመራረት ለማውጣት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የዚህ ቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል፤ ለአርሶ አደሩ ድጋፍ የሚሰጡ እንደ ግብር ሚኒስቴርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያሉ ተቋማት በዚህ ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ ይበልጥ ማሳደግ ይኖርባቸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ይህን የሜካናይዜሽን ሥራ የሚያሳልጡ ባለሙያዎችን፣ የጥገና ማዕከላትን ማዘጋጀት ለነገ የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም፤ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡትም ሆነ በአገር ውስጥ በሚመረቱት ማሽነሪዎችና ትራክተሮች ጥራትና ደረጃ ላይም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት። ይህን የግድ የሚሉ ችግሮች እየታዩም ናቸው። ቀደም ሲል በግብርናው ዘርፍ ስኬታማ ሆነው ባለትራክተር ለመሆን የበቁ አርሶ አደሮች በትራክተሮቻቸው ላይ እያጋጠማቸው ያለው ችግር ይህን የግድ ይላል።
ከዚህ አኳያም በመንግሥት በኩል አንዳንድ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ሜካናይዜሽኑ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በአላጌ ግብርና ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ ትራክተሮችና ሌሎች ማሸነሪዎች በብዛት እንደመግባታቸውና በቀጣይም በብዛት የሚገቡ እንደመሆኑ በዚህ ላይ ከእስከ አሁንም የላቀ ተግባር ማከናወን የግድ ነው። እነዚህ ማሸነሪዎች በቀላሉ የሚጠገኑበት ሁኔታ ለመፈጠር ወርክሾፖችና ባለሙያዎች በአርሶ አደሩ አቅራቢያ መገኘት ይኖርባቸዋል።
የፋይናንስ ተቋማት አሠራራቸውን አሻሽለው አርሶ አደሩን የሚደግፉበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። የፋይናንስ ተቋማት ገጠር ድረስ ዘልቀው አርሶ አደሩን የመደገፍ ኃላፊነት አለባቸው። ከኢትዮጵያ ሕዝብ 85 በመቶ አርሶ አደር ሆኖ እያለ ይህን የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ የፋይናንስ አቅርቦት የግድ መሆን ይኖርበታል።
እርግጥ ነው ባንኮች ብድር ለመስጠት ማስያዣ ይፈልጋሉ። ምን ያህል እየተሠራበት እንደሆነ ባላውቅም፣ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን አስይዞ መበደር የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩ ይታወቃል። አርሶ አደሩ ከብቶቹን እና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹን አስይዞ በመበደር ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎች የሚገዛበትን ሁኔታ ለመፍጠር ለተያዘው አገራዊ ጥረት የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።
ይህ ብቻውን ግብርናው የሚፈልገውን የፋይናንስ አቅርቦት ይሞላል ተብሎ አይጠበቅም። አርሶ አደሩ መሬት የመጠቀም መብት እንጂ የባለቤትነት መብት የለውም። በእርግጥ ይህ አንድ መፍትሄ ይፈልጋል። ማሳ ላይ ያለውን ሰብሉን፣ መሬቱን በኮንትራት ለተወሰኑ አመታት ሊሰጥ የሚችልበትን ሕጋዊ መብት በመጠቀም ብድር የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ፈጥነው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ወቅቱም የሚጠይቀው ይህንኑ ነው።
መንግሥት ለፋይናንስ ተቋማት በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የሀብታቸው ባለቤት የሆነውን አርሶ አደር የግብርና ሥራ ለማሳደግ አዳዲስ አሠራሮችን መተግበር ይኖርባቸዋል።
ግብርናው ስትሰጠው ይሰጥሃል ያሉ አንድ ባለስልጣን ታወሱኝ፤ አዎን ስትሰጠው ይሰጥሃል፤ ለዚያም ወዲያው። ለጥገት ላም የሚፈለገውን መኖ ሳያቀርብ ብዙ ወተት መጠበቅ ትርፉ ድካም ነው። ለግብርናውም አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ፣ ስልጠናና አገልግሎት ሳያቀርቡ ምርትና ምርታማነትን መጠበቅ የዋህነት ነውና ግብርናው በዘመናዊ መሣሪያ እንዲደገፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014