ከሰውነት ክፍላችን ትልቁን ቦታ የሚይዘው ብዙዎች እንደሚስማሙበትም የጉልበት ዘርፍ የሆነው አይናችን ከፍ ያለ ጥንቃቄን ይሻል:: በመሆኑም ለአይናችን የምንሰጠው ጥንቃቄና የምናደርግለት ክትትል ከሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች ከፍ ያለም ሊሆን ይገባል::
የጤና ባለሙያዎችም እንደሚሉት ሰዎች በተለይም እድሜያቸው ከ 40 ዓመት በላይ ሲሆን በየጊዜው ወደጤና ተቋማት በመሄድ የአይናቸውን ጤንነት ማረጋገጥ ይገባቸዋል:: ይህንን ባደረጉ መጠን ደግሞ ቀስ በቀስ በአይናቸው ላይ ከሚከሰትና ምናልባትም የአይን ብርሃናቸውን ሊያሳጣ ከሚችል ከፍ ያለ ጉዳትም ራሳቸውን ያድናሉ ሲሉም ይመክራሉ::
ድምጽ አጥፍቶ የአይን ብርሃንን ከሚሰርቅ በሽታ አንዱ ደግሞ ግላኮማ ነው:: ግላኮማ ምንም ምልክት ሳያሳይ ቀስ በቀስ እየሄደ የአይን ብርሃንን እስከ ማጥፋት የሚደርስ የአይን እክል ሲሆን አይኑን ቶሎ ቶሎ በህክምና ባለሙያ የሚያሳይ ሰው ግን በዚህ በሽታ የመጠቃት እድሉ ዝቅተኛም ስለመሆኑ ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት፤ ምናልባት በጤና ባለሙያ የዓይን ግፊት ህመም (ግላኮማ) እንዳለብዎት ወይም ለዚሁ ችግር ከሌሎች በበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ተነግሮዎት ይሆናል።
አለያም ደግሞ በዓይን ግፊት ህመም የተያዘ (የተጠቃ) ሰው ያውቁ ይሆናል። ስለግላኮማ ምንም ሰምተው ላያውቁም ይችላል። ያም ሆነ ይህ ግን ግላኮማ ምንድን ነው? በሽታው ሲከሰት የሚኖረው ምልክት እንዴት ይገለጻል? በእይታችን፣ በኑሯችን ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖስ ምን ይመስላል? የህክምናው ዓትነት እንዴት ይገለጻል? የመከላከለያ መንገዶቹ ምንድን ናቸው? የሚሉ ነጥቦችን በዚህ ጽሁፍ ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የዓይን ግፊት ህመም (ግላኮማ) ምንድን ነው?
ግላኮማ በብርሃን አማካኝነት ዓይናችን የሚቀበለውን መረጃ ለአንጎላችን የሚያደርሰውን እይታ ነርቭ የሚያጠቃ የዓይን ጤና ችግር ነው።
እይታ ነርቭ ብለን የምንጠራው ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ገመድ ጥቃቅን ሽቦ (ክር /ሐረግ/) መሰል ነገሮች የተሠራ በመሆኑ የዓይን ግፊት ከሚፈለገው በላይ ጨምሮ በእነዚህ ጥቃቅን የነርቭ (ገመዶች) ላይ ጉዳት ሲያደርስ ጉዳት የደረሰበት የነርቭ ክፍል መረጃ ለአንጎላችን በበቂ ሁኔታ ማድረስ (ማቀበል) ስለማይችል ጉዳቱ በደረሰበት የዓይን ክፍል የማየት ችሎታ ይቀንሳል። ይሁን እንጅ በእይታ ነርቭ ውስጥ የሚገኙት የነርቭ ሐረጎች የጉዳት መጠን የከፋ ደረጃ እስኪደርስ በግላኮማ የተጠቃ ሰው ችግሩ መከሰቱን ሳያውቅና ህመም ሳይሰማው ለብዙ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። የጉዳቱ መጠን እየጨመረ ሄዶ በከፍተኛ ደረጃ ወይም ሙሉ በሙሉ ነርቩ ሲጎዳ ምንም የብርሃን መረጃ ከዓይን ወደ አንጎል ስለማይደርስ ዓይነ ስውርነት ይከሰታል።
የኤሌክትሪክ ገመድ ጥቃቅን ሽቦዎች ጉዳት ቢደርስባቸው (ቢበጠሱ) ጉዳት የደረሰበትን (የተበጠሰውን) በመጠገን ወይም ገመዱን ሙሉ በሙሉ በመቀየር አገልግሎት ማግኘት የሚቻል ቢሆንም በእይታ ላይ ነርቭ ሐረጎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ግን በምንም አይነት መንገድ ጥገና አድርጎ ወይም ቀይሮ የእይታ መቀነስን ወይም ዓይነ ስውርነት ማስተካከል አይቻልም።
በሌላ አነጋገር ግላኮማ ድምጹን አጥፍቶ የዓይን ብርሃንን (እይታን) የሚያጠፋ ወይም የሚሰርቅ አስከፊው የዓይን ህመም ነው። ቀስ በቀስ የእይታ አድማስን እያጠበበና የቀጥታ እይታን እያዳከመ ለዓይነ ስውርነት ይዳርጋል ::
ስለሆነም የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ብቸኛው መፍትሄ ግላኮማው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲታወቅ ወቅታዊና ተገቢ የዓይን ምርመራ ማድረግና ጉዳቱንም ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ የህክምና አማራጮችን መጠቀም ነው።
ግላኮማ በዓለም ላይ ዓይነ ስውርነት በማምጣት ከዓይን ሞራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን በሀገራችንም ከዓይን ሞራና ዓይን ማዝ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ የሰዎችን ብርሃን በመንጠቅ ይጠቀሳል። በዓይን ሞራ እንዲሁም በዓይን ማዝ የሚመጣን ዓይነ ስውርነት በቀዶ ህክምና ሰዎች ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ወደነበራቸው እይታ ወይም ተቀራራቢ የእይታ መጠን መመለስ ሲቻል በግላኮማ ምክንያት የመጣን የእይታ መቀነስ (ዓይነ ስውርነት) ግን መመለስ አይቻልም። ለዚህም ነው የግላኮማ ችግር አሳሳቢና አስጊ የሚሆነው። ስለዚህ የህክምናው ዋና አላማ ህመሙ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስና የጉዳቱ መጠን እየከፋ እንዳይሄድ ማድረግ ነው። ይህን እውነታ ችግሩ ያለባቸው ወይም ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በደንብ ሊገነዘቡት ይገባል።
በተጨማሪም እንደ ዓይን ሞራ በአንድ ጊዜ ህክምና ሊድን የማይችል በመሆኑ ችግሩ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ በሕይወት ዘመን ሙሉ ክትትል ማድረግን ይጠይቃል።
ግላኮማ በምን ምክንያት ይመጣል?
እንደማንኛውም የአካል ክፍል ዓይናችንም የሚጠበቅበትን የማየት ሥራ እንዲሠራ (እንዲያከናውን) የተለያዩ ነገሮች ለምሳሌ አየር፣ ውኃ፣ ምግብና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ያስፈልጉታል። ዓይናችን የያዘውን የኳስ መሰል ቅርጽ እንዲይዝ ያስቻለው ዓይናችን ውስጥ ያለው ውኃ መሰል ፈሳሽ ሲሆን ይህ ፈሳሽ የዓይንን ቅርጽ ከመጠበቅ በተጨማሪ ለተለያዩ የዓይን ክፍሎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የማድረስና በጊዜ ሂደት የሚፈጠሩ (ጥቅም ላይ የዋሉ) ንጥረ ነገሮችን ከዓይን የማስወገድ ሥራ ይሠራል።
የዓይን ኳስ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመስጠት ከውስጥ በቂ የሆነ የግፊት ኃይል (አየር) ሊኖረው ይገባል። ኳሱ ውስጥ ያለው የግፊት መጠን ከበዛ ወይም ካነሰ በኳሱ ላይ ጉዳት ይደርሳል። በተመሳሳይም ዓይናችን ውስጥ ያለው ፈሳሽ ሲበዛ ወይም ሲያንስ ዓይን ሥራውን በአግባቡ የማይወጣ ከመሆኑም ባሻገር በዓይናችን ላይ አካላዊ ጉዳት ይደርሳል።
ከላይ እንደተገለጸው ግላኮማ የሚከሰተው በዓይናችን ውስጥ ያለው ዓይነ ውኃ ከሚፈለገው በላይ ተጠራቅሞ (የዓይን ግፊት ጨምሮ) ከዓይን ወደ አንጎል መረጃ በሚያስተላልፈው (በሚያቀብለውዉ)ነርቭ ላይ ጉዳት ሲያደርስ ነው። በደምሳሳው ግላኮማ የሚከሰተው በዓይን ውስጥ የሚገኘው የፈሳሽ መጠን የግለሰቡ ዓይን ከሚቋቋመው በላይ ተጠራቅሞ የዓይን ግፊት በእይታይ ነርቭ ላይ ጉዳት ሲያደርስ ነው።
ለግላኮማ የሚያጋልጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ምንም እንኳን ዘር፣ ፆታ፣ እድሜ፣ ሃይማኖት ሳይመርጥ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም ለዚህ ችግር ሊያጋልጡ የሚችሉ ዋና ዋና ነገሮች የሚከተሉት ናቸው። የእድሜ መጨመር (አርባ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ለግላኮማ ተጋላጭነታቸውም እየጨመረ ይሄዳል፤ የጥቁር (የአፍሪካ) ዝርያ፣ከቤተሰብ ማለትም ከእናት፣ ከአባት ፣ከእህት፣ ከወንድም አንዱ በግላኮማ የተያዘ ከነበረ
ሌላውም የቤተሰብ አባል በበሽታው የመያዝ እድሉ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ይሆናል፤አጠቃላይ የሰውነት ህመሞች ለምሳሌ የስኳር ፣ ደም ግፊት፣ የልብ ና ከፍ ያለ የራስ ምታት (ሚግሬይን) ያለባቸው ሰዎች ፤በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የእይታ ችግር በቅርብ፣ በርቀት የማየት፤ በአደጋ ወይም በሌሎች ህመሞች ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ዓይን ከሆነ ፤ የዓይነ መስታወት ውፍረት መቀነስ ወይም ስስ ዓይነ መስታወት፤ ለረጅም ጊዜ ሳይቋረጡ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ለትራኮማ አጋላጭ ተብለው በባለሙያዎች ይገለጻሉ።
ግላኮማ መኖሩ የሚታወቀው እንዴት ነው?
አንድ ግለሰብ ግላኮማ እንዳለበት ሊያውቅ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ልምድ ባለው ዓይን ሀኪም ሙሉ የዓይን ምርመራ ተደርጎለት ሲረጋገጥ ብቻ ነው። በዚህም አንድ ሰው ግላኮማ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት ለማወቅ የሚከተሉት መሠረታዊ ምርመራዎች ። የዓይን ግፊት መለካት፤የዓይነ መስታወት ውፍረት መለካት፤እይታን ነርቭን በልዩ መሣሪያ ማየትና ጉዳት ካለም የጉዳቱን መጠን መለካት፤ የእይታ አድማስን በልዩ መሣሪያ መለካት ሲሆኑ ከላይ የተጠቀሱት ምርመራዎች ከተደረጉ በኋላ ሀኪሙ አንድ ሰው ግላኮማ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት፤ ካለም የጉዳቱ መጠን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገምግሞ የሚያስፈልገውን የህክምና አማራጭ ከህመምተኛው ጋር በመወያየትና በመምከር ውሳኔ ይሰጥበታል። በምርመራው ወቅት ግላኮማ የሌለባቸው ነግር ግን በግላኮማ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ለሆኑ ሰዎች መደበኛ የሆነ ዓመታዊ የዓይን ምርመራ እንዲያደርጉ ምክር ይሰጣቸዋል።
የግላኮማ ህክምና ምንድን ነው?
አንድ ግላኮማ ያለበት ሰው ሊያውቀውና አምኖ ሊቀበለው የሚገባው ነገር በግላኮማ ምክንያት የመጣ የእይታ መቀነስ በምንም አይነት የህክምና ዘዴ ወደ ነበረበት ሊመለስ እንደማይችል ነው። በመሆኑም የሚደረግለት ህክምናም የበለጠ ወይም ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከልና ያለውን እይታ ባለበት ጠብቆ ለማቆየት መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል።
ለግላኮማ ህመም የሚደረጉ ዋና ዋና የህክምና አይነቶች በሦስት ይከፈላሉ ፤ የመድኃኒት ህክምና፣ የብርሃን ጨረር (ሌዘር) ህክምናና የዓይን ግፊት ቀዶ ህክምና ናቸው:: እነዚህ ህክምናዎች ዋና አላማቸውም የዓይን ግፊትን በመቀነስ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከልና የጉዳቱ መጠን እንዲቀንስ ማድረግ ብቻ ነው።
ግላኮማ የሌለበት ሰው ምን ሊያደርግ ይገባል ?
ጠቅለል ባለ መልኩ የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች ልብ ማለት ከተቻለ ሰዎች እይታቸውን ለመጠበቅ፤ ግላኩማ ከተከሰተም ጉዳቱን ለመቀነስ ይችላሉ። እድሜያቸው ከአርባ ዓመት በላይ ከሆነ፣ በቤተሰብ የግላኮማ ችግር ካለ ወይንም ያለበት ሰው ካለ፣ ሌሎች ለግላኮማ የሚያጋልጡ የጤና ችግሮች ካሉ ግላኮማ የሚያመጣውን ጉዳት መከላከል ስለሚቻል ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የዓይን ምርመራ ማድረግ በጣም ወሳኝ ነው፤ በሌላ በኩልም የግላኮማ ምርመራ የሚደረግባቸውንና በአቅራቢያ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ማወቅ፤ ስለግላኮማ ያለዎትን እውቀትና ግንዛቤ በተለያዩ መንገዶች ማዳበርና እንዴት እይታዎን ሊጎዳ እንደሚችል መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው::
ከ40 ዓመት በኋላ የተለመደ ፣ የዓይን ግፊት የደም ግፊት ለግላኮማ የመጀመሪያ ተጋላጭነት የሚጨምር ጊዜ በመሆኑ እድሜው በዚህ ውስጥ ያለ ሰው በሙሉ በየጊዜው ወደጤና ተቋማት በመሄድ የአይን ግፊት መጠንን መለካት ችግሩም ካለ በቶሎ እርምጃ ለመውሰድ የሚያግዝ ብሎም እንደ እድል ሆኖ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015