ወልዶ መሳም ዘርቶ መቃም የሰው ልጆች ሁሉ ምኞት ነው። በተለይ ሦስት ጉልቻ መስርቶ ጎጆ ቀልሶ ኑሮዬ ላለ ሰው ይህ ምኞት ተገቢም አስፈላጊም ነው። ወልዶ መሳምም ይሁን ዘርቶ መቃም ብሎም ሦስት ጉልቻ መስርቶ ጎጆ መቀለስ ሁሉም እንደየሁኔታቸው የሚጠይቁት ሂደት ደግሞ አለ።
ዘርቶ ለመቃም ሞፈርና ቀንበር አዋህዶ በሬን ከበሬ አዳብሎ አርሶ መዝራትን ዘርቶ ማረምን ፍሬ ሲደርስ አጭዶና ወቅቶ ፍሬን ከገለባ ለይቶ በጎተራ ማስቀመጥን ይጠይቃል።
ሦስት ጉልቻ ለመመሥረትም በቅድሚያ አይን ያረፈባትን ልቡ የከጀላትን ኮረዳ ማግባባቱና መጠየቁ የሚቀድም ነው። ከዚህ በኋላም ሁለቱ ተፈላላጊዎች መስማማት ብሎም ጉዳዩን ወደቤተሰብ ወስዶ ፍቃድን መጠየቅ ተጨማሪው ሂደት ነው። ይህ ሁሉ ከታለፈ በኋላ ደግሞ ለሠርግ የሚሆነውን ነገር ማዘገጃጀቱ ሌላ ጊዜና ገንዘብ ብሎም ጉልበት የሚጠይቅ ይሆናል።
እገሊት እኮ ልጇን ልትድር ነው ከተባለም የቅርቡም የሩቁም ዘመድ አዝማድ ጎረቤት ጓደኛ ተሰብስቦ የሚከውነው ነገር የሚያዋጣው ግብዓት ብሎም ሃሳብ ብዙ ነው።
ወደ ድግስ ሥራው ከተገባም በኋላ ደግሞ እንደ ባህልና ወጋችን ጌሾ ወቀጣው፣ እንጨት ፈለጣው፣ በርበሬ ቅንጠሳው ብቻ ጣጣው ብዙ ነው። እንዲህ ያለው ሂደት ደግሞ ለቤተሰቡም ሆነ ለቤተዘመድ የሚሰጠው ክብርና ሞገስ ትልቅ ነው። እገሊት እኮ ክብሯን የጠበቀችዋን ልጇን ዳረች ይባልላታል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ በጎረቤት አልፎም በዘመድ አዝማድ ዘንድ ምሳሌም ሆኖ እስከመነሳት የሚደርስ ግርማ ሞገስ አለው። በተለይም በቤታቸው ውስጥ አስቸጋሪ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ምን ጊዜም ቢሆን አላየሽም የእገሊትን ልጅ ክብሯን ጠብቃ ተድራ ኮርታ ስታኮራቸው እየተባለ ይነገራል።
እንዲህ ሽር ጉድ ተብሎ ወራቶች ተወስደው የተዘጋጀው የሠርግ ድግስ ደግሞ ዘመድ አዝማድ በተሰበሰበበት ወዳጅ ዘመድ እየበላ እየጠጣ በሚጫወትበት በመጨፈር ሂደት ብዙ አዝናኝ ነገሮች ይፈጠራሉ።
አንዳንድ ነገሮች በተለይም በሠርግ ወቅት የሚፈጠሩ ክስተቶች አዝናኝ ስለሚሆኑ የማይረሱበት አጋጣሚም ብዙ ነው። ነገር ግን በዚህ ተቃራኒው አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሚፈጠሩ አሳዛኝ ነገሮች ሙሽሮቹንም ሆነ የሙሽሮቹን ቤተሰቦች ሰቀቀን ውስጥ ከተው ያልፋሉ። አንዳንድ ጊዜ ሙሽሪት ቁጭ ብላ እየጠበቀች ባልዬው ሊቀር ይችላል፤ ይህ በራሱ ከሙሽራዋ ባሻገር በቤተሰቡ ብሎም በታዳሚው ላይ የሚፈጥረው ሃፍረትና ድንጋጤ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከሙሽሮቹ ቤተሰብ መካከል በዋዜማው አልያም በዕለቱ በአይቀሬው ሞት ተጠርተው የሚያልፉም አይጠፉም ይህም የሚያሳርፈው ጠባሳ ቀላል አይደለም።
ይህንን ሁሉ መንደርደሪያ ያደረግነውም አንድ በጣም አሳዛኝና ልብ ሰባሪ የሆነ ክስተት ስላጋጠመን ነው። የዛሬዋ ባለታሪካችን ዳንሴ ቱፋ ትባላለች ውልደትና እድገቷ ሞጆ ከተማ ነው ወላጆቿ በጥሩ ሁኔታ ነው ያሳደጓት። ዳንሴ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም እንደ እኩዮቿ ተምራ ስደስተኛ ክፍል ደርሳለች። በአካባቢው እንዳሉት እንደማንኛዋም ሴት ደግሞ ዕድሜዋ ለሦስት ጉልቻ ሲደርስ እንደ አገሩ ባህልና ወግ ልትዳር ጎጆ ቀልሳ ሙሉ ሴት ልትሆን በትዳሯ መካከልም ወልዳ ልትስም ተዘጋጀች።
ለትዳር የተዘጋጀው ሰውም ምንም እንኳን እሷ በቅጡ ቀርባ ያወቀችው ባይሆንም አባቷና አባቱ በፈጸሙት ስምምነት መሠረት የተዘጋጀ ነው። ይህ ሰውም የታጨችለትን እጮኛውን በአገር ባህልና ወግ መሠረት ሊያገባ ለቤተሰቦቿ ሽማግሌ ልኮ የሚያስፈልገውን ጥሎሽ ጥሎ አስጠየቀ፤ ቤተሰቡም እንዲህ ባለው ክብር ልጃቸውን ለመዳር መታሰባቸው እጅግ አስደስቷቸው ለመጡት ሽማግሌዎች ልጃችንን ለልጃችሁ ትሁን ብለው ፍቃዳቸውን ሰጡ።
ቤተሰብ በዚህ ክብር ተሰምቶት ሳያበቃ ተከብራ ያስከበረቻቸውን ልጃቸውን እንዴት ባለው መልኩ ደግሰው እንደሚድሯት የትኞቹን ዘመዶቻቸውን ወገኖቻቸውንና ጓደኛ ጎረቤቶቻቸውን በጠቅላላው ወዳጆቻቸውን ጠርተው እንደሚያበሉ የደስታቸው ተካፋይ እንደሚያደርጉ አሰቡ።
ይህንንም እያሰቡ በቤታቸው አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የድግስ ሥራ ተያያዙት ፤ በቅርብም በሩቅም ያለ ስለጉዳዩ የሰማ ወዳጅ ዘመድም ሁሉ የሚችለውን አቅሙ የፈቀደውን በዓይነትም በጉልበትም አስተዋጽኦ አደረገ ለማድረግም ተዘጋጀ፤ ያ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የልጃቸው የሠርግ ቀንም ቀስ ቀስ እያለ አፋፍ ላይ ደረሰ። ዳንሴ ሦስት ጉልቻ ልትመሰርት ከእናት አባቷ ቤት በክብር ተድራ ልትወጣ አንድ ሳምንት ብቻ ቀራት። እነሱም ቢሆኑ ከሞላ ጎደል ዝግጅታቸውን ስላጠናቀቁ የቀኑን መድረስ በጉጉት ጠበቁት እንጂ አልፈሩም።
እሷም የረጅሙን የዕድሜ ዘመን አጋሯን ወደፊት የምትወልዳቸው ልጆች አባትን ባሏን ለማየት እንደናፈቀች ቀን ትቆጥራለች። ነገር ግን ዳንሴ እነዚህ ሁሉ እቅድ ሃሳቦቿን እንደጉም የሚያተን ብሎም ሕይወቷን ባላሰበችው ሁኔታ የሚያመሰቃቅል ጉድ ገጠማት። በዚህም ሰማይ ተደፋባት እንደዛ የተለፋበት ወግ ማዕረግ ሊታይበት የተናፈቀው ነገር ሁሉ ውሃ በላው። ዳንሴ ቱፋም በማታውቀው ምክንያት ለሠርጓ አንድ ሳምንት ሲቀራት መላ አካላቷ መታዘዝ አቃተው ጉልበት ከዳት ከተኛችበት ተነስታ መጸዳጃ ቤት እንኳን መሄድ አቃታት።
በዚህ ሁኔታዋ ደግሞ ቤተሰብ በሙሉ ተደናገጠ የትዳር አጋሯም ክው ብሎ ቀረ። ምን ሆና ነው ? የሚለው ጥያቄ የሁሉም ሆነ ነገር ግን መልሱን ሊሰጥ የተቻለው አንድም የቤተሰብ አባል አልተገኘም። ዳንሴ ቱፋ የደረሰባትን ነገር አሁንም ድረስ ማመን አልቻለችም፤ ስትናገርም እጅግ በጣም ሆድ ይብሳታል መላ አካላቷ ተሳስሮ ከተቀመጠችበት ወንበር ላይ የሚያነሷት ብቸኛዋ እናቷ ወይዘሮ ራዴ ጫካ ናቸው።
ወይዘሮ ራዴም የልጃቸው ሁኔታ ያሳዝናቸዋል የ27 ዓመቷ ዳንሴ እንደዚህ ሆና አያታለሁ እኔ እጅ ላይ ወድቃ ትቀራለች ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር ይላሉ። ወይዘሮ ራዴ ከምንም በላይ ደግሞ አንገታቸውን ያስደፋቸው ነገር ለራዴ ተብሎ የመጣውና የተቀበሉት ጥሎሽ ነው። «የልጄን ጥሎሽ በልቼ አፈርኩ» ይላሉ።
ላለፉት ስምንት ዓመታትም እናት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ልጃቸውን እየተሸከሙ ብዙ ፈተናዎችን አይተዋል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚያማቸው ነገር የልጃቸው ችግር ይህ ነው የሚላቸው ሀኪም ማጣታቸው መፍትሔውን የሚያመላክታቸው መቸገራቸው ነው።
እናት ከምንም በላይ የሚያሳስባቸው ነገር ዕድሜያቸው መግፋቱ ነው። ዕድሜያቸው መግፋቱ ደግሞ ልጃቸውን ለማገላበጥ አቅም አጣለሁ ብለው ሳይሆን ለማን ጥያት አልፋለሁ የሚለው ነገር ነው የሚያሳስባቸው። ዳንሴም ብትሆን ሁል ጊዜ የምትላቸው አንቺን ካጣሁ እኔ ምን እሆናለሁ ነው።
እናት ዛሬ ላይ ትንሽ አመም ሲያደርጋቸው ራሱ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ፤ ልጄን ለማን ልተዋት ነው በሚል ጭንቀት። ዛሬ ላይ እናትና ልጅ የሚረዳቸውም የሚያግዛቸውም የለም ለጋብቻ ያጫት እጮኛዋም ችግሩን አልተካፈለም፤ እንዲያውም ይላሉ እናት ራዴ የልጁ አባት ከእኔ ጋር ለፍቷል ውጤት ባያመጣም ይላሉ።
ይህች የ27 ዓመት ኮረዳ ልትዳር ባልም ለቤተሰቧ 12 ከብት፣ እንዲሁም ሌሎች ባህልና ወጉ የሚፈቅደው ሁሉ መጥቶላታል ይህንንም እናትና አባቷ ተቀብለዋል፤ ዛሬ ላይም እናት ከልጃቸው መሰናከል ባሻገር እንቅልፍ እየነሳቸው ያለው ነገር ይህ የበሉት የልጃቸው የሠርግ ጥሎሽ ነው። እኔ ብሞት ይህንን ዕዳ ማነው የሚያወጣው? የሚለውም እንቅልፍ አሳጥቷቸዋል።
ዛሬ ላይ ተነስተው የጥሎሹን ገንዘብ አይመልሱ አቅም የላቸውም ልጃቸውን ድረው በባህል በወጉ አለማቸውን አያዩ ነገር ልጃቸው እንኳን ለባል ለራሷም መሆን ተስኗት እጅና እግሯን በአግባቡ ማዘዝ አቅቷታል፤ ይህንን እያነሱ ደጋግ ኢትዮጵያውያን ይድረሱልኝ ይላሉ።
«እኔ ዕድሜዬን ጨርሻለሁ የሌት ተቀን ጭንቀቴ ለልጄ ነው፤ ልጄ እኔ ከሞትኩባት የምትቀመጥበትም የላት የሚያስታውሳትም አታገኝ» ይላሉ።
ዳንሴ እንባ እያነቃት ትናገራለች «የምወደውን ሰው ለማግባት በጣም ፍላጎት ነበረኝ ነገር ግን ለሠርጌ አንድ ሳምንት ሲቀረኝ ታመምኩ፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ አባቴ እንዴት ያመማት ልጅ ለባል እሰጣለሁ ብሎ እምቢ አለ፤ ከዳነች የእናንተው ናት ብሎ እኔን ወደማሳከም ሄደ፤ እኔ ግን አልዳንኩም። አሁን ላይ ባለቤቴም ሌላ ሚስት አገባ» ትላለች።
ወደ ሕክምና ሄዳ መጀመሪያ የኩላሊት ጠጠር አለብሽ እንደተባለች የምትናገረው ዳንሴ በብዛት ውሃ በመጠጣት ጠጠሩ ሊወጣ እንደሚችል እንደተነገራት ትገልጻለች። ከሦስት ጊዜ በላይም ራጅ መነሳቷን በመግለጽ አሁን ላይ በሆዷ ውስጥ ተቀምጦ አላስተኛ አላስቀምጥ የሚላትን ሕመሟን በሕክምና መፍትሔ እንዳገኘችለት ትናገራለች። ሆኖም እንደ ልቧ መራመድ በእጆቿ ይዛ ውሃ መጠጣት ልብሷን ለብቻዋ መልበስና መጸዳዳት እንደማትችል ትገልጻለች።
አሁን ላይ ይላሉ እናት ጎረቤት ሄጄ ቡና መጠጣት ይጨንቀኛል፤ ዘመድ ቤት አልሄድም እነሱም አይመጡም ፤ ለቅሶ አልደርስም ፤ ብቻ እሷን አምኖ ቤት ውስጥ ጥሎ መሄድ ያስጨንቀኛል ፈጣሪ ረድቶኝ ልጄ የሚያግዛት ነገር ብታገኝ ይላሉ እንባ በተሞላበት ድምጽ።
በመሆኑም እናትና ልጅ በዚህ መሰል የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ነው ያሉት ዛሬ ላይ የሚያግዛቸው ይፈልጋሉ፤ ደጋግ ኢትዮጵያውያን አለንላችሁ በሏቸው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015