ጓደኝነት ሲነሳ በጎ ሀሳቦች፣ መረዳዳት፣ መተሳሰብ፣ አብሮ መብላት መጠጣት በአዕምሮ ውስጥ ይመላለሱ። እንዲያውም አንዳንዴ ከዚያም በላይ ይሆናል። ጓደኝነት በተለይ የተቃራኒ ጾታ ከሆነ ደግሞ ሁለት ከመሆንም አልፎ አንድ አካል እስከመሆንም ይደረሳል። ጓደኛ ገበና ከታች ነውም ይባላል። የሰው ልጅ በጓደኝነት ደስታና ኀዘንን ሲሻገር፤ ለችግሮቹ መፍትሄ ሲሰጣጥ መመልከት የተለመደ ነው። ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ እንደሚባለው በመደጋገፍ ችግሮችን ለመሻገር ከጓደኝነት የበለጠ መፍትሄ የለም። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ከጓደኝነት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ግጭቶች አይጠፉም። በቅናት፣ በምቀኝነት፣ በክህደት ወይም ደግሞ በሌላ ምክንያት ጸብ ውስጥ የሚገባበት ከዚያም አልፎ ሕይወት እስከመጠፋፋት የሚደርስበት አጋጣሚ በርካታ ነው።
የዛሬዎቹ ባለታሪኮቻችን በሥራ አጋጣሚ የተገናኙት ሁለት ጓደኛሞች ናቸው፡፡ ምሽታቸውን አብረው ማሳለፍ ከጀማመሩ በኋላ ወዳጅነታቸውን እያጠበቁ ይቀጥላሉ። በዚህ ወዳጅነት ውስጥ ችግሮችን ከመጋራት በላይ ደስታዎቻቸውንም አብረው መካፈል ልምዳቸው ሆነ። ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን አንዱ ጓደኛ ልብ ውስጥ የመበለጥ ስሜት፤ ቅናት የወለደው ክፋት ተፀነሰ። ይህ ክፋትን ያረገዘው ልብ ክፋትን ወደ መልካም ከመቀየር ይልቅ ቂምን አርግዞ ጊዜና ቦታ ይጠብቅ ጀመር።
‹‹እኔ የምሠራው ሥራ ውስጥ ሌሎች ገብተዋል›› በማለት ተቀናቃኙ የመሰሉትን በኅብረት ማደግ መፍትሄ አድርገው ሥራቸውን በጋራ የሚሠሩትን ጓደኛሞች በክፉ ዓይኑ መመልከት ጀመረ። ይሄን ልቡ ያረገዘውን ክፋትም ለጓደኛው ተነፈሰለት። ጓደኛውም የቆየ ልማድ ነበረውና የጓደኛውን ባላንጣዎች ለማጥፋት ተስማማ። እንግዲህ ለክፋት የተባበረው ጓደኝነት አዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ ዜሮ አንድ ልዩ ቦታው ሀና ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኝ ቤት ከምሸቱ ሦስት ሰዓት የሰው ነፍስ ለማጥፋት በቃ።
በዚህ ዕለት ከላይ በተጠቀሰው ስፍራ የተገደለ ሰው መኖሩ ለአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ይደርሰዋል። ፖሊስ ጥቆማው ወደ ተሰማበት ቦታ በመሄድ ለምርመራው ያግዛሉ የተባሉ የቴክኒክና የታክቲክ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ ይጀምራል።
ፖሊስ ሟችን የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ በመወጋት የገደለውን ሰው ማንነት ለማወቅ ምርመራ ይጀምራል። የሰው መግደል ወንጀሉ ለምን ተፈፀመ? እንዴት ተፈፀመ? ወንጀል ፈፃሚዎቹስ ይሄንን ወንጀል ከፈፀሙ በኋላ ወዴት ሄዱ? በዚህ የወንጀል ድርጊት ውጤትስ ተጠቃሚው ማነው? ለሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የምርመራ ክፍሉ በቡድን በመሆን ደፋ ቀና ይል ጀመር።
በዚህ ወንጀል ተጠቃሚ ይሆናል የተባለ ከሟች ጋር በቡና ገለባ ንግድ ይተዋወቁ ነበር የተባለ ተጠርጣሪ ጋር ሟች የተለያዩ ጊዜያት ያለመግባባት ውስጥ ገብተው እንደነበረና ስሙም አለልኝ ታደሰ የሚባል ሰው መሆኑን ለፖሊስ ጥቆማ ደረሰው።
ተከሳሹ የቡና ገለባ በሚያከፋፍልበት ወቅት ሳሪስ አካባቢ ከሚገኝ የግለሰብ ድርጅት ውስጥ ይወስድ የነበረና ሟችና የሟች ጓደኛም በተመሳሳይ ይሄ ድርጊት ከመፈፀሙ አስቀድሞ ከሦስት ወይም ከአራት ወራት በፊት ከዚሁ ድርጅት ውስጥ የቡና ገለባ በቀጥታ እየተረከቡ ለተጠቃሚ ያከፋፍሉ ነበር። ገዳይም በዚህ ድርጊት ቅናት ይዞት ‹‹ለምን የቡና ገለባውን ከእኔ አልተረከቡም›› በሚል ከሟችና ከሟች ጓደኛው ጋር ፀብ ውስጥ ገብተው ነበር።
ተጠርጣሪውም ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ዛቻ ያደርስ የነበረ ሲሆን ሟችና የሟች ጓደኛ በተቀመጡበት መጥቶ ‹‹እናንተን ገድዬ ለሁለታችሁ ነፍስ ሰለሳ ሰላሳ ሺ ብር ብከፍል ነው፤ ይህንንም እከፍላለሁ›› በማለት በተደጋጋሚ ይዝት እንደነበር የሰሙ ሰዎች ለፖሊስ ይናገራሉ። ይህም ተጠርጣሪው በፖሊሶች በአይነ ቁረኛ እንዲታይ ያደርገዋል።
ሟች ጌትነት ከሞተ በኋላ ተጠርጣሪው አቶ አለልኝ ታደሰ ከአካባቢው መሰወሩንም ፖሊስ በመረጃው ማግኘት ችሏል። የተጠርጣሪው ማንነት ከተጣራና የሚኖርበት አካባቢ ከታወቀ በኋላ ምርመራው እየተጠናከረ ግለሰቡን ለማግኘት ፖሊሶች አሰሳቸውን ይጀምራሉ።
ይህ የወንጀል ድርጊት በተፈፀመ በአራተኛው ቀን ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ በሚያደርገው ሙከራ አምልጦ ወደ ጫካ ለመግባት ሲሞክር በኅብረተሰቡ ትብብር ይያዛል። ምንም እንኳን የመጀመሪያው ተጠርጣሪ አለልኝ ቢያዝም የምርመራ ቡድኑ ድርጊቱን የፈፀሙት ሁለት ሆነው እንደነበረ መረጃ ስላለው ሌላኛውን ተጠርጣሪ ለመያዝ በተያዘው ተጠርጣሪ ላይ ምርመራ ያደርጋል።
ተጠርጣሪው አለልኝ የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን አምኖ የምርምራ አቅጣጫውን ለማሳት በማሰብ ‹‹ተስፋዬ የተባለ ከዚህ በፊት የማላውቀው ነገር ግን በሀና ማርያም አካባቢ በሥራ አጋጣሚ የማውቀው እና መጠጥ ቤት ውስጥ የተዋወቅኩትን በመገባበዝ ጓደኝነት የመሠረትን ነን። የእዚህ ሰውም መኖሪያ ቤት ሀና ማርያም አካባቢ ነው» የሚል የተሳሳተ መረጃ ሰጠ፡፡
አንደኛ ተጠርጣሪ በቅናት በመነሳሳት የሟችን ነፍስ ማጥፋቱን ቢያምንም የግብረ አበሩን ማንነት በግልፅ ባለመናገሩ ፖሊስ ሌላኛውን ተጠርጣሪ ይዞ ለሕግ ለማቅረብ ዳግም ፍለጋውን አጠናክሮ ቀጠለ። በዚህም ተስፋዬ የሚባለው ሰው ማነው? ተስፋዬ ከሚባለው ሰውና አለልኝ የተባለ ሰው በጋራ ሰው ለመግደል ከቻሉ የጠበቀ ቁርኝት አላቸው ማለት ነው የሚሉ መላምቶችን በማስቀመጥ ፖሊስ ምርመራውን በስፋት እያካሄደ ነው።
ፖሊስ በቡድን ባደረገው አሰሳ ግን ተስፋዬ የተባለው ግለሰብን ማግኘት አልተቻለም። አንድም ሰው ተስፋዬን ስለማወቁ የሚናገር ጠፋ። ምንም ፍንጭ ባለመገኘቱ ከብዙ ድካም በኋላ ተስፋዬ የሚባለው ተጠርጣር ያልነበረ፤ የፈጠራ ሰው መሆኑን የምርመራ ቡድኑ ደረሰበት። አንደኛ ተጠርጣሪ አለልኝ ግን አሁንም ድረስ ግብረ አበሩን ለሕግ አሳልፎ የመስጠት ፍላጎት አልነበረውም።
ፖሊስ ይህንን ጉዳይ ለማጥራት በጥንቃቄ ምርመራውን ቀጠለ። በዚህም ከአለልኝ ታደሰ ጋር ሲወጣና ሲገባ የሚታየው ተስፋዬ ሳይሆን አበበ የሚባል ሰው መሆኑን ፖሊስ ደረሰበት። ይህ አበበ የተባለው ግለሰብም ከዚህ በፊት የሰው ነፍስ ማጥፋቱን ለፖሊሶች መረጃ ደረሰ።
መርማሪው እንደሚናገሩት አበበ ማነው? የሚለውን ጥያቄ የሚመለስ ምንም ነገር ማግኘት አልተቻለም ነበር። ስሙ ብቻ ደግሞ ተጠርጣሪውን ሊያስገኝ አልቻለም። እንደ ዕድል ሆኖ አንደኛ ተጠርጣሪ አለልኝና ይሄው ያልተገኘው ተጠርጣሪ አበበ አንድ ልደት ላይ የተነሱት ፎቶግራፍ በመርማሪዎች እጅ ገባ። ይህ ፎቶ እጃቸው ከገባ በኋላ ተጠርጣሪ አበበ መርኔ እዚያ አካባቢ ለምንና እንዴት እንደመጣ ፖሊሶች መረጃዎች መሰብሰብ ጀመሩ።
በምርመራውም አበበ መርኔ የመጣው ከደበረ ብርሃን አካባቢ መሆኑን ለማወቅ ተቻለ። ከዚህ ቀደም በደብረ ብርሃን የሰው ነፍስ በማጥፋት ወንጀል እስር ቤት እንደነበረ ታወቀ። ስምንት አመታትን በደብረ ብርሃን ወህኒ ቤት ከሳለፈ በኋላ በምህረት ተለቆ አሁን ወንጀሉ የተፈፀመበት ሀና ማርያም አካባቢ የቡና ገለባ የመጠቅጠቅ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ መሆኑንና ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ መሰወሩንም ፖሊሶች ባጠናቀሩት መረጃ ሊታወቅ ተቻለ።
ይህ አበበ የተባለው ተጠርጣሪ ከዚህ በፊትም በሰው መግደል ወንጀል አስራ ስምንት አመት ተፈርዶበት ስምንት አመታትን በደብረ ብርሃን ማረሚያ ቤት ካሳለፈ በኋላ በምህረት የተፈታ መሆኑን ያረጋገጠው የምርመራ ቡድን ይህ ተጠርጣሪ ይገኝበታል የተባለውን አካባቢ ማሰስ ይጀምራል።
ከብዙ ፍለጋ በኋላ ተከሳሹ በመስከረም ወር ላይ በደብረ ብርሃን ከተማ ሕገ ወጥ መሣሪያን ይዞ በደብረ ብርሃን ፖሊስ መያዙንና በጊዜ ቀጠሮ ላይ መሆኑን የምርመራ ቡደኑ መረጃ አገኘ። ፎቶግራፉ በምርመራ ቡድኑ እጅ ስለነበረ ያለበት ቦታ ሲለይ በማረሚያ ቤት መኖሩ ታወቀ። ፖሊስ የፍርድ ቤት ትእዛዝ በመያዝ ወደ ደብረ ብርሃን በመሄድ ተከሳሹ ያለበትን ሁኔታ ለይተው ይሄኛው የምርመራ ቡድን የያዘው ወንጀል ከባድ መሆኑን አስረድተው ከማረሚያ ቤቱ በመረከብ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ተደረገ።
ተጠርጣሪ አበበ መርኔ በምርመራ ወቅት ከሟች ጌታቸው ጋር ትውውቅ እንዳልነበረው ነገር ግን በአካባቢው ያየው እንደነበር ይናገራል። እዚያ አካባቢ ሊያየው የቻለው በአንደኛ ተከሳሽ አለልኝ አማካይነት ነበር። ለአንደኛ ተከሳሽ ደግሞ ገለባ ሲጠቀጥቁና ግሮሰሪ ውስጥ ሲጠጡ የጠበቀ ወዳጅነት መስርተው ነበር። ጓደኝነታቸው እየጠበቀ ሲሄድም በእነ ጌትነት ደረሰብኝ ብሎ የሚያስበውን በደል አለልኝ ለአበበ ይነግረዋል።
መቼስ ልማድ አይለቅ ነውና አበበ ይሄን ሲሰማ ከዚህ ቀደም እንደለመደው ‹‹ተባብረን እናጥፋው›› በሚል ድጋፉን ይገልፅለታል። የወንጀል ድርጊቱንም ለጓደኛው ለአለልኝ ታደሰ ሲል ወንጀሉን መፈፀሙንም ለመርማሪዎቹ ይናገራል።
የምርመራ ውጤቱ ማጠናቀቂያ ላይ ሁለቱም ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን እንዴት እንደፈፀሙት በማስረዳት የእምነት ከህደት ቃላቸውን ይሰጣሉ። ፖሊስ እነአለልኝ ታደሰ ድርጊቱን እንዴትና ለምን እንደፈፀሙ የሰጡትን ቃል በመያዝ የፎረንሲክና የሰው ማስረጃዎችን በማጠናቀር የምርመራ መዝገቡን ለአቃቤ ሕግ አስረከበ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ወንጀል ምርመራ መርማሪ ዋና ሳጅን መንግሥት ታደሰ እንደሚሉት በሥራ አጋጣሚም ሆነ በማህበራዊ ግንኙነት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አለዚያም ወደ ሕግ ማቅረብ ተገቢ ነው።
ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ወይም በሕግ አግባብ መፍታት እየተቻለ በራስ መንገድ በስሜት በመነሳሳት ሕገ ወጥ ድርጊት መፈፀም ጉዳቱ የከፋ ነውና መጠንቀቅ ይገባል። ይህ ድርጊት በወንጀል አድራጊው በማኅበረሰቡና በአገር ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል የሚባል አይደለምና ማንም ሰው በስሜት ጉዳት ከማድረሱ በፊት ቆም ብሎ ማሰብ ይገባዋል ይላሉ።
ውሳኔ
አቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ማስረጃዎችና መረጃዎች በማየት ተጠርጣሪዎቹ በሠሩት የጭካኔ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ሁለቱም በሃያ አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸው።
አስመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015