መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ከሚያደርገው ድጋፍ አንዱ የመስሪያና መሸጫ ቦታ (ሼድ) በአነስተኛ ክፍያ ማመቻቸት ነው። በመሆኑም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል አፍርተው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩትን አስመርቆ በሦስት ዙሮች ለፋብሪካ ግንባታ የሚውል ሰፋፊ ቦታ ሰጥቷል። ከእነዚህም ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚሰሩ ‹‹ወበራ›› እና ‹‹ኤም.ቲ.ኤፍ›› በሚል ስያሜ የሚጠሩ ማህበራት የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች ናቸው።
ማህበራቱ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ግንባታ ቢያከናውኑም አስፈላጊው መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ሥራ መጀመር አልቻሉም። ‹‹መንግሥት ኃላፊነቱን ሳይወጣ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የምንጠቀምበትን የመስሪያ ቦታ (ሼድ) ከሁለት ወር በፊት መጥተው በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ ልቀቁ ተባልን፤ በመሆኑም ዕቃችን ላይም ታሸገብን፤›› ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ወበራ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባል አቶ በርሄ አስፋው እንደገለጹት ሦስት የማህበሩ አባላት በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተሰጣቸው ሼድ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች እያመረቱ ሲሸጡ ቆይተዋል። መንግሥት ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ እስኪሸጋገሩ ድረስ ሲደግፋቸው መቆየቱንና ከተሸጋገሩ በኋላም አስመርቆ ለፋብሪካ ግንባታ የሚውል ሁለት ሺ 500 ካሬ ሜትር ቦታ በመስጠት ከፍተኛ
ድጋፍ ማድረጉን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ላይ ከተረከቡት ሁለት ሺ አምስት መቶ ካሬ ሜትር በሰባት መቶ ካሬ ሜትሩ ላይ ግንባታውን አከናውነዋል። ይሁን እንጂ ከ175 ማህበራት መካከል 53ቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመሟላቱ በገነቡት ፋብሪካ ውስጥ መስራት አለመቻላቸውን አስረድተዋል።
‹‹መንግሥት መሠረተ ልማቱን ቢያሟላልን ሼድ ውስጥ ለአንድ ቀንም ለመቆየት ፍላጎት የለንም። ሰፊ ቦታ እያለ በጠባብ ቦታ ላይ መስራት ምርጫችን አይደለም›› የሚሉት አቶ በርሄ ሼድ ማሸግ መፍትሄ እንዳልሆነም ይናገራሉ። ሼዱ ለሁለት ወራት በመታሸጉ የጀመሩት ሥራ ከደበኞቻቸው ጋር እንዳጋጫቸውና ሠራተኞቻቸውም እየተበተኑባቸው እንደሆነ አመልክተዋል።
የኤም. ቲ. ኤፍ. ፈርኒቸር ማኑፋክቸሪንግ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሊጶስ ጴጥሮስ በ2005 ዓ.ም ተመርቀው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸውንና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ቀርሳ በሚባል ቦታ 1000 ካሬ ሜትር ቦታ እንደተሰጣቸው ይገልጻሉ። ገና በግንባታ ላይ ሆነው ከመስሪያ ቦታቸው ልቀቁ መባሉ አግባብ እንዳልሆነ የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ በአንደኛና በሁለተኛ ዙር የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ተመሳሳይ ችግር እያጋጠማቸው ያሳለፉ መሆኑ አሠራሩን የተለመደ እንዳደረገው ያስታውሳሉ።
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ኃይሌ እንደገለጹት፣ ከመስሪያ ቦታ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ቅሬታ ይነሳል። ‹‹በተለይ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ማፍራታቸው ብቻ መታየት የለበትም። የግንባታ ወጪያቸው ከፍተኛ ነው፤ የብድር አገልግሎት ሳይመቻችላቸው ግንባታ እያከናወኑ በመሆኑ የኢንተርፕራይዞቹ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል፤›› ብለዋል።
‹‹የመስሪያ ቦታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ለኢኮኖሚ ማነቃቂያ፣ ኢንተርፕራይዞችን መፍጠሪያ እንጂ አንድ ኢንተርፕራይዝ ለዘመናት እንዲቆይበት አይደለም። አንድ ኢንተርፕራይዝ ከአምስት ዓመት በኋላ ለቆ ለተተኪው ማስረከብ አለበት›› ሲሉ ምላሽ የሰጡት ደግሞ በሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ የመስሪያ ቦታ ልማት አስተዳደር ኃላፊ አቶ አስመሮም ብርሃኔ ናቸው።
ኢንተርፕራይዞቹ ከበቂ በላይ ተጠቃሚ እንደሆኑና ለተተኪዎች መልቀቅ እንዳለባቸው ይገልጻሉ። እንደ እርሳቸው አባባል ቅሬታቸው ሕጋዊነት የለውም። መስሪያ ቦታ መከራየት፤ አለያም ጀነሬተር የመጠቀም አማራጭ አላቸው የሚሉት አቶ አስመሮም የከተማ አስተዳደሩ ያፀደቀው የመስሪያ ቦታ አጠቃቀም መመሪያን ይጠቅሳሉ።
‹‹ድጋፍ ገደብ አለው፤ ለዓመታት ጊዜ ቢሰጣቸውና እንዲወጡ ቢጠበቁም ቅሬታቸውን በተለያየ ቦታ በማቅረብ እስከ ዛሬ ቆይተዋል። ቅሬታ በማቅረብ በሼድ ውስጥ መቆየት የሚፈልጉ ናቸው፤ ሃሳብ ማስቀየር የለመዱ ናቸው። መጠቀም ከሚገባቸው በላይ ከቆዩ ኢንተርፕራይዞች 151፣ አዲስ ደግሞ 213 የመስሪያ ቦታዎች በሥልጠና ላይ ለሚገኙ ለተተኪዎች ዝግጁ ተደርገዋል። በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይለቁት ደግሞ ንብረታቸውን ሊያወጡ ይገባል፤›› ብለዋል አቶ አስመሮም።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ ያሲን ከአቶ አስመሮም የተለየ ሃሳብ አላቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ከጥቃቅንና አነስተኛ ሀብት አፍርተው ወደ መካከለኛ የተሸጋገሩት ሼድ እንዲለቁና ፍትሐዊ አሠራር ለማስፈን የሚደረገው እንቅስቃሴ ተገቢነት ቢኖረውም የተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች የእነርሱ ችግር ባልሆነ ጉዳይ ሼድ ልቀቁ መባሉ ችግር ውስጥ የሚገቡት እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ሀብትም ያለውጤት ይቀራል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ፣ በመንግሥት ችግርና የኃይል አቅርቦቱም በወቅቱ ባለመድረሱ ክፍተት ተፈጥሯል። ኢንተርፕራይዞቹ ችግሩን ለብቻቸው ሊሸከሙ አይገባም የሚሉት አቶ አብዱራዛቅ ሌላ ሥራ ያለውን ለማምጣት ከአምስት ዓመት በላይ የተለፋባቸውን ማጣት አይገባም ይላሉ።
ሕግ ማስከበር ተገቢ ቢሆንም ለጉዳት መዋል የለበትም ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ምክክር ተደርጎ የኃይል አቅርቦቱ እስኪሟላ ድረስ ባሉበት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አመልተዋል። ቢሮው ለአምራች ዘርፎቹም ይሄንኑ የማሳወቅ ሥራ መስራቱን ገልጸዋል። ኃይል የማሟላቱ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
በ ለምለም መንግሥቱ