ሁለቱም የእኛው ሆነው ሳለ ጥሎብን መልካም የሆኑ ታሪካችን የኔ፤ የጎደፈው የአንተ መባባል ተላምደናል። እስኪ የእኔ ታሪክ እጅጉን ከሌላው የተለየና ድንቅ ፈፅሞም ጠልቶ የማያውቅ የፍካት ብቻ ነው የሚል ወገን የት ይሆን የሚገኘው? የትኛውም ሕዝብ የነጠረ መልካምነት ብቻ የተከተበበት ታሪክ የለውም። አንዱ ገፅታው ሲፀልም ሌላኛው ፍካት ይሆናል። አንዱ ታሪኩ የሚኮራበት ሲሆን ሌላኛው አንገቱ የሚደፋበት ውህድ ነው። ፅልመት ብቻ የለበሰ አልያም ደግሞ ድምቀት ብቻ የሰፈነበት ታሪክ የለም።
የእኛም ታሪክ ገፅ ተከፍቶ ሲነበብ ሁለቱም መልክ ይይዛል። የዚህች ታላቅ አገር ያለፈ ገፅ ወደኋላ ተመልሰን ብንገልፅ ሁለት አይነት ሆኖ እናገኘዋለን። አንዱ በወርቃማ ቀለም ደምቆ በዘመናት የማይሻር በጊዜ ብዛት የማይሸረሸር፣ ሲነገር የሚጥም፣ ሲያወሩት የሚጣፍጥ ሁሌም እንዲያ በተኖረ የሚያስብል ድንቅ ታሪክ:: ሌላኛው ገፅ ደግሞ እንዲህ ይነበባል።
መናገር የማይፈልጉት እውነት፤ መስማት የማይፈቅዱት ሁነት። እንደው ያ ዘመን ባለስታወስነው በዚያን ዘመን የሆነው ወደፊት ባናየ የሚያስብል የታሪክ ጥላት። ነገር ግን ይሄ የኛ ታሪክ አይደለም ብንለው የማይላቀቀን ከኛ ልናርቀው ብንሞክር ፈፅሞ የማይላቀቀን ነው፤ ምክንያቱም እሱም የእኛው ታሪክ ነዋ።
ካለፈ ታሪካችን ላይ ጨልፈን ዛሬን እንሻገር ዘንድ ከበጎው ልምድ ወስደን ብንገልገልበት፤ በአንፃሩ ደግሞ ጥሩ ያልሆነው እንዳይደገም አስተምሮን ቢያልፍ መልካም ነበር። ነገር ግን እኛ በጎው ላይ አትኩረን የምንጠቀም፤ ክፉው ላይ ደግሞ ጥሩ ትምህርት የምንቀስም ጥሩ ተማሪ አይደለንም።
አለም ነቅቶ ወደፊት በአያሌ ሁናቴው ቀድሞን ሲያበቃ አሁንም በመጠበቅ ላይ ነን። ምን መጠበቅ ብቻ በማፈግፈግም ጭምር እንጂ። ተነጋገረን መግባባት ተወያይተን መስማማት እየቻልን እንቢ አሻፈረኝ ብለን ወደኋላ እየተጓተትን የፊቱን እናሰናክላለን።
ወገን አሁን አላግባባ ብሎ እያጋደልን ያለው እኮ ከተረትህ ተረቴ ይበልጣል ነው። ምክንያት አልባ ፉክር በስሜት የታጀበ ውሳኔ ማስላት የሌለው ግብ። አዎን ከዚህ ሁኔታዎች መስከን ይኖርብናል። ዛሬ እየሆነ ያለው መጥፎ ነገር ልክ ዛሬ ላይ ትላንት እኛ ላይ ሆነብን የምንለው መጥፎ ነገር መምሰል ፈፅሞ የለበትም።
የእኛ ነገ መጥፎ ተግባር መባሉና በመጥፎነቱ መነሳቱ ይቀር ይመስል እኛ የትላንቱን እየመዘዝን ያኔ ጥሩ ያልሆነ በእኔ ላይ ተደርጎ ነበር ብሎ ዛሬ ላይ እኩይ ተግባር ላይ መሰማራት ምን ይሉታል። ጥሩ ማህበረሰብ ወደ ጥሩነት የተጠጋ መልካምነት የሚንፀባረቅበት ልማድ ይኖረዋል። ያ ልማዱ ደግሞ ነገ ላይ መልካም የሆነ ተግባርና መልካም የሆነን ማንነት የተላበሰ ታሪክ እንዲኖረው ያስችላል። በተቃራኒው ደግሞ ጥሩነትን መለያው ያልሆነ ማህበረሰብ የደበዘዘ መልክ ይላበሳል።
መጥፎ ታሪካችን መማሪያ ከማድረግ ይልቅ መጠቀሚያ ማድረግ ተላምደን ይህ እሳቤያችን ለሰዎች ሞት፣ ስደት፣ መፈናቀልና የሰብዓዊ መብት መረገጥ ምክንያት ሆኗል። እርስ በርስ ያቀመን ቋጠሮ የተፈታ ያህል የተሰማን እኮ የሌላውና የእኛ ማለት መጀመራችን የፈጠረብን ስሜት መነሻ ነው። ለዚህ ሁሉ መፍትሄ አለ። ሁሉንም ተቀብለን ወደፊት የእኛ ታሪክ ነው ስንለው የምንደሰትበት፤ ስለዚያ ሲወራ የምንፈካበት በጎ ታሪክ መስራት ነው።
እነዚህ ጥያቄዎች እንጠይቅ ስለምን መልካሙን የእኛ መጥፎውን የእነሱ እያልን የምንመድበው? በጎውም ክፉውም ወደኛ አቅርበን ከመልካሙ ልምድ ቀስመን ከመጥፎው ተምረን ወደፊት እንዳንጓዝ ለምን በራሳችን በር ዘጋን? ህዳሴያችን እንዳይቀርብ፣ ድላችን እንዳይጎመራ፣ ለውጣችን እንዲያዘግም ስለምን በእራሳችን ላይ መሰናክል ፈጠርን? እንዴት የሚያጋምደን በርካታ መገለጫ የጋራችን የምንለው ውብ የሆኑ የጋራ እሴቶች እያሉን መነጣጠል ላይ ዘመትን?
አዎን እነዚህ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ናቸው። ሊመረመሩና መነሻ ምክንያታቸው ሊለይ ይገባል። ያኔ የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ ፍንትው ብሎ ይገለጣል። ያኔ ወደመፍትሄው ለመቅረብ ይቀላል። እርግጥ በተናጠል እንደዜጋ ትልቅ ኃላፊነት አለብን። ይህ ዘመን ለእኛ ወደፊት ተመዝግቦ በዚያን ወቅት ሲባል የዘመኑ ግኝቶች ነንና እንዳናፍርበት ዘመኑ ለማፍካት ምን ሰራን አገሪቱን ለማፅናት ምን ነገር አደረግን? የሚለው ምላሽ መስጠት የሚገባን ወቅት ላይ ነን።
ሁሉም ከመስማት ይልቅ መናገር የመረጠበት ሁሉም እኔን ስሙኝ እንጂ የእናንተን አልሰማም ባይ በሆነበት በጎ ሀሳቦች እንኳን ቢነሱ አያግባባም። አዎን ዛሬ ላይ ጀግና ሆኖ መቆም የሚፈለግበት ጊዜ ላይ ነን። አገርን መታደግ ከከበባት ጠላት ላይ ህልውናዋን አስጠብቆ ለማስቀጠል ትንቅንቅ የተያዘበት ወሳኙ ዘመን ላይ ነን።
በእርግጥ ሙሉ እምነት አለኝ ይህቺ ሀያል አገር ስንቱን መከራ ተሻግራ ዛሬ ላይ እንደቆመች አውቃለሁና ሁሉንም በድል አጠናቃ ነገዋን ታፀናለች። ከእኛ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ግን አለብን። ሀላፊነታችን ለዚህች አገር አንድነት መፅናት ዘብ መሆን የዘመኑ የአንድነት ተምሳሌትን የትስስር አርማ መሆን ነው። በዚህ አንድነት የማይገረሰስ ጠላት የማይረታ ባለንጣ ፈፅሞ አይኖርማ። አገራችን ጀግና ያስፈልጋታልና ጀግና ሆነን እንገኝ።
የዚህ ዘመን ጀግንነት ፍቅር መስበክ፤ ሰዎችን ማክበርና መውደድ ነው። ዛሬ ላይ አርበኝነት የሰው ልጆችን በእኩል መመልከት ነው። ጥላቻ ቂምንና ከኔ በላይ ይሉት ፉከራ በዚህ ዘመን የተሸናፊነት ካርድ በራስ ላይ መምዘዝ ነው። እኔ የበላይ ነኝ ሌላው ግን ከእግሬ ስር የምትል ከዚህ ዘመን ብዙ የራቅህ ሰው ከሆንክ አንተ ልታፍር ይገባሃል። በዚህች ሰፊ ምድር መቻቻልን ከመስበክ የሰፋውን አጥበህ የምታመለክት ከሆነ ፍጹም ስህ ተት ውስጥ ነህ።
እንደ ሰው ቆመን ሰዎችን በሰውነታቸው ብቻ እኩል መሆናቸው እንቀበል። ይህ ማድረግ ከተሳነን የእኛ የራሳችን የሰውነት እኩሌታችን ተናግቷል ማለት ነው። ማነው የያዘውን ሳይወዱለት ሳይቀበሉት የሌላን መውደድ የሚችል? አየህ እንዲወደድልህ ቀድመህ መውደድ ጀምር። ሁሉም የራሱን ነገር ይዞ ይቅረብ መንገድ እንክፈትለት መልካም የሆነው ይቆያል፤ ይቀጥላልም።
መልካምነት ውስጡ ከሌለ አንተ እንዲጠፋና እንዲከስም ባትጥር እንኳን መልካም ስላነበረ መቆየት አይችም። እንዲያውም እራሱን ለመግለጽ እየሞከረ ስለሆነ የሚተገብረው መልካም ነገር ከሆነ እርዳው በፍቅር ቅረበውና ከሱ ጋር አብረህ ቁም። እመነኝ ነገ በፍቅር አብሮ ቆሞ የማይፈታ ችግር አይኖርም። ፍቅር የማያሸንፈው ነገር ምድር ላይ አልተፈጠረም። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም