የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤት የዕጣ ዕድለኞችን ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ የዕጣ አወጣጥ ይፋ ካደረገ ማግሥት ጀምሮ በየማኅበራዊ ድረ ገጹ በዕጣ አወጣጡ ላይ የዕጣው ኢ-ፍትሐዊነት ሲገለጽና በከተማ አስተዳደሩ ላይ ስድብ አዘል ነቀፌታዎች ሲቀርቡ እንደነበር አስተውለናል ።
ቅሬታው መነሻ ሆኖ ይሁን የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ጥረት ጉዳዩን ደርሶበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠንከር ያለ እርምጃ ወስዶ ፍትሐዊነትን ለማስፈን ሞክሯል። ዕጣውንም መሰረዙን ይፋ አድርጓል ። ይቅርታም ጠይቋል። ኢፍትሐዊነት የጎደለው አሠራርንና በደል አድራሾችን ማጋለጥ፣በደል የደረሰባቸውም የፍትሕ ያለ እንዳሉ መቅረታቸው የተለመደ ተደርጎ በሚወሰድበት በዚህ ወቅት ፍትሕ ብትቀጥንም አትበጠስም የሚለውን ለማየት ተችሏል ።
አሁንም በጉዳዩ ላይ ብዙ ማጣራትና ሕዝብ ጆሮ መድረስ ያለባቸው ተግባራት ከከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅ ቢሆንም ከእለት ጉርሳቸው ቆጥበው ነገ የቤት ባለቤት ለመሆን በጉጉት ሲጠባበቁ ከነበሩ ዜጎች ላይ ነጥቀው ለመውሰድ አሰፍስፈው በነበሩት ላይ እርምጃ መወሰዱ በመልካም እየተወሰደ ቢሆንም እርምጃው በቀማኞቹ የሴፍትዌር ባለሙያዎችና የሥራ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ በማይገባ መንገድ የማይገባቸውን ቤት ለማግኘት የሞከሩትንም ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል ።
ባልተገባ መንገድ ለማይገባቸው ሰዎች ቤቱን ለማስተላለፍ በማጭበርበር ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ተብለው ስማቸው ከነፎቶግራፋቸው ይፋ የተደረጉ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በብዙዎች በአዎንታዊ ጎኑ የታየ ነው ። እንዲህ ያለው እርምጃ በተመሳሳይ በማጭበርበር ወንጀል ውስጥ ለመሳተፍ የሚንቀሳቀሱትን ብቻ ሳይሆን፣ለሚያስቡትም ጭምር ትልቅ ማስተማሪያ ሊሆን ይችላል የሚል ሀሳብ አለኝ ።
እነዚህ በማጭበርበር ወንጀል ላይ የተሳተፉት ሙያተኞችና ኃላፊዎች መንግሥት አምኖባቸው የሰጣቸውን ሥራ አለመወጣት ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያገለግላቸው ግብር ከፍሎ ባስተማራቸው ሕዝብ ላይም ነው ክህደት የፈጸሙት ።ያሳደጋቸውን ቤተሰብም አንገት የሚያስደፋ ድርጊት ነው ያከናወኑት ። ልጅ ወልደው ቤተሰብ ያፈሩ ከሆኑም በእነርሱ እንዲኮራ አላደረጉትም ። የሥራ ኃላፊነቱን ሲረከቡ ብቻ ሳይሆን ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በቅንነትና በታማኝነት ሕዝብ ለማገልገል ቃል ገብተዋል ። ግን ለቃላቸው ታማኝ ሆነው አልተገኙም ። ይህ ሁሉ ንዋየ አፍቅሮት ያመጣው መዘዝ ነው ።
ከሁሉም አሳሳቢው በማጭበርበር ሂደት ውስጥ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በዚህ ደረጃ መኖራቸው እጅግ አስደንጋጭ ነው ።ይሄ የሞራል ዝቅጠቱ የደረሰበት አንዱ ማሳያ ነው ።ችግሩ ወደቤተሰብ አስተዳደግና ትምህርት ቤቶችም መሔዱ አይቀርም ።የሕዝብ አገልጋይና ሰብዓዊነት የሚሰማቸው ዜጎች በማፍራት ረገድ ቤተሰብና ትምህርት ቤት ሚናቸው ከፍ ያለ ነው ።በተለይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚቋቋሙ እንደስካውት ያሉ ሥነ ምግባርን በማነጽ ሚናቸው የጎላ እንደነበር ይታወሳል ።
በኋላም የሥነ ዜጋ የትምህርት ክፍለ ጊዜም ነበር ።ይህ ሁሉ ሀገርን የሚያገለግሉ ዜጎች ለማፍራት የሚያስችል አንዱ መንገድ እንደነበርም በትምህርት ቤት ያለፈ ሁሉ የሚያውቀው ነው ።‹‹አሳዳጊ የበደለው››የሚል ስድብ የቤተሰብ ስብዕናን የሚነካ በመሆኑ ስማቸውን በመልካም ለማስጠራት በልጆቻቸው ላይ ብዙ የሚደክሙ ወላጆች መኖራቸውም አይዘነጋም ።
ለክብሩና ለስሙ የሚጨነቅ፣ከራሱ ይልቅ ሌላውን የሚያስቀድም ጥሩ የሆነ የኢትዮጵያዊ መገለጫ ያለው ማኅበረሰብ የበዛበት እንደነበርም ከቃል ባለፈ በተግባር ይታወቃል ። አሁን ላይ የሚስተዋለውና የሚሰማው ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ከሚባለውም በላይ የሆነ ድፍረትና ጭካኔ እየታየ ነው ።የመጣው ይምጣ ብሎ ማስለቀስና ማሳዘን እየተለመደ ነው ።
መንግሥት ደሀውንና ዝቅተኛውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎ የጀመረው የቤት ልማት ፕሮግራም በግንባታ ጥራት፣ በሚገነባው ቤት ብዛት፣ቤት ማስተላለፍ በውስብስብ ችግር ውስጥ አልፎ እዚህ የደረሰ ነው ። አሁን ላይ በተደራጀ አሠራር በዕጣ አወጣጥ ላይ የተፈጠረው ችግር ለየት ያለ ቢመስል አንድ ሀገራዊ የሥነ ምግባር ችግር መገለጫ ነው ።ችግሩ ተደርሶበት እርምጃ መወሰዱ አንድ ነገር ቢሆንም ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ተገቢው ሥራ እንዳልተሠራ አመላካች ነገሮች አሉ ።
የቤት ጥያቄ ሰፊ በሆነበትና ሳይደክሙ ቤት በመሸጥና በመለወጥ ሀብት ያካበቱ የአየር ባየር ነጋዴዎች በበዙበት በዚህ ወቅት ማጭበርበር እንደሚኖር መታወቅ ነበረበት ።ዛሬ በየምንኖርበት አካባቢ ይህ ነው የሚባል የመንግሥትም ሆነ የግል የሆነ ሥራ የሌላቸው ቤትና መሬት በመሸጥና በመለወጥ በሀብት የማይወዳደራቸው የሆኑ ሰዎች እያየን ነው ።
በጣም የሚገርመው ደግሞ ማን እንደነበሩ የሚያውቃቸውን ሕዝብ እንኳን የሚያከብሩ አይደሉም ። ጥቅም አሳዳጆች ናቸው ። የሚሸጡት ቦታም የሚያውቁት አካባቢ በመሆኑ የወረዳውንና የክፍለ ከተማውን አስተዳደር በቀላሉ ነው የሚይዙት ። በገንዘብ ኃይል የነዋሪ መግቢያና መውጫ ሳይቀር በመሸጥ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለው ሕዝብ የሚያሳዝኑ መኖራቸው በግልጽ ይታወቃል ።
በፍትሕ ቢጠየቁ እንኳን ገንዘብ ስላላቸው የሚያሸንፋቸው የለም ። የከተማ አስተዳደሩ የልብስ መሸጫ ሱቅ የቸገረው ይመስል ክፍት ቦታዎች ሁሉ ተሸንሽነው ሱቅ የተሠራባቸው ጥቂት የማይባሉ አካባቢዎች በመዲናዋ ውስጥ ይገኛሉ ።የከተማ አስተዳደሩ በ14ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ አወጣጥ ላይ የወሰደውን ፈጣን እርምጃ በተመሳሳይ በየክፍለ ከተማውና ወረዳ ውስጥ ያለውን የመሬት ልማት አስተዳደር ይፈትሽና የሕግ ማስከበር ሥራውን ያጠናክር ።
መውጫ መግቢያቸው ተዘግቶባቸው፣የንግድ ቦታቸውና የመኖሪያ ቤታቸው ፈርሶባቸው ከንቲባዋን በየት በኩል አግኝተናቸው ድምጻችንን እናሰማ የሚሉ ዜጎች በየአካባቢው ስላሉ አጠቃላይ በከተማዋ ያሉ ሕገወጥ ተግባራትን ለማስቆም በቂ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው ። ሕገ ወጦችን ወደ ሕግ የማቅረቡ ሂደት የአንድ ሰሞን ጩኸት እንዳይሆን አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል ።
የከተማ አስተዳደሩ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተገኝተው ‹‹በሾፌር በር ተከፍቶለት በኮብራ መኪና የሚሄድ አመራር ሳይሆን በፒካፕ መኪና እየተዟዟረ ታች ወርዶ የሚሠራ ነው የሚያስፈልገው ።›› ማለታቸው ይታወሳል ። ከፍተኛው አመራር በየወረዳውና ክፍለ ከተማው ስርቆትን ማዕከል አድርጎ የሚሠራውንም ይዘው ለሕግ እንዲያቀርቡ ጭምር ነው በአፈጻጸም ግምገማው ላይ የተናገሩት ።
የከተማ አስተዳደሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት እየተገበረው ይሆን? የሚል ጥያቄ ቢኖርም፣በጋራ መኖሪያ ቤት የዕጣ አወጣጥ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለማረም የወሰደውን እርምጃ አይነት በሌሎችም ይጠበቃል ። ቴክኖሎጂ ሰው ሰራሽ መሆኑ ተዘንግቶ ሙሉ ለሙሉ እምነት መጣሉ ሌላው ክፍተት ነው ።
ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነው የዕጣ አወጣጡ እንጂ ቀድሞ የተሠራው ሥራ ላይ ክፍተት ስለመኖሩ አልታየም። ዛሬ ከባንክ ውስጥ ብር ለመዝረፍ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በተፈጠረበት ዘመን ቴክኖሎጂ በራሱ የሚሠራ አድርጎ መገመት የዋህነት ነው ።በዚህ ረገድም ትምህርት እንደሚወሰድበት ተስፋ አደርጋለሁ ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም