ኢትዮጵያ በተፈጥሮ በህብረ ቀለማቸው ብቻ የሰውን ቀልብ የሚገዙ እንደ ኦፓል፣ ሳፋየር፣ ኤምራልድ፣ ኳርትዝ ያሉ ማዕድናት መገኛ ናት። በጌጣጌጥ ኢንዱስትሪው የላቀ ድርሻ እየተወጣ ያለው የከበረ ድንጋይ የጌጣጌጥ ማዕድን ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ነው፤ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ይታወቃል። መንግሥትም ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
የጌጣጌጥ የድንጋይ ማዕድናት ዘርፉ ለአገር ጠቀሜታ እያስገኘ ያለው ማዕድኑን ከመሬት በቁፋሮ ከሚያወጣው አምራች ጀምሮ በገበያው ውስጥ ሂደቱን ጠብቆ ለተጠቃሚው እስኪደርስ ባለው አሠራር ሲሆን፣ የአስተዳደር ሥራውም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያልፋል።
በዚህ ረገድ ኃላፊነት የተሰጠው ማዕድን ሚኒስቴር ዘርፉን ይመራል፣ ቁጥጥርና ክትትልም ያደርጋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡም ከግብይት ጋር በተያያዘ የማሻሻያ ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔውንም በዘርፉ ላይ ለተሰማሩት አካላት ሰኔ ወር 2014ዓ.ም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪ አድርጎላቸው አሳውቋቸዋል። ውሳኔውንም በድረገጹ አስነብቧል።
ሚኒስቴሩ በድረገጹ ባስነበበው መረጃ ላይ እንደተጠቆመው፤ የጌጣጌጥ ማዕድናት የግብይት ሰንሰለትን ለማሳጠርና አገሪቱም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማስቻል ሲባል እስከ አሁን በሥራ ላይ የቆየው በመንግሥት የዋጋና የደረጃ ተመን ማውጣት ሥራ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መስፈርቶች ተነስተው የንግድ ሥርዓቱ በገበያ ብቻ እንዲመራ የሚያደርግ ነው። ውሳኔው ለምን እንደተላለፈ፣ በአዋጅና መመሪያ የተደገፈ እና አሳታፊ ስለመሆኑና ስሌሎች ተጨማሪ ማብራሪያዎች የሚኒስቴሩን ድረ ገጽ ብንመለከትም ማግኘት አልቻልንም።
ውሳኔውን እንዲያውቁት በሚኒስቴሩ ጥሪ ተደርጎላቸው በስፍራው የተገኙትን በግብይቱ የሚሳተፉ አካላትን ወደ ማነጋገር ገባን። የኢትዮ ደላንታ ኦፓልና ሌሎች የከበሩ ማዕናት ላኪ ኩባንያ ባለቤት አቶ ዘውዱ አድጎ አይቼው የጌጣጌጥ ማዕድን በተለይም ኦፓል የተባለውን ግብአት በጥሬውና እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው። ከ2003ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ሥራ ላይ ቆይተዋል። በኤክስፖርቱ ሥራ ላይ የተሰማሩት የተለያዩ ሂደቶችን አልፈው እንደሆነም ይናገራሉ። ሥራውን ወደው እንደሚሠሩትና ጥሩ እንደሆነም የሚናገሩት አቶ ዘውዱ በሥራው ላይ በቆዩባቸው ጊዜያቶች ለእርሳቸው ከባድ የነበሩት ወቅቶች የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት፣ በአገር ውስጥም የተፈጠረው አለመረጋጋትና ወደ ጦርነት የተገባባቸው ሁኔታዎች ናቸው።
ይሠሩበት የነበረው አካባቢ በጦርነት ቀጣና ውስጥ በመሆኑ ጥሬ ማዕድንን እሴት ጨምረው የሚሠሩበት ክፍልና የሚሠሩባቸው ማሽኖች ወድመውባቸዋል። ድርጅታቸው ከደረሰበት ጉዳት ገና በማገገም ላይ እንደሆነና በሂደትም ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴው እንደሚመለስ በተስፋ እየሠሩ መሆኑን ነው የነገሩኝ። እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የድርጅታቸው የገበያ መዳረሻ ሕንድ ናት።
አቶ ዘውዱ ቀደም ሲል በሚኒስቴሩ የማሻሻያ እርምጃዎች ከመወሰዳቸው በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች ይካሄዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። ማሻሻያዎች በመመሪያና ደንብ ይደገፋሉ የሚሉት አቶ ዘውዱ፣ አሁን የተደረገው ማሻሻያ ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፈ ስለመሆኑ መረጃው እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት። ውሳኔውን ግን በሚኒስቴሩ ሰኔ 24 ቀን 2014ዓ.ም ጥሪ ተደርጎላቸው በአካል ተገኝተው ከሚኒስትሩ ሰምተዋል።
መልዕክቱም የደረሳቸው በቃል ነው። በጽሑፍ ወይንም በደብዳቤ የተደገፈ መልዕክት አልደረሳቸውም። በማሻሻያው ከተመለከቱት ውስጥ አንዱ ደረሰኝ ስለአለመጠየቅ የሚገልጸው ነው። ሌላው የማሻሻያ እርምጃ የይለፍ ሰነድ ደብዳቤ መያዝን ያስቀረው ነው። ሦስተኛው የማዕድን ሚኒስቴር ባለሙያዎች (ኤክስፖርተሮች) ልየታ አድርገውበት የዋጋ ውሳኔ የሚሰጡበት አሠራር መቅረቱን የሚገልጸው ነው።
በነባሩ አሠራር ደረሰኝ መጠየቅን አስመልክቶ ስለነበረው ሁኔታ አቶ ዘውዱ እንደገለጹት፤ በዘርፉ በወጪ ንግድ (በኤክስፖርት) የተሰማራን አካል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማዕድኑን ከየት እንደገዛውና የገዛበትን የዋጋ መጠን በደረሰኝ ማስረጃ ይጠይቃል።
አሠራሩ ግብይቱን ሕጋዊ ከማድረግ አኳያ በተለይም ማዕድን ከየት ተገዝቶ ወዴት እንደገባ ሕገወጥነትን ለመከላከል ሕጋዊ ደረሰኝ በመጠየቅ ነበር የሚያረጋግጠው። ይህ በመሆኑም አምራቹ ለገዥው ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለበት። አሁን በተሻሻለው የገበያ ሥርዓት ማዕድኑ ከየት እንደተገዛ፣ በምን ያህል ዋጋ ግብይቱ እንደተፈጸመ መረጃ የያዘ ሕጋዊ ደረሰኝ አያስፈልግም።
ይለፍን በሚመለከተው ማሻሻያ በቀድሞው አሠራር ሕገወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎችን ለመቆጣጠር ሲባል ማዕድኑ ከሚወጣበት ወይንም ከሚመረትበት ዘርፉን ከሚመራው ወረዳ ስለተገዛው የዕቃ ዓይነትና መጠን እንዲሁም ለወረዳው ገቢ ሰብሳቢ መክፈል የሚጠበቅበት ክፍያ መፈጸሙን የሚመለከት በሰነድ ወይንም በደረሰኝ የተደገፈ የይለፍ የሰነድ ማረጋገጫ ወይንም ደብዳቤ መያዝ ይጠበቅ ነበር።
አቶ ዘውዱ የእርሳቸውን ኩባንያ የአሠራር ሂደት ለአብነት ጠቅሰው ሲያብራሩም ኩባንያቸው ኦፓል የተባለውን ማዕድን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ይገልጻሉ። ይህ ማዕድን በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ ውስጥ በስፋት ይገኛል። ሀብቱን ከደላንታ ወረዳ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ ለመጓጓዝ ከወረዳው የተሟላ ሰነድ የያዘ የይለፍ ደብዳቤ መያዝ ይኖርበታል።
የይለፍ ደብዳቤው ለአምስት ቀናት ነው የሚያገለግለው። ከተጠቀሰው ቀን በላይ የሆነ ደብዳቤ ይዞ የተገኘ አዘዋዋሪ ወይንም በዘርፉ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማራ አካል ሕገወጥ ተደርጎ ይወሰዳል። በመሆኑም በተሰጠው የአምስት ቀን ጊዜ ውስጥ ለማዕድን ሚኒስቴር ማሳወቅ ወይንም ማስመዝገብ ይጠበቃል። ጊዜው ላለፈበት ደብዳቤም የወረዳው ጽሕፈትቤት ኃላፊነት እንደማይወስድ የተደነገገ በመሆኑ ኩባንያቸው በዚህ አሠራር ውስጥ ነበር ሲሠራ የቆየው።
አሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባደረገው የማሻሻያ እርምጃ የይለፍ ደብዳቤ አያስፈልግም፤ አዲሱ አሠራር ይህን አስቀርቶታል ሲሉ ይጠቁማሉ።
የአሠራር ሂደቱ ለወጪ ንግድ (ኤክስፖርተሮች) የማያሠራና የማያንቀሳቀስ ስለመሆኑ በዘርፉ ከተሠማሩት ኤክስፖርተሮች በተደጋጋሚ የሚነሳ እንደነበር አስታውሰው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ቅሬታውን መሠረት አድርጎ አሠራሩን ለማስቀረት መወሰኑን በሚኒስትሩ እንደተገለጸ አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ።
በማሻሻያው የቀረው ሦስተኛው የልየታ አሠራርም ቀደም ሲል በነበረው አሠራር ከሙያ አንጻር ተመዝኖ ዋጋ ይተመን የነበረበት ሁኔታ ነው። ኤክስፖርተሩ ያቀረበው የኦፓል ማዕድን ስንት ብር የሚያወጣ ነው በሚለው ቅድመ ሙያ ምዘና መሠረት ነው ኤክስፖርተሩ ለገበያ ያቀርብ የነበረው።
ኤክስፖርተሩ ባቀረበበት ሰዓት ባለሙያዎቹ ተግባራቸውን የሚወጡ ሲሆን፣ አሠራሩም በማዕድን አዋጅና መመሪያ ላይ ተቀምጧል ይላሉ። በመመሪያው መሠረት የጥራት ደረጃ የወጣለት ማዕድን እንደየደረጃው የመሸጫ ደረጃም ይወጣለት ነበር። እሴት የተጨመረበትና ጥሬ ሀብቱም እንዲሁ የደረጃና የዋጋ ተመን ይወጣላቸዋል ነው የሚሉት።
ለአብነትም በተመኑ መሠረት ኦፓል የጥሬ ሀብቱ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ በኪሎ ሁለት መቶ ዶላር ነው። ደረጃው ከፍ ያለ ሲሆን ደግሞ አንድ ሺ አምስት መቶ ዶላርም፣ ሦስትሺ ዶላርም፣ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ እንዲሸጥ ይወሰናል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ እሴት ተጨምሮበት የተዘጋጀ የማዕድን ሀብት ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ደግሞ በኪሎ 10ሺ ዶላር ነው። እንደ ጥራቱ ዋጋው ከፍ ብሎ ይሸጣል። ዝቅተኛ ዋጋ የተሰጠው የኦፓል ማዕድን ሀብት በጣም ደቃቅና ከአስር ሚሊሜትር ዳይሜንሺን በታች ተብለው በወንፊት የተለዩት ናቸው።
ኤክስፖርተሩ በቀደሙት አሠራሮች ውስጥ ሳያልፍ ግብይቱን እንዲያካሂድ ነው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ያሳወቃቸው መሆኑን አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ። ውሳኔው መተማመን ላይ የተመሠረተ ግብይት እንዲካሄድ ያስችል ይሆን? የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ ዘውዱ በዚህ ላይም ‹‹የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዕቅድ ግልጽ ባይሆንልኝም ግብይቱ በመተማመን ይካሄድ ከሚል እሳቤ ከሆነ በአንድ በኩል የማልችለው ኃላፊነት ተሰጥቶኛል›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ሁሉም በመተማመን በኃላፊነት የሚወጣ ነጋዴ ነው ብሎ ማሰቡ የዋህነት ይመስለኛል ሲሉ የሚገልጹት አቶ ዘውዱ፣ ነጋዴው ላይ ሙሉ እምነት መጣል ካስፈለገ እምነቱ እንደ አገር ነው መሆን ያለበት በማለት ይገልጻሉ። በማዕድን ዘርፉ ላይ የተሰማራው ነጋዴ ብቻ ታማኝ ተደርጎ መወሰድ አለበት የሚል እምነት የለኝም ይላሉ።
ዛሬ በአነስተኛ ንግድ ውስጥ የሚገኘው የጀበና ቡና እንኳን ግብይቱ በደረሰኝ እንደሚከናወን የጠቀሱት አቶ ዘውዱ፣ በእምነት መሠራት ያለበትና የሌለበት ነገር ቢኖርም የጌጣጌጥ ማዕድን ግብይቱ ግን ከደረሰኝ ውጪ በሆነ መከናወኑ አገር ይጎዳል የሚል እሳቤ አላቸው።
አቶ ዘውዱ ሌላውን ስጋታቸውንም ይጠቁማሉ። ማዕድኑ ደረጃ ሳይወጣለት ነጋዴው በፈለገው ዋጋ ገበያ ላይ እንዲያውለው መደረጉ በኪሎ 10ሺ ዶላር ይሸጥ የነበረውን አንደኛ ደረጃ ኦፓል ዝቅ ባለ ዋጋ እንደ ተሸጠ አድርጎ ሊያቀርብ የሚችልበትን መንገድ ይከፍታል። ይሄ ደግሞ መስረቅ ለሚፈልግ ነጋዴ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ሲሉ ያብራራሉ።
አገሪቱ እንደ አገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የገቢ ጥቅም ያሳጣል ባይም ናቸው። በትንሹ እንኳን በኪሎ 200 ዶላር ዋጋ ከሚያወጣው ዝቅተኛ የኦፓል ገቢ 30 እና 50 ዶላር ነው የተገኘው ተብሎ ገቢ ሊደረግ ይችላል። ይሄ ለአገር ትልቅ ጉዳት ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ፤ እሴት ያልተጨመረበትን ጥሬ ሀብት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ የዜጎች የሥራ ዕድልንም አብሮ መሸጥ ይሆናል። ጥሬ ዕቃውን የሚገዙት አገራት ለዜጎቻቸው የሥራ ዕድል ስለሚፈጥሩበት ምርጫቸው ጥሬ ዕቃውን መግዛት ነው። በዚህ ላይ አገራቸው ወስደው እሴት ጨምረው ለገበያ ሲያቀርቡ የተሻለ ገቢ ያገኙበታል።
በዚህ ረገድ የሕንድ የጌጣጌጥ ማዕድን ላኪ ኩባንያዎች ከአገራቸው ዶላር እንዳይወጣ የድርድር አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ዶላር ከአገራቸው እንዳይወጣ ገበያውን እነርሱ በሚፈልጉት መልክ ለማድረግ ይጥራሉ።
በኢትዮጵያም በተመሳሳይ እሴት የተጨመረበት ማዕድን ለገበያ ማቅረብ ላይ ትኩረት ቢደረግ በዘርፉ በተለያየ መንገድ መጠቀም ይቻላል። በእርሳቸው እምነት መንግሥት በዘርፉ የሙያ ክህሎት ስልጠና እንዲሰጥ በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር ቢሠራ ከዘርፉ ብዙ መጠቀም ይቻላል። በማዕድን ሥራ የካበተ ልምድ ካላቸው ሕንድ፣ አሜሪካና ከሌሎችም ተሞክሮ በመቀመር ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻልም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ከዚህ በኋላ በጌጣጌጥ ማዕድን ግብይት ላይ ኤክስፖርተሩና ማዕድን ሚኒስቴር የሚኖራቸው ግንኙነት በምን መልኩ ሊሆን ይችላል ስንል ላቀርብኩላቸው ጥያቄም አቶ ዘውዱ ሲመልሱ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የጌጣጌጥ ማዕድን ሚኒስቴሩ አሽጎ ሲሰጣቸው ለገበያ ማቅረብና የሽያጩን ገቢ በብሔራዊ ባንክ በኩል ማቅረብ ነው ብለዋል።
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡኝ አቶ መቆየት ግርማ ናቸው። የድርጅታቸውን ስም በራሳቸው ስም ሰይመው በ2008ዓ.ም የሥራ ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራው የገቡት አቶ መቆየት፣ የከበሩ ማዕድናትን በመቁረጥና በማስዋብ ሥራ ምሩቅና የሙያው ባለቤትም ናቸው። ሳፋየር የተባለውን የከበረ ድንጋይ ማዕድን ጥሬ ሀብቱን ወደ ሲሪላንካና ታይላንድ ይልኩ ነበር። ጥሬ ግብአቱን የሚያገኙት ደግሞ ከትግራይ ክልል ነበር። ክልሉ ላይ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ግብአቱን ከክልሉ ማግኘት ባለመቻላቸው ኦፓል የተባለውን የድንጋይ ማዕድን በማምረትና እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ተሰማርተዋል።
እሳቸው ማሻሻያው ነጋዴውን ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ። አገርን ግን እንደሚጎዳ በመግለጽ የአቶ ዘውዱን ሀሳብ ይጋራሉ። ቀደም ሲል ኤክስፖርተሩ ጥሬ ሀብቱን ከአምራቾች የገዛበት ዋጋ ግምት ውስጥ ሳይገባ ማዕድን ሚኒስቴር በገመተው ዋጋ ነው ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ ይደረግ ነበር። እሴት የተጨመረበትም እንዲሁ በተመሳሳይ ነው የሚከናወነው ሲሉ ያብራራሉ። አሁንም መነሻ ዋጋ ሊቀመጥ ይገባል ባይ ናቸው።
በማሻሻያውና በግብይቱ ላይ የተሰማሩት አካላት ማሻሻያውን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ዙሪያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ምላሽና ማብራሪያ ለማግኘት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ጥሪ ባለመቀበሉ ምክንያት ጥረታችን አልተሳካም።
አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ማሻሻያው የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለትን እንዲያሳጥር ታስቦ የወጣ እንደሆነ ይታሰባል። ነጋዴውንም ይጠቅማል ይላሉ፤ የአገርን ጥቅም ግን አሳልፎ ይሰጣል የሚል ስጋትም አሳድሮባቸዋል።
ማሻሻያው መተማመን ላይ መሠረት ያደረገ ነው የሚል ግምት እንኳን ቢኖር፣ በንግድ ሥራ ውስጥ የተለያየ አሻጥር እየተስተዋለ ባለበት በአሁኑ ወቅት በጌጣጌጥ ማዕድን ግብይት ውስጥም ይህ ችግር አይፈጠርም ተብሎ አይታሰብም። ለጥራት ከመጨነቅ ይልቅ ትኩረቱ በተገኘው ዋጋ ገበያ ላይ በማቅረብ ገቢ ለማግኘት ከሆነ ማሻሻል ውስጥ የተገባው የጥራት እና እሴት ጨምሮ የመሸጥ ጉዳይ ቦታ አይኖራቸውም ተብሎም አይታሰብም። ማሻሻያው ሊፈጥር በሚችለው ክፍተት ለምርቶቹ የወረደ ግምት እንዲሰጥ በር አይከፍትም ተብሎም አይጠበቅም።
አሳሪ አሠራሮችን ቀላል ማድረጉ ትክክል ነው፤ አሠራሮቹ ግን ሌላ ክፍተት የሚያመጡ አለመሆናቸውንና እርምጃውም ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝና ተገቢነት ያለው ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይገባል።
ሚኒስቴሩ የማሻሻያ ውሳኔውን ሲተገብር እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ቢያደርግ መልካም ነው። በማሻሻያው ላይ በቂ ማብራሪያ ቢሰጥም ሌላው ስጋቱን የሚያስቀርበት ሁኔታም ሊኖር ይችላል እንላለን።
የጌጣጌጥ ማዕድናት እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ ሲደረግ ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፤ አገርም ይበልጥ ተጠቃሚ ትሆናለች።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2014