በብዙ የተከፋ ሰው በሆነው ባልሆነው ሆድ ይብሰዋል። ለበጎ ያሉት እንኳ ለክፋት ይመስለውና ይበልጡኑ ይከፋል። ከብዙ መከፋትና መገፋት በኋላ የሚመጣው ሆድ መባስ ደግሞ ነጭናጫና ፍጹም ተጠራጣሪ ያደርጋል። “የተከፋ ተደፋ “ እንዲሉ ታድያ ዛሬ በብዙ የተከፋው ህዝብ ሆድ እየባሰው ነጭናጫና ፍጹም ተጠራጣሪ ሆኗል። በዙሪያው የከበቡት ችግሮችም ለቁጥር በዝተዋል። አንዱን ሲለው ሌላው፤ ሌላውን ሲል ደግሞ ሌላ እየተናደ ሆድ መባሱና መከፋቱ በዝቷል።
ላለፉት በርካታ ዓመታት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው በሕዝብ ላይ ብዙ በደሎችን ሲያደርሱ የነበሩና ሆድ ያስባሱ አካላትና አሰራሮቻቸውን ቆጥረን አንዘልቀውም። ዛሬም በብዙ ትግልና የሕይወት መስዋዕትነት የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል በብዙ የሚተጉ እንዳሉ ሁሉ የጭቃ ውስጥ እሾ ሆነው ሕዝብን ሆድ የሚያስብሱ ስለመኖራቸው ዕለት ዕለት የሚሰሙ አሳዛኝና አናዳጅ ዜናዎች ምስክሮች ናቸው።
የሰው ልጅ በሕይወት ለመኖር ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ፍላጎቶቹ መካከል መኖሪያ ቤት አንዱ ነው። እንደአለመታደል ሆነና በእኛ አገር ይህን መኖሪያ ቤት ለማግኘት መንገዱ ረጅምና አድካሚ ነው። በማያልቀውና አድካሚ በሆነው ረጅሙ መንገድ ብንጓዝ፤ ብንጓዝ ጫፍ መድረስ አይታሰብም። ዕድል ቀንቶን ጫፍ ብንደርስም እንኳ ነገሩ ሁሉ ‹‹…ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ›› አይነት የልጅ ጨዋታ ይሆናል። ይህ ደግሞ ከመከፋትም በላይ ያስከፋል፤ ሆድ ያስብሳል፤ አመኔታን ያሳጣል።
በተለይም ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣ በርካታ አሻጥሮች ከሚሰሩባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል የቤቶች ልማት አስተዳዳር አንዱ ነው። የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ያውም የጋራ መኖሪያ ቤት ‹‹ኮንዶሚኒየም›› ለአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄ ከሆነ ሁለት አስርት አመታትን ሊደፍን ምንም ያህል አልቀረውም። በእነዚህ ሁሉ አመታት ታድያ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ከጠንካራ ሐሜት ጋር ያስተናገደው ይኸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኤጀንሲ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› እንዲሉ ከ30 አባወራ በላይ ሊይዝ የሚችል ሙሉ የጋራ መኖሪያ ቤት ህንጻ ከነነብሱ ጠፍቶበት እንደነበር እናስታውሳለን።
አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ህንጻ ከነነብሱ መጥፋት የአንድ ሰሞን ሐሜት ሆኖ ቢያልፍም በዕጣ አወጣጡ የሚደረጉ መጭበርበሮችን ጨምሮ ስለመዘረፉ፣ ለሆኑ ቡድኖችና አካላት ስለመተላለፉና በቤተዘመድ ሳይቀር ያልተመዘገቡ አካላት የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል የሚሉ ሐሜቶች የአንድ ሰሞን ጉርምርምታ ሆነው ሳይጣሩ ቀልጠዋል። ችግሩ ዛሬም ቀጥሎ ደሃው ህዝብ አልበላም አልጠጣም በማለት እየቆጠበ በብዙ ተስፋ ከሚጠባበቀው ደሃ ሰርቆ ህዝቡ ሆድ እንዲብሰው ማድረግ እጅግ አሳፋሪና ነውር ነው።
መኖሪያ ቤት ማግኘት የሰማይ ያህል በራቀበት አገር ለአስራ ሰባት ዓመታታ በትዕግስትና በተስፋ መጠበቅ በራሱ አስገራሚ ነው። ከአፉ ጥሬ ነጥቆ መቆጠብ ሲጨመርበት ደግሞ አስገራሚ ከመሆን አልፎ የሕዝቡን ጨዋነት ቢያስመሰክርም ትዕግስቱንም የሚፈታታን ነው። ያም ቢሆን ግን ዛሬ ከትናንት በእጅጉ ይለያል።
አንደኛ ከዚህ ቀደም በማጉረምረም ይሰማ የነበረው ማጭበርበር ዛሬ በገሃድ ሌብነት እንደሆነ መስማት ተችሏል። የጋራ መኖሪያ ቤት መጭበርበሩ ከሐሜት በዘለለ በመረጃ ተደግፎ የዜና ሽፋን ማግኘት በራሱ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደማለት ነው። ሌላ የተለየው ነገር ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ የችግሩን መከሰት አምኖ ይቅርታ መጠየቁ ነው።
“አካፋን አካፋ ዶማንም ዶማ” እንዲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ‹‹ሌባን ሌባ በሉት›› በማለት ለሌባ ሽፋን እንዳይሰጥ ፈቃድ ሰጥተዋል። በዚህ መሰረት ከተማ አስተዳዳሩ መረጃውን በግልጽ ከመስጠት ጀምሮ ጥፋተኛውን ተጠያቂ ለማድረግ እየሄደበት ያለው ርቀት ሆድ ለባሰው ህዝብ ፈጣን ምላሽ መስጠት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሊያስመሰግነው የሚገባ ጉዳይ ነው።
እርግጥ ነው ከተማ አስተዳደሩ ከሰሞኑ ያወጣውን 14ኛው ዙር የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ አወጣጥ ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ እንዲሆን የበኩሉን አድርጓል። ያም ሆኖ ግን ስህተት ከተፈጠረ የማጣራት ሥራ እንሠራለን ብሎ ቃል በገባው መሰረት እነሆ ተፈጠረ የተባለውን ውዥንብር ሊያጠራ ፈቃደኝነቱን ከሙሉ ፍላጎት ጋር እያሰየ ይገኛል። ታድያ ቴክኖሎጂውንም የሚያለማው የሰው እጅ እንደመሆኑ በቴክኖሎጂ ስም የሚሰሩ አሻጥረኞችንም አለመጠራጠር አይቻልምና ሁሉን አቀፍ ማጣራት ቢሆን መልካም ነው።
ህዝቡ በስስትና በጉጉት የሚጠብቀውን የጋራ መኖሪያ ቤት ከእጁ ላይ መዝረፍ ከሌብነትም በላይ ሌብነትና ወራዳነት ነው። ጥሬ ቆርጥሞ መቀነቱን ፈትቶ የሚቆጥበው፤ የነገ ተስፋውም ጭምር የሆነው የጋራ መኖሪያ ቤትን መቀማት ማለት የህዝቡን የደረቀ ቁስል ጭርሱን እንዳይሽር መገሽለጥ ነው። የጋራ መኖሪያ ቤት ጉዳዩ ለዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መዝለቁ ደግሞ ከማንም በላይ በተስፋና በጉጉት የሚጠባበቀውን ህዝብ ሆድ የሚያስብስ ነው።
ሆድ ለባሰው… እንዲሉ ታድያ ህዝቡ በተለያዩ ጉዳዮች በተለይም በሰላምና ጸጥታ፤ በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ባለበት በዚህ ወቅት የምጥ ያህል ተጨንቆና ተጠብቦ የሚያገኘውን ጠብታ ዕድል ማክሸፍ የጭካኔ ጥግ የታየበት ጭካኔ ነው። የተከፋ ተደፋ ሆነና ነገሩ በኑሮ ውድነት እየተናጠ በሰላምና ጸጥታ ስጋት እየተሸበበ ለዓመታት በከፍተኛ ትዕግስት የጠበቀውን ተስፋ ማጨለም ሆድ ከማስባስም በላይ በመንግሥትና በህዝቡ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክርና አመኔታን የሚያሳጣ ነውና በብርቱ ሊወገዝ ይገባል።
ነገን ተስፋ አድርጎ በብዙ እየተፈተነ ያለው ህዝብ መሸሻ መድረሻ ሌላ አገር የለውም። ያለው አንድ አገር ናትና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆን እንፍቀድ። ዛሬ በዳታና በዕጣ አወጣጥ መጭበርበር ምክንያት የበርካቶች ደስታ ውሃ ተቸልሶበታል። ያም ቢሆን ተስፋ መቁረጥ ብሎ ነገር አይታሰብም፤ ነገን ተስፋ በማድረግ ዛሬም ነገም ሌቦችን መሞገትና ማጋለጥ የእያንዳንዱ ዜጋ ተግባር ቢሆን መልካም ነው።
“ዕውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እንዲሉ ከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን የማጣራት ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል መረጃውን በጉጉት ለሚጠብቀውና ሆድ ለባሰው ተስፈኛ ህዝብ በፍጥነት ያሳውቅ። የሚያሳውቀውም ለዘመናት በከፍተኛ ጉጉትና ስስት ሲጠባበቅ የኖረውንና ድንገት በህገወጦች የተነጠቀውን ሀቅ ከእጁ ለማስገባት እንጂ ሆድ ለማስባስ እንዳይሆንም እምነታችን ነው።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም