ቡና ለአገር የኢኮኖሚ ዋልታ በመሆን ይታወቃል፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከሚጠቀሱ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ባለፉት ዓመታትም ይሁን ዘንድሮ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታና ማገር በመሆን የላቀ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በተለይም አገሪቷ የውጭ ጫናዎችን ተከትሎ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ባለውለታነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የዛሬው የስኬት አምዳችንም ቡና ባስመዘገበው ስኬት ላይ አድርጓል።
መንግሥት ለቡና ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ ከቡና እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሬ በየአመቱ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚም ትርጉም ባለው መንገድ እየደገፈ ይገኛል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም፤ አገሪቱ ለአመ ታት ከቡና የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን የቆየች ስትሆን፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ለውጦች እየታዩ መጥተዋል። ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ገቢ ግብርና 20 በመቶውን የሚሸፍን ሲሆን፣ ከግብርና ምርቶቸም ቡና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡
የቡናና ሻይ ባለስልጣን መረጃዎች እንደያስረዱት፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እየሆነ መጥቷል፤ ከቡና ምርት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግም ቡና አምራች በሆነው አርሶ አደር ላይ ሰፊ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻለችበት ሚስጥር
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት በታሪኳ አይታው የማታውቀውንና ታሪካዊ የሆነውን ድል በቡናው ዘርፍ መቀዳጀት ችላለች፡፡ ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለውም በቡናው ዘርፍ መሰረታዊ የሚባሉ ለውጦችን ማምጣት በመቻሉ ነው፡፡
ባለስልጣኑ በዚህም በ2013/14 ዓ.ም በመጀመ ሪያው ወር ላይ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት በዕቅድ ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡ በተለይም የውጭ ንግዱን ለማሳለጥ በቡና ልማቱና በግብይቱ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ተለይተው እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ በቁርጠኝነት ወደ ሥራው መግባት በመቻሉም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የቡና ገበያ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ በአስር ወራት ብቻ አንድ ቢሊዮን 14 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡/ ይህ አሀዝ በበጀት አመቱ መጨረሻ አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ደርሷል/ ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ባለበት ከቡና ብዙም ተጠቃሚ ሳትሆን ለቆየች አገር ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ገበያ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች መካከል ቡና በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በ2014 በጀት አመት ከቡና የተገኘው የውጭ ምንዛሬ አስር ወራት ውስጥ ብቻ አገሪቷ አጠቃላይ በውጭ ገበያ ካገኘችው ገቢ ጋር ሲነጻጸር 30 በመቶ የሚሆነውን መሸፈን ችሏል፤ ከግብርናው ዘርፍ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 50 በመቶ ያህሉን ሸፍኗል፡፡
ይህን ውጤት ለማስመዝገብም ባለስልጣኑ ከሠራቸው በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መካከል በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ ማውጣት አንዱና ቀዳሚው ነበር፡፡ በተለይም በቀጥታ ትስስር አርሶ አደሮችና አቅራቢዎች ምርታቸውን በቀላሉ መቀባባል እንዲችሉ በማድረግ ረጅም ርቀት መጓዝ ውስጥ ተገብቷል፡፡
ጥራቱን የጠበቀ ቡና በመጠን እንዳይባክን አርሶ አደሮች ለአቅራቢዎች፤ አቅራቢዎች ደግሞ በቀጥታ ለላኪዎች ማስረከብ እንዲችሉና ላኪዎችም ዱካውን ተከትለው መለየትና ማወቅ እንዲሁም ምርቱን ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸው ስርዓት ተዘርግቷል፤ ይህም የኢትዮጵያ ቡና በተሻለ ዋጋ በዓለም ገበያ እንዲሸጥና ዳጎስ ያለ ገቢም እንዲገኝ አስችሏል፡፡
በቡናው ዘርፍ የተሰማራ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል በቁርጠኝነት መስራት በመቻሉ የተገኘ ውጤት ስለመሆኑም የባለስልጣኑ ኃላፊዎች ይገልጻሉ። በተለይም በግብይት ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ለኤክስፖርቱ ማነቆ ሆነው የቆዩ አሰራሮችን በመፈተሽ በማስተካከልና የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በሶፍትዌር በመከታተል ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። ቡና ጭነው ከመንገድና ከመስመር የሚያወጡ ባለሃብቶች እንዲሁም አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የኮንትሮባንድ መጠኑ እንዲቀንስና ቡና ወደ ዓለም ገበያ በቀጥታ እንዲገባ ተሠርቷል፡፡ በተጨማሪም እምነት በመፍጠር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተሰራው ሥራ ለተመዘገበው ውጤት የጎላ ድርሻ አለው፡፡
ያለፉት ሁለት አመታት አፈጻጸም
ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ላይ ለዓመታት ሲታይ የነበረውን የቁልቁለት ጉዞ ከመግታት አልፋ አዲስ ታሪክ አስመዝግባ ነበር። ይህ ታሪክ ከተመዘገበባቸው መካከል ደግሞ ቡና አንዱ ነው። በጀት ዓመት 248 ሺህ 311 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 907 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቷን ባለስልጣኑን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህም ገቢ በ2009 ዓ.ም ከተገኘው 882 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ የ25 ሚሊየን ዶላር ብልጫ ነበረው። ያለፈውም አመት ኢትዮጵያ በታሪኳ ከቡና ምርት ከፍተኛ የተባለውን የውጭ ምንዛሪ ያገኘችበት ነው፡፡
የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድና አፈጻጸም
በ2014 በጀት አመት ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመጠንም ሆነ በገቢ ሪከርድ መስበር ተችሏል። በበጀት ዓመቱ ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት የተላከው 300 ሺ ቶን ቡና ሲሆን፣ በዚህም አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡
299 ሺ 340 ነጥብ 13 ቶን ቡና ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ 299 ሺ 314 ነጥብ 32 ቶን መላክ ተችሏል። ከዚህም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል። ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 51 ሺ 002 ነጥብ 66 (20.54%) እና በገቢ ደግሞ በ488 ነጥብ 14 ሚሊየን ዶላር (53.82%%) ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት አስራ ሁለት ወራት የተላከው ቡና በመዳረሻ አገራት ሲታይ ደግሞ ጀርመን በመጠን 63,499.74 ቶን (21%) ድርሻ እና በገቢ 250.88 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር (18%) ድርሻ፣ አሜሪካ በመጠን 28,834.33 ቶን (10%) ድርሻ እና በገቢ 177.17 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር (13%) ድርሻ፣ እና ሳውዲ አረቢያ በመጠን 44,676.00 ቶን (15%) ድርሻ እና በገቢ 176.52 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር (13%) ድርሻ አፈፃፀም በማስመዝገብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን በገቢ አስመዝግቧል፡፡
የተቀሩት በ2014 በገቢ ቅደም ተከተል 4ኛ ቤልጅዬም፣ 5ኛ ጃፓን፣ 6ኛ ደቡብ ኮሪያ፣ 7ኛ ቻይና፣ 8ኛ ጣሊያን፣ 9ኛ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና 10ኛ ታይዋን ናቸው፡፡ ከ1 እስከ 10 ያሉት በአጠቃላይ በመጠን 80 በመቶ እና በገቢ 81 በመቶ ይሸፍናሉ።በጥቅሉ የእነዚህ ዋና 10 መዳረሻ አገራት ከ2013 አፈፃፀም ጋር ሲወዳደር በመጠን 26 በመቶ እና በገቢ 59 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የኤክስፖርት ግቡን ለማሳካት
የኤክስፖርት ግቡን ለማሳካት ባለስልጣኑ በተለይም ለቡና ኤክስፖርተሮችና አቅራቢዎች የብድር አቅርቦት እንዲመቻች በማድረግ ከባንኮች ጋር በመነጋገር አፋጣኝ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ የቡና ኤክስፖርት ሂደትን ለማሳለጥ እና የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የተሻለ የውጪ ምንዛሬ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በኮንቴነር አቅርቦት፣ በምድር ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ እና በአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት ባለስልጣኑ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡
በዓለም አቀፍ ኢግዝቢሽኖች (በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በዱባይ) እና በበይነ መረብ በሚካሄዱ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያ ቡና እንዲተዋወቅ ተደርጓል፤ አዳዲስ ገበያን በማፈላለግ በኩል በኤሽያ አገሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሰርቷል። በዚህም ቻይና እና ታይዋን ወደ አስር ዋና ዋና ገዥ አገራት ተርታ እንዲገቡ ሆኗል፡፡
ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ እና አገራዊ የገበያ መረጃዎችን በማደራጀት እና በመተንተን በቡና ኮንትራት መረጃ በመሰብሰብ፣ ዝቅተኛ ዋጋን በመተንተን ማሰራጨት ተችሏል፡፡ የመረጃ ጥራትን ከማሳደግ እንዲሁም የቡና ግብይት ቁጥጥርን ዘመናዊ ከማድረግ አንጻር የቡና መረጃ ዳታ ቤዝ እና የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ለመዘርጋት በታቀደው መሰረት ከሽኝት ጣቢያዎች በየዕለቱ የሚሸኝ ቡና በሲስተም እንዲደገፍ የማድረግ ሥራም ሰርቷል፡፡
ግብይቱን ለማዘመንና ቁጥጥሩን ለማጠናከር የዳታ ቤዝ ሶፍት ዌር እና በ13 አገልግሎት ዘርፎች የኦንላይን ለደንበኛ አገልግሎት በመስጠቱ ግብይቱ እንዲሳለጥ ሆኗል፡፡ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ሥራም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ለሶስተኛ ጊዜ በአገሪቱ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ጥራት ውድድር ተካሂዷል፡፡ ውድድሩም በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስተባባሪነት በተሳካ ሁኔታ መካሄድ ችሏል፡፡
የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በዘርፉ በተለይም በግብይት ስርዓት ውስጥ የነበሩ ችግሮችና የተለያዩ ማነቆዎችን ነቅሶ ማውጣት ተችሏል፤ ይህን ተከትሎም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለእዚህም ባለስልጣኑ የተለያዩ አሰራሮችንም መከተሉን ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ግብይት እጅግ በጣም የተንዛዛና ምንም እሴት የማይጨምሩ በርካታ ተዋንያኖች የነበሩበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ይህንን የግብይት ሥርዓት በማሳጠር ምርቱን በቀጥታ ከአርሶ አደር ወደ አቅራቢ ከአቅራቢ ደግሞ ወደ ላኪ በመድረስ ሲባክን የነበረውን የቡና ምርት በመጠንና በጥራት መታደግ ተችሏል ይላሉ፡፡
ስለሆነም ዘንድሮ ወደ ውጭ ገበያ በተላከው ቡና ካለፈው አመት በመጠን 52 ሺ ቶን ቡና ብልጫ ተመዝግቧል። የጥራት ደረጃዎቻቸውንም ከፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ቡና በተሻለ ዋጋ ለዓለም ገበያ እንዲሸጥ ተደርጓል፡፡ ሌላው የቡና ሽኝትን አስመልክቶ ቡና ከወረዳ እስከ ቡና ላኪ መጋዘን ማድረስ የሚያስችል ሶፍትዌር በማበልጸግ መከታተል ተችሏል፡፡ ይህም የህገወጥ ንግድን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አስችሏል፡፡ በዚህም በህገወጥ መንገድ ከአገር ይወጣ የነበረውን ቡና ወደ ስርዓቱ እንዲገባ ማድረግ መቻሉም ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል፤ በወጪ ንግዱ መጠን ላይም ከፍተኛ የሆነ የመጠን ጭማሪ ማሳየት አስችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት መቶ ሺ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡ ይህ ውጤት መመዝገብ የቻለው ቅንጅታዊ በሆኑ አሰራሮች ምክንያት እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አዱኛ፣ ውጤቱን ለማስቀጠል ብሎም የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በዋናነት የተዘረጉ የአሰራር ስርዓቶችን በማጠናከር ከቴክኖሎጂ ጋር በማዛመድ እንደሚሠራና በዚህም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የት ቦታ ላይ እንደሚያስፈልጉ መለየቱን ጠቅሰው፣ በተለይም ቡና አቅራቢና ላኪው በኦን ላይን እየተቀባበሉ ግብይቱን ግልጽነት ባለው መንገድ ማከናወን የሚያስችል የአሰራራ ስርዓት ተዘርግቷል ይላሉ። ነባርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ባለፈው ዓመት እንደ ክፍተት የታየውን ችግር በማጥራት በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅቱ መጠናቀቁንም ነው ያስታወቁት፡፡
በቀጣይ ዓመትም ሶስት መቶ ሃያ ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ባለድርሻ አካላት በተመዘገበው ውጤት ሳይዘናጉ ከባለስልጣኑ ጋር በመሆን ቅንጅታዊ አሰራሮቻቸውን አጠናክረው በማስቀጠል የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የደረሰውን የአገሪቱን ዓመታዊ የቡና ሽያጭ ገቢ፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ግብ ማስቀመጡን ሪፖርተር ጋዜጣ በቅርቡ ዘገቧል፡፡
በቡናና ሻይ ባለስልጣን ቴክኖሰርቭ በተባለ የጥናት ተቋምና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ድጋፍ የተዘጋጀው የቡና የ15 ዓመት ስትራቴጂ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ ስትራቴጂው ከምርት እስከ ግብይት ያለውን የአገሪቱን የቡና አሁናዊ እንቅስቃሴና በቀጣይ ዓመታት ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት የሚያመላክት ነው፡፡
በቡናና ሻይ ባለስልጣን የግብዓት አቅርቦትና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ገዛኸኝ ዋቢ ያደረገው ዘገባው እንዳመለከተው፤ በስራ ላይ የቆየው ስትራቴጂ ከአጠቃላይ ግብርና ጋር ተዳብሎ ሲሠራበት የቆየ ሲሆን፣ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ለቡና ራሱን የቻለ የቡና ስትራቴጂ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከስትራቴጂው ዓምዶች አንዱ የሆነው ልማት ሲታይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በሔክታር የሚገኘው የቡና ምርት ከዓለም ጋር ሲገናኝ በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ካልተቻለ ሌሎቹን የስትራቴጂው ዓምዶች ማሳካት እንደማይቻል ተናግረዋል። ስለሆነም የተዘጋጀው ስትራቴጂ ምርትን በተመለከተ አጽንኦት መስጠቱን እንደሚያመለክት ተጠቁሟል፡፡
በስትራቴጂው ከተቀመጡ ግቦች ውስጥ ከቡና ኤክስፖርት አገሪቱ ከአምስት ዓመታት በኋላ ዓመታዊ ገቢዋ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል የሚል ዕቅድ ተቀምጧል። ስትራቴጂው በዚህ ወቅት ይፋ ይደረግ እንጂ ከላዩ ላይ እየተቀነሰ ተግባራዊ መደረግ የጀመሩ የተለያዩ ተግባራት ሁለት ዓመታት ማስቆጠራቸው ተጠቁሟል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014