የወይዘሮ መንበረና የመሳለሚያ ሰፈር ትውውቅ ከ1960 ዓ.ም ይጀምራል። የዛኔ የመላው ቤተሰብ መኖሪያ ፒያሳ አሁን የእሳት አደጋ መሥሪያ ቤት ከተገነባበት ስፍራ ነበር። በዘመኑ ቦታው ለልማት በመፈለጉ አባት ቤተሰቡን ይዘው አካባቢውን መልቀቅ ነበረባቸው።
በወቅቱ መኖሪያ ቤቱ የግል ይዞታ በመሆኑ ለተነሺዎች የሚገባቸው ግምት ተከፍሏል። የነመንበረ አባት በወቅቱ በተሰጣቸው ክፍያ የለቀቁትን ቤት አልተኩም። ከመላው ቤተሰብ ጋር የኪራይ ቤት ኑሮን መረጡ ። መኖሪያቸውንም መሳለሚያ አካባቢ አደረጉ ።
አባት በሞት ከተለዩ በኋላም ከዚሁ ቤት የሚያወጣ አጋጣሚ ሳይኖር ሕይወት ለዓመታት እንደነበረው ሆኖ ቀጠለ። በዘመነ ደርግ የቀበሌ ቤቶች ሲወረሱ በባለቤትነት የሚታወቁት ሴት የነመንበረ ጎረቤት ሆነው ኖረዋል።
ቆይቶ ጥቂት ቤቶች ለቀድሞ ባለቤቶች ሲመለሱ ሴትዬዋ አንድ ቤት የመውሰድ ዕድል ተሰጣቸው ። ይሄኔ እሳቸው ካሉበት ይልቅ ምርጫቸው የነመንበረ ቤት ሆነ ። ቤቱ ይኖሩበት ከነበረው ይዞታ በስፋቱ የተሻለ ነበር። ይህ አጋጣሚ እነመንበረ ትልቁን ቤት አስረክበው ከወይዘሮዋ ጠባብ ክፍል እንዲኖሩ አስገደደ።
የዛኔ የነ መንበረ ወላጅ እናት ከሟች ሴት ልጃቸው በአደራ የተቀበሏቸውን ሁለት ሕጻናት እያሳድጉ ነበር። ያለ አባወራ በብቸኝነት ሕይወትን የገፉት ወይዘሮ ጥቂት ቆይቶ ባለፉ ጊዜ ሙሉ ኃላፊነቱ በዛኔዋ ወጣት መንበረ ትከሻ ላይ ወደቀ። በወቅቱ ተማሪ የነበሩት መንበረ የእናታቸውን ድርሻ መቀበል ግዴታቸው ሆነ።
ይህ አጋጣሚ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡና የሙት እህታቸውን ሁለት ሕጻናት በኃላፊነት እንዲንከባከቡ አስገደደ። መንበረ በወቅቱ ከአስር ወደ አስራ አንደኛ ክፍል ያለፉ ቢሆንም ትምህርታቸውን አቋረጡ። ከዛሬ ነገ እቀጥላለሁ በሚል ተስፋም ዓመታትን ዘለቁ። ከጊዜያት በኋላ ከሕጻናቱ አንደኛዋ በድንገት ሞተችባቸው።
መንበረ የመማር ዓላማቸውን ከነአካቴው ትተው አንዱን ሕጻን እንደራሳቸው ልጅ ማሳደጋቸውን ያዙ። ልጁ ከእሳቸው በቀር እናት አባት ይሏቸውን አያውቅም። ነፍስ አውቆ ራሱን እስኪችል አንዳች ፍቅር ሳይጎድለበት፣ከጉያቸው ሳይርቅ አደገ። የእናትና ልጅ ሕይወት በጠባቧ ቤት በመተሳሰብ ዓመታትን ዘለቀ።
መንበረ ‹‹ የእህት ልጅ ባይወልዱትም ልጅ ›› እንዲሉ ሆኖ ከሕጻንነቱ የተቀበሉትን ልጅ እስከ ጉልምስና ዕድሜው አደረሱ። በዚህ መሐል ትዳርና የራስ ሕይወት ለሚሏቸው ጉዳዮች ቦታ አልሰጡም ። ስለእርሱ መኖር ውድ ዋጋን ከፈሉ። ድንጋይ ተሸከሙ፣ ሸማ ፈትለው ፣ ቋጭተው ሸጡ፣ ጉልት ተቀምጠው ነገዱ ። የዛኔው ሕጻን ዛሬ ላይ አርባዎቹን አጋምሷል። አሁንም ከእሳቸው ጉያ አልራቀም። አብሯቸው እየኖረና የአቅሙን እየሠራ፣ ይደጉማቸዋል።
የእህል በረንዳና አካባቢው ዕለታዊና ፈጣን የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ነው ። ከዚሁ ተያይዞም የሀገሪቱ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በዚህ ስፍራ ሲዘዋወር እንደሚውል ይነገርለታል። ከእህል በረንዳው ግዙፍ የንግድ አውታር በስተጀርባ ደግሞ እነ ወይዘሮ መንበረን የመሰሉ ምስኪኖች የጎሰቆለ ሕይወትን ይገፋሉ።
ዕድሜ ጠገብ በሆኑ ጠባብ መኖሪያዎች በርካታ ቤተሰቦችን አቅፈው የሚኖሩ ነፍሶች ዓመታትን ከእጅ ወደአፍ በሚባል ችግር ዘልቀዋል። እነ እመት መንበረም አስቸጋሪውን የኑሮ መንገድ እየተሻገሩ ከዕድሜያቸው ማምሻ ደርሰዋል። አሁን መንበረና አቻ ጎረቤቶቻቸው ዕድሜና ድካም እየተጫናቸው ነው ። ልክ እንደእነሱ ሁሉ ለዓመታት ችግርን ከደስታ የገፉባቸው ጎስቋላ መኖሪያ ቤቶቻቸው በቁማቸው ማዝመም ይዘዋል።
ቤቶቹ ተጠጋግተው እንደመሠራታቸው ገጽታቸው እምብዛም አይለይም ። ካንዱ ቤት የሚሰራ ወጥ ከሌላው ቤት መሽተቱም ብርቅ ሆኖ አያውቅም ። ከዚሁ ብሶ ክረምቱ በገፋ ጊዜ ዶፍ የሚወርድበት ጣራና ግድግዳ በዘመናት ዕድሜ ሆድ ከባሰው ቆይቷል። በነወይዘሮ መንበረ ቤት ደጃፍ አልፎ የሚሄደው የመጸዳጃ ፍሳሽም ለነዋሪው ጤና ማጣት ምክንያት እንደሆነ ነው።
ዛሬ የነመንበረ ቤትና አካባቢው በመልካም ዓይኖች እይታ ተቃኝቷል። ጉስቁልናውንና አስቸጋሪውን የሕይወት እውነታ ያረጋገጠው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከኢ-መደበኛ ነጋዴዎች ጋር ተጣምሮ የአዲስ ምዕራፍ ጉዞውን በስኬት ጀምሯል።
ዛሬ እነዛ ዕድሜ ጠገብና ጎስቋላ፣ የጭቃ ቤቶች ሙሉ አካላቸው በብሎኬት እየተቀየረ ነው። እንዲህ መሆኑ ለነዋሪዎቹ ብሩህ ተስፋን ሰንቋል። በስፍራው በተገኘን ጊዜ በቤቶቹ ግንባታ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ሲተጉ ካገኘናቸው ብርቱዎች መካከል ወጣት መዲና መሐመድን ልናነጋግራት ወደድን። ሀሳባችንን ተቀብላ ልታወጋን ፈቀደች።
መዲና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስድስት ነዋሪ ናት። ዕለቱን በእህል በረንዳ መንደሮች መሐል ያቆማት ግን የበጎ ፈቃድ አገልግሎቷ ነበር። እሷና መሰል ባልንጀሮቿ በኢ.መደበኛ የንግድ እርከን ውስጥ ይገኛሉ።እነሱ መንግሥት በየጊዜው በሚከውነው የአቅመ ደካማ ወገኖች ቤት ጥገና መርሐ ግብር ተጨማሪ እጆች ለመሆን ፈቃደኞች ሆነዋል። በራሳቸው አቅምና ሙሉ ወጪ በሚጠግኗቸው ቤቶች በርካቶች ታሪካቸው ተለውጧል።
መዲና አምናን ጨምሮ በሥራው በተሳተፈችበት አጋጣሚ በርካታ እውነታዎችን አስተውላለች። የአካባቢው ቤቶች ስሪት በአብዛኛው ከመጸዳጃ ፍሳሽ ጋር የተያያዘ ነው። በእነዚህ ቤቶች ዓመታትን በስቃይ የሚገፉ አረጋውያን ይኖራሉ። በተለይ ጧሪና ቀበሪ ለሌላቸው አዛውንቶች ይህ አይነቱ ሕይወት በእጅጉ ፈታኝ የሚባል ነው። መዲና በነዚህ ወገኖች መሐል ተገኝታ የችግራቸውን ቀንበር የማንሳቷ ትርፍ የሕሊና እርካታና ደስታ ሆኗል።
አቶ ዲነጋ ተማምም ልክ እንደነመዲና ሁሉ ከመርካቶ ተነስተው ወደነዚህ ሰፈሮች የመገኘታቸው ሚስጥር የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎታቸው ነው።ነጋዴዎቹ ጉልበት ጊዜና ገንዘባቸውን አዋጥተው በሚሳተፉበት የቤቶች እድሳት የበርካቶችን ዕንባ አብሰው የተሰበሩ ልቦችን ጠግነዋል። እንዲህ በመሆኑም ትርፋቸው ገንዘብ አልሆነም ። የሕሊና ደስታና እርካታ እንጂ።
ወጣት የሱፍ ዑስማን በአካባቢው በሚጠገኑት መኖሪያ ቤቶች የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ነው። የሱፍ በአስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ሕይወት በመጋራቱ በእጅጉ ደስተኛ ሆኗል። እሱ የሚገኝበት የንግድ ስራ ሮጦ የሚያድርበትና የንዋይ ትርፍ የሚገኝበት ነው። በነዚህ መንደሮች ውስጥ ግን ሕይወት ከገንዘብ ትርፍ ባለፈ ትርጉሙን የተለየ ሆኖ አግኝቶታል።
ፈታኙን የኑሮ ገጽታ በወጉ መልክ ለማስያዝ የአንድ ወገን ጥረት ብቻ እንደማይበጅ የተረዳው የሱፍ በነዚህ ወገኖች መሐል ተገኝቶ መፍትሔ መሆኑ ያኮራዋል። እሱም በሥራ ውሎው ከሚጠብቀው ትርፍ በላቀ ለሕሊናው እርካታና ደስታን ሸምቷል።
እነሆ! ዛሬ በጎነት የተዋለላቸው ነፍሶች ውዳሴ፣ሙገሳቸው ከልብ ነው። አዛውንቶች በማምሻ ዕድሜያቸው ምርቃት ይዘዋል። በርካታ እናቶች ለምስጋና ቆመዋል። በጎ አድራጊዎችም መልካሙን ዘር በትነው ፍሬውን በዓይን አይተዋል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም