አዲስ አበባ፡- የደቡብ ክልል ሁሉም ዞኖች የክልል እንሁን በማለት ያነሱትንና የሚያነሱትን ጥያቄ መረጃ መሠረት አድርጎና ምክንያታዊ ሆኖ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መወሰን ተገቢ እንደሆነ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበርና የመድረክ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ አሁን ያለው የክልል እንሁን ጥያቄ ጊዜ የሚጠብቅ ጉዳይ ነበር። ይህም የሆነው የሽግግር መንግሥቱ
ሲዋቀር በኢትዮጵያ 14 ክልሎች እንዲኖሩ፤ ደቡብ ደግሞ በአምስት ክልል እንዲደራጅ ነበር የተስማማነው፤ ይህም የተወሰነው የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት ከሚባለው ተቋም የተጠና መረጃ በመሰብሰብና በማጥናት የደቡብ ክልል በቋንቋ እንዲዳኝና ባህሉን እንዲያሳድግ በመፈለጉና በመስማማት ነው።
በዚያው አወቃቀር ክልል ሰባት የነበረው ጉራጌ፤ ሀድያ፤ ከንባታና የም ሆሳዕናን ማዕከል አድርጎ አንድ ክልል ነበር። ሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ ቡርጂና አማሮ ሀዋሳን ማዕከል አድርገው አንድ ክልል እንዲሆኑ ነበር የተወሰነው፤ ሌሎችም እንደዚህ እያለ በአጠቃላይ ደቡብ ክልል በአምስት ነበር የተደራጀው። ይህ ስምምነትም በአዋጅ ቁጥር 7/1984 የተደነገገ ነው። በሽግግሩ ወቅትም በክልልነት ሲሰሩ ነበር። ይህን አፍርሰው በአንድ ማዕከል ያደረጉት ኢህአዴጎች ናቸው።
ክልሎች የተደራጁት በምክንያታዊነትና በብዙ ጭንቀትና ክርክር ነው። የኢትዮጵያ አስተዳደር ክልሎች 14 እንዲሆኑ የተደረገውም በብዙ ክርክር ነበር። በኋላ ግን የዚያን ጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አምስቱን የደቡብ ክልሎች ሀዋሳን ማዕከል አድርገው በአንድ ክልላዊ መንግሥት ትንቀሳቀሳላችሁ በማለት ወሰኑ። በምክር ቤት የተወሰነን እናንተ ማፍረስ አትችሉም ስላልን ከምክር ቤትና ከኃላፊነታችን የተባረርንበት አንዱ ምክንያት ሆነ።
ያኔ ያለሕዝብ ፍቃድ ያፈረሱት ክልል አሁን ሁሉም ተበጣጥሶ የተወሳሰበ ችግር ይዞ መጣ ለሕዝቡም የመረረ ችግር ሆኗል። እያንዳንዱ ዞን ክልል ካልሆንኩ አለ። የሲዳማን ብንወስድ የሚቀረው ሕዝበ ውሳኔ ነው። እብድ ካልሆነ ይህን የሚቃወም ሲዳማ የለም። ሁሉም ዞኖች ክልል ካልሆንን የሚል ጥያቄ አላቸው። ይህ እንዴት ይሰብሰብ የሚለው ትልቅ እራስ ምታት ነው። ኢህአዴግም የዘራውን እያጨደ ነው።
አሁንም የሚሻለው መረጃ መሠረት አድርጎና ምክንያታዊ ሆኖ መወሰን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙት ኮሚሽን ይዞት የሚመጣውን ውጤት ማየት እፈልጋለሁ። ማንም ጤነኛ የሆነ ሰው ምክንያታዊ ሆኖ ሲመጣ መደራደርና መቀበል አለበት። አለበለዚያ አገር መገንባት አይቻልም። የትኛውም ክልል አፈሩን ዝቆ ወይም ሕዝቡን ይዞ አይሄድም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ