ከ12 ዓመታት ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።ይሁን እንጂ ባንኮቹ በቁጥር ከሚጨምሩና በተበታተነ ሁኔታ ከሚንቀሳቀሱ ተዋህደው አቅም ቢፈጥሩ የሚል ሃሳብ በአንድ ወቅት የውይይት መድረክ ተፈጥሮ ነበር። በወቅቱ ውህደቱን የሚደግፉም የማይደግፉም ነበሩ። ጉዳዩ ከሃሳብ አልዘለለም።
በዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ከምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርገናል።እንግዳችን በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ምክርቤት ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል፤ አሁን ደግሞ የአፍሪካ ንግድ ምክርቤት ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ክቡር ገና ናቸው፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– ባንክን ማን እንደሚመሰርትና አስፈላጊነቱን ቢገልጹልኝ?
አቶ ክቡር፡- ባንኮች በግል ነው የተጀመሩት፤ የብዙ ሀገሮች ታሪክም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው። አገልግሎታቸውም ገንዘብ በማስቀመጥና በመመለስ ብቻ ነበር። በኋላ ነው አገልግሎቱ እየሰፋ የመጣው። በኢትዮጵያም ጅምሩ ተመሳሳይ ነው።
ባንክ ለመመስረት ደንቦችና ህጎች አሉ።በጋራም በቡድንም ሊቋቋም ይችላል። በአንዳንድ ሀገር ከሀገሩ ውጭ የሆኑ፣በሌሎች ደግሞ ተባብረው የሚሰሩበት ሁኔታ አለ። እንደየሀገራቱ አመሰራቱ ይለያያል። ባንክ የመንግስትና የግል የሚባለው የባለቤትነት ድርሻው ነው የሚወስነው። ይሄ አሰራሩ ክፍት መሆኑን ያሳያል።
ባንክ በብዙ መልኩ አስፈላጊ ነው። ሰው ገንዘቡን ወይም ወርቁን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ማስቀመጥ ይፈልጋል። ለሥራ ገንዘብ የሚፈልግም የብድር አገልግሎት ለማግኘት ይረዳዋል። የባንክ ሥራ በአሁኑ ጊዜ ተራቅቋል።
ባንኮች እራሳቸው ገንዘብ ፈጣሪዎች ሆነዋል። ችግሩ አስቀማጮች አንዴ መጥተው ገንዘቤን አምጣ ቢሉት ባንኩ ገንዘብ የለውም። ሁሉም ባንኮች አሰራራቸው ተመሳሳይ ነው። በአንዴ የሚጠይቅ አስቀማጭ አይኖርም በሚል እሳቤ በመስራት ነው በንግድ ኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ሚናቸውን የሚወጡት።
አዲስ ዘመን፡–የባንክ ሥራ ሲጀመር በግል ነበር። በኋላ ደግሞ በመንግሥት ይዞታ ስር ሆነ። መልሶ የግል ባንኮች እየተስፋፉ ነው እዚህ ላይ ሃሳብ ቢሰጡ።
አቶ ክቡር፡-በመንግሥት ይወሰናል። ያሳለፍነው የደርግ መንግሥት ፖሊሲ እንደባንክ ያሉ ትላልቅ ድርጅቶች በሀገሪቷ ውስጥ አስፈላጊነታቸው አልታመነባቸውም። ባለሀብት የሚለውን ወደ ህዝብ የመለወጥ አሰራር ነበር።ባንኩም የህዝብ መሆን አለበት በሚል የመንግሥት ሆኖ ማገልገል አለበት ከሚል ፍልስፍና አቅጣጫ ነው እርምጃ የተወሰደው።በዓለም ላይ ግን አብዛኛቹ ባንኮች የግል ናቸው።የመግሥት ጥቂት ናቸው።
ከአገልግሎት ጥቅማቸው አንጻር ሲታይ ግን የመንግሥት ባንክ ሆነው የሚሰሩት በልማቱ ላይ አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። የግል ባንክ ትርፉን ለግሉ ነው የሚያውለው። የመንግሥት ደግሞ የሚያገኘውን ትርፍ መልሶ ለሀገር ልማት ነው የሚያውለው።ለዚህ ነው የመንግሥት ባንክ ከግሉ በተሻለ ለሀገር ይጠቅማል የሚባለው።
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ የባንክ አሰራር በመንግሥት ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ነው?
አቶ ክቡር፡-አዎ ማለት ይቻላል። የመግንሥት የፖሊሲ አቅጣጫና ፍልስፍና አንዳንድ የንግድ ዘርፎች ለግል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የመንግሥት ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል። አሁን ያለው የሀገሪቱ መንግሥት ለግል ዘርፎች ከፈቀዳቸው አንዱ የግል ባንክና ኢንሹራንስ ነው።
ለዚህም ነው ዛሬ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና ኢንሹራንሶች የተስፋፉት። በምን መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ብሄራዊ ባንክ ኃላፊነትተሰጥቶታል። ብሄራዊ ባንክ የመንግሥትንም ገንዘብ ይይዛል። የባንኮችንም ገንዘብ ያስቀምጣል። ባለቤት ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– የመንግሥት ባንክ ትርፍ ለልማት፣የግሉ ደግሞ ለራሱ መልሶ የሚጠቀም ከሆነ የግል ባንኮች መኖራቸው ፋይዳው ምንድነው?
አቶ ክቡር፡-ጥሩ ጥያቄ ነው።የግል ባንኮችን ከመንግሥት በተሻለ ተመራጭ የሚያደርጋቸው አገልግሎት አሰጣጣቸው ነው። አዳዲስ አገልግሎት ሥራ ላይ ለማዋል ፈጣኖች ናቸው። በቅልጥፍና ከመንግስት ባንኮች ይበልጣሉ። በመንግሥት ባንኮች ይሄ አይስተዋልም።
በህዝብ አገልጋይነት ግን የመንግሥት ባንኮች ይበልጣሉ።ትርፍም ባያገኝ መንግሥት የኢትዮጵያ ጠረፍ ድረስ ሄዶ አገልግሎት ይሰጣል።የግሉ ትርፉን መሰረት አድርጎ ነው የሚንቀሳቀሰው። አንድ የማይካደው ነገር መንግሥት የሚሰራው ለህዝብ በመሆኑ ግዴታም ኃላፊነትም አለበት።
አዲስ ዘመን፡– የግል ባንኮች ከቅልጥፍና የዘለለ ጥቅም የላቸውም ማለት ነው?
አቶ ክቡር፡-መንግስት መጨረሻ ዓመት ላይ ሂሳቡን አስልቶ ትርፉን መልሶ የመንግሥት ካዝና ውስጥ ነው የሚያስገባው። የግሉ ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ለባለድርሻዎቹ ጋር ያከፋፈላል። ትርፍ ተካፋዮቹ ገንዘባቸውን ለግል ጉዳያቸው ነው የሚያውሉት። የግሉና የመንግሥት ሲመዘኑ ልማቱን ማነው የሚያመጣው ሲባል ሊያከራክር ይችላል። ይህ ሲባል ለልማት የሚያውሉ የሉም ማለት አይቻልም።
አሜሪካን ሀገር ኖርዝ ካሮናላይና ውስጥ አንድ የግል ባንክ አለ። ባንኩ አትራፊና በተሻለ ገንዘቡን ለኖርዝ ካሮናይላ ነዋሪና ለአካባቢው እድገት በማዋል ይጠቀሳል። ንጽጽሩ ከግልና ከመንግሥት በአብዛኛው ለልማት በማዋል ረገድ የሚል በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የግል ባንኮች በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ያላቸው ሚና እንዴት ይታያል?
አቶ ክቡር፡-በሀገሪቷ የግል ባንኮች በቁጥርና ተደራሽ በመሆን እየተስፋፉ ነው። የግል ባንኮች ባይኖሩ የመንግሥት አሁን በሀገሪቷ ያሉትን ቅርጫፎች ሁሉ መክፈት ይችል ነበር የሚለው ያነጋግራል። የግል ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመራቸው የባንክ አገልግሎት እንዲሰፋ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የግል ባንክ መኖሩ ለኢትዮጵያ ዕድገት ተጨማሪ ጉልበት ሰጠ እንጂ የጎደለ ነገር የለም። የሥራ ዕድልም ፈጥረዋል።
ክርክሩ ልማትን ለማምጣትና ለማፋጠን የግሉ ወይንስ የመንግሥት ባንክ ይሻላል የሚለው ነው። ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ብንወስድ በቢሊዮን ነው የሚያተርፈው። 30 በመቶ በላይ ገበያውን ተቆጣጥሮታል። 60 በመቶ ለግሉ ዘርፍ ነው የተሰጠው። ትርፉን መልሶ ለመንግሥት ወይም ለህዝብ ነው የሚያውለው።ለልማት ነው ቦታ የሚሰጠው።
ከዚህ አንጻር የግሉ ህዝባዊ ልማት ይኖረዋል ማለት ያስቸግራል። የግል ፍላጎቱን ለማሟላት ነው ቅድሚያ የሚሰጠው። የግሉ ባንክ ለባለድርሻዎቹ ነው የሚያከፋፍለው። ለምሳሌ አንድ ባንክ አንድሺ ባለድርሻ ቢኖረውና ኢትዮጵያ ውስጥ 10 ባንኮች ቢኖሩ ትርፉ ለስንት ሰው ነው የሚሄደው።የትኛው ነው ልማታዊ? መገመት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– የመንግ ሥት ባንኮች ሚና የጎላ ከሆነ የግሎቹ አስተዋጽኦ እንዴት ይታያል?
አቶ ክቡር፡- መግባባት ያለብን የግል ባንኮች ልማት አያመጡም ማለት አይደለም። ልማት ያመጣሉ። ቅርጫፎች በማስፋት የሚሰጡት አገልግሎት ሰው ገንዘቡን እንዲያስቀምጥና የብድር አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል።
በሚሰሯቸው ሥራዎች ሳይሆን የሚያገኙትን ትርፍ ልማት ላይ በማዋል ነው የእነርሱን ለየት የሚያደርገው። በእኔ እምነት ብዙ የኢትዮጵየ ንግድ ባንክ ቢኖር ኢትዮጵያ ታድጋለች። ይሄን ስል ግን የግሉ ዘርፍ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡
አዲስ ዘመን፡–በዚህ ረገድ የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ምን ይመስላል?
አቶ ክቡር፡-የተወሰኑ ሰዎች ጋር ሀብት እንዲሰበሰብ ያደረገ ዓለም ነው። 90በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ብዙ ገንዘብ የለውም። አንድ በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ያለው ዓለምን ያስተዳድራል ይባላል። በጣም ትንሹን ሰው ነው እያስደሰተ እና እያጎለበተ ያለው።
እስከመቼ ይቀጥላል? አይታወቅም። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ቀደም ሲል እንዳልኩት 60 በመቶ የሀገሪቷን ገበያ የተቆጣጠሩት ቁጥራቸው ወደ 30 የሚሆኑ የግል ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ናቸው። ለ60 በመቶ ገበያ የሚሰጡት አገልግሎት እንዳለ ሆኖ የተጠቃሚው ወይም ቤቱ ገንዘብ ይዞ የሚሄደው ከ20ሺ አይበልጥም።
አዲስ ዘመን፡–የባንኮች መብዛትስ ጥቅም አለው?
አቶ ክቡር፡-በገበያ ይወሰናል። ባንክ ሲበዛ አገልግሎቱ የተሻለ ይሆናል የሚሉ አሉ። በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ከጎረቤት ሀገር ኬንያ ጋር እንኳን ሲነጻጸር ኋላቀር ነው።ብዙ መስራት ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የግል ባንኮች ብዙ የሚባሉ ናቸው?
አቶ ክቡር፡-ቁጥራቸው 16 አካባቢ ናቸው፤ በዝተዋል አያስብልም።
አዲስዘመን፡– ባንኮቹ እንዲዋሃዱ በአንድ ወቅት ሃሳብ ተነስቶ ነበር ምን ይላሉ?
አቶ ክቡር፡-አቅም አለመኖር የባንኮቹ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቷም አቅም የላትም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የካፒታል አቅም ደካማ ነው። ሀገሪቷ ውስጥ ያሉት ባንኮች የሚሰበስቡት ካፒታል አነስተኛ ስለሆነ ካፒታል ለማሳደግ ደግሞ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ መፍትሄ ነው ።
ቢዋሀዱ የሚለው ሃሳብ አሁን ያለው የካፒታል መጠናቸው ደካማ ስለሆነ ጠንካራ ባንኮች እንዲሆኑ ነው። ይሄ ለህዝቡ ዋስትና ይሰጣል። እኔ የማስቀምጥበት ባንክ ካፒታል አለው። በቀላሉ ላይፈርስ ይችላል የሚል መተማመን ይፈጥራል።
አስታውሳለሁ የኢትዮጵያ ባንክ ሲጀመር በ10ሚሊዮን ካፒታል ነበር። ዛሬ ደግሞ 10 ሚሊዮን ብር የአንድ መኖሪያቤት ዋጋ ሆኗል። እና አስፈላጊነቱ ከታያቸው የማይዋሀዱበት ሁኔታ የለም።
አዲስ ዘመን፡– የግል ባንኮች ይወሃዱ የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት የለውም ማለት ነው?
አቶ ክቡር፡-የካፒታል ምንጭ ማሳደግ ነው መፍትሄው። እኔ በግሌ የምሰጠው ሃሳብ ግን ሃምሳ እና አንድ መቶ ሰዎች ተሰብስበው የግል ባንክ ከሚያቋቁሙ እያንዳንዱ ክልል የራሱን ባንክ ቢያቋቁም የተሻለ ነው። የራሱን ባንክ ሲያቋቁም የራሱን ቅርጫፍ ያቋቁማል። ይህ ደግሞ የራሱን ልማት እንዲያካሂድ ያግዘዋል። እና የክልሉ ህዝብ ተሰባስቦ የሚያቋቁመው ባንክ የተሻለ ውጤት ያመጣል የሚል ሃሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ክቡር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
በ ለምለም መንግሥቱ