ያልሰለጠነ ፖለቲካ በበሃሪው የእኔ…የእኔ ማለትን ስለሚወድ በሀሳብ ልእልና ሳይሆን በጉልበት አሸንፎ መውጣትን፤ በሴራ ጠልፎ የመጣልን መንገድ ይከተላል። ፖለቲከኞች መተዳደሪያቸው ሕገእግዚአብሄር ሳይሆን ሕገመንግሥት ነው። በመሆኑም ላይተዳደሩበት ሕግ ያረቅቃሉ፣ ሕግያሻሽላሉ፣ መልሰው ራሳቸው ያወጡትን ሕግያፈርሳሉ። ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞችን እንደታዘብናቸው ትኩረታቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አድርገው ግላዊ ፍላጎታቸውን ያስቀድማሉ።
የስልጣኔ ቁንጮ ተብላ በምትጠራው አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ፖለቲከኞች በንግግራቸው መጨረሻ ‹‹God bless America›› እግዚአብሄር አሜሪካን ይባርክ ይላሉ። ፖለቲካው በቅጡ ባልሰለጠነባቸው ሀገራት የሚኖሩ ፖለቲከኞች ግን ምድራዊውን እንጂ ሰማያዊውን ዓለም ብዙም ስለማይናፍቁት ይመስላል ለሞራልና ለሃይማኖታዊ እሴቶች ግድ የላቸውም፤ ለህሊና ዳኝነትም አይገዙም። አንዳንዶቹ እንደውም የትጥቅ ትግል ውስጥ ገብተው በሰበበ ፖለቲካ መለኮታዊ ሕግጋትን እየጣሱ ያልታጠቁና ጉዳዩ የማይመለከታቸው ንጹኃን ወንድሞቻቸውን ይጨፈጭፋሉ።
ሃይማኖት መተዳደሪያው ሕገ- እግዚብሄር ስለሆነ ፍቅርን፣ መቻቻልን፣ አንድነትን፣ መደጋገፍንና መተዛዘንን ይሰብካል። አንዱ ለተቸገረ ወንድሙ እንዲደርስ ያስተምራል። ሕገ- እግዚአብሄር፤ ሰዎች ይቅርባይ፣ እርቅን ተቀባይና ሰላም ወዳድ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ግድያን፣ጥላቻን፣ ዘረኝነትን፣ ወገንተኝነትን፣ በዳይነትንና ግፍአድርጊነትን ያወግዛል።
አንድ የፖለቲካ ቡድን የሚከተለው አስተሳሰብ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ ይሁንም አይሁንም፤ በአንድ ሀገር የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የእርሱ ሀሳብ ብቻ ገኖ እንዲታይ ይፈልጋል።በተለይም ተቀራርቦ የመነጋገርና የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረባቸው ሀገራት እንዲህ አይነቱን ችግር መመልከት የተለመደ ነው።
በሊቢያ፣ በየመንና ሶሪያ የተከሰቱት የእርስ በርስ ጦርነቶች መነሻቸው ብዙ ውጪያዊ ጉዳይ ቢኖረውም እስካሁን መፍትሄ ማግኘት ያልቻለው የእኔ ፖለቲካዊ መስመር ትክክል ነው፤ የእናንተ የተሳሳተ ነው ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው።
ተቀራርቦ በመነጋገር ሀሳቦችን ማስታረቅ እየተቻለ የአንድ ሀገር ዜጎች በሁለትና ሶስት ጎራ እየተከፋፈሉ አላስፈላጊ ጦርነት በማድረግ ለበርካታ ንጽኃን ዜጎቻቸው እልቂትና ለኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት ሲሆኑ መመልከት ክፉኛ ያስቆጫል። ማስቆጨት ብቻ ሳይሆን ሰው ሆነን የመፈጠራችንንና ከፍጡራን ሁሉ ተለይቶ የተሰጠንን የማሰብ ጸጋ እንድንጠራጠር ጭምር ያደርጋል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ በየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ውስጥ ያሉና መለኮታዊ ትዕዛዝ አድርገን የተቀበልናቸውን አትግደል፣ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፣ እናትና አባትህን አክብር ወዘተ የሚሉትን ሃይማኖታዊ እሴቶች ሸርሽሮብናል፤ አርክሶብናልም።
በሰበበ ፖለቲካ ፈጣሪ የማይወደው ሥራ በሰው ልጆች ላይ ሲፈጸም እያየን፤ ያለነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ወይስ ሌላ ሀገር? እስከማለት ደርሰናል። በሰው ሀገር ሲፈጸሙ እየሰማን ስንገረምባቸውና ስናዝንባቸው የነበሩ የጭካኔ ተግባራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ተደጋግመው ሲከሰቱ እያየ ግራ ያልተጋባ ኢትዮጵያዊ አለ ማለት አይቻልም።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ስልጣን መልቀቁን ተከትሎ ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ለማስገባት ያልፈነቀለው ድንጋይ አለመኖሩ ይታወቃል። በጥቂቶች የግል ፍላጎትና በፖለቲካ አሻጥር ምክንያት በዚህ አራት ዓመት ውስጥ ከፖለቲካ ጋር ምንም አይነት ንክኪ ሳይኖራቸው ያለምንም ጥፋታቸው የተጨፈጨፉትን ንጽኃን ዜጎች ቤቱ ይቁጥራቸው።
ቡድኑ አንዳንዴ በቀጥታ አንዳንዴም በእጅ አዙር ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግፍ የፈጸመባቸውና ያስፈጸመባቸውን፣ የገደላቸውና ያስገደላቸውን ዘርዝረን አንጨርሳቸውም።
በኢትዮጵያ ላይ የተለያየ ጥቅምና ፍላጎት ባላቸው የውጭ ሃይሎች እየተደገፈና እንዳለውም ከሲኦል መልዕክተኞቹ ጋር እየተባበር የሰውልጅ በሰው ልጅ ላይ ይፈጽማቸውል ተብለው የማይገመቱ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈፅሟል፤ አስፈጽሟል።
በተለይም ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በጋራ እንደሚሠሩ በይፋ ካወጁ በኋላ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እሳት እየጫሩ ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያንን ጨፍጭፈዋል። በቅርቡ በወለጋ ማንነታቸውን መሰረት አድርጎ በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ምናልባት በአገራችን ታሪክ ፋሺስት ጣሊያን አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ያደረሱበትን ጥቃት ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማና በደብር ሊባኖስ ገዳም የፈፀመውን ጭፍጨፋ የሚያስታውስ ነው።
ሰላማዊ ትግል እንዲያደርግ ጥሪ ተደርጎለት ከነ ሙሉ ትጥቁ ወደ ሀገር ቤት የገባው የኦነግ ሠራዊት መቀሌ ላይ ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ለውጡን ለማደናቀፍ ተማምሎ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ለራሱ ‹‹ሸኔ›› የሚል አዲስ መጠሪያ በመስጠት ማንነትን መሰረት ያደረጉና ለጆሮ የሚሰቀጥጡ፤ ለአይን የሚዘገንኑ ጭፍጨፋዎችን በንጹኃን ዜጎች ላይ አካሒዷል። ይህ ሁሉ ግፍና ሰቆቃ የግለኝነት፣ የጥቅመኝነት፣ የዘረኝነት፣ የጨለምተኝነት ወዘተ አስተሳሰቦች መገለጫ ቢሆንም ሰበቡ ፖለቲካ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት ሞቼለታለሁ የሚለውንና ብዙኃኑ ድምጽ ሳይሰጥበት ያጸደቀውን ሕገመንገሥት ሳይቀር እየሻረ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የማይፈቅዱትን ግፍ በሰው ልጆች ላይ ፈጽሟል። የእርሱ ደቀ መዝሙር የሆነው ሸኔም ተልእኮ እየተቀበለ በሚሠራው ሰይጣናዊ ሥራ ‹‹ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ›› አስብሎናል።
ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ሶስት ሺ ዓመታት በሕገ መንግሥት መተዳደር የጀመረችባቸው ዓመታት ቢታሰቡ ጥቂት ናቸው።አባቶቻችን ሕገመንግስት ጽፈው መተዳደሪያ ደንብ ከማወጃቸው በፊት በሕገ ልቦና እና በሕገ እግዚአብሄር የቀረጹት ተውልድ ቅን፣ ሩህሩህ ስርቆትን፣ ግፍንና በደልን የሚጠየፍ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የተላበሰ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየትኛውም ሃይማኖት ጥላ ስር ይኑር ዛሬም ድረስ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያለውና ሕገመንግሥት ባይኖረውም በሕገ እግዚአብሄርና በሕግልቦና ስሪቱ ብቻ መኖር የሚችል ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጸሙ ይቅርና ይፈጸማሉ ተብለው ሊታሰቡ የማይገባቸው የጭካኔ ተግባራት ተፈጽመው ሲታይ ከየት ተነስተን ወደየት እየሄድን ነው የሚል ስጋት ፈጥሮብናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካን ምክንያት አድርጎ እየተፈጸመ ያለው ኢሰብዓዊ ድርጊት እጃችንን አፋችን ላይ ያስጫነን አሳፋሪ ተግባር መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የነበርንን ክብርና ስም ያጎደፈና ያዋረደንም ጭምር ነው።
ሰው የሚያስብ ፍጡር እንደመሆኑ ከየትኛውም ሕግ በላይ ተገዢነቱ ለህሊናው መሆን አለበት። ሆድ ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለጤናማ ሰውም መልካም ሥራን መሥራት የህሊና እርካታ ይሰጠዋል። ማዘን፣ መርዳት፣ መተባበር፣ መደገፍ ከሰው ልጆች ልብ የሚፈልቁ ቅን አስተሳሰቦች ናቸው። እነዚህ በተፈጥሮ የተጎናጸፍናቸው ጸጋዎቻችን ሕገመንግሥትን ከማክበር በላይ ሰው የመሆናችንን ምስጢር የምንገልጽባቸው ተፈጥሯዊ ባህሪዎቻችን ናቸው።
መጥፎ ነገርን የማንሠራው ሕግን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯችን ስለማይፈቅድልን ነው። ሕገልቦና አንቀጽና ቁጥርን ሳይጠቅስ በሠራነው መጥፎ ሥራ ሰው መሆናችንን እስከምንጠላ ድረስ በህሊና ጸጸት ይቀጣናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ከክፋት የራቀ የልቦና ወቅር ስላለን በመጥፎ ድርጊታችን ምክንያት የሚሰማንን የጸጸት ስሜት መሸክም የሚያቅተን ለዚህ ነው። በእርግጠኝነት ሰውን የገደሉ ሰዎች የአዕምሮ ሰላም አያገኙም፤ ዘመናቸውን ሁሉ በጸጸት አለንጋ እየተገረፉ ይኖራሉ። ከዚህ ምድር ሲያልፉም ሰማያዊውን ጸጋ እንወርሳለን የሚል ተስፋ አያደርጉም።
ሰው ከሕገልቦናው ቢያፈነግጥ እንኳ ሰማያዊ ፍርድን በመፍራት ወይም የጽድቅ አክሊልን ለመቀዳጀት በማሰብ ሕገእግዚአብሄርን ወይም ሕገፈጣሪን ያከብራል፤ ለዚህም ፈጣሪ ለሰው ልጅ የሰጣቸውን መተዳደሪያ ደንቦች በተግባር ሊኖራቸው ይጥራል። ግፈኞች፣ ጨካኞችና ፈሪሃ እግዚአብሄር በውስጣቸው የሌላቸው ሰዎች ግን ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪያቸውም ጋር የተጣሉ ናቸው።
እያንዳንዱ ሃይማኖት የየራሱ አስተምህሮ አለው። ነገር ግን ፈጣሪ በታላቅ ጥበብ የፈጠረውን የሰው ልጅ ‹‹መግደል›› ሀጽያት መሆኑን ሁሉም ሃይማኖቶች ይስማሙበታል። ንጽኃንን ካልጨፈጨፉ ትግል ያደረጉ የማይመስላቸው ታጣቂዎች ሕገመንግሥትን ሳይሆን ሕገእግዚአብሄርን የሚፈራ ልብ እና አስተዋይ ህሊና ስላልተሰጣቸው የሰውን ነፍስ ለማጥፋት ይሽቀዳደማሉ። እንደ ሃይማኖታችን አስተምህሮ ፍርድ ይጠብቃቸዋል። ወየውላቸው ለነፍሰ ገዳዮች።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም