የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብትን የማስተዋወቅ ስራ በፖሊሲና በስትራቴጂ የተደገፈ ከፍተኛ የተግባር ስራዎችን ማከናወንን ይጠይቃል። አገሪቱ ካላት ውስን ሃብት አንፃር የቱሪዝም ዘርፉን ለመላ ዓለም በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅ የሚጠይቀውን ከፍተኛ ወጪ የሚቀንስ መንገድ ማግኘትንም የግድ ይላል። ያለውን እምቅ የባህል፣ የታሪክ፣ ቅርስ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብትና ሰው ሰራሽ የመስህብ ስፍራዎችን ለጎብኚዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ያልተሞከሩና ያልተለመዱ አሊያም ደግሞ በትኩረት ያልተሰራባቸው መንገዶችን እንደ አማራጭ መውሰድም ያስፈልጋል።
በቀላል ወጪና ጉልበት የቱሪዝም ሃብቶችን ከማስተዋወቅና የአገሪቱን ገፅታ ከመገንባት አንፃር የኢትዮጵያን መንግስት ወክለው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢምባሲዎች፣ ቆንፅላ ፅህፈት ቤቶች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች ተቋማት ሰፊ እድል አላቸው። ከዚያም ባለፈ በልዩ ልዩ ምክንያት ከአገር ውጪ የሚገኙ ዜጎች ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ያላቸው እድል ሰፊ ነው።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምዱ የተለያየ ተልእኮን አንግበው በውጪ አገራት የሚገኙ ተቋማትና ሌሎች ግለሰቦች ይህን እድል በምን መልኩ መጠቀም ይኖርባቸዋል? መንግስትስ ስልቶችን እና አካሄዶችን የሚደግፉ መንገዶችን በምን መልኩ ቀርፆ ወደ ትግበራ መግባት ይኖርበታል? እስካሁን ድረስ ያሉ አሰራሮችስ ምን ይመስላሉ? በሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ከእንግዳችን የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያው ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀ ጋር ቆይታ አድርገናል። ዶክተር ተስፋዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሃገር ልማት ጥናት ኮሌጅ ዲን ናቸው፤ በቱሪዝም ልማትና አስተዳደር፣ የቱሪዝም ምርቶች ሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ የማስተማር፣ ከማስተዋወቅ አኳያም ምርምርና ጥናት በማድረግ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአቶችን በማበርከት አስተዋጽኦ ያበረከቱም ናቸው። መልካም ቆይታ!!
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በቱሪዝም የመስህብ ሃብቶች ቀዳሚ ከሚባሉ አገራት ተርታ እንደምትመደብ በተደጋጋሚ ይነገራል። ለመሆኑ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር ተስፋዬ፦ በትክክል። ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሃብት ካላቸው አገራት በቀዳሚነት ትመደባለች። በዚህ በኩል ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚ ሃብትም አላት ።
ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ያለው ማንኛውም ነገር የቱሪዝም እምቅ ሀብት ነው። ይህን ወደ ቱሪዝም አገልግሎትና ምርት መቀየርና ማሳደግ እስከቻልን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ የሆኑ ሃብቶች እንዳሉ ይታወቃል። ከኛ የሚጠበቀው ትልቁ ስራ እነዚህን እምቅ ሃብቶች ወደ ቱሪዝም ምርትና አገልግሎት ቀይሮ ለዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ማበርከት ነው። መንግስትም ሆነ በቱሪዝም ዙሪያ የሚሰሩ የግል ዘርፉ አንቀሳቃሾች ይህን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል። የትምህርት ተቋማትም ይህንን ያገናዘበ ስርዓተ ትምህርት ቀርፀው ብቁ የሰው ሃብት ማፍራት ይኖርባቸዋል። ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተቻቸው እንደ መስቀል፣ ጥምቀት፣ ኢሬቻ፣ እና ሌሎችም የተፈጥሮ እንዲሁም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ናት።
አዲስ ዘመን፦ እርሶ ከላይ ያነሷቸው እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች እንዳሉ ቢታወቅም፣ በተገቢው የማስተዋወቅና የማልማት ስራ ተሰርቷል ማለት እንችላለን? ይህን ማድረግ ቢቻል የሚገኘው ጠቀሜታስ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ተስፋዬ፦ ቱሪዝም በተፈጥሮ ሰላምን ይፈልጋል። ዘርፉ ስሱ ወይም “sensitive” ከሚባሉ ዘርፎች ይመደባል። ስለዚህ ጎብኚዎች ወደ አገር ውስጥ በሚመጡበትና ሃብቱ በሚተዋወቅበት ጊዜ መንግስትና ህብረተሰቡ አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ማረጋገጥና ለዚያም በጥንቃቄ መስራት ይኖርባቸዋል። ይህንንና ሌሎች ሃብቶችን የሚያስተዋውቁ ተግባራት ሲከናወኑ በሚፈለገው ደረጃ ቱሪስቱ ወዶ እንዲመጣ ከመሳብም ባለፈ የተቀዛቀዘው ዘርፍ እንዲነቃቃ ማድረግ ይቻላል።
የቱሪዝም ምርትና አገልግሎትን ማዘመንና ማሻሻልም ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ይህን ማድረግ ሲቻል በዘርፉ ስራ ከመፍጠር አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ማግኘት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ የቱሪዝም ሃብቱን ለማስተዋወቅ ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የመንግስት ሃላፊነትን ይዘው ከሚሰሩ ተቋማት በተለይ ደግሞ ከዲፕሎማቶች፣ ኢምባሲዎች፣ ቆንፅላ ፅህፈት ቤቶችና መሰል አካላት ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ተስፋዬ፦ በቅርቡ እየተከሰተ ካለው የፀጥታ ችግር አንፃር ኢትዮጵያ እንደፈረሰች፣ ከፍተኛ ችግር እንዳለ አድርገው ፕሮፓጋንዳ የሚሰሩ ብዙ መገናኛ ብዙሃን ይኖራሉ። ይህንን የሚያዳምጥ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እና ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ተመልክቶ ራሱን አዝናንቶ ለመሄድ ይከብደዋል። ስለዚህ በውጪ አገራት የመንግስት ሃላፊነት ይዘው የሚገኙ ቆንፅላዎች፣ ኢምባሲዎች እንዲሁም ዲፕሎማቶች መሬት ላይ ያለው እውነታ በመገናኛ ብዙሃን ከሚወራው የተለየ መሆኑን፣ ችግሮችም እንዳሉ ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው ጥረትም ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ማሳየት ያስፈልጋል።
ከዚህ ባለፈ የኛ ኢምባሲዎች ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሃብት በሚገባ ማስተዋወቅ አለባቸው። ማስተዋወቅ ሲባል የመጀመሪያው ቴክኖሎጂን መጠቀም ነው። ቆንፅላዎችም ይሁኑ የዲፕሎማሲ ተቋማት ለዚህ አጋጣሚ ሰፋ ያለ እድል አላቸው። ስለዚህ ይህን አጋጣሚ መጠቀም አለባቸው።
እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ያላትን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ባህላዊና መሰል መስህቦችን ሲያስተዋውቁ በእቅድና በሳይንሳዊ ሰነድ ላይ ተመርኩዘው መሆን ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለሁሉም ኢምባሲዎች፣ ቆንፅላዎች እንዲሁም በውጪ አገር ለሚኖረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መዳረስ ያለበት የጋራ ጠንከር ያለ ሰነድ መዘጋጀት አለበት። በተለይ የቱሪዝሙን ሃብት በመዳሰስ በተለያዩ ስልቶች ቱሪዝሙን ማነቃቃት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማድረግና ከዚያም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ያስፈልጋል።
እነዚህ አካላት አገር ለመገንባት የሚያስችል ጥሩ እድል አላቸው። ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሃብት ዘርፍ ያላትን አቅም መረዳት እንዲችሉ በባለሙያዎች ስልጠና ሊያገኙ ይገባል። ይህ አካሄድ ደግሞ እቅድና ጥናት ላይ የተመረኮዘና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚካሄድ ሊሆን ይገባል። የሚፈጠረው ግንዛቤ በተለይ በውጪው መገናኛ ብዙሃን እየተሰራጨ ያለውን የተዛባ መረጃ ሊቋቋም የሚችል መሆን አለበት። ይህን ማድረግ ከተቻለ ቱሪስቶችን ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችን ጨምሮ የቱሪዝም ሃብቶችን እንዲጎበኙና ፍሰቱም እንዲጨምር ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያን የወከሉት እነዚህ የዲፕሎማሲ ተቋማት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከላይ ካነሱልኝ ሊሰሩ ከሚገባቸው ተግባራት አንፃር ስንመዝናቸው የሚጠበቅባቸውን ያህል ሰርተዋል ማለት እንችላለን? ያሉት መልካም ጎኖችና ክፍተቶችስ ምን ይመስላሉ?
ዶክተር ተስፋዬ፦ ኢትዮጵያ ልትታወቅባቸውና የቱሪስት መስህብ ልትሆን የምትችልባቸው መልካም አጋጣሚዎች አሉ። አለም አቀፍ ገበያውን እና ማህበረሰቡን በዚህ ረገድ በማሳመን በምእራቡ፣ በምስራቁ፣ በመካከለኛውም ሆነ በሩቅ ምስራቁ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ቱሪስቶችን አሳምኖ ወደ አገራችን እንዲመጡ፣ የቱሪዝም ምርቶቻችንን እንዲያውቁና እንዲጠቀሙ ለሌሎችም እንዲያሳውቁ ከማድረግ አንፃር በጣም ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅብናል።
በእርግጥ ይህን ለማሳካት ፍላጎቱና አንዳንድ ጥረቶች እንዳሉ መረጃዎች አሉኝ። እነዚህ በተለያየ አገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶችም ሆኑ ኢምባሲዎች አንዱ የስራ ድርሻቸው እንደሆነና ስራዎችን እንደሚሰሩ አምናለሁ። ግን የሚጠበቀውን ያህል ነው ወይ ብለህ አስረግጠህ የጠየከኝ ከባድ ጥያቄ ነው። ከዚህ አንፃር አመርቂና የሚጠበቀውን ለውጥ ለማምጣት ግን አሁንም ተጨማሪ ስራዎች መሰራት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ።
ይህን ለማድረግ መጀመሪያ ከእውቀት መጀመር አለበት። የመጀመሪያው ሃብቶቻችን ምንድን ናቸው? ኢትዮጵያ ውስጥ መጎልበት ያለበት የቱሪዝም አይነት የቱ ነው? የሚሉትን በአግባቡ መረዳት ይኖርባቸዋል። ከዚህ ቀደም የተዘጋጁ ሰነዶች ካሉም እነዚህን በማቀናጀትና ምክረ ሃሳቦችን በመጠቀም ለተሻለ ውጤት መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ምሁራንና የልህቀት ማእከላት የቱሪዝም ዲፕሎማሲው ውጤታማ እንዲሆን ከመንግስትም ሆነ ኢትዮጵያን ወክለው በውጪ አገራት ካሉ ኢምባሲዎችና ቆንፅላዎች ጋር ምን መስራት ይኖርባቸዋል?
ዶክተር ተስፋዬ፦ ባህልና ቱሪዝም አንድ ላይ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር አውቃለሁ። በተለይ ምሁራንና ሃሳብ አመንጪ ሰዎች (think tank) ቡድኖች ተመስርተው በተለያየ ጊዜ እየተገናኙ ሃሳብ እንዲያዋጡ ሲደረግ ነበር። የመነጨው ሃሳብም ተፈትሾና ታይቶ ወደ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሄድና አሰራሮች አንዲሻሻሉ አስተዋጽኦ የማድረግ ጥረቶች ነበሩ። አሁን ግን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አላውቅም። የተቀዛቀዘ ይመስለኛል። እንደዚህ አይነት አደረጃጀቶች በጣም ወሳኝ ናቸው። በዚህ ረገድ ራሱ ፖሊሲው ተፈትሾ መታየት ይኖርበታል። የምሁራን ሚና ለምሳሌ በዚያ ውስጥ አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ።
ቱሪዝም ሁሉም ዘርፎች ባለቤት ሊሆኑበት ይገባል። ግብርና፣ጤና፣ ትምህርት፣ ኢንቨስትመንት፣ ስፖርት ውስጥ ቱሪዝም አለ። የቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን የማስተባበርና የማቀናጀት ሚና ነው ያለው። ስለዚህ በሁሉም ዘርፍ ላይ የሚገኙ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት የጎላ ሚና ሊኖራቸው ይገባል።
በተለይ በጋራ በትብብር የመስራት አዳዲስ ሃሳቦችን የማፍለቅ፤ እንዲሁም ያሉትን እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች ወደ ምርትና አገልግሎት መቀየር የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ ይኖርባቸዋል። ስርዓተ ትምርት ሲቀየስ ባለድርሻ አካላት ሃሳብ ማዋጣትና የተሻለ አቅጣጫ ማሳየት ይኖርባቸዋል። ከዚህ ባሻገር የቱሪስትን ቆይታ ለማራዘም፣ የአገር ገፅታን በዘርፉ ለመገንባት ምሁራንና ሃሳብ የሚያፈልቁ አካላት ሚና በእጅጉ ወሳኝ ነው።
ኢምባሲዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ቆንፅላዎችና ልዩ ልዩ አካላት በተሻለ መልኩ ስራቸውን እንዲከውኑም፣ ስልጠና በመስጠት አዳዲስ መንገዶችን በመጠቆምና ጥናቶችን በማካሄድ ድጋፍ የማድረግ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ የቱሪዝም ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመስራት እያስተዋወቀ ነው። ይህን ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ እነዚህ በውጪ አገር የሚገኙ ተቋማት ሚና ምን መሆን አለበት?
ዶክተር ተስፋዬ፦ አዳዲስ መዳረሻዎች በተለይ ተሰርተው የተጠናቀቁት የስራ እድል የፈጠሩ የቱሪዝም ፍሰቱን የመጨመር አቅም ያላቸው ናቸው። በተመሳሳይ በግሉ ዘርፍም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መሰራት ይኖርባቸዋል። ቱሪስቱ በኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥቶ ቆይታውን ከሚያራዝምባቸው መንገዶች አንዱ እንዲህ አይነት ልዩ ልዩ መዳረሻዎች መኖራቸውና በዚህ ላይ የሚሰሩ ስራዎች መጠናከራቸው ነው። ስለዚህ ኢምባሲዎች፣ ቆንፅላዎችና በነዚህ ውስጥ የሚሰሩ ዲፕሎማቶች እንዲሁም በውጪ የሚኖሩ አጋጣሚው ያላቸው የኢትዮጵያ ዜጎች አዳዲሶቹን መዳረሻዎች ለቱሪስቱ ማስተዋወቅና ብራንድ ሆነው ተጨማሪ የመስህብ ስፍራ እንዲሆኑ መስራት ይኖርባቸዋል።
በዚህ ረገድ ስኬታማ የሆኑ ኢምባሲዎችም ሆኑ ዲፕሎማቶች በየጊዜው የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች በሚገኙበት አገር በተመሳሳይ የሚገኙ የሌሎች አገራት ኢምባሲዎችና ዲፕሎማሲዎችም አገራቸውን ለማስተዋወቅ ምን እየሰሩ እንደሆነ ማጥናትና ማስተዋል ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ በማሳደግ ረገድ ተጨማሪ መሰራት ይኖርባቸዋል የሚሏቸው ሃሳቦች ካሉ ቢያነሱልን?
ዶክተር ተስፋዬ፦ አሁንም መንግስት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመጡና የቱሪዝም ዘርፉ እንዲጠናከር የሚያበረታታበት አግባብ መቀጠል አለበት። በተለይ በአገራቸው ከሁለት ሶስት ወር በላይ እንዲቆዩ የተለያዩ የቅናሽ ማበረታቻዎችንና መሰል መንገዶችን መቀየስ ይኖርበታል። ይህንን አድርጎ የዲያስፖራ ቱሪዝምን ማሳደግ ከተቻለ ብዙ ዶላር ከማስገኘቱም በላይ በአገር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ይህንን ሃላፊነት በውጪ የሚገኙ ኢምባሲዎች፣ ቆንፅላዎችም ሆኑ ዲፕሎማቶች በተሻለ መንገድ የመፈፀም አቅም አላቸው። ስለዚህ አጋጣሚውን መጠቀም ያስፈልጋል እላለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ሙያዊ ሀሳብ በዝግጅት ክፍላችን ስም እናመሰግናለን!!
ዶክተር ተስፋዬ፦ እኔም አመሰግናለሁ!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም