ኢትዮጵያውያን አገር ወዳድ መሆናችንን ከሚያመላክቱ ማረጋገጫዎች መካከል ጠላት ኢትዮጵያን ለማጥቃት ሲነሳ አገር ለማስከበር ቀፎ እንደተነካ ንብ ግር ብሎ ስለ አገራቸው መትመማቸው አንደኛው ነው። ሌላኛው ደግሞ ለአገር ሲሉ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ በውድድር አሸናፊ ሆኖ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ማድረግ ነው። ይህም እ.አ.አ በ1952 ዓ.ም በሮም አደባባይ በነ አበበ ቢቂላ ተጀምሮ፤ በእነኃይሌ ገ/ስላሴ፣ በእነደራርቱ ቱሉ፣ በእነቀነኒሳ በቀለ እና በሌሎችም ቀጥሎ ዛሬ ላይ በተረኛው ትውልድ እንደ ቀጠለ ነው።
ሰሞኑን በአሜሪካ በሚካሄደው 18ኛው የአለም አትሌቲክስ ውድድር የውድድሩ ተሳታፊ ቡድን ተቀናጅቶና ተናቦ በመንቀሳቀስ ከፍ ያሉ ድሎችን እያስመዘገበ ነው። የአገሪቱ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ፣ መላውን አለም እያስደመመ ይገኛል። በዚህም ኢትዮጵያውያን በመላ ደማቸው ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከስረኛው የልባቸው ክፍል ያለውን አገር ወዳድነታቸው ዛሬም እየገለጡ ነው።
ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ በሚቻልባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግሬ፣ አፋር፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ ብቻ የትኛውም ብሔርም ሆነ ጎሳ ተወላጅ ስለአገሩ ስለኢትዮጵያ ይታገላል። ድል ሲያገኝ እንዳሰበው አገሩን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እና ማስጠራት ሲችል ሰሞኑን እንዳየነው ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠ እንባውን ያፈሳል። ታዲያ የሚያነባው ድል ያገኘው ሰው ብቻ አይደለም። በድሉ የሚደሰተው እና ስሜቱን እንባውን በማፍሰስ የሚገልፀው መላው ሕዝብ ነው።
‹‹ በ18ኛው የአለም አትሌቲክስ ውድድር በሴቶች 10 ሺ ሜትር ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች ›› ሲባል ልቡ ጮቤ የረገጠው ብዙ ነው። የወንዶች ማራቶን የፍጻሜ ውድድር ታምራት ቶላ የዓለም ሻምፒዮና ከማሸነፉ በላይ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ ሲገለፅ አንዳንዶች ደስታቸውን በማጨብጨብ እና በመሳቅ በመፈንደቅ ብቻ ሳይሆን ስለድሉ የተሰማቸውን ስሜት እንባቸውን እያፈሰሱ ደስታቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጎይተቶም ገብረሥላሴ የሴቶች ማራቶን 1ኛ በመውጣት ለሀገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቷ ሲሰማ ደግሞ ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆኗል። የባለወርቆቹ ብቻ ሳይሆን በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር ፍጻሜ ጉዳፍ ጸጋይ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ማምጣቷ፤ አትሌት ሞስነት ገረመው፤ ለሜቻ ግርማም— ሜዳሊያዎችን ማግኘታቸው በሁሉም ውስጥ የተለየ የደስታን ስሜት ፈጥሯል። በዚህም በ18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከተሳታፊዎቹ 192 አገራት መካከል በአራት ቀን ቆይታ ከአሜሪካን ቀጥላ የ2ኛ ደረጃን መያዝ ችላለች።
እዚህ ላይ አሸናፊው ማን ነው? ከተባለ መልሱ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ናቸው። እነዚህ ዜጎች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ስሟን ከፍ ማድረጋቸው የሰላም እና ደህንነት ስጋት ወጥሮት ያስጨነቀውን ሕዝብ ትልቅ የደስታ ስሜት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ችለዋል። ምስጋና ለእነርሱ እና በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ስሟ እንዲገኝ ላደረጉ በሙሉ ይሁንና፤ በዚህ ድል በመከራ ውስጥ ድል እንደሚገኝ ለመላው አለም እያረጋገጥን ነው።
የተለያዩ የኢትዮጵያ የቅርብም ሆነ የሩቅ ጠላቶች አንዳንድ ምዕራባውያንን ጨምሮ አስበውበት ላዘጋጁት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ፤ እንደዚህ አንድ የሚያደርጉን የደስታ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ፤ አጋጣሚውን በተገቢው መልኩ እውቅና መስጠት ይገባል።
እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ያሸነፈው ወይም ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ነች። እንደዚህ በመሰሉ አጋጣሚዎች ብሄራዊ አንድነትን አንድነትን ማጠንከር የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት ከተቻለ የድሉ ትርጉሙ አድማሱ እየሰፋ መሄዱ የማይቀር ነው። በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እንዲኖር መስራት ከተቻለ ሌሎችም ተጨማሪ ትልልቅ ድሎች መመዝገባቸው ያስችላል።
ከትንሿ የሰፈር አስተሳሰብ ወጥቶ ከልብ ስለአገር ብቻ ማሰብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሁሉም ከተረባረበ፤ ከተባበረ እና አንተ ትብስ ከተባባለ ኢትዮጵያን መውደድን በቃል ሳይሆን በተግባር መፈፀም ከተለመደ፤ በእውነትም ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ብዙ አስርት ዓመታትን እንዳንፈጅ ሊያግዘን ይችላል።
ኢትዮጵያን ታላቅ ሃያል አገር ለማድረግ ያሉባትን ብዙ ችግሮች ማራገፍ ያስፈልጋል። ለዚህ በትልቁ ስለኢትዮጵያ ማሰብን ይጠይቃል። ስለኢትዮጵያ የሚያስቡ ያሰቡትንም ተግባር ላይ የሚያውሉ ያስፈልጉናል። ይህንን ታላቃነት በትንሹም ቢሆን ያየነው በአሸናፊዎቹ ብቻ ሳይሆን አሸናፊዎቹን በብሔርም ሆነ በሌላ መስፈርት ሳይሆን በብቃት ላይ ብቻ ተመስርተው ሁሉንም እኩል አይተው እንዲወዳደሩ የሠሩ እና ያመቻቹ በሙሉ የኢትዮጵያን ስም ያገነኑ አመራሮችን ነው።
ይህ ሲባል ድሉ ከወቅቱ ጋር በትክክል መመዘን ከቻልን እንዲህ በብሔረሰቦች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር እና አንዳንዴም ቅራኔው አድጎ እየተጋጋለ ወደ እርስ በእርስ እልቂት እንዲያመራ እየሞከሩ ላሉ የውጭ ጠላቶችም ሆነ ተደልለው ኢትዮጵያን እያመሱ ላሉ ሽፍቶች ቅስም ሰባሪ ነው። ታዲያ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያቀዱ አካላትን የሚያሸማቅቅ እና የአንድነት ስሜትን ለመፍጠር የሚያስችል ዕድገትን የሚያመጣ ሥራን መሥራት እጅግ አስደሳች ነው።
ብሔረሰቦችን እየጠቀሱ አንዱን ለይቶ በማጥላላት፣ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ በመቀስቀስ በማጣላት፣ አንዱን ለይቶ የታሪክ ጨቋኝ በማድረግ ሌላውን ደግሞ ለይቶ የጊዜው ጨቋኝ ለማስመሰል የሚሠራው ተንኮል ፍሬ አፍርቶ ኢትዮጵያ ከዛሬ ነገ ፈረሰች ብለው ጓጉተው ለሚጠብቁ የኢትዮጵያ ጠላቶች ይሔ ድል ባቀጣጠሉት እሳት ላይ ውሃ እንደመከለስ ነው። ይህን ላደረጉ ደግሞ በእርግጥም ትልቅ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።
አንዱ የበታችነት ሲሰማው ሌላው የበላይነት እየተሰማው ቆይቶ ዘላቂ ግጭት ቂምና በቀል ስር እንዲሰድ ሲደክሙ የነበሩትን በሙሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ መላው የኢትዮጵያን ጠላቶች የሚያስደነግጥ ብሔረሰቦች ተብለው የተለያዩ እንደሆኑ እንዲሰማቸው የተሸረበው ሴራ እንዲከሽፍ ከመስራት በላይ አገር ወዳድነት የለም። ይህ ውጤት ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ያላቸውን ሃይሎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ምን ያህል ተስፋ ያላት አገር መሆኗንም የሚያሳይ ነው።
በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ከልብ በቃል ሳይሆን በተግባር ተባብረን ከሠራን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ውድድር ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ሆነ በታላቅ አገርነት ሃያል ሆና በዓለም ተገቢውን ስፍራ የምታገኝበት፤ የጥቁሮች የነፃነት አርማ መሆን ብቻ ሳይሆን በአለም ተገቢውን ስፍራ አግኝታ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጥምክህት የምንሆንበት ጊዜው እሩቅ አይሆንም።
የኢትዮጵያ ሃያልነት በተንኮል አገሮችን በተዘዋዋሪም ሆነ በግልፅ በመበደል ወይም የሰው ልጆችን በማጥፋት ሳይሆን ከአገራት ጋር በፍቅር፣ በሰላም እና በመግባባት አብሮ በመሥራት፤ ለዜጎችም እኩልነትን በማስፈን ይሆናል። ኢትዮጵያ ስታድግ አፍሪካም እንደሌሎቹ አውሮፓውያን ማደግ የምንችል መሆናችንን ጥቁሮች ከነጮች እኩል የትም መድረስ እንደሚችሉ ማሳያ እንሆናለን።
በአጉል ከዓለም ተሞክሮ ባፈነገጠ መልኩ አስተሳሰብ ላይ ሳይሆን ብሔር ላይ የተወሸቀ የፖለቲካ ሴራ ውስጥ በመወተፍ አንድ ከሚያደርገን ጉዳይ ይልቅ በሚያለያየን ጉዳይ ላይ በማተኮር በነጋ በጠባ ቁጥር ስለልዩነት ከሰበክን ለኢትዮጵያ ጠላት መሳሪያ ከሆንን አውራው እንደተያዘ የንብ መንጋ እንበተናለን።
ስለዚህ ከልዩነት ይልቅ ስለአንድነት እና አንድ ስለሚያደርጉን ጉዳዮች በመስራት ችግራችንን መፍታት እና ኢትዮጵያን ታላቅ እና ሃያል የማድረግ ዕቅዳችን እንዲሳካ እንደአትሌቶቹ የአገር ፍቅራችንን ከአፍ ባለፈ በተግባር ሠርተን ማሳየት ይኖርብናል። ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም