በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ግብፅ ጦርዋን ልካ ብትወረንስ? ተብለው ተጠይቀው ነበር፤ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ እኛ እኮ የያዝነው የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አይደለም አሉ። ተሰብሳቢውን ሁሉ ሳቅ በሳቅ አደረጉት። በርግጥ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድናችን ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ከግብፅ ጋር በተጋጠመ ቁጥር መሸነፉ የተለመደ ነበር። ዘንድሮ ግን ታሪክ እየተቀየረ ነው።
ባለፈው ወር በማላዊ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድናችን ባደረገው ግጥሚያ የግብፅ ብሔራዊ ቡድንን ሁለት ለባዶ አሸንፎ ድልን አብስሮናል ። ድሉን ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ለሚሞላው ሕዳሴ ግድብ እንደ መክፈቻ የምሥራች አድርጌ አይቼዋለ ሁ።
የዘንድሮ ክረምት ለሦስተኛ ጊዜ የሕዳሴ ግድብ የሚሞላበት በመሆኑ የሀገራችን ሰላምና ደስታ የሚያስቀናት፤ ሤራ በመምዘዝና ከባንዳዎች ጋር ደባ በመፍጠር ግጭት በማማዘዝ ጭምር የምትታወቅው ታሪካዊ ጠላታችን እርሟን ታወጣለች።
ባንዳዎችን ብር እና ጠብመንጃ እያስታጠቁ በእርስ በርስ ግጭት ሊያተራምሱን የሚሞክሩት ሀይሎችም ልፋታቸው ሁሉ ከንቱ ይሆናል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ግድቡን ለማሳካት የሄዱበት ርቀትና ስኬት አንዱ ማሳያ ነው።
ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ተባባሪዎቻቸው የግድቡን ግንባታ ለማስቆም የሄዱበት የከፋ የጥፋት መንገድ በብዙ ሲያንገዳግደን ከመታየቱ ውጪ አቅም አግኝቶ ሊጥለን አልቻለም ። ለዚህ ደግሞ አንድነታችን ወሳኝ አቅም ሆኖልናል ።
በሕዳሴ ግድቡ በሀገራችን በየቦታው የምናየው የጽንፈኝነት ዕትብቱ ይቀበራል። በሕዳሴው ግድብ ለግጭቶች የታንክም የባንክም ምንጩ ይገደባል። እርስ በርስ እያናከሱን ከበሮ የሚመቱ ሁሉ ደረታቸውን ይመታሉ። በዚህም ልፋታቸው ሁሉ ድንጋይ መንክስ እንደሆነ በስኬታችን አሳይተናቸዋል።
በቅርቡ በየቦታው በባንዳዎች የተከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች የውክልና ጦርነቱ አካል ናቸው ማለት ይቻላል። ለዓመታት በዓባይ ጉዳይ የበይ ተመልካች ሆነን በኖርንባት ሀገር ህዝብን ከጠላት እና ከድህነት ነፃ ማውጣት እንደ ቀላል ሥራ የሚቆጠር አይደለም።
በዚህም ‹‹የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› የሚለውን በርግጥም ተረት እናደርገዋለን። በዓባይ ጉዳይ ሤራ የሚጎነጉኑ ቅስማቸው ይሰበራል። የሤረኞችም ተላላኪ ባንዳዎች የገቢ ምንጫቸው ይነጥፋል፣ ይጠፋል።
‹‹ከሞት ወዲያ ማልቀስ ድንጋይ መንከስ ነው›› እንደሚባለው ሁሉ ግድቡ ለሦስተኛ ግዜ ሲሞላ አደብ ይገዛሉ እርማቸውን ያወጣሉ። ያላቸው ብቸኛ አማራጭም ይህንኑ እውነታ መቀበል ነው። ግድቡ እራሱን በራሱ የመጠበቅ አቅም ያለው መሆኑ ለሁላችንም በራሱ ማስተማመኛ እንደሚሆንም ይታመናል።
ባለፈው ዓመት በክረምቱ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሚከናወንበት ወቅት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት 80 በመቶ የደረሰ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል። በወቅቱ በካርቱም ታይቶ የማይታወቅ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቶ ነበር። ባለሥልጣናቱ የሕዳሴው ግድብ ባይኖር አደጋው ይከፋ ነበር ማለታቸው ይታወሳል።
እንደሚታወቀው የዓባይን ወንዝ የመገደብ ሀሳብ የተወጠነው በንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው። በወቅቱ ከዓለም አቀፍ ገንዘብ ተቋማት ዓባይን በብድር ለመገንባት የተደረገው ሙከራ ግብፅ ባደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጫና አልተሳካም። ንጉሡ ግን ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕውቀትም ገንዘብም ሲያገኝ ይገነባዋል›› ብለው ነበር። ታዲያ ጊዜው ደርሶ የዓባይ ግድብ ተጀምሮ፤ አሁን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተንደረደርን ነው።
የህዳሴው ግድብ ስኬት ሕዝብና መንግሥት እጅ ለእጅ ተያይዘው በትጋት በመሥራታቸው ያስገኙት ነው። ሕዝብ ከዓመት ልብሱ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ እያዋጣ ቦንድ እየገዛ የበኩሉን ሲወጣ፤ መንግሥት ደግሞ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ አስፈላጊ ባለሙያዎች በመመደብ በመቅጠርና ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በዲፕሎማሲው ረገድም የሚከሰቱ ጫናዎችን ሁነኛ ባለሙያዎችን በመመደብ በመነጋገር ተግዳሮቱን ለማርገብ ተችሏል።
በተጠናቀቀው ዓመት እንኳ በዓባይ ጉዳይ ላይ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ምዕራባውያን እና የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ለግብፅ ያደላ አካሄድ ሲያራምዱ ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያውያን አንድነት አሸንፎ የግድቡ ግንባታም ተጠናክሮ ሦስተኛውን ዙር ውሃ ሙሌትን እየጠበቅን እንገኛለን።
በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት የዓባይን ውሃ በታዛቢነት ሲከታተል ቆይቶ የግብጽ የውሃ ‹‹ሴኩሪቲ››አይነኬ ነው በማለት መግለጫ ማውጣቱ ፤ ይህም የተቋሙን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ፤ወጥ አቋም የሌለው እና ወደ አንድ ወገን ያደላ አካሄድ እየተከተለ ስለመሆኑም በአደባባይ ምስክርነት እየሰጠ ነው ።
በዲፕሎማሲው እየታገልን ግድባችንን እየገነባን ዓባይን እዚህ ማድረሳችን ትልቅ ስኬት ነው። ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች ጭምር ምሳሌ መሆን ችለናል። በቅርቡ አዲስ አበባ ተገኝተው የነበሩት የቡርኪና ፋሶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹ህዳሴ ግድብ የአፍሪካ ኩራት መገለጫ ነው!›› ማለታቸውም የዚሁ እውነታ ማሳያ ነው ።
በሀብት ማሰባሰብ በኩልም ግድቡ ከተጀመረበት ከ2003 ዓ.ም እስከ ተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ፤ ከሀገር ውስጥ እና በውጪ የሚገኙ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች በአጠቃላይ 16 ቢሊየን 915 ሚሊየን 312ሺህ137 ብር መሰብሰቡን ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ከሐምሌ 1 ቀን 2013 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም 1 ቢሊዮን 186 ሚሊየን 297ሺ 461 ብር ተሰብስቧል። ገንዘቡ የተሰበሰበው ከሀገር ውስጥና ከዲያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስጦታ አካውንት ገቢ፣ ከፒን ሺያጭ ገቢና ከ8100 አጭር የስልክ መልዕክት አገልግሎት ነው።
“ዓባይ ዓባይ የአገር አድባር የአገር ሲሳይ“ የሚለው ዘፈን ዕውን ሆኖ እናየዋለን። ፍቺው ዓድባር ተራሮች ዛፎች ማለት ሲሆን፤ ሲሳይ ማለት ምግብ ወይም ራት ነው። በቅርቡ የሕዳሴው ግድብ መብራት ራትና ኩራት ይሆነናል። ከሕዳሴው ኤሌክትሪክ ብዙሃኑ ተጠቃሚ ይሆናል፤ ምግብ ለማብሰል ዛፍ ከመጨፍጨፍ ይቆጠባል፤ ይህም ለአካባቢ ጥበቃ ይረዳል፣ደን ልማት ይስፋፋል።
ለጎረቤት ሀገሮች በሚሸጠው ኤሌክትሪክም የውጪ ምንዛሪ እናመነጫለን፤ በሚከፈቱ ብዙ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ። ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ያለመጉዳት ፖሊሲዋን አጥብቃ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም ፍላጎቷን ዕውን ታደርጋለች።
ይቤ ከደጃች. ውቤ
የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል