አዲስ አለም ከተማ በ1925 ዓ.ም ነው የተወለዱት፤ የገበሬ ልጅ ቢሆኑም ገና በህፃንነታቸው ነጋዴው ታላቅ ወንድማቸው አዲስ አበባ አምጥተዋቸው ቀጨኔ መድሃኒያለም በሚገኘው የቄስ ትምህርት ቤት አስገባቸው፤ ዳዊትም ደገሙ:: ብዙም ሳይቆዩ ግን በአዲስ አለም ከተማ ታዋቂ የሆኑ የዜማ መምህር ጋር እንዲማሩ ዳግሞ ወደ ትውልድ ቀያቸው ተላኩ:: ሁለት ዓመት ዜማ ከተማሩ በኋላ አዲስ አበባ መጥተው በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው በስምንት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቁ::
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በከፈቱትና በቀድሞ ሥያሜው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው በኢኮኖሚክ አድሚኒስትሬሽን ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል:: ቤስ በተባለ የፈረንሳይ ጅምላ አከፋፋይ ኩባንያ እንደተቀጠሩ ነፃ የትምህርት እድል አግኘተው አሜሪካ ተላኩ:: በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት ኢኮኖሚክስና አለም አቀፍ ንግድ ላይ ጥናት አድርገው የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀበሉ:: ወደሃገራቸው ተመልሰውም የላካቸው ድርጅት ውስጥ ዳግም ተቀጥረው በቡና ምርትና ሽያጭ ዘርፍ እንዲሁም የድርጅቱ የወጭ ንግድ ሃላፊ ሆነው ሰሩ::
በመቀጠልም ልማት ባንክ ተቀጥረው የፕሬዚዳንቱ ረዳት ሆነው ለጥቂት ጊዜያት ከሰሩ በኋላ በኢንዱስትሪያል ፋይናንሲንግ ትምህርት ዘርፍ ለስድስት ወራት እንግሊዝ ተልከው ስልጠና ወሰዱ:: ወደ ባንኩ ተመልሰውም በኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን የሚባል አዲስ የስራ ክፍል ሃላፊ ሆነው ለአስር ዓመታት አገለገሉ:: ከልጅነታቸው ጀምሮ ነጋዴ የመሆን ህልም የነበራቸው እኚሁ ሰው የመንግስትን ስራ በመተው ቡና ፤ ቦሎቄና ማሾ የተባሉ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ እንዲሁም የተለያዩ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ከውጭ በማስመጣት ሙሉ ለሙሉ ንግድ ውስጥ ገቡ:: ከዚህም ባሻገር በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት ጥጥና ሌሎች ምርቶችን በማምረት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ፈጥረውም ነበር:: ሆኖም ከደርግ ሥርዓት መምጣት ጋር ተያይዞ የእርሻ መሬታቸውም የንግድ ሱቆቻቸው ተወረሰባቸው፤ የነበረውም የፖለቲካ ስርዓት አልጥም ስላላቸው ሃገር ጥለው ከነቤተሰባቸው አሜሪካ ተሰደዱ::
ሥርዓቱ ከወደቀ በኋላ ደግሞ ወደሚወዷት ሃገራቸው ተመልሰው በንግድ ስራቸው ቀጥለዋል:: ከዚሁ ጎን ለጎን አሁን በህይወት የሌሉት ባለቤታቸው የከፈቱትን ‹‹አማ›› የተባውን የበጎ አድራጎት ድርጅት በማስቀጠል ለሃገራቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ:: በዚህም የበጎ አድራጎት ድርጅታቸው የአካባቢውን ህፃናት በስነምግባርና በእውቀት ተገንብተው እንዲያድጉ ብሎም ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ልዩ ልዩ ስጦታ እንዲያሳድጉ በማድረግ በርካታ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት ችለዋል::
እንግዳችን የይርጋ ጨፌን የተፈጥሮ ቡና ለአለም ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በማስተዋወቅ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል:: በዚህም በቅርቡ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ እውቅና ተበርክቶላቸዋል:: አዲስ ዘመን ጋዜጣም የይርጋ ጨፌ ቡና አባት እየተባሉ የሚጠሩትን አቶ ሃይሉ ገብረህይወትን የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ እንደሚከተለው ይዞላችሁ ቀርቧል::
አዲስ ዘመን፡- የይርጋ ጨፌ ቡናን ያገኙበትና ለአለም ያስተዋወቁበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሃይሉ፡– ትምህርቴን እንዳጠናቀኩኝ መጀመሪያ የተቀጠርኩት ቤስ በተባለ አስመጪና ላኪ ኩባንያ ውስጥ ነው:: ይህ ኩባንያ አንድሬ በተባለ ፈረንሳይ ባላሃብት የተቋቋመ ሲሆን ለኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማደግ ትልቅ መሰረት ጥሎ የሄደ ኩባንያ ነው:: በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ላይ ትልልቅ መጋዘኖችን በመገንባት የወጭና ገቢ ንግድ ስራ ይሰራ ነበር:: በጣም ብዙ ሰው ይቀጥር ነበር::
ከየአካባቢው የሚመረተውን ምርት ወደ ውጭ ይልክ ነበር:: ከውጭም ከመኪና ጀምሮ እስከ ተራ የቤት ቁሳቁስ ድረስ እያስመጣ ያከፋፋል ነበር:: ይሄ ብቻ ሳይሆን በወጭ ንግድ በተለይ ጥራጥሬ፣ ቆዳ፣ ቡና ይልክ ነበር:: እኔ እዚያ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ የቡና ምርትና ንግድ ዘርፉ ላይ ተመድቤ በምሰራበት ጊዜ አሁን ይርጋጨፌ ቀድሞ ደግሞ መልካ ሎሌ እየተባለ የሚጠራውን ቡና ያገኘሁት::
በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ቡና ከዚህ ቀደም ሳይታጠብ ነበር የሚላከው:: ይህ ድርጅት ግን ማጠብና መፈልፈል ጀምሮ ነበር:: ቡናው ታጥቦና ተዘጋጅቶ ነው የሚላከው:: እናም ሲዳሞ ውስጥ ከይርጋለም ጀምሮ እስከ ይርጋጨፌ ድረስ በየቦታው አልፎ አልፎ ስምንት ጣቢያዎች ነበሯቸው:: የእኔ ስራ የነበረው በየጣቢያዎቹ እየዞርኩኝ የሚዘጋጀውን ቡና ጥራት መከታተል ነበር:: ሃገሩ አንድ መንገድ ነው ያለው:: ጣቢያዎቹ ደግሞ ከመንገድ ወጣ ያሉ ስለነበሩና መንገዱ ድጥ ስለነበር ለመመላለስ አስቸጋሪ ነበር:: በተለይ በክረምት በጣም ያስቸግር ነበር:: ያም ቢሆን የቡና ማምረቻ ቦታዎች እየተዟዟርኩኝ ስራውን እከታተል ነበር::
ይህንን በማደርግበት ጊዜ ቡናውን በመጠኑ እንለይ ነበር፤ የሲዳሞ ቡና በፍሬው አነስ ያለ ነበር፤ አንዳንድ ደግሞ ረጃጅምና ወፈር ያለ ቡና ዝርያዎች ስለነበሩ በመጠናቸው ለይተን እናስቀምጥ ነበር:: ከስምንቱ ጣቢያ የተፈለፈለውን ቡና በምንለይበት ጊዜ የአንዱ ጣቢያ ቡና በጣም ተለየብኝ:: መልኩ በጣም ያምራል፤ ፍሬም ከሌሎቹ ተለቅ ያለ ነው:: ይሄ የቡና ዝርያ ለምን ከሌሎቹ ተለየ? የሚለውን ነገር ማጥናት ያዝኩኝ:: ይህንን የተለየ ቡና ለብቻው አንድ ናሙና እንዲሁም ሌላውን እንዲሁ ለብቻው አዘጋጅቼ አዲስ አበባ የሚገኘው አለቃዬ ጋር ላኩት:: ያን ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የቡና ቀማሽ አልነበረም፤ ይህንን የሚያደርጉት ገዢዎቻችን ናቸው::
የላኩላትን ናሙናዎች ጀርመንና እንግሊዝ ለቅምሻ ላካቸው:: ሁለቱም ኩባንያዎች ተመሳሳይ የሆነ ግብረ መልስ ነበር የሰጡት:: ይህንን በአይነቱ ለየት ያለውንና ‹‹መልካ ሎሌ›› ብዬ በአካቢው ባለ ወንዝ ስም የሰየምኩት ይህንን ቡና ከሲዳሞ ቡና እንዳንቀላቅል፤ በተቻለ መጠን በብዛት እንድናመርት፤ ለዚህ ቡና ብልጫ ያለ ክፍያ እንደሚከፍሉ ነበር ሁለቱ የውጭ ሃገር ኩባንያዎች በደብዳቤ ያስታወቁን:: ይህንን ስሰማ በጣም ነበር የተደሰትኩት፤ ምክንያቱም በአይኔ አይቼ በቅምሻ ባለሙያዎች ለይተው ያረጋገጡልኝ በመሆኑ ነው::
በጣም በመደሰቴ የተመረተችውን ቡና ለሁለቱም ኩባንያ ሰዎች አካፍለን ላክንላቸው:: እናም ከዚያ ጊዜ ወዲህ እነሱ ባሉት መሰረት እዚያ ጣቢያ ላይ ብዙ ማምረት ጀመርን:: ለምን ይሄ ልዩነት እንደመጣ ለማወቅ ጥናት ማድረግ ጀመርኩኝ:: በእርግጥ ከይርጋጨፌ የሚገኙ ሌሎች ሁለት ጣቢያዎች ነበሩን:: ግን መልካ ሎሌ ቡና ለየት ያለ ነበር፤ አንድም የቡናው ዛፎች ገና ወጣት ወይም ብዙ እድሜ ያላስቆጠሩ ነበሩ:: ብዙዎቹ ቡናዎች ግን ሽማግሌ ዛፎች ነበሩ:: የሚገኙትም ቆቄ ተራራ ላይ ነው፤ የሚታጠበውም ከዚያው መልካ ሎሌ ወንዝ ከሚገኘው ንፁህ ውሃ ነው:: ስለዚህ እነኚህን ልዩነቶች ነው ከሌሎቹ ያገኘሁት::
የሆኖ ሆኖ ይሄ ቡና በጣም ከፍ ባለ ዋጋ መሸጡን ቀጠለ:: የምንሸጠው ቡና በብሔራዊ ባንክ ይመዘገባል:: የመልካ ሌሎ ቡና ዋጋ ግን ሁልጊዜ ከፍ ባለ ዋጋ ነው የሚሸጠው:: ይህንን ያዩ የብሔራዊ ባንክና የእርሻ ሚኒስቴር ሰዎች የቡና ባለሙያዎች ያሉበት አንድ ቡድን አቋቋሙ:: ጣቢያው ድረስ በመሄድ አካባቢውን ማጥናት ጀመሩ:: በእርግጥም እዛ አካባቢ የሚመረተው ቡና ከሌላ አካባቢ ከሚመረተው ቡና የተሻለ ነው:: ስለዚህ ይህንን አረጋገጡና ወደ 19ሺ 500 ሄክታር ከይርጋ ጨፌ ከተማ ዙሪያ ያለውን ቡና ይርጋጨፌ ብለው ሰየሙት::
እያንዳንዱ ከዚያ አካባቢ የሚወጣው ቡና ይርጋጨፌ የሚል ስያሜ ባለው መሸኛ እየተሰጠው ነው እንዲወጣ የተደረገው:: ከዚያ ውጪ ሲዳሞ እየተባለ ነው የሚወጣው:: እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሲዳሞ ቡና ከሚያመጣው ገንዘብ የይርጋ ጨፌ ቡና የሚያመጣው ገንዘብ በሶስት ሚሊዮን ብር ይበልጥ ነበር:: ይሁንና የቡና ሻይ ከመጣ ወዲህ ደግሞ ቡናው ላይ የነበረው የጥራት ልዩነት ተረሳና ለሁሉም አንድ አይነት ዋጋ ሰጡት:: ኢትዮጵያ ከዚያ ከይርጋጨፌ ታገኝ የነበረው ብልጫ ያለው ክፍያ አጣች:: ይህም የሆነው በእውቀት ስላልተመራ ነው:: እንደሚታወቀው በሃገራችን ብዙ ስህተቶች ይሰራሉ፤ አንዱ የሚታየው ግልፅ የሆነው ስህተት ይሄ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ረዳት እንደነበሩ ሰምተናል፤ እስቲ ስለዚህም አጋጣሚ ያጫውቱን?
አቶ ሃይሉ፡- ልማት ባንክ የገባሁት አስመጪና ላኪ ድርጅቱ የኤክስፖርት ክፍሉ ሃላፊ ሆኜ ለሁለት ዓመት ተኩል ከሰራሁ በኋላ ነው:: በነገራችን ላይ ልማት ባንክ የገባሁትም በምክንያት ነው:: የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ቡትከስ የተባለ ጀርመናዊ ሰው ጋር እንተዋወቅ ስለነበር ወደዚያ እንድመጣ ጋበዘኝና ነው ወደዚያ የሄድኩት:: እሱ ወደ ሃገሩ ሲሄድ የሚተካው ኢትዮጵያዊ ለማሰልጠን ቃልገብቶ ስለነበር በዚያ መሰረት ከፍ ባለደመወዝ፤ መኪና ተመድቦልኝ እሱ የሚሰራውን ከስር ከስሩ እየተከተልኩኝ እንድሰለጥን ነው የተደረገው:: ከእርሱ ቢሮ ጎን ያለች ክፍል ተሰጥቶኝ ለባንኩ የሚመጣ ነገር በሙሉ መጀመሪያ የማየው እኔ ነበርኩ:: ቀጥሎም ለእርሱ አሳልፋለሁ:: እርሱም የትኛውንም ነገር በመጀመሪያ የሚሰጠው ለእኔ ነው:: ወይ ያስረዳኛል፤ አሊያም ደግሞ የጨረሰውን ይሰጠኛል:: ዓላማው በባንኩ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር በሙሉ እንዳውቅ ነበር:: በዚህም አይነት የእርሱ ረዳት ሆኜ እዛ ሰራሁ::
ቃል ከገባልኝ ውስጥ አንዱ ውጭ አገር ልኬ በኢንዱስትሪ ፋይናንሲንግ ትምህርት መስክ አሰለጥንሃለሁ የሚል ነበር:: በቃሉ መሰረትም ለስድስት ወር ኢንዳስትሪያል ፋይናንሲንግ እንዳጠና እንግሊዝ አገር ላከኝ:: በወቅቱ እኔን ሲልከኝ የእርሱ ኮንትራት ሊያልቅ የቀረው ትንሽ ጊዜ ነበር:: እንግሊዝ አገር እያለሁ የኮንትራት ማደሻ ጊዜው ደረሰ:: እርሱ ለባንኩ የቦርድ አባላት አንድ ሐሳብ በጽሁፍ ያቀርባል:: ይኸውም እርሱ ያጠናውን ሶስት ፕሮጀክቶች ነበር:: እንዴት ፋይናንስ ቢደረጉ ከጀርመን አገር ባንኮች ብድር እንደሚሰጡ እና እነዚህን ሶስት ፕሮጀክቶች በስራ ላይ ቢውሉ ይህቺን አገር በአጭር ጊዜ ለመክፈትና ወደኢንዱስትሪ ወደማኑፋክቸሪንግ ስራ ኢኮኖሚዋ እንዲዛወር ማድረግ ይቻላል ብሎ ሃሳብ አቀረበላቸው:: ይሁንና በሚኒስትሮቹ ተቀባይነት አላገኘም ነበር::
አዲስ ዘመን፡- በምን ላይ የሚያጠነጥኑ ፕሮጀክቶች ነበሩ?
አቶ ሃይሉ፡- አንዱ ከአሰብ እስከ አዲስ አበባ ዛሬም ድረስ በቦቴ የሚመላለሰው ነዳጅ የቱቦ መስመር ተዘርግቶለት በቀጥታ ማምጣት የሚያስችል ፕሮጀክት ነበር:: ይህም ይባክን የነበረውን ሃብትና ጉልበት በከፍተኛ መጠን ይታደጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት ነበር፡ ሁለተኛ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሰራ የአውቶብስ መስመር መዘርጋት ሲሆን ሌላኛው መላ ሃገሪቱን የሚያስተሳስር የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ የያዘ ትልቅ ፕሮጀክት ነበር::
ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚሆን ፋይናንስ ከጀርመን ራሱ እንደሚያስመጣ በወቅቱ ለነበሩት የቦርድ አባላት ቢነግራቸውም ሐሳቡን ሊቀበሉት አልፈቀዱም:: ይልቁንም በየቦታው ብዙ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች መክፈት እንደሚፈልጉ፤ ለሚቀጥለው ትውልድ አሁን እዳ ማስተላለፍ እንደማይሹ ገለፁለት:: ይገርምሻል! ይህ ሰው በጣም አዝኖ ‹‹እናንተ የተማራችሁ ሚኒስትሮች ናችሁ፤ አገሪቱን የምትመሩ እናንተ ናችሁ፤ እናንተ እንዲህ ካላችሁማ ይህቺ አገር ማደግ አትችልም›› ብሎ ከእነርሱ ጋር ይጣላል:: ኮንትራቴንም አላድስም በሚል አቁሞ ወደካሜሩን በአገሩ ከሚገኘው በሁለት እጥፍ ደመወዝ ተቀጥሮ ነው የሄደው:: እኔም ለስልጠና ከሄድኩበት ሀገር ስመጣ አንድ ሚኒስትር የነበሩ ሰውዬ ተሹመው አገኘኋቸው:: በእኔ ቦታም ሌላ ሰው ተተክቶ ስለነበር ለእኔ ሲባል ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን የሚባል ዲፓርትመንት ተቋቋመና ያንን ክፍል እንድመራ ተደረኩኝ::
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ እንዴት ነበር የንግዱን አለም የተቀላቀሉት?
አቶ ኃይሉ፡– ልማት ባንክ አስር ዓመት ካገለገልኩኝ በኋላ ድሮም ቢሆን ነጋዴ የመሆን ህልም ስለነበረኝ ጥዬ ወጥቼ የራሴን የንግድ ድርጅት አቋቋምኩኝ:: አፍሪካን ሴልስ ፓወር የተባለው ይሄው ድርጅት የግንባታ እቃዎችን ያስመጣ ነበር:: ህንጻዎች ሲሰሩ ጣሪያውን ወተርፕሩፍ ያደርግም ነበር:: በነገራችን ላይ ይህንን ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ በሃገራችን ያስተዋወቀው የእኛ ድርጅት ነው:: ጳውሎስ ሆስፒታል፣ መርካቶ የገበያ አዳራሽና መሰል የወተር ፕሩፍ ስራዎችን ሁሉ የእኛ ድርጅት ነበር የሚሰራው:: ከዚህ በተጨማሪ ከቡና ላኪዎች ቡና እየተረከብኩኝ በቀጥታ ለውጭ ሃገር ገዢዎች በመላክ የወጭ ንግዱ በተሳለጠ መንገድ እንዲሄድ የበኩሌን ሚና ተጫውቻለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ከንግዱ ባሻገር ወደ እርሻም የገቡበት አጋጣሚ ነበር:: እስቲ ያስታውሱን?
አቶ ኃይሉ፡– ልክ ነሽ፤ ወደሻሸመኔ ሲኬድ 190 ኪሎ ሜትር ላይ ወደምዕራብ ወደቀኝ ሶስት ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኝ ሜቶ በተባለ ስፍራ ላይ ነው የእርሻ ስራ የጀመርኩት:: ያ አካባቢ ሰፊ ጫካ ነበር:: ያ ሰፊ ቦታ የጃንሆይ የወንድም ልጆች ሳምሶን በየነ እና ወንድሙ ያንን መሬት ጃንሆይ ሰጥተዋቸው መሬቱን እነርሱ በጋሻ አሸነሸኑትና ለሚፈልግ ነጋዴ፣ ዳኛ ፣አስተማሪ ሳይቀር ሰጡ:: ይህንን መሬት የሚሸጠው ሰውዬ ወዳጄ ነበር:: እርሱ አንድ ሃያ ጋሻ ያዝ አለኝ::
እኔ በወቅቱ በጣም ትርፋማ ስራ ሆኖ ያገኙሁት ንግዱን ነውና ምንም እንኳን የገበሬ ልጅ ብሆንም እንደገና ግብርና ውስጥ መግባት አይታየኝም አልኩት:: ይሁንና ከአንተ ላለመለየት ትልቅ ወንዝ አለ፤ እዛ ወንዝ ላይ አንድ ሁለት ጋሻ ያዝልኝ አልኩት:: እርሱ ለመስኖ የሚመች ሶስት ጋሻ ያዘልኝ:: ግን ሥራ የጀመርኩት ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር:: ባለችኝ ሶስት ጋሻ ላይ እርሻዬን አለማሁ:: በነገራችን ላይ እዛ አካባቢ ያለው ነዋሪ የሚተዳደረው በከብት ርቢ ላይ ነበር:: ከዚህ ጎን ለጎን ትንሽ ትንሽ በቆሎ ያመርታሉ እንጂ እርሻ አያውቁም ነበር:: ስለዚህ ለዚህ ገበሬ ያሳየሁት ነገር ቢኖር ትራክተር እስጣቸውና የእነርሱን መሬት ሄዶ ያርስላቸዋል:: በሰዓት አስር ብር ደግሞ ይታሰባል:: የቦለቄ ዘርና ማዳበሪያም እኔ አቀርብላቸዋለሁ:: ይህን የሚከፍሉት ደግሞ የጉልበት ስራ በመስራት ነው::
በተጨማሪም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ወሰድኩና እዛ ያሉትን የእነርሱን ልጆች ማስተማር ጀመርኩ:: በአካባቢው ክሊኒክም ሆነ ትምህርት አልነበረም:: በመሆኑም የእነርሱን ልጆች ማስተማር ጀመርኩ፤ እናም ገበሬዎቹ ህይወታቸውን በአንድ ጊዜ ለወጡ:: ይሔ የሚያሳየው የእኛን ገበሬ ኑሮ ወይም ሕይወት ለመቀየር እንዴት እንደሚቻል ነው:: በዚህ መልክ ስንሠራ ደርግ መጣና መሬት ላራሹ አለ:: ያለንን የእርሻ ስፍራና የንግድ ቦታ በሙሉ ወረሰብንና ሥራውን ዘግተን እኛም ወጣን:: የሚያሳዝነው ግን ያ ቦታ ተመልሶ ጫካ መሆኑ ነው:: እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያን ዕድሏን ነው ያኮላሹት:: አሁንም ይህ ምን ምን ዓይነት ዕድል እያመለጠን እንደመጣ ያሳያል::
አዲስ ዘመን፡- እርሶ መሬት ላራሹ የሚለውን የደርግ አዋጅ አይደግፉትም ማለት ነው?
አቶ ሃይሉ፡- እንደሱ ለማለት ሳይሆን ከእኛ ተቀምቶ ሲያበቃ ገበሬውም የመሬት ባለቤት ያለመሆኑ ነው የሚያሳዝነኝ:: በእርግጥ ደርግ በመምጣቱ ብዙ ነገር መጥቷል:: አንደኛ የከተማን ትርፍ ቤት በመውረሱ ኢትዮጵያኖችን ድሃ አድርጓል:: ሁላችንም መሠረታችን መሬት ነው:: ግብርና ነው:: ከተማም መጥተን አከራይተን የምንኖረው እና የምንሻሻለው በራሳችን ጥረት ነበር:: ነገር ግን መንግስት ድሃ አደረገን::
እርሱ የሶሻሊስትን ስርዓት አምጥቶ የማምረቻውን ሃይል መንግስት ይዞ እያመረተ የህዝቡን ኑሮ ማሻሻል በፅንሰ-ሃሳቡ ውስጥ ወይም በወረቀት ያለ ነበር:: በተግባር ግን አልሆነለትም::ደርግ ሲወድቅ ወደ ድሮው ቦታ መመለስ ሲገባው አልተመለሰም:: የተወረሰው ቤትም ሆነ መሬት መመለስ ሲኖርበት አልተመለሰም:: ይልቁኑ ለኢህአዴግ መንግስት ያ ለእርሱ ትልቅ ገቢ ሆነ:: ጥንካሬው እርሱ ነው:: ቤት ያከራያል::
የፈለገውን ይጨምራል:: እርሱ ሃብታም ሆነ:: ድሃው ቢሰቃይ የራሱ ጉዳይ ተባለ:: ስለዚህ ያ ስርዓት ለሰፊው ሕዝብ ሳይሆን ለገዢው መደብ ነው የጠቀመው:: የሚገርምሽ በኢህአዴግም ጊዜ ከጓደኛዬ ጋር እርሻ ጀምረን ነበር:: አፋር ገዋኔ ላይ ሰባት ዓመት የጥጥ ሥራ እንሰራ ነበር:: ለመጥረጊያ የሚሆን አገዳም እናመርት ነበር:: እርሱ እዚህ አገር አልተለመደም:: ያንን እያመረትን ወደ ውጪ እንልክ ነበር:: ሁለተኛ ጥጥ እናመርት ነበር:: ሌላም የግብርና ሥራ እንሠራ ነበር::
አንድ ጥሩ ኢትዮጵያን ይጠቅማል ብለን ማሾ ማምረት ጀምረንም ነበር:: ይህች ምስር ማሳይ ዘር በተዘራች በሁለት ወር ውስጥ ትደርሳለች:: በዓመት ሁለት እና ሶስቴ ማምረት ይቻላል:: ወደ ውጪ ስትላክ ዋጋዋ ከሌላው በልጦ ቁጭ አለ:: ከሁመራ ሰሊጥ በላይ የምትሸጠው ማሾ ነበረች:: እርሷን ማምረት ጀምረን ነበር:: የሆነው ሆኖ የአፋር የመሬት አያያዝ አስቸጋሪ ነው:: መሬቱን የሚያኮናትረው የሚመረጥ የሽማግሌ ስብስብ ነው:: እነርሱ ካልፈለጉ ነጥቀው ለሌላ ይሰጣሉ:: እኛ ላይም ይኸው ሆነ:: የምንሰራበትን መሬት ኮንትራት እያለን፤ ሌላ ገንዘብ ለሰጣቸው ሰጡት:: እኛ ከእነርሱ ጋር አንጨቃጨቅም ብለን ወጣን::
አዲስ ዘመን፡- ከሃገር የወጡበት ምክንያት ምን ነበር?
አቶ ሃይሉ፡– እንዳልኩሽ የደርግ አጠቃላይ ሁኔታ ለእኛ ጥሩ አልነበረም:: ለዚህም ነው ግማሹን የደርግ ዘመን የምንኖረው አሜሪካን የኖርነው:: እዚህ ስላልተመቸን ቤተሰቤን ይዤ አሜሪካ እኖር ነበር:: እነመለስ ሲመጡ ወዲያው ሮጠን ተመለስን:: ሥራዬን እንደገና ቀጠልኩ:: ባለቤቴም የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቋመች:: አሁን እርሷ ከሞተች 15 ዓመት ቢሆናትም እኛ ተረክበን እያስቀጠልነው ያለነው:: በነገራችን ላይ ድርጅቱ ከተቋቋመ 29 ዓመቱ ነው:: አሁን ትልቁ ህልማችን ይህንን ሥራ ማስፋፋት ነው:: መንግስት መሬት ሰጥቶናል:: እዛ ላይ ሕንፃ ሰርተን ከፍ ከፍ ያለ ስልጠናን የመስጠት ዕቅድ ይዘናል::
አዲስ ዘመን፡- የተራድኦ ድርጅት ሆኖ ነገር ግን የስልጠና ተቋም ይሆናል ማለት ነው?
አቶ ሃይሉ ፡– አዎ! አናስከፍልም በነፃ ስልጠና እንሰጣለን:: አሁንም በምግብ ስራና በተለያዩ የሙያ መስኮች የተቸገሩ ዜጎችን እናሰለጥናለን:: ከዚህ ቀደምም ከአረብ ሃገር የተመለሱ በርካታ ሴቶችን አሰልጥነን ሥራ እንዲያገኙ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፡- የገቢ ምንጫችሁ ምንድን ነው?
አቶ ሃይሉ ፡- ከድሮ ጀምሮ ግብርና ላይ ነኝ፤ ምርት ወደ ውጪ እልካለሁ:: ከደንበኞቼ መካከል አንዱ የአሜሪካን ኩባንያ ባለስልጣናት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የእኛን ድርጅት አሳየናቸው እና ነገርናቸው:: ልጆቹ እናት አባት የሌላቸው እና በጣም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ የመጡ መሆናቸውን ነገርናቸው:: እንግዲያው እኛ እንረዳችኋለን፤ የእኛ ሰራተኞችም ይረዷችኋል ብለው የእነርሱ ሰራተኞችም ስፖንሰር ማድረግ ጀመሩ:: ለአንድ ልጅ በዓመት 200 ዶላር ነበር:: አንዱ አንድ እና ሁለት ልጅ እየረዱ ይህንን እያካሔድን ነበር:: ነገር ግን ኮቪድ ከተከሰተ በኋላ ኩባያው ከሶስት ሺ በላይ ሰራተኞችን አስወጣ፤ ስለዚህ እኛም አሁን የምናገኘው ገንዘብ ትንሽ ነው:: በዚህ ምክንያት የምንረዳቸው ልጆች ብዛት ከ130 ወደ 50 ዝቅ ብሏል::
አዲስ ዘመን፡- የእርዳታ ተቋሙ የተጀመረው ባለቤትዎ ትውልዱ ላይ ባዩት የሥነምግባር ችግር ምክንያት ያንን ለመቅረፍ ሲባል ታስቦ መሆኑን ሰምቻለሁ:: ይህንን መነሻ በማድረግ አሁን ትውልዱ ላይ የሚታየውን ችግር በምን መልኩ ማረቅ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
አቶ ሃይሉ ፡– ይሄ ጉዳይ ሁላችንንም እያሳሰበን ያለ ነገር ነው:: በተለይ በእድሜ ጠና ያልነው ማለትም እንደ እኔ ሶስት አገዛዞችን ያየን ሰዎች ያሳስበናል:: በጣም ቁልጭ ባለ መልክ ኢትዮጵያ ከምን ወደ ምን እየመጣች እንደሆነ እየታዘብን ነው:: በአፄ ሃይለስላሴ ጊዜም ሆነ በደርግ ጊዜ የብሔር ልዩነት ብሎ ነገር የለም:: እኔ ሳገባ ብታምኑም ባታምኑም እኔ አማራ ብሆንም ሚዜዎቼ ግን ሁለቱ ኦሮሞ አንዱ አማራ ነበር:: ይሄ ጥሩ ምሳሌ ነው:: አሁን ልዩነት ላይ መሰረት ያደረገው ሃገራዊ ችግር ገዝፎ ነው የሚታየው:: ፅንፍ የያዙ ሃሳቦች ናቸው ወጣቱ እያራመደ የሚታየው:: በእኛ ጊዜ ዘር ቆጠራ የሚባል ነገር አልነበረም:: ይሄ አይነቱ ልዩነት ወደ ጫፍ በመድረሱም ነው በምዕራብ ወለጋም ሆነ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ጭፍጨፋና ግድያ እየሰፋ የመጣው:: ይህ አይነቱ ጭካኔ በፊት ለነበረው ለእኔ አይነቱ ትውልድ በጭራሽ የማይገባው ነገር ነው።
ይህ አይነቱ ጎሳ እየቆጠሩ የሚደረግ ጭፍጨፋ በየትም የአለም ሃገር ላይ የሚታይ አይደለም:: አሜሪካ ከአለም የተፈጠረ ህዝብ ሁሉ የሚኖርባት ሃገር ናት :: እዚያም በመኖሬ አውቃለሁ:: እዚያ ሃገር ትልቁ ቁም ነገር በዘር መለያየት ሳይሆን በስራና በእውቀት በልጦ መገኘት ነው:: ይሄ ነው ቁም ነገሩ እንጂ አንተ መጥፋት አለብህ ፣ አንተ መስራት የለብህም የሚባል አመለካከት የለም :: ስለዚህ አሁን በእኛ ሃገር ላይ እየሆነ ያለው ነገር ለቀደምነው ትውልዶች ግራ የሚያገባ ነው። ይህንን ልዩነትም አናውቀውም :: እንዲህ አይነቱነ ችግር ጊዜ ነው የሚያስተካክለው። አስተሳሰቡ ጉዜያዊ ነው። በጣም መርዛማ የሆኑ አስተሳሰቦች አሁንም አለ፤ እኛ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣን በኋላ ነው መሬት ላራሹ የሚለው አስተሳሰብ የመጣው። እኛ ባለን ጊዜ አልነበረም መሬት ላራሹ። አሁን ቁም ነገሩ ተመርን የሚሉት እሳቱን እፍ እፍ የሚሉት ትንሽ ሰዎች ናቸው:: እነሱ ማስተካከልና ማረቅ ደግሞ ከባድ አይሆንም ብዬ ነው የማስበው::
ይህች ሀገር የአማኝ ሀገር ናት ፤ እስልምና ክርስትና ሌላውም የተስፋፋበት ሀገር ነው። የእነዚህ ሁሉ እምነቶች ትምህርት የበጎ ነው እንጂ የክፋት አይደለም።በግብረ ገብ በጎ ትምህርት የተስፋፋበት ነበር። አሁንም ለወጣቱ ትምህርቱን ማስፋፋት ያስፈልጋል። በእርግጥ ይሄ ትውልድ ያለፈውንና አሁን እየሆነ ያለውን እየታዘበ ነው የሚመጣ። ይሄ አፍርጦ ማስረዳት ያስፈልጋል። እየተደረገ ያለው ስህተት ምን እንደሆነ ማወቅ አለበት። በግብረገብ ትምህርት የትውልዱን አስተሳሰብ መቅረጽ ነው። ኢትዮጵያ ፈጣሪዋ አይጥላትም፤ ወድቃም ተንከባላም ቢሆን ትነሳለች።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ካገጠመው ፈተና እንዴት መውጣት ይችላል ብለው ያምናሉ
አቶ ኃይሉ ፤ አሁን የተከሰተው ችግር በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ። ቀውስ ሲመጣ ኢኮኖሚ ይዛባል፤ በሚዛባበት ጊዜ የኢኮኖሚው መሰረታዊ አቋሙ ደካማ በሚሆንበት ጊዜ ይበልጥ ይዛባል። በእርግጥ እኛ ብዙ አናመርትም፤ አሁንም አብዛኛው ምርት የሚመጣው በበሬ የታረሰ ነው። በዚህ ዘመን በበሬ ማረስ ሀጥያት ነው። በዚህ ዘመን በዘመናዊ መንገድ በትራክተር፣ በኮምባይነር ነበር ማምረት ያለብን ።ሆኖም አሁን ተጀምሯል። ዶክተር ዐቢይ እንዳለውም በዘመናዊ መንገድ በጣም ብዙ ስንዴ እየታረሰ ነው። ይህን ማድረግ የነበረብን ግን የዛሬ 20 ና 30 ዓመታት ነበር፤ ያኔ አድርገን ቢሆን ኖሮ አሁን እኛ ከሌሎቹ ሀገሮች በላይ ማምረት እንችል ነበር።
ኢኮኖሚው ለምን እንደዚህ ሆነ ከተባለ ስላልሰራን ነው።አመት ሙሉ መስራት አለብን ። ምክንያቱም ይች ሀገር በጣም ትልቅ አቅም አላት። አሁን ያለው ችግር እንዴት ይቀረፋል ለሚለው አላውቅም! ነገር ግን የሚሰራ ሳይሆን የሚበላ እያፈራን ነው። አሁን የምለው የዚህ ሀገር የኢኮኖሚ ችግር የሚፈታው በመስራትና በመስራት ብቻ ነው። ከችግር መውጪያ መድሀኒቱ መስራት ብቻ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ
አቶ ሃይሉ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015