ከሰሞኑ በአንደኛው ቴሌቪዥን ጣቢያ ኪነ ጥበባት ላይ ባተኮረ ፕሮግራም ላይ አንድ ታዋቂ አርቲስት ይቀርባል:: እንደተለመደው ሕይወትና ሥራዎቹ ያተኮሩ ጉዳዮች እየተነሱ ቃለ መጠይቁ ይካሄዳል::
ታዲያ የነገ ተስፋው ምን እንደሆነ ሲጠየቅ የመለሰው መልስ ግን የብዙዎቻችን የቤት ሥራ የሚፈልገውን ጉዳይ ያነሳ ነበር:: ’’በትናንት ከመኖር አልወጣንም’’ አለ:: ነጋችንን የሚያጠቁር፣ ተስፋ የሚያሳጣን ዛሬን ብንኖርም፤ ከትናንት የማያወጣ ቆሞ መቅረት ከመሰለ ነገር አልወጣንም ማለቱ ይመስላል::
ትናንትን ከዛሬ የሚደባልቁ፣ ዛሬን ከነገ ያልለዩ ባሉበት አገር ነገን በተስፋ ማሰብ ይቸግራል:: በተለይ አሁን ባለንበት ሁኔታ::
ፖለቲከኞቻችን
ዕድሜ መጨመር እንጂ፤ መብሰል የማይሞክራቸው አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ዛሬም የሚያወሩልን አንድነትን ሳይሆን፣ መለያየትን፤ የብሄር ጭቆና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥላቻና ማግለል የአንድ ብሄርና እምነት የበላይነት፤ ዛሬም አንድነታችንን የሚሸረሽሩባቸው መሳሪያዎቻቸው አድርገው ነው::
በኢትዮጵያ ከላይ የተቀመጡት ጉዳዮች ችግሮች የሉም ባይባልም፤ እንደ አንዳንዶቹ አክራሪ ብሄርተኛ ፖለቲከኞቻችን ሐሳብ በአገሪቱ ራሱን ነጥሎና ተገንጥሎ የሚኖር በርካታ ብሄር/ብሄረሰብ ይኖር በበረከተ ነበር:: አገሪቱም ህብረ ብሄራዊነቷን አጥታ ስንት ትናንሽ አገሮች ሆና የዓለም መሳለቂያ ሆና ትቀርም ነበር:: ኢትዮጵያም ኢትዮጵያን ሆና ለመቀጠል ዋስትና አልነበራትም::
ሉላዊነት
ይሄ ዘመን የሉላዊነት (የግሎባላይዜሽን) ነው:: ዓለም በኢንተርኔት እንደተሳሰረች ሁሉ ነዋሪዎቿም ድንበር ሳይገታቸው አብረው ለመኖር፣ ለመዋለድና ለመባዛት ሰው መሆን ብቻ በቂ በሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል:: አገሮች ሰዎችን ‘’ከየት ነህ ወዴት ነህ’’የሚሉት መነሻና መድረሻቸውን አውቀው በስደተኝነት ገብተው እንዳያጥለቅልቋቸው ብሎም በሽብርተኝነትና በሕገ ወጥነት መንገዶች ገብተው ችግር እንዳይፈጥሩባቸው እንጂ፤ ሰው መሆናቸውን በመካድ ዘርና እምነት መሰረት አድርገው እንቅስቃሴያቸው ለመግታት አይደለም::
መንግሥታትና አገሮች በሽብርና በሕገ ወጥ ድርጊቶች በሚሰማሩ ሰዎች እንዳይጎዱ ቁጥጥር ያደርጋሉ ወጪና ገቢ መንገደኞችን ሕጋዊ ሥርዓት ባለው መንገድ ይቆጣጠራሉ፤ ይከታተላሉ::
በዛሬዋ ብዝኃነት በሞላባት ዓለም አርጀንቲና ተወልደህ ጀርመናዊት አግብተህ ኑሮህን ናይጄሪያ ሆኖ ንግድህ ከሕንድ ብታደርግ ማንም ግድ የላትም:: አልያም ቻይና ተወልደህ ዛምቢያዊት አግብተህ ትምህርትን በእንግሊዝ አጠናቀህ ልጆችህን ታይላንድ ወልደህ አውስትራሊያ መኖሪያህ ብታደርግ ዓለም ምን ገዷት! ምድር የሁላችንም ናትና !!!
የእኛዎቹ
ከ1960ዎቹ የአብዮተኝነት ዘመን አስተሳሰብ ያልወጡትና ዛሬም ‘’ጭቆና’’ በሚል ዜማ የሚያቀነቅኑ የእኛዎቹ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ማንነትን በመፈለግ ላይ ናቸው:: በብሄርና በእምነት ስም ለዘመናት ተፋቅሮና ተከባብሮ የኖረውን ሕዝብ ለመነጣጠል ይጥራሉ:: ከትናንት የተሸጋገረው ዜማቸው ዛሬም የሚዘፍነው መነጣጠል ነው:: ማንን ከማን እንደሚያለያዩ ሌት ተቀን ያነበንባሉ:: ስምም ይጠራሉ እገሌን ከእገሌና ከነእነገሌ በእያሉ:: ግን የተለየና ያልተበረዘ ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊ ለማግኘታቸው እነሱም እርግጠኛ አይደሉም::
በዚህች በልቶ ማደር በቸገራት ዓለም ኑሮን በጋራ መግፋት በቸገረበት ዘመን ዘር እየመረጠ ተነጠል ይላሉ:: የሕዝቡን ትውልዶች የተሸጋገረ ማንነትና ውሁድነት በቅጡ አያውቁምና መነጠልና መነጣጠልን ሲያለሙ የራሳቸውን የነገ መኖሪያ የሚያውቁ ሆነው አይደለም ::
ሉላዊነትን ከማንም በላይ ጠንቅቀው የሚያውቁት የልዩነት አቀንቃኞች ‘’ቆምንለት’’ የሚሉትን ሕዝብ በአግባቡ አላወቁትም:: በአንድነትና በህብረት መኖርን ሳይሆን፤ በዚህ ዘመን ተለያይቶ ስለመኖር ሲሰብኩ ያሳዝናሉ::
የማይክዱትና የሚክዱት ዜግነት
አክራሪ በብሄርተኛ ሰሌዳ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ሲመቻቸው ከእነሱ በላይ ኢትዮጵያዊ የለም:: አንዳንዴም የሌላ አገር ዜግነት ደርበው ሊገኙ ይችላሉ:: ኢትዮጵያዊነትን ሲበርዳቸው የሚለብሱት ጋቢ፤ ሲሞቅ ከትከሻቸው የሚጥሉት ኮት አድርገው መገኘታቸው ነው:: እንዲያው ለነገሩ ዜግነት ወቅት ተለይቶ የክረምትና የበጋ ተብሎ ይለበሳል እንዴ!?
የእኛዎቹ ጉዶች አገርን ከራስ ጥቅምና ሥልጣን በላይ አድርጎ ያለመመልከት ዋነኛ ችግራቸው ነው:: እነሱ ሲመቻቸው አገር አልፎለታል ብለው ያስባሉ:: እነሱ ሲመቻቸው የፖለቲካና እምነት የበላይነታቸውም እንደተረጋገጠም ይነግሩናል:: አንዱ በሆነ ነገር ቅር ካላቸው ግን አገርም፣ ፖለቲካም እምነታቸውም እንደተጎዳ አድርገው ይለፍፋሉ:: ‘’ይህቺ አገር ምን ተስፋ አላት?’’ ብለው ሊያስተዛዝኑን ይሞክራሉ::
የእነሱ ምቾት ደግሞ የሚለካው ማንነት መሰረት አድርገው የሚያደርሱት የጥፋት ተልዕኮ ሲሳካ ነው:: ከዚያ ውጭ ያለው ጉዳይ አይመለከታቸውም:: አገር በአክራሪ ብሄርተኞች ስሜትና ፍላጎት ስትነዳ ከማየት የበለጠ ምን መጥፎ ነገር አለ! ለዚያውም እናት አገር ኢትየጵያ::
እነዚህ የጽንፈኝነትና የአክራሪነት መሳሪያዎች ሉላዊነትን በሚገባ ያውቁታል:: ዓለም በአንድ ገመድ ስትተሳሰር በዓይናቸው ያዩ ምስክር በሆኑበት ዘመን እየኖሩ ነው:: የዓለምን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ሲተንትኑ ተወዳዳሪ የላቸውም:: በሉላዊነት አስተሳሰብ የመጠቀውን አስተሳሰባቸውን ወደ መንደርተኝነት ያወርዱትና ያረከሱታል:: ’’አንተ/አንቺ እኮ የዚህኛው ብሄር/ብሄረሰብ በመሆንህ/ሽ የጭቆና ቀንበር ተሸካሚ ሆነሃል/ሻል:: ስለዚህ ነጻ ልትወጣ ይገባሃል/ሻል’’ የማያኗኑር ዲስኩራቸውን ይቀጥላሉ::
ዓለም አንድ እየሆነችበት በመጣችበትና ሰውነት ከምንምና ከማንም በላይ መሆኑን የሰው ልጅ ግንዛቤ በያዘበት በዚህ ዘመን በትናንሽ ሐሳቦች ተሸንፎ የመንደርተኝነት አስተሳሰብ ተሸክሞ መኖር ይሰቀጥጣል:: በአመለካከትና በአስተሳሰብ ዘቅጦ በሰብዓዊነት ኮስምኖ መገኘት ምንኛ አሳፋሪ ነው!!
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ አገራዊ ለውጥ ማካሄድ ከጀመረችበት ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ተስፋ የሚያሳድር መንገድ ጀምራለች:: ሾተላይ የሆነባት ለውጥ ዳግም ወደ ሌላ ለውጥ እንዳይመልሳትም ጥረት ተይዟል:: ብሄር/ብሄረሰቦቿ ተሳስበውና ተዋደው የሚኖሩባት አገር እንዲኖራቸው ህብረ ብሄራዊነትን ለማንገስ እየተሞከረ ነው:: ችግሮችን በጋራ ምክክር ለመፍታትም ጥረቱ አልተቋረጠም:: ለዘመናት የተከማቹ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስም ሙከራዎች እየተደረጉ ነው:: ምሉዕ በኩለሄነት ባይኖርም::
ለውጡ የአምስት አስርታትን ለውጥና አብዮት የወለዳቸውንና ከዚያም በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑም ይታወቃል:: ምንም እንኳን በለውጥ አደናቃፊ ኃይሎች ዕለት በዕለት እየተፈተነ ቢሆንም::
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በትናንቱ የአፋኝነት መንገድ ላለመጓዝ ሲሞክር ‘’ልፍስፍስ’’ና ‘’ደካማ’’ እየተባለ ይወቀሳል:: ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ሲነሳ ደግሞ ‘’አምባገነን’’ና ‘’ፋሺስት’’ እየተባለ ይወነጀላል:: ከምንም በላይ ግን የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ባለማስከበር በእጅጉ ተወቅሷል:: ተወንጅሏል:: በዚህም ሆነ በዚያ ግን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚባሉ አካላት እንደታገዘ በሚጠረጠረው ጠባብ አስተሳሰብ ዜጎች ለጭፍጨፋ ተዳርገዋል::
ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ከውስጥም ከውጭም በኢትዮጵያ ላይ በተነሱ ኃይሎች ዜጎች በገዛ አገራቸው ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን፤ ብሄራቸውን አስበው እንዲኖሩ ሙከራ አድርገዋል:: ኢትየጵያ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሄር/ብሄረሰብ መኖሪያ ነች ተብላ የተከለለች የአፓርታይድ ግዛት ትመስል:: አስተሳሰብህና አኗኗርህ ከመንደር አይውጣ የተባለባት በዘመነ ሉላዊነት ራሷን ያገለለች ደሴትም ለማስመሰል የሚጥሩ ወገኖች ተከስተውባታል::
ቅንጅቱ
ስማቸውን ከፋፋዮች በሉት ጥቅመኞች፤ ባንዳዎች በሏቸው ከሃዲዎች ሁሉም ፀረ ኢትየጵያ አቋም ያላቸው ከውጭ ኃይሎች ጋር ተባብረውና ተደጋግፈው ይንቀሳቀሳሉ:: የውጭዎቹ ኃይሎች ደግሞ አንድም ኢትዮጵያን ቢችሉ ለመበታተን፤ ካልቻሉ ደግሞ ማዳከምና ማንበርከክን ዒላማ አድርገው ይሰራሉ::
የሁለቱ ኃይሎች ጥምረት ዓላማው አንድ ነው:: ውጥናቸውና ዓላማቸው ኢትዮጵያን ከጥፋት እንደማይዘል መገመት አያዳግትም:: እነዚህ ኃይሎች ቢችሉ ኢትዮጵያን ከውስጥ በሚነሳ እሳት አቃጥለው አመድ ለማድረግ ይሰራሉ:: ካልተሳካላቸው ደግሞ የፈራረሰችና አጎብዳጅ አገር እንድትሆን ጥረታቸውን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችም ይቀጥላሉ::
በሁለቱም መንገዶች የሚደረገው ቅንጅት አገረ ኢትዮጵያ ክምድር ገጽ ለማጥፋት የሚሰነዘር የጥፋት ተልዕኮ መሆኑን ለማወቅ የተለየ ጥበብና ዕውቀት አያስፈልግም:: ጨዋታው በስውር መሆኑ ቀርቶ የአደባባይ መሆኑ ከታወቀ ሰነባብቷልና:: እነ አጅሬ ግን ኢትዮጵያን ለማፈራራስ የሸረቡት ሴራ ዛሬም በጓዳ እያከናወኑት መስሏቸው ሲጃጃሉ ትዝብት ጥለው ወድቀዋል::
እንመካከር
በኢትዮጵያ ተቀራርቦ መነጋገርን እንደ ጦር የሚፈሩ መንግሥታት ነበሩን:: በአገሪቱ ታሪክ በአገር ጉዳይ ላይ ‘’በጋራ እንምከር’’ ሲሉ የቆዩ ወገኖች ለውይይት ጊዜ ያገኙበት ሁኔታ የተፈጠረው ዘንድሮ ነው:: ኢትዮጵያ ከተደነቁባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመውጣት ምክክርን እንደ መፍትሄ ያስቀመጠ ኮሚሽን በማቋቋሟ::
አንዳንድ ወገኖች በኮሚሽኑ አሰያየም ዙሪያ ቅሬታዎች ቢያሰሙም፤ የኢትዮጵያን ችግሮች መርምሮና መክሮ መፍትሄ ለማፈላለግ መሰየሙ በበጎ ጎኑ ወስዶ መደገፍ አንድ አዎንታዊ ጉዳይ መሆኑን ማወቅ ይገባል:: አንዳንዶች ባነሷቸው ጥቃቅን ችግሮችና ጉድለቶች ምክንያት አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጅምር ሥራዎቹን ማጣጣል አያስፈልግም::
ለዚያውስ ኮሚሽኑ ራሱን በአግባቡ አስተዋውቆ ወደ ሥራ እስኪገባ መቼ መፈናፈኛ ጊዜ ሰጠነውና ነው ሥራውን ለመገምገም የተጣደፍነው? በ’’ትናንት ከመኖር’’ በመውጣት ለአዲስና አገርን ወደ አንድነት ለማምጣት ለሚሞከሩ ነገሮች ዕድል መስጠት ያስፈልጋል::
የኮሚሽኑን እንቅስቃሴ ማበረታታት፣ ጉድለቶቹን እንዲያስተካክልና ስህተቶችን ካየን እንዲያርም ማድረግ ይገባናል:: ከዚህ በኋላ አገራችንን በጋራ ለመገንባት በሩን በይበልጥ ከፈት እናደርጋለን ብለን እናስብ::
ኢትዮጵያን ቢያውቋት
ትናንት ስንት ጥሩ ነገሮች ነበሩት:: ለዛሬ ምን አሸጋገረልን ብለን ማሰብ እንዴት ያለ መልካም ነገር ነው:: ፖለቲካችን አገርን በመሰሉ ጉዳዮች ግን ከትናንት የወረስናቸው ለዛሬ የማይበጁን ነገሮች ሞልተውታል:: ስለዚህም አርቲስቱ እንዳለው‘’በትናንት መኖር’’ መብቃት አለበት:: ዜጎች ‘’በትናንት መኖር’’ን እስከ መቼ ማለት አለብን::
ሰዎቹ ምሁራን ይሁኑ አክቲቪስቶች፤ ፖለቲከኞችም ሆኑ ጋዜጠኞች የጠባብነትና የጎሰኝነት አስተሳሰብ የሆኑት ምርኮኞች የጠሉት ኢትዮጵያን ነው:: ህብረ ብሄራዊነትን አስጠብቃ በሁለንተናዊ መንገዶች የምታድግና የምትበለጽግ አገር የማትመቻቸው የውጭም የውስጥም ኃይሎች ስላሉ:: ኢትዮጵያ ደግሞ አንድና ሁለት ሳይሆን ከ75 በላይ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ያሏት ህብረ ብሔራዊ አገር ናት::
ኢትዮጵያ ደግሞ የአንድና ሁለት ሃይማኖቶች ሳይሆን የብዙ ሃይማኖቶችና እምነቶች ባለቤት የሆነች በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሰረተች አገርነቷን ስታመሰክር ኖራለች::
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም ሥልጣኔ ድርሻዋን ያበረከተች አገርም ናት:: ኢትዮጵያ አፍሪካን ተሻግራ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ ለዓለም ሰላምና ደህንነት መከበር አስተዋጽኦ ያደረገች አገር መሆኗንም ማወቅ ተገቢ ነው::
ስለዚህ ኢትየጵያ ሊኮሩባት፣ ሊንከባከቧትና ሊያሳድጓት የሚገባ ድንቅ አገር ናት:: የሚያፍሩባትና የሚሸማቀቁባት ዜጎች ካሉ የማያውቋት ብቻ ናቸው:: ዓለም ሲያደንቃትና ሲያከብራት ዜጎቿ ባዕድ ከሆኑ ችግሩ የራሳቸው ከመሆን አያልፍም::
የሚበጀው
ዓለምን የሚያስደምም ታሪክና ባህል ብሎም ማንነት ያለን ዜጎች በትናንሽና አሳፋሪ ትርክቶች ተጠልፈን መኖር የለብንም:: ያለፉት ትውልዶችና ዘመናት ቁርሾዎችን እያነሳን ስንቆዝም፤ ዓለም ጥሎን እየነጎደ ነው:: በማያሳፍረው ስናፍር በሚያኮራው ስንሸማቀቅ ማንነታቸንን አጥተን ማፈሪያ ሆነን መቅረት አይገባንም:: አይመጥነንምም::
ስንፈጠር ባልመረጥነው ማንነት መብቀል ባለብን ሥፍራ የተተከልን ዜጎች ሆነን ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደናል:: ዕድልም ይሁን አጋጣሚ የአንዲት አገር ዜጎች አድርጎናል:: እንደ እኔ ከሆነ፤ የዚህች ውብ ኩሩና የብዙ ነገሮች መገኛ የሆነች አገር ዜጎች በመሆናችን ታድለናል:: ኢትየጵያዊነት ያልተመቸው ዜጋ ካለ አገሩን ስላላወቃት ነው ባይ ነኝ ::
ለዜጎቿ የምትመች አገር ገና በመፍጠር ላይ በመሆናችን በኑሮአችንና በሕይወታች ያልተመቹን በርካታ ጉዳዮች አሉብን:: የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የራስ ምታት መሆናቸውን ቀጥለዋል:: የጤና የትምህርትና የመሰረተ ልማት ተቋማት ችግሮች ገና አልተፈቱልንም::
የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ሲባባስ እንጂ፤ ሲሻሻል እያየን አይደለም:: ወጥቶ በሰላም መግባት መታደል የሆነበት አጋጣሚም ተፈጥሯል:: ይህም አይካድም:: እንዲህ እንዲያ እያልን ችግሮችን መዘርዘር ብንቀጥል ማባሪያ የሌላቸው የሚመስሉ ችግሮችን መደርደር እንችል ይሆናል:: ተስፋ ሊያስቆርጡንም ይችላሉ::
ከችግሮቹ ጋር አብረን መኖር በመለማመዳችን የማይፈቱ ይመስሉናል እንጂ፤ በጥረትና በጊዜ የማይፈቱ አይደሉም:: ልማትን በማምጣት መልካም አስተዳደርን በማስፈንና የጋራ ደህንነታችንን በመጠበቅና በማስጠበቅ እንፈታቸዋለን::
ከዚህም በላይ የታሪክ ቁርሾዎችና ማንነትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ጉዳዮች ኢትዮጵያዊነትን አንግሰን እንደ አንድ ሰው ስንቆም ይወገዳሉ:: ለዚህም አሉን ለምንላቸው ችግሮች መሰረታዊ መፍትሄዎች በማፈላለግ ብንሰራ ምላሽ ያገኛሉ:: አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ይሄንኑ ሊያግዝ የተቋቋመ ተቋም በመሆኑ ችግሮቻችን በማንም ሳይሆን በእኛው ይፈታሉ:: የሚያሻን ጊዜና ቅንነት ብቻም ይሆናል::
ከውጭ ኃይሎች የሚደርሱብን ችግሮች ከቅርብና ከሩቅ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ ዘርፍ አልፈው ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያሳርፉ ናቸው:: ታዲያ ከነዚህ መልከ ብዙ ችግሮች ለመውጣት አንድነታችንን ማጠናከር የግድ ይለናል::
ችግሮቹ ከቅርቦቹ ጋር ጦርነት መግጠም ራቅ ካሉት ደግሞ ምንደኞችን ከማሰማራት አንስቶ በህልውናችን ላይ ተጽዕኖ እስከማሳደር ሊደርሱ ይችላሉ:: ደርሶብንም አይተነዋል:: በአብዛኛው ተቋቁመን ብናልፈውም::
ሆኖም በተለያዩ መልኮች የሚመጡትን የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ ለመመከት መሥራት አስፈላጊ ነው:: መዋጋት ለሚፈልገው ምሱን መስጠት በሌሎች መንገዶች ለሚመጡት ደግሞ አመጣጣቸው ባገናዘበ መልኩ ምላሽ መስጠት ይገባናል::
የአገራችን ችግሮች ‘’በትናንት በመኖር’’ አይፈቱም:: ይልቁንም ተዋደንና ተከባብረን ዴሞክራሲን ስናሰፍን ሰላማችንን ስናስጠብቅና ስንነጋገር ይፈታሉ:: ለኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያውያን ሌላ ማንም የለም:: ሊኖርም አይችልም:: ስለምን “የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ ” እንዲሉ::
ኢትዮጵያውያን ከመናቆርና ከመጠፋፋት አረንቋ ውስጥ ወጥተን ለልጆቻችን የምንመኛት አገር የምንገነባበት ጊዜ ላይ እንገኛለን:: ትናንት በደል ግፍ ጭቆና ነበረ:: ዛሬም ከዚያ ሁኔታ አልወጣን ይሆናል:: መፍትሄው ግን እዚያ ላይ እያላዘኑ መኖር አይደለም:: ’’በትናንት መኖር’’ ማክተም አለበት:: ‘’በትናንት መኖር’’ ከዘመኑ የማይራመድ ከመሆኑም ባሻገር፤ የሰውን ልጅ ክብር ነጻነትና እኩልነት መብቶች ይጋፋልና መቅረት አለበት::
ቂመኛና እልከኛ ሆነን ትናንት ስንረግም ብንኖር ትናንት ላይመለስ ሄዷል:: እስከ ዛሬ ያቆየነው እኛ ልንሆን እንችላለን:: መልካም መልካሙን ይዘን ትናንትን መሻገር ችግር የለውም:: ክፉውንና የማይጠቅመውን በዚህ ላይ ተጠያቂዎቹ የሌሉበትን ትናንት በአንቀልባ አዝለን መሻገርን ለምን እንፈልጋለን? ትናንትን እያልን ዛሬ ለማስተኛት እንሞክራለን?
ሆኖም በትናንት አስተሳሰብና አመለካከት ተቸንክረው ዛሬን ከትናንት ያልለዩ ችግሮች ካጋጠሙን በመነጣጠልና በመከፋፈል ሳይሆን፤ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና አንድነታችንን ሳናፈርስ ልንታገላቸው ይገባል:: የትናንቱን ለትናንት ትተን ዛሬን ወደ ነገ መሸጋገሪያ አድርገን ነገን በሥራና በተስፋ መቀበል ሥልጡንነታችን የምናሳይበት የዘመናዊነት መገለጫ ነው::
አንድ ታዋቂ የአገራችን ዘፈን እንዲህ አቀንቅኗል ፣፤
ወደኋላ እየሄድሽ
በሐሳብ ከማለም
ቀን እንዳይመሽብሽ
ትናንት ዛሬ አይደለም::
ዓለም በሥልጣኔና በሉላዊነት ጀልባ ሲቀዝፍና ወደ አንድነት ሲያመራ የሥልጣኔ አውራና የህብረ ብሔራነዊነት ዓርማ ኢትዮጵያ በተምሳሌትነቷ ወደፊት እንድትጓዝ በማድረግ ድርሻችንን መጫወት ይጠበቅብናል:: ’’በትናንት መኖር ‘’ለማንም አይበጅም:: አልበጀምም:: ከዓለም ኋላ ያስቀረንና መተረቻ ያደርገን ካልሆነ በስተቀር:: ለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በላይ ማን መጥቶ !!!
ከብርሃኑ ተሰማ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም