የኢትዮጵያ አምላክ ይመስገንና አውሮፓና አሜሪካ በሙቀትና በሰደድ እሳት እየተንገበገቡና እየተለበለቡ ሀገራችን ግን በአብዛኛው መደበኛውን የክረምት ዝናብ እያገኘች ነው ። ሀምሌ እንደ አምናውና ካች አምናው እኝኝ እያለ ነው ። በሀገር አማን በቆሎ አንዱ 15 ብር ድንች ኪሎው 20 ብር ገብቶ ኪስ ቢያራቁትም ፤ ኑሮው አልቀመስ ቢልም ፤ ነዝናዛው ሀምሌ ያለእነሱ አይገፋም ። የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስና ለመቆጣጠር መንግስት ለምን ሮኬት ሳይንስ እንደሆነበት ግራ እያጋባኝ ሳለ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዋጋ ግሽበቱን የሚያባብሱ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። በነዳጅ ድጎማው ያለ ትክክለኛ ጊዜው መነሳት ስብሰከሰክ ፤ ሰሞኑን ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዚህ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ወቅት የታሪፍ ማሻሻያ አደርጋለሁ ብሏል።
ምክንያቱ ደግሞ አለማቀፍ የዋጋ ግሽበቱ መሆኑን ሲገልጽ ይች ሀገር ወዴት እየሄደች ነው እንድል አስገድዶኛል። ይህ ሕዝብ በየቀኑ የሚተኮሰው የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ ኑሮውን ሲኦል ማድረጉ ሳያንስ ፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደግሞ ሌላ ግሽበት ሊጭንበት ሲዘጋጅ መመልከት በሀገሩ ሀይ ባይ የለም እንዴ እንድል ገፋፍቶኛል። የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንደ ነጋዴ በየጊዜው እየተነሱ ታሪፍ የሚያሻሽሉ ከሆነ ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውና የሕዝብ ሀብትነታቸው ምኑ ላይ ነው !?መንግስትስ በዋጋ ግሽበቱ ትይዩ መቼ የደመወዝ ማሻሻያ አደረገና ነው አዳሜ ከመሬት እየተነሳ እንደፈለገ የግሽበት ማወራረጃ የሚያደርገው!? ለዛውም አሁን ስራ ላይ ባለው ውድ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ደንበኛው እየተማረረ በየሚዲያው እየጮኸ ባለበት ሰዓት ፤ ለሌላ ዙር ጭማሬ መዘጋጀት ምን ይሉታል ። መንግስት ደመወዝ ጨምር ሲባል ግሽበቱን ያባብሳል እያለ ፤ በተቃራኒው እሱ ግን የዋጋ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ እርምጃዎችን በጀ ብሎ ይዟቸዋል ። እንደ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ይሄን ያለጊዜው የታሰበ ታሪፍ ማሻሻያ እንቃወማለን። መንግስትም ሊያስቆመው ይገባል። የሕዝብን ሆደ ሰፊነት ፣ አርቆ አሳቢነትና ትዕግስት በተደጋጋሚ ከመፈታተን ቢቆጠብ መልካም ነው። ሁሉም ነገር ልክና ገደብ አለው።
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ ሰውነት በጋቢ ፣ በከሰል ፣ በበቆሎና በድንች ሲሞቅ አእምሮ ደግሞ እራቁት ሆኖ ቆፈን እንዳይዘው የሞኅዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ፤ “ከእቴጌ ዕሌኒ እስከ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ፤” ድንቅ መጽሐፍ በቀኝ ፤ የታዋቂዋን የታሪክ ሊቅ ዶሪስ ከረንስ ጉድዊንን ፤ “Lyndon Johnson the American Dream”በግራ ይዤ ፤ ማህበራዊ ሚዲያውን እርም ብዬ ፤ ዶንኪ ቲውብንና የስቲቭ ሀርቪን ሾ እያዛነቅሁ ሰላሜን ከሚያውኩ በሬ ወለደና የሴራ ፖለቲካ ተጠብቄ ከህጻናትና ከፈጣሪዬ ጋር ክረምቱን እየገፋሁ ሳለ ከፍ ብዬ በጠቀስሁት የሞሐዘ ጥበባት መጽሐፍ ገጽ 316 ላይ በ16ኛው መክዘ አጼ ሱስንዮስ ከእየሱሳውያን ጋር አብሮና አገዛዙን ለማጠናከር ብሎ ከሮም የጦር መሳሪያና የሰራዊት ድጋፍ አገኛለሁ በሚል ቀቢጸ ተስፋ የካቶሊክን ዕምነት በመቀበሉ የአባቶቻችንን የእስክንድርያ ሀይማኖት አንለውጥም ባሉ ኦርቶዶክስ ተዋህዶውያን ላይ መከራ አዘነበባቸው። በዚህ የተማረሩ ሀይማኖታቸውን ለማስከበር ከንጉሱ ጋር ጦር ገጠሙ። የአጼ ሱስንዮስ ፈረሰኛ ጦር አይሎ ከ5000 _6000 ቀናኢ ኦርቶዶክሳውያን ጨፈጨፈ። በዚህ ያዘኑ አበው በድፍረት ንጉሱን ወዳለቁት ዜጎች ትኩስ ሬሳ ወስደው እንዲህ አሉት ።
“…ተመልከት ከእነዚህ አጽማቸው ሜዳውን ከሞላው ሰዎች መካከል አንድም የውጭ ሀገር ሰው የለም። ገዳዮቻቸውም የውጭ ሰዎች አይደለንም። ወንድሞቻችንና የቅርብ ዘመዶቻችንን አጣን። ብናሸንፍም ብንሸነፍም ያው ነው። በሁለቱም ተሸናፊዎች ነን። ምንም መሳሪያ ሳናገኝ ይሄው አምስት አመት ሆነ። አሁን ግን ጊዜም ብርታትም ከእኛ ጋር አይደለም። ለፈረሶቻችን ሳር የሚያጭድ ሰው አናገኝም። በቅሎዋችንም ጠባቂ የላቸውም። መሣሪያ የሚሸከም አይኖርም። የዚህ ሁሉ ጣጣ መነሻ የሮም ሀይማኖት የሚባል ነገር ነው። ለእነዚህ ገበሬዎችና ያልተማሩ ሰዎች የጥንት ልማዳቸውን ካልመለስክላቸው በቀር መንግስትህን አንተም የልጅ ልጆችህም ታጣላችሁ።…”
በዚህ ከባድ ትችትና ወቀሳ መንፈሱ የተነካው ንጉስም የሔደበት መንገድ ስህተት መሆኑን አምኖና ተጸጽቶ ብዙም ሳይቆይ ሽሮት የነበረውን የአባቶቹን ዕምነት የኦርቶዶክስን ስርዓት መልሶ፤ ዙፋኑን ለልጁ ልዑል ፋሲለደስ አስረከበ ።”ፋሲል ይንገስ፣ ሀይማኖት ይመለስ፤” በተባለው አዋጅ አጸናው። ዛሬ በ2014 ዓም ያ ሁሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ትግራዋይ ወጣት እንደ ቅጠል እረግፎ፤ ክልሉ ወጣት አልባ ሆኖ ፤ እናት የወላድ መካን ሆና፤ የትግራይ ከተሞች የመናፍስት ከተማ መስለው ፤ ትግራዋይ በርሀብ ፣ በቸነፈርና በርዛት እየተገረፉ አጼ ሕወሓትን በቃህ ! የሚሉ ምሁራን ፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዴት ይጠፋሉ።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አስተዳደርማ ጦርነቱ እንዳይቀሰቀስ ያልጠየቀውና ያላከው ሽማግሌ የለም። እናቶች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ ታዋቂ ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በመቀሌም በአዲስ አበባም ሕወሓትን ለምነዋል አስለምነዋል። አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ አባቴ ጉልበት ላይ ያላደረግሁትን ሕወሓት ጉልበት ላይ ወድቄ ለምኛለሁ ብሏል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይም በግል ጦርነቱ እንዳይቀሰቀስ ያልወጡት አቀበት ያልወረዱት ቁልቁለት የለም። በዚያ ሰሞን ፓርላማ ቀርበው መንግስታቸው ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ፤ በጦርነት በዚያም ሆነ በዚህ ወገን የሚሞተው ሰው ነው ብለዋል። መንግስታቸው የሚፈልገው ልማትና እድገት እንጂ ጦርነት አለመሆኑን አረጋግጠዋል። ከዚህ አልፈው ከሕወሓት ጋር የሚደራደሩ ሰዎችን ሰይሟል። የሕወሓትን ማንነት ልቅም ጥንቅቅ አድርገው ቢያውቁትም ዛሬም ለትግራይ ሕዝብ ሲሉ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ ፣ ገንዘብ ፣ መዳኒት ፣ የዕለት ደራሽ እርዳታ ፣ ወዘተረፈ እየላኩ ነው።
ሕወሓት ግን በእብሪቱና በማንአህሎኝነቱ እንደገፋበት ነው። ዛሬም ለሌላ ዙር እልቂት የጦርነት ነጋሪቱን እየጎሰመ ነው። ክተት እያወጀ ነው። ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ነው። ዛሬም የትግራይ ሕዝብ ሞትና መከራ ከስልጣን ጥሙና ከተላላኪነቱ በታች መሆናቸውን እያረጋገጠልን ነው። የትግራይ የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ዛሬ እንኳ ሕወሓትን በቃህ ለማለት ድፍረት ያጡት ምን እንዳይቀርባቸው ነው !? ልጆቻቸውን አጥተዋል፣ ሰላማቸውን ተነጥቀዋል ፣ ኑሯቸው ተጎሳቁሏል፣ ተስፋቸውንና ህልማቸውን ተነጥቀዋል። ታዲያ ዛሬ እንኳ ምን እንዳያጡ ነው በድፍረት ወጥተው ሕወሓትን በቃህ ለማለት የተሳናቸው። የ16ኛው መክዘ አባቶች አጼ ሱሰንዮስን በቃህ ! ሲሉ ፤ በ21ኛው መክዘ የትግራይ አባቶች አጼ ሕወሓትን በቃህ ለማለት ምነው አቅም ከዳቸው !?
በ21ኛው መክዘ ታሪክ እራሱን ደግሞ ሕወሓት በ27 አመታት ያልቆረጠለትን የአገዛዝ ጥም ለማርካት እና የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ ለማሳካት ሲል ከአንድም ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት ከፍቶ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ዘለውና ሩጠው ያልጠገቡ ትግራዋይ ወገኖቻችንን ማስጨፍጨፉ አልበቃው ብሎ የተዘረጋለትን የሰላም እጅ እየገፋና የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል። የትግራይ ሕዝብ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል ከ60 ሺህ በላይ ፤ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችህን እህት ወንድሞችህ ወላጆችህን ሕይወት ገበርክ። ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ዘለውና ሩጠው ያልጠገቡ የአብራክህ ክፋዮች አካል ጉዳተኛ ሆኑ።
የትግራይ ሕዝብ ሆይ ! ልጆችህም ሆኑ አንተ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያመጣኸው “ነጻነት” ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር (ደርግ) የከፋ ፈላጭ ቆራጭና ዘራፊ አምባገነን በሆነው ሕወሓት ተነጠቅህ ። በአንድ ለአምስት ጠርንፎ እርስ በርስህ እንዳትተማመን፤ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገንህ ጋርም በጥርጣሬ እንድትተያይ ፤ ይህ አልበቃ ብሎት ልጆችህን ትርጉም ለሌለው ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግዶ ከኤርትራ ወረራ ነጻ ያወጣውን መሬት የሄጉ የድንበር ኮሚሽን አስረክቦ እንደተቀረው ዜጋ አጨብጭበህ ባዶ እጅህን እንድትቀር አደረገ ። የልጆችህን ደም የውሻ ደም አድርጎት ቀረ። የሌላውን ኢትዮጵያዊ ደምም እንደዚሁ። ትርጉም ላልነበረው ለዚህ ጦርነት በቢሊዮኖች የሚገመት የአገር ሀብት ወደመ።
ይህ አልበቃ ብሎት እንደ አስቆርቱ ይሁዳ የሰሜን ዕዝን በመጨፍጨፍና የጦር መሳሪያ ፣ ትጥቅና ስንቅ በመዝረፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዳግም በአደባባይ ከዳ። ክህደት ለአሸባሪው ሕወሓት ግብሩ ምሱና ማንነቱ ነውና። ክህደት ጥርሱን የነቀለበት መርገሙ ነው። የትግል ጓዶችን ፣ ትግራዋይ ወላጆችን ፣ ትግራይን፣ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን ወዘተረፈ በአደባባይ ሲከዳ የኖረ ባንዳ ነው። ክህደት ብርቁም ሆነ ድንቁ ያልሆነው አሸባሪው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይሉት ክህደት በመፈጸም የሰሜን ዕዝን በማጥቃት ትጥቁንና ስንቁን ከመዝረፍ ባሻገር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሰሜን ዕዝ አባላትን በመጨፍጨፉና በማጥቃቱ አገራችን ተገዳ ወደ ጦርነት ገብታለች ።
እፉኝቱ አሸባሪው ሕወሓት በሕዝባዊ ተቃውሞና በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠሩ የለውጥ ኃይል የተናበበና የተንሰላሰለ ትግል ኢ-ፍትሐዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ከነበረው ከማዕከላዊ መንግሥት አገዛዙ ሲነሳና በልክህ ሁን ሲባል በእኩልነትና በፍትሐዊነት ላይ አኩሩፎ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ በመመሸግ ዕቅድ “ለ”ውን ከመሳቢያው አቧራውን አራግፎ በመሳብ እንደ አፄ ልብነ ድንግል መሬትን 40 እየገረፈ ጦር አውርድ እያለ የጦርነት ነጋሪቱን መጎሰም ጀመረ ። በዚህም ብዙዎች አለቁ ። ዳግም አብረን የማንኖር እስኪመስል በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሰቆቃና ግፍ ፈጸመ። በሀገርና በሕዝብ ሀብት ላይ ሰፊ ዘረፋና ውድመት አደረሰ።
በየግንባሮች እንደ ቅጠል የረገፈውን የቆሰለውን ፤ ባሰብሁ ባሰላሰልሁ ቁጥር የትግራይን ሕዝብ ምንም እንኳ በሕወሓት የአንድ ለአምስት ጥርነፋ የታፈነ ቢሆንም በቃ ለማለት እንዴት እንጥፍጣፊ ወኔ ያጣል ፤ አብዛኛው የትግራይ ልሒቃንስ ይሄን እልቂት እያየና እየሰማ እንዴት በቃ ማለት ይቅርና ከአመክንዮና ከተጠየቅ በዚህ ደረጃ ወርዶ ከእብሪተኛው ጋር የጦርነት ነጋሪት ይጎስማል። አጼ ሕወሓትን በቃ ለማለትስ ዋጋው ስንት ነው!? የአምስትና የስድስት ዓመታት ሕጻናት ለሌላ ዙር እልቂት እስኪማገዱ !? ወይስ ከመጪው ትውልድ “ተበድሮ” ሕዝባዊ ማዕበል እስኪያስነሳ !? መቼም ምድር ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢል እብሪተኛው ሕወሓት ይሄን ጦርነት አያሸንፍም። ለዛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ የተፋው ጭላጭ እንኳ ማህበራዊ መሠረት የሌለው ሕወሓት። የሚያሳዝነው ነበልባሉን ከስር ከስር በትግራዊ ብላቴናዎች የሚቆሰቁሰው የሽብር ኃይሉ አመራርም ሆነ ልጆቹና ቤተሰቦቹ ዳር ቆሞ ተመልካች መሆናቸው ነው። ልጆቹና የቅርብ ዘመድ አዝማዶቻቸው በአውሮፓና በአሜሪካ ከሕዝብ በተዘረፈ ሀብት የተቀማጠለ ኑሮ ይመራሉ። እዚህ ተራው ትግራዋይ እብሪትና ማንአህሎኝነት በፈጠረው ጦርነት በረሃብ በእርዛት ይገረፋል።
የትግራይ ሕዝብ ከአምላኩ ከተቀረው ኢትዮጵያዊና ከኤርትራዊ ወገኑ በጥል ግድግዳ የለየውን የሽብር ኃይል በቃ ብሎ ለመነሳት ምን እንዳያጣ ነው ዝምታን የመረጠ የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አእምሮ ይመላለሳል። ልጆቹን ክብሩን እምነቱን ህልሙን ራዕዩን ወዘተረፈ የነጠቀው ኃይል ምን ከዚህ የከፋና የባሰ ነገር እንዳያመጣበት ነው በቃ ! ለማለት ድፍረት ያጣው !? በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በ30 የዓለም ከተሞች ጣልቃ ገብነትን ሽብርን ውሸትን በቃ ! ሲሉት የከሀዲውና የሽብር ቡድኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ገፈት ቀማሽ የሆነው ትግራዋይ በቃ ለማለት ድፍረት ያጣው ምን የከፋ ነገር እንዳይመጣበት ነው ? ለዘመናት በክፉው በደጉው ቀን አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለህ ተጋብተህና ተዋልደህ ከኖርከው ከአማራ ከአፋርና ከመላው ኢትዮጵያዊና ከኤርትራውያን ጋር እንድትቆራረጥ አደረገህ። በየሰዓቱ ጠላት እየቀፈቀፈልህ በጥርጣሬ እንድትተያይ አደረገህ። በገዛ አገርህ ባይተዋርነትና ባዕዳነት እንዲሰማህ በአገርህ በወገንህ ተስፋ እንድትቆርጥ አሴረብህ። አጥንትህን ከስክሰህ ደምህን አፍስሰህ ባቆምካት አገር ላይ እንድትነሳ ሸፍጥ ሰራብህ።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ብሎ ተማምሎ ማገደህ። እንግዲህ ምን ቀረኽና ምንስ የባሰ ሊመጣ ነው በቃ ለማለት አንደበትህ የተያዘው !? የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዳግም ጭቆና የማይንበረከክ መሆኑን እና አሸባሪው ሕወሓት ዳግም አይደለም ኢትዮጵያን ትግራይን እንደማይገዛ እያወቅህና ይሄን ህልቆ መሳፍርት ዋጋ ከከፈልክ በኋላ በቃ ያላልኸው የበቃ ዋጋው ስንት ቢሆን ነው ? ከሕወሓት በላይስ ምን ጠላት አለህና ነው የሥልጣን ጥሙን ለማርካትና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ጠላት እንደጫጩት እየፈለፈለ ከወገንህ የሚያናክስህ ?።
የትግራይ ሕዝብ ሆይ ! ዛሬም በቃ ! ለማለት አረፈደምና ንቃ ! ተደራጅ ! ተነስ ! በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች የምትኖር ትግራዋይ ሆይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመህ ሰንኮፉን የምትነቅልበት ጊዜው አሁን ነውና ሕወሓትን በአንድ ድምጽ በቃ በለው። እጣ ፈንታህ ከኢትዮጵያና ከሕዝብ ጋር እንጂ ነገ የታሪክ አተላ ከሚሆነው አሸባሪ ጋር አይደለም። በቃህ ! በለው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም እንደትናንቱ ከጎንህ ነው።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
ዘመን ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም