ኢትዮጵያ የማዕድን ልማቱ በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ የሚያስችል የሚያሰራ ፖሊሲ እና አዲስ አደረጃጃት አዘጋጅታ እየሰራች ትገኛለች። በአስር አመቱ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሪ እቅድ ላይም ዘርፉ ከአምስቱ የእድገት ማእዘኖች አንዱ ተደርጓል።
ዘርፉን በማልማት በአገሪቱ የሚካሄደውን ልማትም እንዲደግፍ ማድረግ ይገባል። የኃይል አቅርቦት ችግር በስፋት ላለበት ኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰል አንድ አማራጭ መሆኑ ይገለጻል። አገራችን የድንጋይ ከሰል ሀብት አላት። የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያጋጥማቸውን የድንጋይ ከሰል ግብአት አቅርቦት ችግር ለማቃለልና ተያያዥ ተግባራትን ለማከናወን የማእድን ልማቱ ወሳኝ ነው። ከዚህ አኳያም እየሰራ ነው።
ይህን ተከትሎም ወጣቶች የድንጋይ ከሰል እያመረቱ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እያቀረቡ ይገኛሉ፤ ልማቱን ከዚህም በላይ በማሳደግ ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ማእድን ሚኒስቴር ይገልጻል። ይህን ለማድረግ ግን በልማቱ የሚሳተፉ አካላትን በፋይናንስ፣ በስልጠናና በቴክኖሎጂ አቅርቦት መደገፍ ግን ያስፈልጋል።
በአገራችን ወርቅ በባህላዊ እና በዘመናዊ መንገድ በስፋት ይመረታል። ወርቅ በባህላዊ መንገድ በስፋት ከሚመረትባቸው ክልሎች አንዱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው። በተያዘው በጀት አመት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ በባህላዊ መንገድ 22 ኩንታል ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማስገባቱን አስታውቋል። ይህን ያህል መጠን ያለው ወርቅ ማግኘት የተቻለው በሁዋላቀር መሳሪያዎች በመጠቀም ነው። ከዚህም ማእድን እየተመረተ ያለበት ሁኔታ ሁዋላ ቀር መሆኑን እንረዳለን። አምራቾቹን ከእዚህ አይነቱ የአመራረት ስርአት ማውጣት አገርንም ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል።
በአጠቃላይ የማእድን ዘርፉ ከባህላዊ አመራርት እንዲወጣ፣ ከወቅቱ የአለም ሁኔታ ጋር እንዲራመድ፣ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲያድግ፣ ተወዳዳሪም እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የማእድን ሚኒስቴር ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለመስራት የጀመረው እንቅስቃሴ ከዚህ አኳያ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
የማእድን ሚኒስቴር አንዳንድ ድጋፎችን እያደረገ ቢሆንም፣ ከልማቱ አስፈላጊነት አኳያ ድጋፉ ይበልጥ መጠናከር ይኖርበታል። ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ግንዛቤያቸው አንዲያድግ፣ ዘመናዊ አመራረትን አንዲከተሉ ለማድረግ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ለወርቅ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ማእድናት ልማትም ያስፈልጋል።
በአገሪቱ በርካታ ማእድናት እንዳሉ ይገለጻል። ማእድናቱ የት የት ስለመኖራቸውና በምን ያህል መጠን ያሉ ስለመሆኑ ብዙም መረጃ አይገኝም። የማእድን ሚኒስቴር በቅርቡ ካስመረቀው የማእድን ሙዚየም ብዙ መረጃዎችን ማግኘት ቢቻልም፣ ማእድናት ላይ ጥናት ማድረግ ግን አስፈላጊ ነው። ለእዚህ ሁሉ የመንግስትና የሌሎች የልማት አጋሮች ድጋፍ ሚና ከፍተኛ ነው።
እንደ ተፈጥሮ ጋዝ፣ ድንጋይ ከሰል ያሉት ማእድናትም እንዲለሙ የመንግስትና የልማት አጋሮች ሚና ወሳኝ ነው። የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ ማዕድን ሚኒስቴር ሰሞኑን አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሆኑት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ አፍሪካ ልማት ባንክ፣ የኔዘርላንድ ልማት ባንክና የፈረንሳይ ልማት ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉን በድረገጹ ማስነበቡ ይታወሳል።
በተለይም የጂኦተርማል የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ ከተቋማቱ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል። በውይይቱ የገንዘብ ሚኒስትሩን አቶ አህመድ ሽዴን ጨምሮ የአለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ከመሳሰሉ የተለያዩ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና አጋሮች ጋር በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላትን አቅም በተመለከተም ለፋይናንስ ተቋማቱ ተወካዮች ገለጻ እንደተደረገላቸውና የፋይናንስ ተቋማቱ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የማዕድን ፕሮጀክቶችን ለማገዝ እንዲሁም የማዕድን የግል ክፍለ ኢኮኖሚን በፋይናንስ ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውንም ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል።
ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማቱ በዚህ ደረጃ ዘርፉን ከሚመራው ተቋምና ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጋር መነጋገራቸው ለዘርፉ እድገት አንድ ተስፋ ነው። ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የተደረገውን ምክክር መነሻ በማድረግ ውይይቱ ለማዕድን ዘርፉ እድገት የሚኖረውን ፋይዳ የምጣኔ ሀብትና የፖሊሲ ተንታኝ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ ትንታኔ እንዲሰጡን ጋብዘናቸዋል።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በትንታኔያቸው እንዳሉት፤ በቅኝ ግዛት ሥር የቆዩ በርካታ የአፍሪካ አገራት ያላቸው የማዕድን ሀብት በጥናት ተለይቶ የተቀመጠ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ ግን በዚህ ደረጃ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የማዕድን ሚኒስቴርንም ሆነ የምርምር ማዕከል ድረገጾችን ለማየት ሞክረው ወርቅና ውስን የሆኑ የማዕድን አይነቶችን ካልሆነ በስተቀር አጠቃላይ በጥናት የተደገፈ መረጃ ማግኘት አልቻሉም።
እንደ አገር በተደራጀ ሁኔታ የማዕድን ሀብት መረጃ ባለመኖሩ በመጠንም ይሁን በአይነት ያለውን ሀብት ደፍሮ ለመናገር ያስቸግራል። በዚህ ረገድ ተሰርቶ ቢሆን ዜጋውም ቢሆን በቀላሉ ለማወቅ ያስችለዋል። ስለሀብቱ እውቀት ሲኖረው ደግሞ ጥበቃና እንክብካቤ ያደርጋል። ከዘርፉ ገቢ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረትም የተሻለ ያደርገዋል።
ከማዕድን ዘርፍ አንዱ የሆነውን የተፈጥሮ ጋዝ (ካሉብ ጋዝ) አንድ የአሜሪካ ኩባንያ ጋዙንም ነዳጁንም ለማውጣት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር በ1960ዎቹ ላይ በመንግሥት መረጃዎች ሲሰጡ ነበር። ይሁንና ኩባንያ ብዙም ሳይቆይ ገበያው አዋጭ አይደለም ብሎ ሥራውን ጥሎ ወጥቷል። በወቅቱ አንድ በርሜል ጋዝ በሶስት ብር ሂሳብ ነበር የሚሸጠው።
በተለያየ ጊዜ በመጡ መንግሥታትም በዘርፉ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልታየም። አሁንም የቻይና ኩባንያዎች ጋዙን ከመሬት ውስጥ አውጥተውና ጅቡቲ በመውሰድ ወደ ፈሳሽ ቀይረው ወደ ቻይና ለመውሰድ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር መረጃዎች ቢኖሩም በውጤት ደረጃ ግን የተገለጸ ነገር የለም።
የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ናፍጣና ጋዝ በመቀየር ለአውሮፕላን ነዳጅም ሆነ ለሌላ ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ መኖሩን ያወሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሀብቱን ጥቅም ላይ ማዋል ቢቻል ለነዳጅ ግዥ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ በመቀነስ የአገር ኢኮኖሚን መታደግ ይቻል ነበር ይላሉ። በምን ደረጃ ላይ እንደሆነ እርግጠኛ ባይሆኑም ቴክኖሎጂው ያላቸው ኩባንያዎች የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ነዳጅ ለመለወጥ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ፖታሽንም እንዲሁ በተመሳሳይ ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ለግብርና ግብአት የሚውል ማዳበሪያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጭ ተደርጎ ከውጭ በግዥ ወደአገር እንዲገባ እየተደረገ መሆኑንም የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የሀብት ክምችቱ በአፋር ክልል መኖሩንም ይገልጻሉ። ለማዳበሪያ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት በአገር ውስጥ ያለ ሀብትን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
ይሁን እንጂ ከንግግር ያለፈ ተግባራዊ ሥራ ግን እየታየ አይደለም ነው የሚሉት። በተለይም የአገር ኢኮኖሚን ሊቀይሩ በሚችሉ ከፍተኛ በሚባሉ የማዕድን ሀብቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የግድ ይላል። ማዳበሪያ ከውጭ በግዥ በማስገባት መቀጠል አይቻልም። ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ ገቢ ለማግኘት ጥረት መደረግ ይኖርበታል። ነዳጅም እንዲሁ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በመሆኑ ትኩረት ይፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ።
ዘርፉን መሠረት በማድረግ መንግሥት ከዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያደረገውን ምክክር በተመለከተ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በሰጡት ትንታኔ እንዳሉት፤ከዓለምአቀፍ ድርጅቶች የዓለምባንክ ትልቁ ሲሆን፣ የተቋቋመበትም ዓላማ እንዲህ ያሉ መሠረታዊ የልማት አውታሮችን ለማደራጀት ነው።
የማዕድን ልማት መሰራት ያለበት በግል ባለሀብቶች መሆኑ ግን መዘንጋት የለበትም። በዓለም ውስጥ ያሉት የማዕድን ልማት ኩባንያዎች በጣም ውስን ናቸው። እንደ የአውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ አሜሪካን፣ ቻይና ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች በማዕድን ልማቱ ላይ ቢሳተፉ የተሻለ ይሆናል።
የማዕድን ልማት በአጭር ጊዜ ውጤት የሚገኝበት አይደለም። ብዙ ስራንና ምቹ ሁኔታም ይፈልጋል። ከፀጥታ ስጋት ነጻ መሆን አለበት። ከአየር ንብረትና ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘም ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሥራ በመሆኑ ድጋፍና ክትትሉ መጠናከር ይኖርበታል።
ባለሀብቶቹ የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸትና በገቡት የኮንትራት ውል መሠረት እንዲሰሩ ማድረግ፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት ለመስራት መጥተው ነገር ግን ሥራቸውን አቋርጠው የወጡ ኩባንያዎች ለምን አቋርጠው እንደወጡ በጥናት በመለየት ለክፍተቱ መፍትሄ ሰጥቶ ችግሩ መልሶ እንዳያጋጥም ማድረግ ይጠበቃል ሲሉም ያስገነዝባሉ።
በአገር ውስጥም ዩኒቨርሲቲዎች የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ናቸው የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ሙያተኛው እንዲሰራ እየተደረገ ነው ወይ የሚለው ግን ያጠያይቃል ይላሉ። ‹‹ለእኔ የሚመስለኝ ውሃና መሬት አለን። ግን ደግሞ ምግብ ከውጭ ነው የምናመጣው የሚባል አይነት ነው›› በማለት በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ያስገነዝባሉ። ይህን መሙላት እንደሚገባም ይገልጻሉ።
በአገር ውስጥ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በአግባቡ በመጠቀም የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መፈተሽ፣ ዘርፉ በሙያተኞች እንዲመራ ማድረግና ሥራቸውንም በአግባቡ እንዲወጡ ማስቻል ይጠበቃል ብለዋል። በተለይም የማዕድን ልማት ሥራው ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ላይ የሚከናወን በመሆኑ ዞንና ወረዳ ላይ የሚሰሩትን ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ማብቃትና ጠንካራ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።በመሆኑም የፋይናንስ አቅም ካላቸው ተቋማት ጋር መንግሥት ውይይት ማድረጉ በበጎ ይወሰዳል ነው የሚሉት።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንዳሉት፤ ዓለምአቀፍ ባንኮቹ በሁለት መንገድ ነው ገንዘብ የሚሰጡት። አንዱ በዘርፉ ልማት ለመሰማራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች ወይንም ኢንቨስተሮች የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው የሚያስችል የጥናትና ምርምር ሥራ እንዲሰራ የሚያስችል ድጋፍ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቀጥታ ገንዘብ በመስጠት ወይንም በመርዳት ሳይሆን፣ለልማቱ ሥራ የሚውል ገንዘብ በማደራጀት ነው።
ይህም በልማቱ ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት ይገለጻል።ለአብነትም ከአውሮፓ በልማቱ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ከአውሮፓ ማእከላዊ ባንክ ገንዘብ ሊበደሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ። አፍሪካ ልማት ባንክም እንዲሁ በተመሳሳይ ብድር በመስጠት ነው ድጋፍ የሚያደርገው። ባንኮቹ በአነስተኛ የወለድ መጠንና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር መስጠታቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል። ብድሩን የመመለሻ ጊዜ እስከ 30 አመት ይደርሳል። የወለድ ሁኔታውም ቢሆን ወቅታዊ ሁኔታን መሠረት አድርጎ የሚዋዥቅ ወይም ተለዋዋጭ አይደለም።
ባንኮቹ ለጥናትና የምርምር ሥራ እንዲሁም ለአቅም ግንባታ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። በልማቱ ሥራ ላይ የሚሳተፈው ግን ከባንኮቹ ብድር ነው ማግኘት የሚችለው።ባንኮቹ ዋና ተግባራቸው ብድር ማመቻቸት ነው።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በትንታኔያቸው ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማዕድን ዘርፉም ቢሆን የሚያደርጉት ትብብር የተለመደ ነው። ዋና ዓላማው አገራት የኢኮኖሚ አቅም እንዲፈጥሩ ነው። አይ ኤም ኤፍ የተቋቋመበት ዓላማም የዓለምን የገንዘብ ሁኔታ ለማረጋጋት ነው። የዓለም ባንክ የተቋቋመው ደግሞ ደሀ አገሮች ከድህነት ወጥተው እራሳቸውን በመሠረተ ልማት እንዲያሳድጉ ለማስቻል ነው።
የዓለም ባንክ በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም አጀንዳ ውስጥም በመሳተፍ ላይ ቢሆንም ግድብ፣ መንገድ፣ የባቡር ሀዲድ፣ ኃይል ማመንጫና ማሰራጫዎች በመሳሰሉት መሠረተልማቶች ላይ ነው የትኩረት አቅጣጫው።
በአጠቃላይ ተቋማቱ በአቅም ግንባታ ላይ መሠረታዊ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው ይናገራሉ። በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የነበረውን የቅርብ ጊዜ መረጃ በመጥቀስ ሲያስረዱም ደቡብ አፍሪካ በመጠኑ ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ ከሰል ልማት እንደሚከናወን ይገልጻሉ። በአገሪቱ እየለማ ያለውን የድንጋይ ከሰል በሌላ ልማት ለመተካት ለተያዘው እቅድ የአውሮፓው የፋይናንስ ተቋም ስምንት ቢሊየን ዶላር ለመስጠት በአየርንብረት ለውጥ ዙሪያ በእንግሊዝ አገር በተካሄደ ስብሰባ ላይ ቃል መግባቱን ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያም ያላትን መሬትና ውሃ እንዲሁም የማዕድን ሀብቷን ጥቅም ላይ በማዋል የኢኮኖሚ አቅሟን ለማሳደግ ያሉትን የብድርና የእርዳታ አሰራሮች መጠቀም ይጠበቅባታል ነው የሚሉት። በተለይ እንደ ነዳጅ ያለ ሀብት ሲኖር አገሮች ከየራሳቸው ጥቅም አንጻር ስለሚያዩት ድጋፍ ለማድረግ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ነዳጅ ከወጣ በኋላ እዳው ስለሚመልስ ይፈልጋል ይላሉ። ብድሩ በአገር ደረጃም ቢሆን አገሪቱ ማዕድኑን አልምቶ በመሸጥ መመለስ ስለሚቻል ትኩረት ማድረጉ የተሻለ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በዩክሬይንና በሩሲያ መካከል በተፈጠረ ጦርነት ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተፈጥረዋል ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ራስን ለመቻል መስራት ይጠበቃል ይላሉ። ሌሎችም ፊታቸውን ወደ አፍሪካ የሚያዞሩበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ከዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር እንዲህ ያሉ የድጋፍና ትብብር ውይይቶች ሲኖሩ እድሉን በደንብ መጠቀም እንደሚገባ፣ የዲፕሎሚሲ ሥራ እንደሚፈልግና በዲፕሎማሲውም የተሻለ ልምድ ያላቸውን በውይይቱ ማሳተፍ እንደሚገባ ምክረሀሳብ ሰጥተዋል። መገናኛ ብዙሃንም በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራትን ተከታትሎ ለህዝብ የማሳወቅ ተግባሩን መወጣት እንዳለበትም በምክረሀሳባቸው ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2014