(የፕሬዚዳንት ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣ ትንሿ ሳምሶናይት፤)
ከዚህ በቀደመው መጣጥፌ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ስለማይለየው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣ ሳምሶናይት “ፉት ቦል” አስነብቤ ነበር ዛሬ ደግሞ ከራሽያው ፕሬዚዳንት ፑቲን አጠገብ ስለማትጠፋው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣ ትንሿ ሳምሶናይት “ቼጌት”አጠናቅሬያለሁ።የራሽያና የዩክሬን ጦርነት ከባተ ዛሬ አምስት ወር ሊሞላው አንድ ቀን ይቀረዋል። ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም አያደርገውም የተባለውን ሁሉ በተቃራኒው ማድረጉን ቀጥሏል። ክሬሚያን አይዝም ተባለ ያዘ። ዶንባስን ላይ ጦርነት አይከፍትም ተባለ ከፈተ። ካላበደ ዩክሬንን አይወርም ተባለ ወረረ። ግን አላበደም።
ወደ አውሮፓ የሚልከውን ጋዝና ነዳጅ አያቋርጥም ተባለ የፖላንድንና የቡልጋሪያን በማቋረጥ ጀመረ ፤ የጀርመንን ሰለሰ። የውጭ ምንዛሪ አቅሙን ለማዳከም አውሮፓና አሜሪካ በማዕቀብ መዓት ሲያጣድፉት ያልተጠበቀ የአጸፋ ምላሽ ይዞ በመምጣት አሜሪካንና አውሮፓን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ጉድ አደረገ። ለራሽያ ጠላቶች ከዚህ በኋላ ነዳጅና ጋዝ በሀገሬ ገንዘብ ሩብል ካልሆነ በዶላርም ፣ በዩሮም ፣ በፓውንድም አልሸጥም አለ። ወዲያው የመግዛት አቅሙ እየተዳከመ የነበረው ሩብል ማንሰራራት ጀመረ። ዶላር በታሪኩ እንዲህ ተደፍሮ አያውቅም። ዶላርን የሚገዳደር አማራጭ ዓለማቀፍ የውጭ ምንዛሪ ለመፍጠር ውስጥ ውስጡን እየሠሩ ላሉት ለእነ ቻይና የልብ ልብ እንዲሰማቸው አደረገ። ለዩሮ ከዶላር አንጻር መዳከምና እኩል መሆን አንዱ መግፍኤም እሱ ነው። አሁንም የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ቁልፉን እንደማይጫነው እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ኔቶ የጠብጫሪነትና የወረራ ድቤውን እየደለቀ ነው በሚል የኒውክሌር ጦሩ በልዩ ሁኔታ በተጠንቀቅ እንዲቆም አዟል። ሰሞኑን ደግሞ ራሽያ ልዩ ዘመቻዋን አጠናክራ መቀጠሏን አስታውቆ እግረ መንገዱን ለኔቶ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል። “በዚህ ጦርነት በቀጥታ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክር ካለ በታሪኩ አይቶትና ሰምቶት የማያውቅ ቅጣት ይጠብቀዋል። ይሄን ለማድረግ ራሽያ መሣሪያውም ዝግጁነቱም አላት፤”ሲል አስጠነቅቋል። የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ዲሚትሪ ሙራቶቭ ይሄን የፕሬዚዳንት ፑቲን ማስጠንቀቂያ ፤ ያለምንም ማቅማማት የኒውክሌር ጦርነት እጠቀማለሁ ማለቱ ነው ሲል ተርጉሞታል።
ሚዛናዊነትን ፣ ገለልተኛነትንና ተጨባጭነትን እርም ያለው የምዕራባውያን ሚዲያ ለዩክሬን በግልጽ ውግንናውን ከማሳየት አልፎ የሰብዓዊ እርዳታ አሰባሳቢም ሆኗል። የቢቢሲው ስቲቭ ሮዘንበርግ ከፍ ብሎ የተሰማውን የፕሬዚዳንት ፑቲን ማስጠንቀቂያ ፤ “ፑቲን እንደ ራሽያ ሳይሆን እንደ ዓለም መሪ ነው እያደረገው ያለ፤”በማለት ተሳልቋል። የቢቢሲው ጋዜጠኛ በፑቲን መግለጫ ላይ ልግጫውን ቀጥሏል። “የሚሸጠውን መኪና ቁልፍ ቀለበት በጣቱ እያሽከረከረ እንደሚያስጎበኝ ዲታ የመኪና ሻጭ ፤ ፑቲንም መግለጫውን ሲሰጥ በምናቡ የኒውክሌር ቁልፉን እየነካካ የሚሰጥ ይመስላል።”ሲል ያሽሟጥጣል።
የቢቢሲው ስቲቭ መልሶ ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቁልፉን መጫኑ አይቀርም ለሚል መከራከሪያው በማሳመኛነት ያግዘኛል ያለውን መረጃ ወደ ኋላ ተመልሶ ያወሳል። ፑቲን በአንድ ቃለ መጠይቅ ፤ “ለራሽያ ያልሆነች ፕላኔት ለምን እንድትኖር እንጨነቅ እንጠበባለን!?” ብሏል ይለናል። መቼ ይሄ ብቻ በ2018 ዓም በተሰናዳ አንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ፑቲን ፤”ራሽያን ደፍሮ የሚያጠቃ ካለ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ሕጋዊ መብት አለን። ምላሹ ለመላው ሰብዓዊ ፍጡርና ለዓለም ዕልቂት ነው የሚሆነው። እኔ የራሽያ ዜጋና ርዕሰ ብሔር ነኝ። ለራሽያ ቦታ ስለሌላት ዓለም ለምን እጨነቃለሁ፤ “ብሏል። (በነገራችን ላይ የዘመን አቆጣጠሮቹ እንደ ጎርጎሮሳውያን ናቸው፤”)
አሜሪካና አውሮፓ እንዲሁም የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ)በሌላ በኩል ለዩክሬን የሚያጎርፈው ዘመናዊ የጦር መሳሪያና የወታደራዊ መረጃ ድጋፍ የጦርነቱን የመጨረሻ ውጤት ባይቀይረውም ማወሳሰቡ አይቀርም። አሜሪካ እስከዛሬ ካደረገችው የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ 33 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች ነው። ሰሞኑን እንኳ ኤሮቫይሮንመንት የተባለ ኩባንያ እጅግ ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮንና ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለዩክሬን ጦር ረድቷል።
ወዲህ የኔቶ አባል ሀገራትና ሌሎች በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ራሽያ ላይ የኢኮኖሚና የፋይናንስ የማዕቀብ ናዳ መልቀቃቸውን በጀ ብለው ተያይዘውታል። የተመኙትን ያህል ባይሳካላቸውም ኢኮኖሚዋን ሽብ ለማድረግ ያልወጡት አቀበት ፣ ያልወረዱት ቁልቁለት የለም። ለዚህ ነው መቀመጫውን ሞስኮ ያደረገ የመከላከያ ተንታኝ ፓቬል ፌልገንሀውር ፤ “ምዕራባውያን በራሽያ ማዕከላዊ ባንክና በፋይናንስ ሥርዓቷ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲንን አማራጭ ስላሳጣው መጀመሪያ ወደ አውሮፓ የሚላከውን የጋዝና የነዳጅ መስመር አንድ በአንድ ያቋርጣል። ይህ የማያንበረክካቸው ከሆነ በመጨረሻም በእንግሊዝና በዴንማርክ መሐል ወደ ሚገኘው ሰሜን ባህር የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ሊተኩስ ይችላል ፤”ይለናል።
በማከልም የሰይጣን ጆሮ አይስማውና ፕሬዚዳንት ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቁልፉን ለመጫን ከወሰነ ማንም አያስቆመውም። የራሽያ ልሒቃን ከጎኑ ናቸው ይለናል ዲሚትሪ ታዲያ እሱ ፈጣሪ ይሁነን እንጂ ማን ሊያስቆመው ይችላል። ዲሚትሪ ለዚህ ነው አጣብቂኝ ላይ ነን የሚለው።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዚያ ሰሞን፤” የማይታሰብ የነበረው የኒውክሌር ጦርነት ዛሬ ደጃችን ላይ ቆሞ እያንኳኳ ነው።”ማለታቸው አይዘነጋም። የራሽያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የዕዝ ጠገግን አስመልክቶ በ2020 ዓም በተዘጋጀ አንድ ሰነድ ፤”የኒውክሌር የጦር መሣሪያን ቁልፍ የመጫን ኃላፊነትን ለራሽያ ፕሬዚዳንት ይሰጣል። በማንኛውም ሰዓት ፤ በየትኛውም ቦታ ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጎን የማትለይ አነስ ያለች “ቼጌት” የተሰኘች ሳምሶናይት አለች።
የ1993 ዓም የራሽያ ሕገ መንግሥት ፕሬዚዳንቱ የጦሩ ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደሆነ ይደነግግና ይህን ኃላፊነቱን በሆነ ምክንያት መወጣት ባይችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክቶት ይሠራል በማለት ይደነግጋል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ”ቼጌት”ን አይዝም። በ1996 ዓም ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን ለልብ ቀዶ ጥገና ሆስፒታል ሲገባ እሱን ተክቶ የተሰየመው የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ትንሿ ሳምሶናይት አብራ ትሰጠው አትሰጠው መረጃ የለም።
ይቺ ሳምሶናዊት የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ቁልፉን የያዘች ሳትሆን ፤ የኒውክሌር ጦር እንዲተኮስ የሚያዝዘው የፕሬዚዳንቱ ጥብቅና ሚስጥራዊ መልዕክት ለወታደራዊ ጠቅላይ ማዘዣው የሚተላለፍባት የሞት መልዕክተኛ ናት። የራሽያ ጦር ጠቅላይ ማዘዣ ከፕሬዚዳንት ፑቲን “ተኩስ!”የሚለው ወታደራዊ ትዕዛዝ በ”ቼጌት”እንደ ደረሰው ፤ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለሚተኩሰው ምድብተኛ ሚስጥራዊ መግባቢያ(ኮድ) የሚያስተላልፍበት ሁለት መንገድ አለው።
የመጀመሪያው የኒውክሌር ጦር መሣሪያው በተጠመደበት ምድብ ለሚገኘው አዛዥ “ተኩስ!” የሚለውን ትዕዛዝ አረጋግጦ የሚያስፈጽምበት ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ይህ መገናኛ መስመር ድንገት ባይሠራ በመጠባበቂያነት የሚያገለግለውና “ፕሬሚትር” በመባል የሚታወቀው ነው። የራሽያ ጦር ጠቅላይ ማዘዣ ይሄን የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ በማዕከል ሆኖ ማስተኮስ ይችላል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ላይ የራሽያ የመከላከያ ኃይላት የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ጨምሮ በተጠንቀቅ እንዲቆም ባዘዘው መሠረት የስትራቴጂካዊ ሚሳየል ኃይሉ ማለትም የሰሜናዊ ፣ የፓሲፊክ የጦር መርከቦችና የረጅም ርቀት የአየር መቃወሚያ ሚሳየሎች በተጨማሪ ወታደራዊ ኃይል ተጠናክረው ዝግጁ መሆናቸውን የራሽያ መከላከያ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። ራሽያ ወደ 6000 የሚጠጉ ኒውክሌር የታጠቁ የጦር መሣሪያዎች ሲኖራት ፤ ከእነዚህ ወደ 1600 የሚጠጉት ለመወንጨፍ ዝግጁ ሆነው እንደሚገኙ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ገልጸዋል። ሚሳየሎቹ ከባህር ሰርጓጅ መርከብ ፣ ከምድርና ከተዋጊ አውሮፕላን የሚተኮሱ ናቸው።
“ሳርማት” የተባለውና ለዓመታት በሚስጥር ተይዞ ሲገነባ የነበረው አህጉር አቋራጭ ሚሳየል ተጠናቆ የተሳካ ሙከራ የተደረገ ሲሆን በስፋት የማምረት ሥራው መጀመሩንና በቅርብ ለውጊያ ዝግጁ እንደሚሆን ታስ የተሰኘው የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ወታደራዊ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል። በ2020 ዓም ይፋ የሆነ አንድ ሰነድ ራሽያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያን መቼና ለምን እንደምትጠቀም በዝርዝር ይደነግጋል። የመጀመሪያው በራሽያ ላይ በኒውክሌር ጦር መሣሪያ ወይም በጅምላ ጨራሽ የታገዘ ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ አጸፋዊ ምላሽ ትሰጣለች።
በራሽያ ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የሚጠቁም ተጨባጭ መረጃዎች ሲገኙ ቀድማ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን ትጠቀማለች ሲል ሁለተኛ አንቀጽ ይደነግጋል። ሦስተኛው አንቀጽ በራሽያ ወሳኝ የሲቪል ወይም ወታደራዊ ተቋም ላይ ጥቃት በመፈጸም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን እንዳትጠቀም የሚያደርግ ጥቃት የተፈጸመ ከሆነ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን ለመጠቀም ትገደዳለች ሲል ያትታል። አራተኛውና የመጨረሻ አንቀጽ ደግሞ በራሽያ ሕልውና ላይ አደጋ የተደቀነ እንደሆነ ራሽያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን መጠቀም ትችላለች ሲል በግልጽ ይደነግጋል።
ለዚህ ይመስላል የታዋቂው የ”ፎሪን አፊርስ”መጽሔት ጸሐፊዎች ኤማ አሽፎርድና ጆሹዋ ሽፍሪንሰን በዚያ ሰሞን ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ ፤ ራሽያ የአሜሪካንና የምዕራባውያንን ጫና መቋቋም ሲሳናት ተስፋ በመቁረጥ የኔቶ አባል በሆነ አንድ ሀገር ላይ እንኳ የሳይበር ጥቃት ብትፈጽም ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊገባ ይችላል የሚለው። የኔቶ አባል ሀገራትና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ፣ ጃፓን ፣ ደቡብ ኮሪያ ፣ ካናዳ ፣ አውስትራሊያና ሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማት በመናበብና በመቀናጀት እየጣሉት ያለው የማዕቀብ መዓት የራሽያ እስትንፋስ የሆነውን የኢነርጂና የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ግንባታን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያስተጓጉል ስለሆነ ራሽያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን ለመጠቀም በቂ ምክንያት ሊሆናት ይችላል።
ኔቶ ወደ ምስራቅ አውሮፓ የሚያደርገው መስፋፋት በራሽያ ሕልውና ላይ አደጋ ይደቅናል በሚል ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት እንደገባች ሁሉ ከኔቶ ጋር በቀጥታ የኒውክሌር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ይህ አንቀጽ ይፈቅዳል ማለት ነው። እንዲሁም ለዩክሬን እየጎረፈ ያለው የከባድ መሣሪያ እርዳታ በራሽያ ቀጣይ ሕልውና ላይ አደጋ የሚደቅን ነውና ሕልውናዋን ለማስከበር ስትል ተገዳ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን ልትጠቀም ትችላለች።
የኒውክሌር ነገር ከተወሳ አይቀር ዓለማቀፍ ሽፉኑን እንመልከት። ቻይና ፣ ሰሜን ኮሪያ ፣ ፈረንሳይ ፣ ሕንድ ፣ እስራኤል ፣ ፓኪስታን ፣ ራሽያ ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና አሜሪካ በአጠቃላይ 13,080 የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ታጥቀዋል ቢባልም ፤ 90 በመቶው ማለትም 11,000 የአሜሪካና የራሽያ ነው። ይፋ ያልሆኑ መረጃዎች ግን በዓለማችን የሚገኘውን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ብዛትን እስከ 20,000 ያደርሱታል።
የሁሉም ኔቶ አባል ሀገራት እያሳዩት ያለው ኅብረት አስገራሚ ቢሆንም ዩክሬንን በጦር መሣሪያ መርዳትና ማስታጠቅ ላይ አጠንክረው እየወተወቱ ያሉት ግን የራሽያ ጎረቤቶች እነ ፖላንድ ፣ እስቶኒያ ፣ ላቲቪያና ሊቶኒያ መሆናቸው ለራሽያ ብቀላ ካጋለጣቸው ፤ የኔቶ አባል ሀገር ስለሆኑ ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊወስዳቸው ይችለል። ባለፈው መጣጥፍ ለመግለጽ እንደሞከርሁት ራሽያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረችና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግሥት በኃይል ከለወጠች ጦርነቱ ጎረቤት ሀገራትን መሠረት ወዳደረገ የሽምቅ ውጊያ ስለሚቀየር ፤ በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ የዩክሬን የአማጽያኑን ማሰልጠኛና ወታደራዊ ካምፓችን ካጠቃች ኔቶን ጎትቶ ወደ ጦርነቱ ያስገባዋል።
የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት
/ኔቶ/ የተመሠረተበት መርሕ የማዕዘን ድንጋይ በአንቀጽ 5 ላይ የተደነገገው ከአባል ሀገራቱ አንዱ ቢጠቃ በጋራ መከላከል/collective defence/የሚለው ነው። የኅብረቱ አባል የሆኑ 30 ሀገራት እንደተጠቁ ስለሚቆጠር በአንድነት የመሰለፍ ግዴታ አለባቸው። ለዚህ ነው ራሽያም ሆነች አሜሪካ አንዳች ነገር ቢከሰት የኒውክሌር ጦር መሣሪያቸውን ለመጠቀም በጥፍራቸው ቆመው የሚጠባበቁት። ከየብስ የሚተኮሰው የአሜሪካ የኒውክሌር ሚሳየል በአራት ደቂቃ ውስጥ ለመተኮስ ዝግጁ ነው። ይሁንና ኔቶ ወደ ምስራቅ አውሮፓ ሲስፋፋ ሲስፋፋ ዛሬ ሞልዶቫ ፣ ዩክሬንና ጆርጂያ ላይ እንዲደርስ በማድረግ አሜሪካ የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተች መሆኑ ባይካድም በዚህ መዘዝ ግን የኒውክሌር ጦርነት እንዲቀሰቀስ አትፈልግም።
ለዚህ ይመስላል ማንኛውንም የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን ሙከራ ላልተወሰነ ጊዜ ያራዘመችው። በነገራችን ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦርነት ላይ የዋለው በ2ኛው የዓለም ጦርነት ሲሆን ፤ እሱም አሜሪካ ስትሆን ጃፓንን ለማጥቃት ተጠቅማበታለች። በዚህም 2ኛውን የዓለም ጦርነት መቋጨት ቢቻልም ወደ 226000 የሚጠጉ ባብዛኛው ሰላማዊ ሰዎችን በመፍጀት ዛሬ ድረስ ጠባሳው ሳይሽር አለ። አንድ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የማጥፋት አቅም ሲኖረው በአካባቢና ሕይወት ባላቸው ሌሎች ፍጥረታት ላይ ዘላቂ ጠንቅ የማምጣት ጉልበት አለው። ለዚህ ነው ዓለም ስጋት ላይ የወደቀው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com