አባቶቻችን ከፍ ያሉ እውቀቶችን የተሸከሙና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩ ተረትና ምሳሌዎችን አስቀምጠውልን አልፈዋል ። እነዚህ ተረትና ምሳሌዎች ሀሳብን በቀላሉና በአጭር ከማስተላለፍ ባለፈ ከአንባቢ ጋር በቀላሉ ለመግባባት አቅም ያላቸው ናቸው ።
ይህንን ለማለት የተገደድኩት አሁን ላይ በየጓዳችን የምናንጎራጉርበት አለፍ ሲልም በየአደባባዩ የመንግስት ያለህ እያልን የምናለቅስበትን የዋጋ ንረት /በአለማዊና ሃገራዊ ጉዳይ/ ምክንያት በማድረግ ከአፋችን ላይያለችውን ለመመንተፍ ያሰፈሰፉ ቀማኛኞችን ነገር ሆድ ሆዴን ሲበላኝ መክረሙን ተከትሎ ነው ፡፡
በተለይ ሆድ አደር ነጋዴዎች (ታማኞቹን ሳይጨምር) የመረቀዘው የኑሮ ቁስላችን ላይ እንጨት እየሰደዱበት ህመማችንንና የኑሮ ጣራችንን አብዝተውታል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› የሚለውን የአበው ቢሂል ጊዜውን የሚዋጅ ሆኖ ስላገኘሁት የጽሁፌ መንደርደሪያ ያደረኩት፡፡
እናንተዬ ‹‹ነግ በእኔ›› የሚባል ነገር ቀረ አይደል!? ከጉሊት ቸርቻሪው ጀምሮ እስከ ጅምላ አካፋፋዩ ድረስ በሰበብ በአስባቡ የምስኪኑን ህዝብ ኪስ መቦጥቦጡ አላንስ ብሏቸው በአጥንት ሊያስቀሩት ከግራ ከቀኝ ወጥረው ይዘውታል፡፡ እንዲህ ምንተ- እፍረት የሌለው የአደባባይ ዘረፋ መጨረሻው ምን እንደኒሆን ማሰብ ቢከብድም የሚገርመው፤ ጉዳይ ግን አለምአቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ተገን እያደረጉ ከእያንዳንዱ ዜጋ ጉሮሮ እየነጠቁ ኪሳቸውን እያደለቡ ያሉ ግለሰቦች መልሰው የሚኖሩት ከዚሁ ምስኪን ህዝብ መሃል መሆኑ የመዘንጋታቸው እውነታ ነው ፡፡
በተለይ ሰሞኑን የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ነው የሚለው ወሬ እንደተሰማ ምርት በመደበቅ፤ ያለውንም ከጣሪያ በላይ ዋጋ በማናር ብዙዎችን በብዙ መልኩ አራቁተዋል፡፡ የብዙዎችንም ጓዳ ተፈታትነዋል ።የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎም በአዋጅ ህዝቡን አራቁቱት የተባለ ይመስል በሳር በቅጠሉ ላይ ዋጋ በእጥፍ በመጨመር የነዋሪውን ፈተና አብዝተውታል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ከነዳጅ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነገር ባይኖርም በተለይ ቀድሞ በገቡ ምርቶች ላይ ሳይቀር ዋጋ በመጨመር ቁጥሩ ቀላል የማይባለውን ለፍቶአደር ህይወት በከፍተኛ ሁንታ ተፈታትነውታል ።በዚም ለችግር እየተዳረጉ ያሉ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም ፡፡
እስቲ ፈጣሪ ያሳያችሁ፤ ወቅቱ ክረምት ነው፤ መሬቱ ሁሉ በአረንጓዴ የሚሸፈንበት፤ እሸት ምርት በስፋት የምናገኝበት እረ እንዳውም ለወትሮው ጥጋብ በጥጋብ የምንሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ዘንድሮ ግን “ሃባ” በቆሎ እንኳን 15 ብር የሚሸጥበትና እንደስጋው ሁሉ የበቆሎው ጥብስ ብርቅ እየሆነ ያለበት ሆኗል ፡፡
ከሰሞኑ ወደ ቤቴ እያዘገምኩ ሳለሁ ከሰፈራችን በሚገኝ አንድ ዳቦ ቤት የሚወጣው የትኩስ ዳቦ ማዕዛ አወደኝና ለእኔም ሆነ ለልጆቼ ዳቦ ልገዛ ጎራ አልኩ፡፡ ለወትሮው አራት ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ ዳቦ ዋጋ ሁለት ብር ታክሎበት ስድስት ብር መግባቱን አረዱኝና ባይሆን እኔ ይቅርብኝና ለልጆቼ ይዤ ልጋባ ብዬ አምሮቴን ውጬና ራሴን አሳምኜ ገንዘቤ መግዛት የቻለውን ይዤ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡
ወገኖቼ የአንዱ ዳቦ ዋጋ በዚህ ደረጃ መቆለሉ አይደለም የሚገርመው፤ ዳቦው ራሱ ቆሌ የራቀው መሆኑ ነው፤ ከሁሉ በላይ ውሥጤን ያነደደኝ፡፡ ያ መልኩን አሳምሮና ማዕዛውን አውዶ ግዙኝ ግዙኝ የሚለው ዳቦ በማሻሻያና በእርሾ ያበጠ ፤ልክ እንደቅል ውስጡ ባዶ ነበር ለካ፡፡ እንዳንጠለጠልኩበት ፔስታል እየተንኮሻኮሸ ከልጆቼ አፍ ሳይደር ወለሉ ላይ ተጎዘጎዘ፤ በቃ ብሽቀቴን አትጠይቁኝ!፤ ብቻ ለእኔ የተረፈኝ የዳቦውን ቄጤማ መጥረግ ብቻ ነበር፡ ፡ መቼም ልክ እንደእኔ በእየለቱ የስግብግብ ነጋዴዎች እጅ ላይ የወደቃችሁ ብዙዎች እንደምትሆኑ አልጠራጠርም፡፡
እናንተ ይሉኝታ ቢስ ነጋዴዎች ግን እስቲ ልጠይቃችሁ፤ እናንተ ገና ድክ ድክ ብላችሁ ንግዳችሁን ስትጀምሩ ከጎናችሁ ሆኖ የደገፋችሁን ህዝብ በዚህ ደረጃ ከሰውነት ተራ እዲወጣ መግፍፍ እንደምን አስቻላችሁ? እንዴትስ ዞራችሁ መግቢያችሁ፤ መደበቂያችሁና መቀበሪያችሁ ይህው ምስኪን ህዝብ መሆኑን ተዘነጋችሁ? ፡፡
ዳሩ ልፊ ብሎኝ እንጂ እናንተ እንደሆነ የሰውን ሰውነት ከሸቀጥ ከመደባችሁት ቆይታችኋል፡፡ ህዝቡ ግን ዛሬም እየጮኸ ነው ፤ሰሚ እስኪያገኝም
ይጮሀል ፡፡ ከዚህ ሁሉ ችግር ያወጡናል ብለን በጣታችን መርጠን የሾምናቸው እንደራሴዎቻችን ከወዴት አሉ? ይህ ሁሉ የህዝብ ጩኸት አልሰማ፤ እምባውም አልታይ ብሏቸው ይሆን፡፡
ውድ አንባቢያን መርቃችሁና አጨብጭባችሁ የሾማችኋቸው እንደራሴዎቻችሁ የተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አላረካ ብሏቸው ከነውረኛ ነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው ህዝቡን እየቦጠቦጡ መቀመቅም ሲወርዱ እየታዘብን ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰሞንኛ ዜናዎቻችን ዋቢ ናቸው፡፡
ግን ስር ከሰደደውና ከመረቀዘው ከዚህ ለህዝብ ያለመታመን /የሌብነት አባዜ መቼ ነው የምንወጣው ፤አብሮን ለሚኖረውና እጣ ፈንታ ለተጋራነው ህዝብ የምናስበው ከገባንበት እራስ ወዳድነትና ስግብግብነት መንገድስ ወጥተን ሀላፊነት በሚሰማው መንገድ የምንጓዘውስ መቼ ነው?።
ችግሩ ካለበት አሁነኛ ደረጃ አንፃር አሁን ላይ ያየነው ህጋዊ ርምጃ ቤት የሞላውን ቆሻሻ በስንጥር የማጽዳት ያህል እንደሆነ ይሰማኛል፤ጅመሩ እንደ ጅምር የሚበረታታና የሚመሰገን ቢሆንም ፡፡
የዛሬውን ትዝብቴን “ከማክተሜ” በፊት ነውረኞቹ ነጋዴዎችም ሆነ ያበላጀውን እጅ የነከሱት ሹመኞች ሊረሱት የማይገባው ጉዳይ እሽኮኮ ብሎ ከስልጣንና ከሃብት ማማ ያወጣቸው ህዝብ አንድ ቀን የብሶት አርጮሜውን አንስቶ ከፍ ያለ ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል መርሳት እንደሌለባቸው በማሳሰብ ነው፡፡
ያካባቱት ስምና ዝና በአንድ ጀምበር እንደሸክላ ወደ አመድነት ሊቀየር እንደሚችል ከትናት ታሪኮቻችን ሊማሩ ይገባል፡፡ እናንተ ምስኪን የእኔ አይነቶችም ብትሆኑ እለት ቁስላችሁን እየነካካ ከሚያመረቅዝ ሃሜት ተላቃችሁ የመጠየቅ፤ የማጋለጥና ለፍርድ የማቅረብ መብታችሁን ተጠቀሙበት ብዬ ልመክራችሁ እወዳለሁ፡፡
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም