በመርካቶ ተገኝቶ ሸመታ ለማድረግ የሚመላለሱ ሰዎች ከቀማኛ ራሳቸውን እየጠበቁ ግራ ቀኛቸውን እየገላመጡ የሚንቀሳቀሱ ናቸው:: መርካቶ የብዙ ነገሮች መገኛ ቦታ እንደሆነችም ይነገራል:: ከአፍሪካ ቀዳሚው የገበያ ቀጠና የተባለው መርካቶ በውስጡ የያዘው ታሪክ በልኩ የተነገረ እስካይመስል ድረስ ነው:: በአመታት መካከል እጅግ አስገራሚ የሆኑ ክስተቶች በመርካቶ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ:: ከመርካቶ ጓዳ አንዳንዶች የገባቸውን በፊልም፣ በግጥም እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ለማቅረብ ጥረት አድርገዋል:: ስንቶቻቸው በሚገባ እንደገለጡት ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም::
በቦሌ መንገድ ላይ ዘናጭ መኪና ይዞ የሚነዳ የመርካቶ ነጋዴ መርካቶ ውስጥ ግን አለባበሱ በተቃራኒው ሆኖ አንድ ተራ ሰው መስሎ ሊታይ ይችላል:: ምክንያቱም ቦታው መርካቶ ነውና ሰዎች ዝቅ ብለው ከፍ ለማለት የሚታትሩበት ስለሆነ:: መርካቶ የብዙ ሃሳቦች እርስ በእርስ ፍጭት መድረክ አድርገን ልንወስደውም እንችላለን፤ በተግባርም ነው:: ነጋዴው በታታሪነቱ ወይንም ግብር በማጭበርበሩ፤ ግለሰቡ ሠርቶ ለማደር በመወሰኑ ወይንም ቀማኛ በመሆን በመሰለፉ፤ የመንግሥት ሰዎች ንግድን ተቆጣጥሮ ለሕዝብ በመሥራት ወይንም ለሙስና እጃቸውን ሰጥተው የሙስና ገበያ በመሆናቸው፤ ወዘተ::
ከመርካቶ ገጠመኞች መካከል አንዱን እንደመነሻ ተመልክተን የግራ ቀኙን ነጥብ እናንሳ:: አባት፣ ሚስትና ሁለት ልጆች በመርካቶ መካከል ዕቃ ተሸክመው ወደ አውቶቡስተራ ለመድረስ እያቀኑ ነው:: አውቶቡስ ይዘው ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ፤ አዲስ አበባን እንደ መሸጋገሪያ እያደረጉ:: አባት ፍራሽ ተሸክሞ በሌላ እጁ አንዱን ልጅ ይዟል:: እናትም ዕቃ ይዛ በሌላኛውን ልጅ ይዛለች:: በዚህ መሃል ተወንጫፊ ሌባ የአባትን እጅ መትቶ ከእጁ ያለውን ሰዓት ቀምቶ እግሬ አውጪ ብሏል:: አባትም ፍራሹን ከመሬት ላይ ጥሎ ሌባውን በማሳደድ መንገድ ውስጥ ነው:: «ሌባ ሌባ ሌባ» በሚል ጩኸት አካባቢው በግርግር ውስጥ ነው:: ሌባው በሚያውቀው የመርካቶ ጉራንጉር ውስጥ ገብቶ ተሰወረ:: አባትም ሰዓቱን አስረክቦ ያለ ውጤት ተመለሰ:: የሁለት ሀሳቦች ትንቅንቅ የሌብነት እና የራስን ሀብት የማስጠበቅ::
ሌሎች መሰል የመርካቶ ገጠመኞችን ብንሰማ የምናገኘው ታሪክ አስደማሚ ይሆናል:: የስርቆት ድራማዎች በሚገባ ተቀርጸው የሚተወንባቸው ቦታ መርካቶ እስኪመስል ድረስ በመርካቶ ጀርባ ላይ መሰል ትእይንቶች ይገኛል:: ትልቅ ልውውጥ፤ ገንዘብ ለብዙ ነገሮች ገንዘብ ሆኖ የሚቀርብበት ስፍራ፤ ግራ ቀኙ ሌባ መስሎ በነፃነት መመላለስን የሚገድብበት ቦታ፤ መርካቶ:: በሰዎች ዘንድ ያለ የበዛን ሀሳብ የሚያሳይ የቁሳቁስ ብቻም ሳይሆን የሀሳብ አተገባበር ማሳያ ስፍራ:: ሀሳብ ተጽንሶ፤ ሀሳብ የሚወለድበት:: በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊነቱ የሚነበብበት ስፍራ::
በግራም በቀኝም ስላለው በሀሳብ መስመር አልፈን ከማየታችን በፊት አንድ የልቦለድ መጽሐፍ ማንበብ የሚወድ ወጣትን እናንሳ:: ወጣቱ አንባቢነቱን ብቻም ሳይሆን ተቀያያሪ ባህሪውንም ያውቀዋል:: ተቀያያሪ ባህሪው የሚመጣው ከሚያነበው መጽሐፍ የሆነ:: ራሱንም «እንዳነበብኩት» እያለ ይጠራል:: እንዳነበብኩት ዙሪያ ገባውን የሚያየው እንዳነበበው መጽሐፍ ነው:: የስለላ መጽሐፍ ባነበበ ጊዜ አጠገቡ ያለው ሰው ሁሉ ሰላይ ይመስለዋል:: የስነልቦና መጽሐፍ ካነበብ አጠገቡ ያለው ሰውን ድርጊት በስነልቦናው መጽሐፍ ዓይነት እያየ ይመለከታል:: ከትንሽ ተነስቶ ቱጃር ስለሆነ ሰው ካነበበ የሚያየውን ነገር በሙሉ እንዴት ወደ ቱጃርነት እንደሚወስደው ይሆናል፤ በአጭሩ እንዳነበበው ነው::
በግራም በቀኝም የበረከተ ድምጽ ባለበት ዘመን ውስጥ ስንኖር ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባው ነገር ዛሬ እየኖንበት ያለው ኑሮ ትናንት በተዘራው ሀሳብ ምን ያህል ተጽእኖ ውስጥ መሆኑን ነው:: ትናንት የተዘራው ዛሬ ላይ ሕይወታችን ነው፤ የዛሬው ደግሞ ነገ:: ግራ ቀኝ! የከበረውን መለየት መቻልና በከበረው ውስጥ መሆኑ ያለውን ፋይዳ ስንረዳ ለከበረ ሀሳብ ቦታን ሰጥተን ሕይወታችንን እንቃኛለን::
የከበረውን መለየት መቻል
በግራም በቀኝም ያለው የሀሳብ ውጤት ነው:: ሀሳቡ የታሰበበት ይሁን ያልታሰበበት የዛሬውን መልክ በብዙ ወስኗል:: መልካም ሃሳብ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሕይወትን ሲመራ ክፉ ሃሳብ ደግሞ በተቃራኒው:: ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ስለ ሀሳብ በጻፈው ጽሑፍ ውስጥ ሃሳብ ምን ያህል የከበረ ነገር መሆኑን ለማሳየት አንድ ታሪክን አቅርቦ ነበር::
ታሪኩ የሚከተለው ነው፤
አንድ ጊዜ አንድ የሮም የጦር መሪ ወደ አንድ የአይሁድ ከተማ ይገባል:: የከተማዋን ሕዝብም ወደ አንድ የማጎርያ ሥፍራ ይሰበስባቸዋል:: የከተማዋ ቤቶች አንድ ሳይቀሩ እንዲቃጠሉ ለወታደሮቹ ትእዛዝ ይሰጣል:: በዚያ ጊዜ ሕዝቡ በቤቶቹ ውስጥ ያለውን ሀብት ለማውጣት ለመነ::የሮም ወታደሮች ግን አልፈቀዱም:: የሕዝቡ ልመና እየበዛ ሲሄድ የወታደሮቹ አለቃ አንድ ነገርፈቀደ::
ሕዝቡ ሁሉ ተስማምቶ አንድ እጅግ የሚፈልጉትን ነገር ብቻ እንዲያወጡ:: ሕዝቡ ተተራመሰ::አንዱ አንድ ሌላውም ሌላ ይላል:: ከዚያ ሁሉ ሀብት መካከል እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ነገር መርጦ ማውጣት አስቸጋሪ ሆነ:: ማንንም የሚያስማማ ሀሳብ ማግኘትም አልተቻለም::
በመጨረሻ ሕዝቡ በአንድ ነገር ተስማሙ:: ረቢው (የአይሁድ መምህር) በጉዳዩ ላይ እንዲወስን:: ረቢው ወደ ከተማው ገቡ:: ያቀኑትም ወደ ምኩራቡ ነበር:: ሕዝቡ ሁሉ ምን ይዘው ሊወጡ እንደሚችሉ የየራሱን ግምት ይሰጥ ነበር:: አንዳንዱ ደግሞ የሚሆነውን ለማየት በጉጉት ይጠብቅ ነበር::
ረቢው ወደ ሕዝቡ ሲመለሱ አንዳች የሚታይ ነገር አልያዙም:: ወደ ወታደሮቹ አለቃ ሄደው አንዲት ያረጀች በብራና የተጻፈች መጽሐፍ መሳይ ነገር አሳዩት:: የወታደሮቹ አለቃ ስቆ አሰናበታቸው:: እናም ከተማዋ ተቃጠለች::
የከተማዋ ሕዝብ በጉዳዩ ላይ በጣም በመበሳጨቱ ረቢውን ሊገድላቸው ተነሣ:: ስንት የወርቅ እና የብር ሀብት እያለ:: ስንት በከበሩ ድንጋዮች ያጌጠ ሀብት እያለ አንዲት ያረጀች ብራና ይዘው በመምጣታቸው በምርጫችን ተሳስተናል አለ::
ወታደሮቹ ከተማዋን አቃጥለው ሲሄዱ የከተማዋ ሰዎች ሜዳ ላይ ፈስሰው ረቢውን ጠየቋቸው:: ለምን? ሲሉ::
ረቢው እንዲህ አሉ:: «አዎን በከተማዋ ለዓይን የሚያጓጓ ብዙ ሀብት አለ:: ወርቅ አለ:: ብር አለ:: የከበሩ ድንጋዮችም አሉ:: የሐር ልብሶች አሉ:: ከተልባ እግር የተሠሩ ልብሶች አሉ:: የጌጥ ዕቃዎች አሉ:: ሁሉም አሉ:: ይህ ግን ከሁሉ ይበልጣል::
“እንዴት?” አለ ሕዝቡ::
«እነዚያ ያለቁ ነገሮች ናቸው:: አንድ ጊዜ ይሸጣሉ፤ ይበላሉ:: ያልቃሉ:: ለጊዜያዊ ችግር ይሆናሉ:: እኛን ከረሃብ ያላቅቃሉ:: ነገር ግን አያዘልቁንም:: ሰው የሚበላ ብቻ አይደለም:: የሚጠጣም ብቻ አይደለም:: ሰው ማለት ሁለት ነገር ነው:: መንፈስ እና ሥጋ:: ሥጋ ማለት ምንድን ነው? ሥጋ ውሱን ነው::
በቦታ፣ በጊዜ እና በዐቅም ይወሰናል:: መንፈስስ? መንፈስ ግን አይወሰንም:: መንፈስን በአንድ እሥር ቤት ልትወስነው አትችልም:: ወደ ላይ ወደ ምጥቀቱ፤ ወደ ታችም ወደ ጥልቀቱ ይወርዳል:: መንፈስ አገር የለው:: ይዋኛል:: ይቀዝፋል:: መንፈስን በጊዜ አትገድቡትም:: ወደ ኋላ ወደ ትናንት፣ ወደ ፊት ወደ ነገ ይጓዛል:: ሥጋን በአንድ ቅርጽ ብቻ ማኖር ይቻላል:: በአንድ ሞላላ ቤት፤ በአንድ አራት ማዕዘን ቤት፤ በአንድ ጉድጓድ ማኖር ይቻላል:: መንፈስን ግን በአንድ ቅርጽ ማኖር አይቻልም::
ለተወለደ ልጅ ስም ይወጣል እንጂ ለወጣ ስም እንዴት ልጅ ይወለዳል? ዳዊት የሚባል ስም አውጥቶ እንዴት እንደ ዳዊት ያለ ልጅ ለመውለድ ይቻላል? መንፈስን በቅርጽ መወሰን እንዲህ ነው:: ማሰብ ያለብህ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ነው፤ አንተ የዚህ ወይንም የዚያ ቡድን አመለካከት አለህ፤ አንተ ይህንን ወይንም ያንን ብቻ ሁን ማለት አይቻልም:: መንፈስ ነፃነትን ይፈልጋል:: ዓይኑን ጨፍኖ ወደ ውስጥ፣ ዓይኑንም ገልጦ ወደ ውጭ መጓዝ ይሻል::
«እዚህ ውስጥ ወርቅ ወይንም ብር የለም:: እዚህ ውስጥ ሀሳብ አለ:: ሰውን ሰው የሚያደርግ ሃሳብ አለ:: ሰው ለሕልውናው ዓላማ እንዲኖረው:: የሚኖርበት ምክንያት እንዲኖረው፤ ሰው ከመብላት እና ከመጠጣት በላይ ማሰብ እንዲችል:: ሰው ከመኖር በላይ ማሰብ እንዲችል:: ሰው ከችግሮቹ በላይ መኖር እንዲችል:: ለነገ ሲል ዛሬን፣ ለጭንቅላቱ ሲል ሆዱን፣ ለነፍሱ ሲል ሥጋውን፣ ለሌላው ሲል ራሱን መሠዋት እንዲችል የሚያበቃ ሃሳብ አለ::
«ይህ ሃሳብ ሲሞት ያን ጊዜ ከተማችን ፈጽማ ትጠፋለች:: ይህ ሃሳብ ካልሞተ ግን ዘጠኝ ጊዜ ብትጠፋ እንኳን አሥር ጊዜ አብልጠን እንገነባታለን:: ይህ ሃሳብ ከሞተ ሆዳችን አድጎ ጭንቅላታችን ይቀጭጫል:: ይህ ሃሳብ ካልሞተ ግን ሆዳችን ቀጭጮ ጭንቅላታችን ያድጋል:: ይህ ሃሳብ መቶ ሀገራችን ሀብታም ትሆን ይሆናል:: ነገር ግን ሆዳሞች የሞሉባት ሀብታም ሀገር ትሆናለች:: ሆዳሞች ደግሞ መጀመሪያ የሀገራቸውን ሀብት ይበላሉ:: ቀጥለው ሕዝባቸውን ይበላሉ:: በመጨረሻም እርስ በርሳቸው ይበላላሉ::
ያለ ሃሳብ ከመሠልጠን፣ ያለ ሥልጣኔ ማሰብ ይሻላል:: ያለ ሃሳብ መሠልጠን ያለ ልክ የተሰፋን ልብስ መልበስ ነው:: ሰውዬው እየወፈረ ይሄድና ልብሱን መቅደዱ አይቀርም:: ልብሱ ለሰውዬው እንጂ ሰውዬው ለልብሱ ሊሰፋ አይችልምና:: ያለ ሃሳብ መሠልጠን ሰውዬውን ለልብሱ እንደማዘጋጀት ያለ ነው:: ሰውዬው ከልብሱ በላይ እንዳይሆን ወይ ታስርቡታላችሁ፣ ያለበለዚያም በወፈረ እና በረዘመ ቁጥር ትቀንሱታላችሁ፣ ያለበለዚያም ውፍረቱን እና እድገቱን ለመቀነስ ሌላ ቅጣት ትቀጡታላችሁ::
ሃሳብ የሌለበት ዕድገት እና ሥልጣኔ እንደዚህ ነው:: ሰው ምንም ቢሆን ማሰቡን አይተውም:: ያለ ሰው የሚኖር ሃሳብ፣ ያለ ሃሳብ የሚኖርም ሰው የለም:: ስለዚህ ለኛ ሃሳብ ይበልጥብናል:: ይህ መጽሐፍ ከኛ በፊት የነበሩ ሰዎች ያሰቡትን፤ በዘመናችን ያላችሁ ሰዎች ያሰባችሁትን ነገር ይዟል:: ለሀገር ትልቁ ሀብቷ ሃሳቧ ነው:: በሀገር ዋናዎቹ ሰዎች ቀድመው እና ልቀው ማሰብ የሚችሉ ዜጎቿ ናቸው:: የበቁ አሳቢዎች የበቁ መሪ ዎችን መፍጠር ይችላሉ፤ የበቁ መሪዎች ግን የበቁ አሳቢዎችን መፍጠር አይችሉም::
ሃሳብ እና ሃሳቢ የሞተባት ሀገር ወይ ሞታለች፣ ወይ ለመሞት ተዘጋጅታለች:: እናም ወዳጆቼ አትዘኑ:: ሃሳባችሁን የወሰደባችሁ የለም:: ማሰብ ከቻላችሁ ዓለም ሁሉ የእናንተ ናት:: ከሀገር የሚበልጥ መቼም የለም:: ሀገርንም ቢሆን እንኳን የሚፈጥራት ሀሳብ ነው:: ያለ ሃሳብ በሀገር ከመኖር፣ ያለ ሀገር እያሰቡ መኖር ይበልጣል:: ማሰብ ካልቻላችሁ ግን በጣታችሁ ያለው ቀለበት እንኳን የእናንተ አይደለም:: ለዚህ ነው ይቺን መጽሐፍ የመረጥኳት::
እንዳትበሉ የሚከለክሏችሁ፣ እንዳትኖሩ የሚከለክሏችሁ፣ እንዳትሠሩ የሚከለክሏችሁ ብዙም አይጎዷችሁም:: እነርሱ እንስሳነታችሁን ነው የከለከሏችሁ:: እንዳታስቡ የሚከልክሏችሁ ግን አደገኞች ናቸው:: ምክንያቱም የከለከሏችሁ ሰውነታችሁን ነውና::»
በዚህ ታሪክ ውስጥ የምናገኘው ቁምነገር የሰው ልጅ የሰውነት ክብሩ የሚገኘው በሀሳብ ውስጥ መሆኑን ነው:: ሀሳብ የከበረውን መለየት መቻል የከበረውን ምርት አድርጎ ለማስገባት ይረዳል:: የሃሳብ መጥራቱም ለዚህ ነው የሚጠቅመው:: ከቁስ ነገር ይልቅ ለጤናማ ሃሳብ ትኩረት መስጠት የቻሉ በሕይወታቸው ውስጥ የሚብላላውን ነገር ጥራት ይወስናሉ::
የሀሳብ ሕይወት የከበረ ሆኖ ሳለ ግን ሀሳብን ማሰብና ያሰቡትን መኖር ውስጥ የምንኖርበት ከባቢ የማይመች ሆኖ ሊገኝ ይችላል:: ማሰብ የተፈቀደ መሆኑ አለመሆኑ ላይ እርግጠኝነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እየኖርንም ያለን ይመስላል:: ጥያቄውን አስቀድመን ጥቂት እንበል፤
ማሰብ ይፈቀዳል?
የጥያቄው መልስ ከሁለት አቅጣጫ ሊሆን ይገባዋል:: በአንድ አቅጣጫ አንድ ሰው በውስጡ የወደደውን ማሰብ ይችላል ወይ? ሲሆን ሌላው ግን ያሰበውን መተግበር ይፈቀድለታል ወይ? ወይንም እንዳሰበው መኖር ይፈቀድለታል ወይ? የሚል ነው::
አስተዳደጋችን ሃሳብን በማበረታታት ዘንድ ያለው መገለጫ የደበዘዘ ነው:: ሃሳብን ከማበረታታት ማሳነስ በሰፊው እንደ ማህበረሰብ ይታይብናል:: አዳዲስ ሃሳቦችን ሰዎች ለመተግበር ሲነሱም ዙሪያ ገባው በእሾህ የታጠረ ሆኖም ይጠብቃቸዋል:: ተቋማት አዳዲስ ሃሳብ እንዳይወጣ አንቀው የሚጠብቁም ይመስላሉ:: ማሰብ በሕግ ደረጃ የተከለከለ የሆነ ይመስል ለአዲስ ሃሳብ በመጣ ቁጥር የሚወረወረው ጦር ብዙም ነው::
ማሰብ ይፈቀዳል ወይ የሚለውን ጥያቄ አንባቢው እያሰላሰለ የሀሳብ መንገዳችን የቀና ይሆን ዘንድ የማሳረጊያ ሁለት ነጥቦች እናንሳ፤
1. ትኩረት በመስጠት ማሰብ፤
ትኩረት በመስጠት ማሰብ ማለት የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ ነገር በቅድሚያ በትኩረት በማሰብ ስለሌሎችም ነገሮች አስከትሎ ማሰብ ማለት ነው:: አንድ ግለሰብ በሕይወቱ ውስጥ ጉልህ ለሚላቸው ነገሮች የሚያደርገው ሃሳብ ነው:: ጉልህ ጉዳዮች ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲታሰብባቸው የሕይወት አቅጣጫ ጤናማውን መስመር ይይዛል:: ከጉልህ ጉዳዮች ቀዳሚው ለግለሰቡ ራሱ ግለሰቡ ነው:: አንድ ግለሰብ እንደ ግለሰብነቱ ስለ ብዙ ነገሮች ሊያስብ ይችላል:: ነገርግን ስለ ራሱ የሚያስበው ከሁሉም ሊቀድም ይገባዋል:: ባልንጀራህን እንደ እራሱ ሊወድ የተነሳ ሰው ከባለንጀራው በፊት ስለራሱ ሊያስብ የተገባው ነው:: ግለሰባዊ ጤናማነት ነውና ወደ ቤተሰብ፣ ወደ ሥራ ወደ ማህበራዊ ሕይወት የሚጋባው::
2. የተግባር ሰው ሆኖ ማሰብ፤
በጤናማ ሃሳብ ሊቃኝ የማይገባው ምንም ነገር የለም:: ሁሉም ነገር በጤነኛ ሃሳብ የተቃኘ ሊሆን ይገባዋል:: ጤነኛ ሃሳብን ወደ መተግበር መሄድ ደግሞ ሌላኛው ወሳኝ ነጥብ ነው:: ሃሳብን ለመተግበር መነሳት የሚፈልገው ጊዜ፣ ገንዘብ እንዲሁም ሌሎች ሀብቶች አሉ:: የተግባር ሰው ሆኖ ለመገኘት ሃሳብን መተግበር ግድ የሚልም ለዚሁ ነው::
መልካም ለሀሳብ ጊዜ የመስጠት ቀናት ከፊታችን ይምጡ!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015