በዛሬው የ‹‹ተጠየቅ›› አምዳችን በአማራ ክልል ሕግ ለማስከበር የተሠራውን ሥራ፤ ስለ ክልሉ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም አሁናዊ ሁኔታ በተጨማሪ ያሉ ቀጣይ ስጋቶችንና አማራጮች ፤ በተጨማሪም አማራ ክልል ከአጎራባች ክልሎችና ከፌደራል መንግሥት ጋር በጥምረት እየተገበሩት የሚገኘውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን አንስተን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሆኑት አቶ እንግዳው ጠገናው ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ እንደሚከተለው ለንባብ አብቅተነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ እንግዳው፡- በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል አንፃራዊ ሰላም አለ ብሎ መውሰድ ይቻላል ። ጠላት ካሰበው ፍላጎትና ዓላማ አንፃር በሕግ ማስከበር ሥራ ትልቅ ኪሣራ ደርሶበታል ። ኪሳራውም የውስጥና የውጭ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ የአማራ ክልልን ሕዝብና አመራር ለዳግም መከራ፣ ስቃይና ስደት ለመዳረግ ውስጥ ለውስጥ ከኢ-መደበኛ ኃይሎች፣ ከቅማንት ጽንፈኛ ኃይሎች፣ ከጉሙዝ አማፅያን እና ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በተቀናጀ መንገድ ውጭ ካሉ ጠላቶቻችን ጋር ተሳስረው የክልሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ኋላ ለመመለስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር ። ስለዚህ የሕዝባችን እና የክልሉ መንግሥት በተለይም ሕዝባችን ሕግ ይከበርልን ጥያቄ በሰፊው አንስተዋል ።
በጦርነቱ ማግስት በጦርነት የተሳተፈውም ያልተሳተፈውም በተቀላቀለ መንገድ ዘምቻለሁ በሚል እራሱን እንደጀብደኛ በመቁጠር በአመራሩ እና በሕዝባችን ላይ ብዙ ሕገ-ወጥ ድርጊት ለመፈፀም ጥረት አድርጓል ። ስለዚህ ይህንን ለመመከት ከሕዝባችን ጋር ባደረግነው ውይይት የመንግሥት አንዱና ዋነኛ ማሳያው ሕግ ማስከበር በመሆኑ ከሕዝብ ጋር በተግባባንበት መንገድ ሕግ የማስከበር ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች ተሠርተው በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ። የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰዋል ። የሕዝቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ከዚህ በፊት ከነበሩበት የፀጥታ ስጋት ወጥቶ ወደ የተረጋጋ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለመግባት ጥረት ተደርጓል ።
የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ለማከናወን በሚደረገው ጥረት ሕገ ወጥ ኃይሉ የመንግሥትን ሚና በመቀማት ባለሃብቶችን የሚያስፈራራበት፤ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲቆሙ መኪና የሚያስቆምበት፣ ኬላ አስቀምጦ ግብር የሚያስከፍልበት ሁኔታዎች ነበሩ። እነዚህን ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ማስቆም ተችሏል ። ሕገ ወጦችን ለመቆጣጠርና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን አስችሏል ። ይህ አንዱ ትልቅ ስኬት ነው ። ስለዚህ ሕዝብና መንግሥትን ያገናኘ ትልቅ የሰላም ድልድይ ለመገንባት ጥረት ተደርጓል ማለት ነው ።
ጠላት ከድንበር ላይ ሆኜ ከምዋጋ ውስጥ ሆኜ ማፍረስ እችላለሁ የሚለው ሃሳቡ ከሽፏል ። ከዚህ አኳያ የሕግ ማስከበር ዘመቻው እጅግ ስኬታማ ነበር ማለት እንችላለን ። በዚህም አልሳካ ሲለው ደግሞ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ተደራጅቶ እና ተሳስሮ በወለጋ የተፈፀመውን የዜጎች ጭፍጨፋ መሠረት አድርጎ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል ዜጎችን እርስ በእርስ ለማጋጨትና ግንኙነትን ለማላላት እንዲሁም ሀገር ለማፍረስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ባደረገበት ልክ፤ ዜጎች ተገደሉ ተብሎ መጮህ ነበር ። ይህን ሲያደርግ የነበረው እራሱ ጠላት ነው ። ይህም ‹‹ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል›› የሚሉት ቢጤ ነው ።
ጭፍጨፋው የአማራንም ሆነ የኦሮሞ ሕዝብን በአጠቃላይ የሰው ልጅ የሆነውን ሁሉ ያሳዘነ ነው ። ነገር ግን ይህ ታስቦበት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ። ይህንን ሁላችንም እናውቃለን ። ነገር ግን ግድያው እናወግዛለን በሚል በዩኒቨርሲቲዎች፣ በመንግሥት ተቋማትና በኅብረተሰቡ ከፍተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር ። በሰላማዊ መንገድ ወጥቶ የተፈፀመውን ድርጊት ማውገዝ ትክክል ነው። ይህ አንዱ ሰብዓዊ መብት ማሳያ ነው ። ዜጎች ባልመሰላቸውና ቅር በተሰኙባቸው ጉዳዮች ላይ ቅሬታ ማሰማታቸው ችግር የለውም ። ነገር ግን ውስጡ የተቀመመው ቅመም ሕገ-ወጥ የሆነው ሰልፍ በሚካሄድበት ጊዜ የሽብር ጥቃቶችን ለመፈፀም፣ መንግሥትን ለመገልበጥም ጭምር ‹‹ሞብላይዝድ›› የተደረገ ነው ። ስለዚህ ይህ አንዱ ትልቅ ችግር እንደሆነ ተገምግሞ በሰላማዊ መንገድ ወጥተን ከምናሰማው ድምፅ በላይ ሌሎች ሊፈጽሙት የተዘጋጁት ችግር በሚዛን ደረጃ ሲታይ ሰልፉ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ መውሰድ ይቻላል ።
ዜጎችን ሰልፍ መከልከል ሊያሳድረው የሚችለው ተፅዕኖ፤ ውስጥ ላይ ያደራጇቸውና የላኳቸው ኃይሎች እንቅስቃሴ ጭራሽ ሰላማዊ ሰልፍን ሳይሆን ሕዝብ ከሕዝብ እንዲጫረስ ለማነሳሳት የታሰበበት ነበር ። በመሆኑም በአንድ በኩል ጠላት ያሰበውን አጀንዳ እያከሸፍን በቀጣይ ደግሞ ከሕዝባችን ጋር እየተወያየን ለመግባባት ተሞክሯል ። በአጠቃላይ በክልሉ ሆነ ከክልሉ ውጭ የሚደረጉ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ማክሸፍ ተችሏል የሚለው ጉልህ ነጥብ ተደርጎ መወሰድ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ሰልፎቹ ሕጋዊ ፈቃድ አልነበራቸውም ?
አቶ እንግዳው፡- አልነበራቸውም! ዜጎች ሕጋዊ ሆነውና መብታቸው ተጠቅመው መግለጽ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ነገሮች ባልተረጋጉበት ወቅት፤ ስጋት ባልቀነሰበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ሰልፉን ሲዘውሩት የነበሩት ጠላቶች ነበሩ ። ስለዚህ ሰልፉ ሕጋዊ አልነበረም፤ የትም ቦታ ላይ አልተፈቀደም ። የተፈለገው ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም ሳይሆን ሕገወጥ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ነበር ። ሰልፍ አደርጋለሁ እና ሰልፍ አታደርግም በሚለው ኃይል መካከል በተለይም በፀጥታ ኃይሉ እና በኅብረተሰቡ መካከል ግጭት በማስነሳትና ንብረትን በማውደም ተቋማትን ለመምታት የታሰበበት ነበር ። ስለዚህ የሚጠራው ሰልፍ ሕጋዊ አለመሆን አንዱ ስጋት ነበር ። ይሁንና አንዱ መሰናክል ሲገጥመን ሌላውን በጥበብ ለማለፍ ጥረት ተደርጓል ።
ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በጋራ በተሠራ ሥራም እጅግ በርካታ ሕገ ወጥ ኃይሎችን በመቆጣጠር ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የተሠራው ሥራ አንዱ መልካም ነገር ነበር ። ስለዚህ ጠላት በከፈተው አጀንዳ ሳይሆን በልማትና በሕዝባዊ ትስስሮች የጠላትን አጀንዳ ማክሸፍ ላይ በመሠራቱ በርካታ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰው ወደ እርሻቸው ገብተዋል ።
የጉሙዝ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ‹‹የአማራ ኢ-መደበኛ ኃይል ሊያጠቃህ›› ነው በሚል ወደጫካ የወሰዱትን የኅብረተሰብ ክፍል ሁሉ መመለስ ተችሏል። ሕዝብ በሰላማዊ መድረክና ውይይቶች ላይ እያለ ያለው ‹‹እኛ ተጣልተን አናውቅም፤ ይህን ያደረገን ጠላት ስለሆነ በጋራ ሆነን የምትገድሉንም ከሆነ ግደሉን ። ከዚህ ውጭ የአማራ ሕዝብ ወንድማችን ነው፤ የጉሙዝ ሕዝብ ወንድማችን ነው፤ የሺናሻ ሕዝብ ወንድማችን ነው›› ብሏል ። ከዚህ በኋላ የጠላት አጀንዳ ማራገፊያ ሳንሆን የልማትና ማኅበራዊ ትስስር መሠረት ነን በሚል በዚያ መንገድ እየተሠራ ነው ። በመሆኑም ብዙ መልካም ነገሮች እንዳሉ ማወቅ ይገባል ።
ከአፋር ክልል ጋርም ያካሄድናቸው በርካታ መድረኮች አሉ ። የተደረሰበት ድምዳሜ መሰናክሎችን በጋራ እንዴት እንለፋቸው የሚል ሲሆን ውይይቱ መሬት እየነካ ነው ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የፀጥታ ስጋት በነበረባቸው አካባቢዎች ላይ የአመራር ለአመራር እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል ። ስለዚህ ሕግ የማስከበር ሥራው በዘመቻ ሳይሆን ተቋማዊ ሆኖ በየአካባቢው የሚፈጠሩ የፀጥታ ስጋቶችን በአካባቢ ያለው የጸጥታ መዋቅር በራሱ አቅም ማስተካከል የሚችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ስለዚህ ተቋማዊ ግንባታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ። ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴያችንም ዕውን ይሆናል ። ይህም ቀጣይነት ባለው መንገድ እየተሠራ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ሕግ በማስከበር ዘመቻው ‹‹ኢ-መደበኛ ኃይሎች›› የተባሉት የቂም በቀል ሥራ ነው በማለት ሕዝብን ለማነሳሳት ይጠቀሙበታል ይባላል ። የክልሉ ግምገማ በዚህ ላይ ምን ይላል?
አቶ እንግዳው፡– ከሕዝብ በላይ የሕግ ይከበርልን የሚለውን ጥያቄ ያቀረበ የለም ። በእያንዳንዱ መድረክ ተወያይተናል ። ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አግኝተናል ። በሁሉም መድረኮች ላይ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕዝብ ጠይቋል ። ምክንያቱም ወጥቶ መግባት አይቻልም፤ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይቻልም፤ በራስ ንብረት ማዘዝ አይቻልም፤ ባለሀብት ዘንድ ተደውሎ በሚሊዮን ብር ይጠየቅ ነበር ።
አዲስ ዘመን፡-እውነት ብር የተጠየቁ ባለሃብቶች ‹ተጠይቀናል› ብለው ለእናንተ መረጃ ሰጥተዋል?
አቶ እንግዳው፡- እንዴ! በሕዝብ መድረካችን ሕግን በትክክል ማስከበር ከቻላችሁ እኛ እስከ ሕይወት መስዋዕት እንከፍላለን ። ሌባውን እና አጭበርባሪውን በትክክል አውጥተን መስጠት እንችላለን የሚለው ሕዝብ ቀላል አልነበረም ። ስለዚህ በጥፋት ላይ የተሰለፉ በሕግ የሚፈለጉ፤ ከማረሚያ ቤት ያመለጡና ውሳኔ ያረፈባቸውን በርካታ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል ። የተረጋጋ ሁኔታ ከተፈጠረ እና የሕግ የበላይነት ካለ በፈፀሙት ድርጊትና ወንጀል መጠየቅ የማይቀር ስለሆነ ይህ ኃይል ይረብሻል ። ስለዚህ ይህን ኃይል መቆጣጠር ተችሏል ። በመሆኑም ለቂም በቀል ነው የሚለው አግባብ አይደለም ። ከፌደራል መንግሥትና ከሌሎች ፀጥታ መዋቅሮች ጋር ለማጋጨት የሚደረግ የጠላት ሴራና የግለሰቦች ፍላጎት ነው ።
ኢ-መደበኛ አደረጃጀት የምንለው የፋኖ ሥም ይዞ ነገር ግን የፋኖን ምግባር እና ተግባር ያልያዘና ያልተላበሰ ሌባ፣ ዘራፊ ነው ። በመሆኑም ሕዝቡ ሕግ ይከበርልን እያለ ቂም በቀል ነው ማለት የሚጣረስ ሃሳብ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- የክልሉን ሰላም ለማስከበር የፌደራል መንግሥት በእጅጉ ጣልቃ ገብቷል የሚል ወቀሳም ይሰማል ። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ እንግዳው፡– እኛ ሕግ እያስከበርን ያለነው በራሳችን ኃይል ነው ። ሕግ እያስከበርን ያለነው በራሳችን ልዩ ኃይል፣ በራሳችን ሚሊሻ፣ ፖሊስና እና በራሳችን ፀጥታ መዋቅር ነው ። ስለዚህ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እየገባ ነው የሚለው በአንድ የፌደራል ሥርዓት ውስጥ እስከተዳደርን ድረስ የፌደራል መንግሥት ከክልል መንግሥት ጋር ሆነው በቅርበት ይሠራሉ ። በዋናነት ግን የችግሩም ሆነ የፀጥታው ባለቤት የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ነው ። ሆኖም ሕግን የማስከበር ሥራዎች በቅንጅት የሚሠሩ ናቸው ። ሌላው ቀርቶ ከጎረቤት ሀገራትም ጋር በጋራ የፀጥታ ሥራዎች ላይ በትብብር ይሠራል ።
ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ባለችበት ወቅት በጋራ በሚሠራበት ሁኔታ ፌደራል መንግሥት በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል የሚለው ወቀሳ ውሃ የሚያነሳ አይደለም። በአጠቃላይ እኛ ሕግ እያስከበርን ያለነው በራሳችን የፀጥታ መዋቅርና አደረጃጀት ነው ። ነገር ግን እንደ አመራር፤ የአመራር ድጋፍ እንደሚኖር መታሰብ አለበት። ምክንያቱም ዋነኛ አጀንዳ ተደርጎ የተወሰደው አማራ ክልልን ማፍረስ ከተቻለ፤ ኢትዮጵያን ማፍረስ ይቻላል የሚል ነው ። ይህ የጠላት ዓላማ ነው ። ምክንያቱም ለሕገ-ወጥ ኃይሉ እና ሕወሓት ላስታጠቃቸው የውስጥ ጠላቶች በዋናነት የአማራ ክልልን ማፍረስ ከተቻለ የፌደራል መንግሥትን መቆጣጠር ይቻላል የሚል ሕልምና ዓላማ ነው ያለው ። ይህንን በጋራ ተባብሮ መስመር ማስያዝ የፌደራል መንግሥትም ጉዳይ ነው ።
እኛ እየተወጋን ያለነው ከአሸባሪው ሸኔ፤ ከጉሙዝ አማፂ ቡድን፣ ከቅማንት ፅንፈኛ ቡድን እና ኢ-መደበኛ ኃይሎች ጋር ብቻ አይደለም ። ጠላት በተዘዋዋሪ መንገድ የገዛቸው፤ ያደራጃቸው አፍራሽ ኃይሎችና ተላላኪዎችም ጋር ነው ። እነዚህ ኃይሎች ከፊት ለፊት ይኑሩ እንጂ ከኋላ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ፣ በማኅበራዊ ሚዲያም የመንግሥትን ሥራ የሚያብጠለጥሉት የውጭ ኃይሎችና ሕወሓት መሆኑ መታወቅ አለበት ። ሕወሓት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ጠላት ነው ። በመሆኑም በጋራ ጠላት ላይ የፌደራል መንግሥትም እንደሚመለከተው መግባባት ያስፈልጋል ።
አዲስ ዘመን፡- የሱዳን በአማራ ክልል አዋሳኝ ላይ የሚያደርገው ትንኮሳ፣ በወለጋ የአማራ ተወላጆች ጭፍጭፋ፣ የሕወሓት ዳግም ትንኮሳ፣ የኢ-መደበኛ ኃይሎች መግነን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ወቅት ጋር መያያዙ አንድምታው ምንድነው?
አቶ እንግዳው፡- እነዚህ ኃይሎች ተጠናክረው እየሠሩ ያሉት ከምዕራባውያን እና ግብጽ ከምታስታጥቃቸው ኃይሎች ጋር በተቀናጀ መንገድ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማለት ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምትሻገርበት አንዱና ዋነኛ መሠረት ነው ። ስለዚህ ይህን ማደናቀፍ ማለት የፌደራሉንም ሆነ የክልሉን መንግሥት ውጥረት ውስጥ በማስገባት የተጀመረው ልማት እንዳይጠናቀቅ ማድረግ ነው ።
ክልሎችን እርስ በእርስ በማጋጨት ዓላማችን ማሳካት እንችላለን የሚል ነው ። የህዳሴ ግድብን ማስተጓጎል ማለት ወይንም አማራን ማፍረስ ኢትዮጵያን ከማፍረስ ጋር የተያያዘ ነው ። ሕወሓትም የሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ያለችበት ወቅት ነው ። ስለዚህ እነዚህ አንድ ላይ ተዳምረው ያለውን ፍላጎት ማወቅ ይገባል ።
የሚስተዋሉት ትንኮሳዎች ተራ የጥቅም ሽኩቻ አይደሉም ። የሚደረገው እንቅስቃሴ ጠላት ያሰለፋቸው በማኅበራዊ እንቅስቃሴ፤ በፖለቲካ ዘርፎች የተሰለፉ ኃይሎችን በመጠቀም ነው ። በመሆኑም የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ከመቼውም በበለጠ ተጠናክረው ለመሥራት የሚገደዱበትና ጠላትን ለማሳፈር መስዋዕትነት የሚከፈል መሆኑን መገንዘብ ይገባል ።
ብዙ ትንኮሳዎች ቢኖሩም መንግሥት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ በመስጠት ብልህነት የተሞላው አካሄድ እየተከተለ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው ። ከዚህም አለፍ ሲል ሕግን የማስከበር ጉዳይ የአንድ መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ተደርጎ እየተሠራ ነው ። በየቦታው የሚታዩና ጥቃቅን የሚመስሉ፤ ነገር ግን ትስስር ያላቸው፤ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በተናበበ ሁኔታ በገንዘባቸው በገዟቸው ኃይሎች አማካኝነት የበለጠ ውጥረት ለማንገስ፤ ‹‹ኮሪደር›› ለማስከፈት ያለመ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የህዳሴውን ግድብ ሙሌት ለማስተጓጎል የሚደረግ ሲሆኑ እልፍ ሲልም ኢትዮጵያን የማፍረስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ለየትኛውም አካል ግልፅ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ‹ኢ-መደበኛ› በተባሉ ኃይሎች ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት በሰላማዊ መንገድ መወያየት ለምን አልተቻለም?
አቶ እንግዳው፡– በመሠረቱ ኢ-መደበኛ ኃይሉን ተቆጣጥረናል ስንል የተወሰደው እርምጃ አይደለም። የአጥፊው ድርጊት እየታወቀ ቅድሚያ የተሰጠው የሰላም አማራጭ ነው ። ሰው እውቀት አለው፤ ገንዘብ አለው። መገደል የለበትም ። ሰው በራሱ ለሀገሪቱ ሃብት ነው ። ስለዚህ እጅ እንዲሰጡ የተደረገው በአብዛኛው በመስዋዕትነት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ነው ። ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው ። የፀጥታ ኃይላችንም የመጀመሪያ ሥራው ከእነዚህ ኃይሎች ጋር መወያየት ነበር ። በድርጊታቸው ተፀፅተው መንግሥትን እና ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀው ለተመለሱት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና ወስደው ወደማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል ።
በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ውስጥ ዓላማው ሳይገባቸው እና ዓላማውን አውቀው የገቡበት አሉ ። በሌላ በኩል ደግሞ የኃይል ሚዛን እየተመለከቱ ከመሐል ሆነው የሚዋልሉ ኃይሎች አሉ ። በመሆኑም ለእነዚህ ትክክለኛውን የጠላትን ፍላጎትና እንቅስቃሴ በማስረዳት በሰላማዊ መንገድ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እና መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል ።
ከእነዚህ ውጭ ያሉት ወደ 500 የሚሆኑት ከማረሚያ ቤቶች ያመለጡና ከዚህ በፊት ውሳኔ አርፎባቸው ጠላት በነበረባቸው አካባቢዎች እንዲወጡ የተደረጉ ነበሩ ። ስለዚህ እነዚህን ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ተደርጓል ። ሦስተኛው በፍርድ ቤት ውሳኔ አርፎባቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ተደብቀው የሚኖሩ ግን በዚህ ወቅቱን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ከኢ-መደበኛ ኃይሎች ጋር ሆነው ፋኖ ነን ከሚሉት ውስጥ 500 በላይ የሚሆኑትን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። በመሆኑም እነዚህ ኃይሎች ፋኖ ሊሆኑ አይችሉም ። ሰው የገደለ፤ የዘረፈ፤ ፀጥታ ኃይሉን ያሰናከለ መቼም ቢሆን ፋኖ ሊሆን አይችልም ። ነገር ግን ‹‹ፋኖ ››ነን የሚል ሽፋን ይጠቀማሉ ።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ተጠርጣሪዎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት የሕግ ሂደቱን ያልተከተለና በዘፈቀደ የሚከናወን ነው የሚሉ ወቀሳዎች ይሰማሉ ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ እንግዳው፡– የመጀመሪያው የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ባከበረ መልኩ ነው ። ተጠርጣሪዎች የትኛው ማረሚያ ቤት እንዳሉ ይታወቅ ነበር፤ አሁንም የት እንዳሉ ይታወቃል ። የሚወራው ነገር ትክክል አይደለም። የሚያስጮኸው ጠላት ነው ። የሕገ ወጡ ክንፍ የሆነውና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚጠቀመው የሚያጯጩኸው ያ ኃይል ነው ።
መብታቸውን በጣሰ መንገድ አይደለም ። ነገር ግን ለፀጥታ ኃይሉ እጃቸውን በሰላም ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑና የኃይል ዕርምጃ የወሰዱት እንዲመቱ ተደርጓል። እያስከበርን ያለነው ሕግ ነው ። ሕግ ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ እስካሁን ከ27 በላይ የፀጥታ አካላት መስዋዕት ሆነዋል ።
ሕግን ለማስከበር መስዋዕት ለሚሆነው ኃይል የሚጮህለት አካል የለም ። ነገር ግን ሕገ ወጥ ሆኖ ሲዘርፍ ለነበረው አካል የሚጮኸው እጅግ ብዙ ኃይል ነው ። ይህ በጣም ያሳዝናል ። የአንዳንድ አካላት ምልከታም ሚዛናዊ አለመሆኑን መረዳት ይገባል ።
በሰላማዊ መንገድ እጅ የሰጡት እየተሰጣቸው ያለው የአቅም ግንባታ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ምን ያክል ክልሉን እና ሕዝቡን አደጋ ውስጥ አስገብተው እንደነበር እየተገነዘቡ ነው ። ከዚህ በፊት የተያዙትም ሆኑ በቀጣይ በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚውሉት ሕግን ተላልፈው ግድያ የፈፀሙ፣ ሕዝብን ያፈናቀሉት ላይ የሕግ የበላይነት ማረጋገጡ የማይቀር ጉዳይ ነው ። ስለዚህ ይህን የምርመራ ሂደት መረጃ እና ማስረጃን መሠረት አድርጎ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግሥት ኃላፊነት ነው ።
አዲስ ዘመን፡- በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ‹‹ኢ-መደበኛ›› ኃይሎች ከሕዋሓት፣ ከሸኔ እና በሌሎች ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ የሰላም ጠል ኃይሎች ጋር ወዳጅነት አላቸው የሚል ግምገማ አላችሁ?
አቶ እንግዳው፡– ምንም ጥያቄ የለውም ። ጠላት የሚጠቀመው ማንን ነው? ጠላት ብድግ ብሎ የአማራ ክልልን ሊደፍር የሚችልበት መሠረት የለውም። በውስጥ ያሉ ማናቸውንም ሕገወጦችን ወይንም ከመንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት የሌለው ማነው በሚል ጥናት አድርገው እየሠሩ ነው ። ስለዚህ እነዚህ ኃይሎች ከቅማንት ጽንፈኛ ኃይሎች፤ ከጉሙዝ አማጺያን ጋር እና ከሕወሓት ጋር ትስስር አላቸው። ስለዚህ ችግር ፈጣሪዎች ከየትኛውም ሕገ-ወጥ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መታወቅ አለበት። የሁሉም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች መዳረሻቸው ክልሉን የማዳከምና ሀገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ መሆኑ መታወቅ አለበት ። ቁሳዊ በሆነ ሃብት እየተገዙ የሚገድሉትና የሚጎዱት የራሳቸውን ማኅበረሰብ፤ ያደጉበትን አካባቢ እና የሚኖሩበትን ሀገር የማፍረስ ጥረት ነው ። ጠላትም የሚጠቀመው እነዚህን ኃይሎች ነው ።
አዲስ ዘመን፡- በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ‹‹ኢ-መደበኛ›› ኃይሎች ዕድሉን ቢያገኙ በክልሉ ሊስፋፉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ ?
አቶ እንግዳው፡– የመጀመሪያው ሕዝባዊ መሠረት የላቸውም ። በሕዝብ ግንኙነት ሥራችንም ሕዝብ እና መንግሥት የማይቀበላቸውና አንቅሮ የተፋቸው ናቸው። ስለዚህ በአማራ ክልል ሊያድጉ የሚችሉበት ዕድል የላቸውም ። ምክንያቱም ሕዝባችን፣ አመራሩ እና የፀጥታ መዋቅራችን በጋራ እስከሠሩ ድረስ ወደዚህ የሚያድጉበት ዕድል አይኖርም ። ተራ የሆነ ሕገወጥ ድርጊት ሊፈፅሙ ይችላሉ ። ባህርዳር ላይ ሰሞኑን አመራርና ሕዝብን ለማሸበር ቦንብ ሊጥል የነበረ አካል በቅፅበት በቁጥጥር ስር ውሏል ። ይህ የሚያሳየው ደጀን የሆነ ሕዝብ መኖሩን ነው ።
አዲስ ዘመን፡- በሕወሓት ወረራ ወቅት በርካታ የጦር መሣሪያ በግለሰቦች እጅ እንደሚገባ ይገመታል ። እንደክልል እነዚህ የታጠቁ ኃይሎችን ሕጋዊ መስመር ለማስያዝ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ እንግዳው፡- ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ። በየአካባቢው ሕገወጥ የጦር መሣሪያ እንዳይኖር፤ የያዙትም መሣሪያ ስልጠና ወስደው ወገንን ለማስፈራራት ሳይሆን ከጠላት ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያስችላቸው አሠራር እየተፈጠረ ነው ። በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር መሣሪያዎች በፀጥታ መዋቅር መያዝ ተችሏል ። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጠላት ሊተላለፍ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል ። በርካታ ሸቀጣ ሸቀጥ፣ ነዳጅ፣ አልባሳት፣ ጫማ እና ተንቀሳቃሽ ስልኮችም ለጠላት ተላልፈው ከመሰጠታቸው በፊት ተይዘዋል ። ይህ የሚያሳየው የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ በአንድነት እየሠራ መሆኑን ነው ። ስለዚህ በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ከክልሉ የፀጥታ መዋቅርና መንግሥት አቅም በላይ የሚሆን አንድም ነገር እንደማይኖር መታወቅ አለበት ።
የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግሥት ኃላፊነት ነው ። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ጤናማ መሆን አለበት ። ለዚህም የክልሉ መንግስሥት በትጋት ይሰራል። ሕዝባችንንም ደጀን አድርገን ሥራችንን እንሠራለን ። አንድ ክልል ሠላም ስለሆነ ሌላው አካባቢ ሰላም አይሆንም ። በመሆኑም ሕዝባችን ከፀጥታ መዋቅር ጋር በመተባበር ለክልሉ እና ሀገር ሠላም ስጋት የሆኑ ኃይሎችን በጋራ መጋፈጥ ይገባል ። ሕዝባችንም ከፀጥታ ሥጋት ነፃ ሆኖ ወደ ልማት ፊቱን ማዞር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለጥያቄያችን ወቅታዊ መረጃና ማብራሪያ ስለሰጡን እናመሰግናለን ።
አቶ እንግዳው፡- እኔም አመሰግናለሁ ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2014