አብሽጌ ወረዳ በጉራጌ ዞን ውስጥ ካሉ ወረዳዎች አንዱ ነው። ወረዳው በ29 ቀበሌዎችና በሦስት ማዘጋጃ ቤቶች የተዋቀረ ነው። አብዛኛው የወረዳው ቀበሌዎች ከዞኑ መዲና ወልቂጤ ከ42 እስከ 60 ኪሎ ሜትር እንደሚርቁ ይነገራል። ወረዳው የራሱ ማዕከል የሌለው ሲሆን የወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ሁሉም የወረዳው ሴክተር መስሪያ ቤቶች መቀመጫ ወልቂጤ ከተማ ነው። ይህም የወረዳውን ሕዝብ ለአላስፈላጊ እንግልትና ወጪ ሲዳርግ ቆይቷል።
በአብሽጌ ወረዳ ዳርጌ ከተማ ቀበሌ 26 ነዋሪ አቶ በየነ ግርማ እንደተናገሩት፤ ቀበሌያቸው ከዞኑ መዲና ወልቂጤ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ወልቂጤ ከተማ ለመግባት የቀቤና ወረዳን አልፈው ይሄዳሉ። ማዕከሉ ወልቂጤ ላይ በመሆኑ እሳቸውና ቤተሰባቸው ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረጉ ቆይተዋል።
ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ተዳርገዋል። ጉዳይ ለማስፈጸም አልጋ ተከራይተው ለማደር የተገደዱበትን ወቅት ያስታውሳሉ። በርቀቱ ሳቢያ ሕዝብ ፍትህ ለማግኘት ፍትህ አካላት ጋር መሄድ እንዲያቆም ምክንያት ሆኗል።
መኪና ቢገኝ እንኳ ወልቂጤ ደርሶ ለመመለስ በጣም ከባድ መሆኑን የሚናገሩት አቶ በየነ፤ ከወልቂጤ ደርሶ ለመመለስ ከተፈለገ እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት በመኪና መጓዝ ግድ እንደሚሆን ይናገራሉ። የማዕከሉ እና የነዋሪዎች መራራቅ ለግብርና ሥራቸው ጭምር እጅግ ፈታኝ ሆኖባቸዋል።
እንደ አቶ በየነ ማብራሪያ የወረዳ ማዕከል ጥያቄ መቅረብ ከጀመረ ሰንብቷል። የክልልና የዞን አመራሮች የወረዳ ማዕከል እንደሚቋቋም ተደጋጋሚ ቃል ቢገቡም እስካሁን አልተሳካም
ብለው፤ ነገር ግን ጥያቄው ለምን ተነሳ በሚል ቂም ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አልቀረበም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመቅረፍና ወረዳው የራሱ ማዕከል እንዲኖረው ለማድረግ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋቁሟል። የሕግ ባለሙያና የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘካሪያስ ዮሐንስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ሁሉም ጽሕፈት ቤቶች ያሉበት ወልቂጤ ከተማ የወረዳው ሕዝብ ካለበት አብሽጌ ወረዳ ቢያንስ የ47 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረግ መቆየቱን ይናገራሉ። በዚህም ለተለያዩ ለኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ተዳርጓል ይላሉ።
የወረዳ ጽሕፈት ቤቱ በወልቂጤ ከተማ በመሆኑ ሕዝቡ አገልግሎት ፈልጎ ወደ ወልቂጤ በሚመጣበት ወቅት ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ መሆኑን ይናገራሉ። ሕዝቡ አላስፈላጊ የትራንስፖርት ወጪ ለማውጣት ተገዷል። ወልቂጤ ከተማ ከደረሰ በኋላ እንኳን ጽሕፈት ቤቱ ያለበትን ቦታ ስለማያውቅ አገልግሎት ሳያገኝ የሚመለስበት አጋጣሚ የበዛ ነውም ሲሉ ያብራራሉ።
የወረዳው ሕዝብ የተለያዩ የመልካም አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንዳሉት የሚናገሩት አቶ ዘካሪያስ አመራሮችና ባለሙያዎች ከሕዝቡ ርቀው በመኖራቸው ምክንያት የወረዳውን ሕዝብ ችግር መረዳት እንኳ አልቻሉም ይላሉ።
እንደ አቶ ዘካሪያስ ማብራሪያ፤ የወረዳው አስተዳደር በወልቂጤ ከተማ ጽሕፈት ቤቶችን ተከራይቶ አገልግሎት መስጠቱ በወረዳው ሕዝብ ላይ እያስከተለ ካለው ጉዳት ባሻገር የወረዳውንም አስተዳደር ለአላስፈላጊ ወጪ እየዳረገው ነው። የተወሰኑ ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ለቢሮዎች ኪራይ የወጣው ወጪ ቢሰባሰብ የወረዳውን ጽሕፈት ቤቶች ለማስገንባት ያስችላል ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የወረዳው ማዕከልና አመራሮቹ አብዛኛው ሕዝብ ወደሚገኝበት አካባቢ ቀርበው አገልግሎት መስጠት አለባቸው የሚል ጥያቄ ማንሳት ከጀመረ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኖታል ያሉት አቶ ዘካሪያስ፤ የመንግሥት ኃላፊዎች ግን የተለያዩ ምክንያቶችን በመጠቀም በተለይም የሚቋቋሙ ኮሚቴ አመራሮችን በማስፈራራት፣ በማሰር፣ በገንዘብና በሥልጣን በመደለል የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዳያገኝ ሲያደርጉ ቆይቷል ይላሉ። በዚህም ምክንያት የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል።
ከ2010 ዓ.ም ወዲህ በሀገሪቱ ውስጥ የታየውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የሕዝቡ የዓመታት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አዲስ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚገልጹት አቶ ዘካሪያስ፤ የተቋቋመው ኮሚቴ ጥያቄው የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ለሚመለከታቸው አካላት በተጨባጭ ለማሳየት የሕዝብ ድጋፍ ማሰባሰቡን ተናግረዋል። የመንግሥት አካላትም ጥያቄው ተገቢ መሆኑን አምነውበታል ብለዋል።
በሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል የሚመራ ልዑካን ቡድንም በቦታው በመገኘት ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ ቃል መግባታቸውን አቶ ዘካሪያስ ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ዘካሪያስ ማብራሪያ፤ የተገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥ የተጀመረ እንቅስቃሴ ግን የለም። የወረዳ ማዕከል ለማቋቋም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመጀመሩ በሕዝቡ ዘንድ ቁጣ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። ‹‹ግብር አንከፍልም›› የሚሉና መንገድ የመዝጋት እርምጃዎች ተወስደዋል። በሕዝቡ ዘንድ የተቀሰቀሰውን ቁጣ ተከትሎ የዞኑ አስተዳዳሪ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፤ አቶ ዘካሪያስ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንደሚፈታም ቃል መግባታቸውን በመግለጽ።
የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ ጀማል እንደተ ናገሩት፤ የአብሽጌ የማዕከል ጥያቄ በዞኑ ውስጥ ካሉ ጥያቄዎች መፍትሄ ከሚሹ ጥያቄዎች አንዱ መሆኑ ታምኖበታል። የወረዳው ሕዝብ ጥያቄ ሲመለስ ግን ሌላው ሕዝብ ላይ ቅሬታ እንዳይፈጥር በጥናት መመለስ አለበት ይላሉ። ጥያቄው በጥናት መመለስ እንዳለበት ከሕዝቡ ጋርም ከስምምነት ተደርሷል። ወልቂጤ የአብዛኛውን ወረዳ ሕዝብ ያማከለ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭምር በጥናት ይመለሳል ብለዋል።
ተቋም የሚቋቋመው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ስለሆነ አብዛኛው ሕዝብ በመረጠበትና ባማከለ ቦታ ላይ ማዕከል ይቋቋማል ያሉት አቶ መሀመድ፤ ሕዝቡ መደመጥ ስላለበት ከመላው የወረዳው ሕዝብ ጋር ውይይቶች ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ለውይይት ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አንስተዋል። በሚደረጉ ውይይቶች የወረዳው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ወልቂጤ በመሆናቸው ያጋጠሙ ችግሮች እንደሚዳሰሱ ተናግረዋል።
እንደ አቶ መሃመድ ማብራሪያ ሕዝቡ ያቀረበውን የማዕከል ጥያቄ ምክንያት በማድረግ መንገዶች ተዘግተው ነበር። መንገዶች በመዘጋታቸው ገበያ እንዲስተ ጓጎልና ሕዝቡ የደህንነት ስሜት እንዳይሰማው አድርጓል። ጥቂት አመራሮች ምላሽ አልሰጡም ብሎ የሕዝብና የመንግሥት መንገድ መዝጋት ሕገ ወጥ መሆኑን ከመግባባት ተደርሷል።
መንገዶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ከሕዝብ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የቀረበው የማዕከል ጥያቄ መንገድ በመዝጋት ሳይሆን በጥናትና በውይይት የሚመለስ መሆኑን ከሕዝቡ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል። ሕዝቡም ዳግም መሰል ሕገ ወጥ ተግባር ላለመፈጸም ቃል ገብቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
በመላኩ ኤሮሴ