ትምህርትን በሥራ ፣ በትዳርና በልጆች ጫና መካከል ሆኖ መማር እጅግ ፈታኝ ነው። ብዙ ጊዜ በእንዲህ ዓይነት ተደራራቢ አጣብቂኝ ውስጥ አልፎ ትምህርትን ካሰቡበት ዳር ማድረስም ጀግንነትን ይጠይቃል።
አብዛኞቹ ሰዎች መማር እየፈለጉ የማይሞክሩት ለዚሁ እንደሆነ አጫውተውናል። ደፍረው የሞከሩትና የዘንድሮ ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያየ ትምህርት ክፍልና መርሐ ግብር ተመራቂ ሴት ተማሪዎች ጫናው ከባድ ቢሆንም ይቻላል ብለው ከገቡበት ለስኬት መብቃት እንደሚቻል አሳይተዋል። እኛም በዛሬው በሴቶች ዓምዳችን ያልሞከሩት እንዲሞክሩት ብርታትና አቅም ሊሆን ይችላል ያልነውን የነዚህ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ዓመት ስኬታማ ሴት ተመራቂዎችን ተሞክሮ ልናጋራችሁ ወደናል።
ተመራቂ ተማሪ ግርማዊት አበራ ዘንድሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተከታታይ (ኤክስቴንሽን) ትምህርት መርሐ ግብር ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። በጀንደር ስተዲ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀችው ፎር አምጥታ ነው። እሷ እንደምትናገረው ይሄ ደግሞ ሴቶች ትምህርታቸውን መከታተል ብቻ ሳይሆን በአጥጋቢ ውጤት ማጠናቀቅ መቻላቸውንም ያረጋግጣል። በትምህርት ሂደት የገጠማት ፈተና ቀላል ባይሆንም በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ መብቃቷ ለሌሎች እንደ እሷ በፈተና ውስጥ ላሉና ፈተናውን ለማለፍ ፈራ ተባ የሚሉ ሴቶች ቁርጠኝነትን የሚያስታጥቅ አርአያ ይሆናል ብላ ታስባለች ።
ተመራቂ ትዕግስት ፍቃዱም በዚሁ ትምህርት መስክ ነው በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀችው። ትግስት ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናት። ደግሞ በአንድ የመንግስት ተቋምም ትሰራለች። ከትዳር ከልጅና ከሥራ በተጨማሪም የተለያዩ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችም አሉባት።
ትዕግስት ባለፈው ቅዳሜ በጀንደር ስተዲ መስክ ልትመረቅ የቻለችበትን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የዛሬ ሦስት ዓመት የጀመረችው በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሆና ነው። ትምህርቱን የጀመረችው የመጀመሪያ ዲግሪ ፤ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን ካጠናቀቀች ከ12 ዓመት በኋላ እንዲሁም ትዳር ከመሰረተች ከ10 ዓመት በኋላ ነው ። በተጨማሪም ትምህርት ቤት ስትገባ ወንዱና ትልቁ ልጇ የአምስት ሴቷ ልጇዋ ደግሞ የአንድ ዓመት ነበሩ። ዕድሜያቸው እሷን አብዝተው የሚፈልጉበት በተለይ ትንሽዋ ገና ጡት ያልጣለችበት ነበር።
ሆኖም ባለቤቷ ትምህርቷን እንድትማር ከማነሳሳትና ከማበረታታት ጀምሮ ልጆቹን በመከታተሉ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግላት ቆይቷል። በተለይ ትልቁ ልጅ ለትምህርት ከደረሰ በኋላ ትምህርት ቤት እንዲሄድ በማድረጉና ምን ላይ እንዳለ በማጤኑ ረገድ ያደረገላት ድጋፍ የጎላ ነው። ከልጆቹ ባሻገር የቤቱን ኃላፊነት በመጋራቱም ቢሆን ያደርግላት የነበረው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።
‹‹ባለቤቴ ባያግዘኝና ባያበረታታኝ ፍፁም ልጀምረውና ልጨርሰው አልችልም ነበር›› ስትልም የክብደቱን ኃያልነት ገልፃዋለች። ትዕግስት እንዳጫወተችን በሥራዋ በኩል እጅግ የበዙ ተደራራቢ ኃላፊነቶች አሉባት። ሥራዋ ቶሎ ቶሎ መስክም ያስወጣታል። በዚህ መካከል ቅዳሜን ጨምሮ በሳምንት ሁለት ሙሉ ቀን ትምህርት ተምሮ መመረቅ ይከብዳል። ለእንደ እሷ ዓይነት ጫና ለበዛባቸው ሴቶች ላይታመን የሚችል እጅግ ፈታኝም ነው። በዛ ላይ ውድድሩ ጠንከር ያለ ነበር።
የጀንደር ስተዲ ኮርሶችም ቢሆኑ አዲስ ናቸው ትላለች ትዕግስት፤ የትምህርት ሂደቱን የክብደት መጠን ስትገልፀው። ይሄም ብቻ አይደለም አዝወትራ መስክ በምትሄድበት ጊዜ የሚያልፏት ፈተናዎችና የማትከታተላቸው የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች እጅግ ብዙ ነበሩ። በዚህ በኩል ደግሞ የክፍል ጓደኞቿ አግዘዋታል። ያለፏትን ፈተናዎች በሜካፕ መውሰዷም በእጅጉ ረድቷታል።
‹‹ሆኖም በነዚህ ሁሉ በመታገዝና በግሌም ከጠበኩት በላይ በመጣር ትምህርቴን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ በቅቻለሁ ብላናለች ያመጣችው ነጥብ ከትምህርት ክፍሉ ፎር ከዘጋችው የማይተናነሰው ተማሪ ትዕግስት።
ሌላዋ የዩኒቨርሲቲው ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተመራቂ ተማሪ እመቤት ረጋሳ ናት። የተማሪዎች ተወካይ ኃላፊም የሆነችው እመቤት የመጀመሪያ ዲግሪዋን በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር በፕሎሶፊ መያዟን ትጠቅሳለች። እመቤት እንደ ትምህርት ክፍሉ ትምህርት የጀመሩት 2011 ግማሽ ሴሚስተር ላይ መሆኑንም ትናገራለች። ባለፈው ቅዳሜ የያዘችው የሁለተኛ ዲግሪዋ በተጨማሪ በሌላ የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪ ቀደም ሲል ይዛለች፡፡ በቅርቡም ሦስተኛውን በፖለቲካል ሳይንስ ሶስተኛ የማስተርስ ዲግሪ ለመያዝ እየተማረች መሆኑን ታወሳለች ።
አሁን ላይ የምሰራው ውሜን ኢንፖወርመንት ላይ በመሆኑ ሥራዬ ከትምህርቴ ጋር ይገናኛል። ራሴን አርአያ ማድረግ እፈልጋለሁ። በመሆኑም ሌላ ሦስተኛ ማስተርስም በፖለቲካል ሳይንስ እየተማርኩ ነው ትላለች እመቤት። እንዳከለችው የጀንደር ባለሙያ እንደመሆኗ ሴቶች ተምረው ብቁ ሆነው ካልተገኙ የራሳቸውን ችግር መፍታት አይችሉም። ራሳቸውን ለመቻልና ያለባቸውን ጫና ለማስተካከል የግድ መማርና ራሳቸውንም መቻል አለባቸው የሚል አቋም አላት። ከዚህ ተነስታ ለጾታ አጋሮቿ እራስን ማበርታት እንደሚገባም ትመክራለች ።ሴት ስለሆንኩ ብዬ እጄን መስጠትና ለራሴ ይቅርታ ማድረግ አልፈልግም። ምክንያቱም መጀመሪያ እኔ ካልተማርኩና ካልተለወጥኩ የሌላዋን ሴት ሕይወት መለወጥ አልችልምና ትላለች። ችግር ለመፍታት በችግሮች እየተፈተኑ ማለፍንም እንደሚጠይቅ የራሷን ተሞክሮ ዋቢ አድርጋ ታካፍላለች ። ፈተናው ከቤት ስትጀምረው ቤት ውስጥ በተለይ ሴት ሲኮን ልጆች ከመንከባከብና ቤት ከመምራት ጀምሮ ብዙ ኃላፊነቶች ይኖራሉ። ባለቤቷ በሀሳብም ሆነ የቤቱን ኃላፊነት በመሸፈንም በብርቱ ሲያግዛት ነው የቆየው። እንድበረታ ፤ እንዳጠና አጥንቼና ተዘጋጅቼ ለፈተና እንድቀርብ ያበረታታኝም ነበርም፡፡ ልጆቻችንን ትምህርት ቤት ከመውሰድ በተጨማሪ አጠቃላይ የሚከታተላቸውም እሱ ነበር። በዚህ በኩል ነፃነት ሰጥቶኛል ብላናለች። እንደ እመቤት ትምህርቷን ለማጠናቀቅ የሄደችበት ሂደት በራሱ ፈተና የበዛበትና አስቸጋሪ ነበር። ትምህርቱም ትንሽ የሚከብድና ጊዜ የሚፈልግ ሆኖ አግኝታዋለች። አብዝቶ ማጥናትንና ሌሊት ተነስቶ መሥራትም ይጠበቅባት ነበር። ብዙ ጊዜም በትምህርት ሰዓት መስክ የምትወጣበት ጊዜም ቀላል አልነበረም። ሆኖም አስተማሪዎቻቸው በትምህርት ክፍለ ጊዜ መቅረቷን ስለማይፈልጉ በጣም ትቸገር ነበር። ይሄን ሁሉ ከትምህርቱ ጋር አቻችሎ መወጣትም ይፈልግ እንደነበር ታወሳለች። እሷ ደግሞ ችግሩን መወጣት አልችልም ብሎ ወደ ኋላ ሳይቀሩ ጨክኖ መማር እንዳለባት አምና ስለገባች ለውጤት በቅታለች።
በመሆኑም በአጋጣሚ የተማሪዎች ተወካይ ነበረችና ጫና ሲመጣባቸው ከመምህራኖች ጋር የሴት ተማሪዎችን ጊዜ በማመቻቸት ጫናውን ለመቀነስ ስትሞክር ቆይታለች። ከተማሪዎች ጋር በመነጋገር መምህራኖችን በማሳመንም ሰርታለች። የፈተና ስኬጁል በጣም ሲቀርብም ስኬጁሉን ከሚያዘጋጁት ጋር በመነጋገር ቀኖች እንዲያራዝሙላቸው ታደርግ ነበር። ተወካይ መሆኗ በግሏ በዚህ መልኩ ጠቅሟታል። ሌሎች እንደ እሷ ጫና ያለባቸውን ሴቶችም መጥቀሙን ማስተዋል ችላለች።
እኛ ሴቶች በተለይ በትዳርና በሥራ ዓለም ከገባን በኋላ በሚገጥሙን ድርብርብ ኃላፊነቶች መማር እስከፈለግንና እስከሚገባን እንድንማር በማድረግ በኩል የትዳር አጋሮቻችን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።
የኔ ባለቤት አቶ አማኑኤል ደስታ በዚህ በኩል የአንበሳውን ድርሻ በመወጣቱ ዛሬ ትምህርቴን በተገቢው መንገድ በመከታተል 3 ነጥብ 53 አጥጋቢ ውጤት አምጥቼ ለመመረቅ በቅቻለሁና እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ ያለችን ደግሞ ተመራቂ ተማሪ ሳራ ወልደአማኑኤል ናት።
ሳራ እንደነገረችን የመጀመሪያ ዲግሪዋን በዚሁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽን ሲስተም በመያዝ ነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀለችው። ሳራ የሶስት ልጆች እናትና ባለ ትዳር ነች።ባለቤቷ አቶ አማኑኤል ደስታ ጎልታ እንድትወጣ ይረዳት ነበር። ትምህር ቤት ገብታ ሁለተኛ ዲግሪዋን እንድትይዝ በጣምም አበረታቷታል። እሱ ስለረዳኝም ነው የተማርኩትና የጨረስኩት የምትለው ሳራ በአንድ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ እንደምትሰራም አጫውታናለች።
የምትሰራው ሥራ ብዙ መስክ የሚያስወጣ ባይሆንም ቢሮ ውስጥ ፋታ አይሰጣትም። ትምህርቷን በርቀት ትምህርት መርሐ ግብር ስትከታተል የነበረችውም ለዚህ ነው። ቲቶርያል ክላስ መከታተሉ፤ ሙጁል ማንበቡ እጅግ ሰፊና የተረጋጋ ጊዜ የሚፈልግ ነበር። በዚህ ላይ የዋናው ፈተና ሰሞን የመጨረሻ ልጇን ልትወልድ መቃረቧ ጫናውን ከማክበድ አልፎ እመረቃለሁ የሚለውን ተስፋዋን አጠራጣሪ አድርጎባት ነበር። ከዚህ ጋር ቢከብዳትም ባለቤቷ ልጆቻቸውን መከታተሉን ጨምሮ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን ስለሸፈነላት ልትወጣው ችላለች። ትምህርቱን ኮቪድ ከመግባቱ ከአንድ ዓመት በፊት መጀመሯን የምታወሳው ሳራ፤ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀሙ ትምህርታቸው ሳይቋረጥ በየቤታቸው ሆነው እንዲከታተሉ ማስቻሉንና በእሷ ላይ የሚደርሰውን ጫና በእጅጉ የቀነሰላት መሆኑን ታወሳለች።
በባለቤቷ እገዛና በእርሷ ጥንካሬ ዛሬ ላይ ትምህርቷን አጠናቅቃ ለምረቃ በቅታለች ። ይሄ ጥሩ ውጤት ነው።ከእግዚአብሄር እርዳታ ጋር ባለቤቴ ደግፎኝ ጨርሻለሁ።ትምህርት የመለወጥ መሣሪያ ነው። የተማረች ሴት መሆን ከራስ ጀምሮ ለቤተሰብና ለአገር ትልቅ ጥቅም አለው። በመሆኑም የሚፈልጉትን ያህል በትምህርት ሳይገፉ እንደ እሷ በሥራ፤በትዳርና ልጅ የተጠመዱ ሴቶች የፈለገውን መስዋእትነት ከፍለው መማር እንዳለባቸውም ትመክራለች። ሴቶች ሲማሩ የነሱን ያህል የተማሩትም ሆነ ያልተማሩት የባለቤታቸው ድጋፍ ከሌላቸው ስኬታማ አይሆኑም።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ቅዳሜ በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉልን መልዕክት እንዳሉት፤ መማር ማለት የባህርይ ለውጥ ማምጣት ነውና የትዳር አጋሮች እባካችሁ ሚስቶቻችሁን እንደ እኔ ባለቤት ሁሉ በማገዝ ለውጤት አብቁ የሚል መልዕክቷን በማስተላለፍ አስተያየቷን አሳርጋለች ተመራቂዋ ሳራ።
የ72 ዓመታት ዕድሜ ባለፀጋ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዕለተ ቅዳሜ ሐምሌ 9/2014 ዓ.ም ካስመረቃቸው 5 ሺህ 58 ተማሪዎች መካከል የሴት ተማሪዎች ቁጥር ቀላል ባለመሆኑ ይበረታታል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ ካሉት ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዲሁም ከዚህ ቁጥር ውስጥ 40 በመቶ ከሆኑት የድህረ ምረቃ ተማሪዎች መካከል 33 በመቶው ሴቶች መሆናቸውም ሴቶች በከፍተኛው ትምህርት መስክ በዚህ ዘመን እምርታ እያሳዩ መምጣታቸው አመላካች ነው።
በሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2014