ዮሴፍ ኃይለማርያም ይባላል። የራሱን መጽሐፍቶች ለማሳተም የበቃ ጋዜጠኛ፤ ደራሲና የፎቶግራፍ ባለሙያ ሲሆን በአዲስ ዘመንና በቀድሞው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች፣ በለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ፤ እንዲሁም አሁን እየሰራበት በሚገኘው በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ኤፍ ኤም 96.3 ሬዲዮ ጣቢያ ላይ ከመስራቱም ባሻገር በርካታ መጽሔቶች ላይ ምርኩዝ በተሰኘ የብዕር ስም እጅግ አስተማሪ፤ ሳቢና ማራኪ ጽሑፎችን በመፃፍ ፤ አጫጭር ግጥሞችን፤ ጭውውቶችን፤ የቲያትርና ድራማ ስክሪፕቶችን በማዘጋጀት፤ በጆሮ ገብ ድምፁ በመተረክና በማቅረብም አብዝቶ ይታወቃል።
በሕክምና ስህተት በተወጋው መርፌ በሕፃንነቱ የሥር መሸማቀቅ ደርሶበት ከቁርጭምጭሚቱ በታች የአካል ጉዳት ያጋጠመው ቢሆንም በአካል ጉዳተኝነቴ አጣሁት የሚለው ስለሌለው ጉዳቱ ሕይወቱን ሙሉ ተሰምቶት አያውቅም። ዘንድሮ የሚይዘውን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አራት ዲግሪዎችን ከያዘበት ትምህርት፤ ሥራም ሆነ ብዙ ጥቅሞች አላገደውም።
አባቱ ከልጅነቱ ጀምሮ በአካሉ ጉዳት የተለየ እንክብካቤ ሳያደርጉ ጉዳቱ ሳይሰማው በሁሉም ነገር እችላለሁ ብሎ እንዲሳተፍና በራሱ ተማምኖ እንዲያድግ ማድረጋቸው፤ መብቱን ማስከበሩና ለማስከበር መታገሉም አግዞታል።
ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት፤ ተሳታፊነትና መብት መከበር በፅኑ ታግሎም አብነት ሆኗል። እራሱ በሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ከሕብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ፤ ከአመለካከት ችግር አኳያ አካል ጉዳተኞች መብት ለማስከበር፤ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽንን፤ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች፤ የእግርና የእጅ ኳስ ማህበርን መመስረቱ ይወሳለታል። የአካል ጉዳተኞች ሕይወት እንዲለወጥ፤ እንዲማሩ አካል ጉዳታቸው ከምንም ነገር እንደማያግዳቸው ባላቸው የማስተዋልና ተስጥኦ ጥበብ ተጠቅመው አገራቸውንና ራሳቸውን እንዲረዱ ቤተሰቦቻቸውን ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ለረጅም ዓመታት አስተምሮና ተሟግቷል። የተጓደለና እነሱን የማያካትት ሕግ እንዳይወጣ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
ልዩ ልዩ መጽሔቶችንም ሲያዘጋጅ ቆይቷል። ብሩህ ተስፋ፤ የአካል ጉዳተኞች ድምፅ የሬዲዮ ፕሮግራም ከጓደኛው ጋር ጀምሯል። በዚህ ዙሪያ ተተኪዎች አፍርቶ እንዲሰሩም አስችሏል። በተለይ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የቀሰመውን የሕግ ትምህርት መሬት በማውረድ በርካታ አካል ጉዳተኞችን አካታች የሆኑ አዋጆችና መመሪያዎች እንዲወጡ ግፊት አድርጓል። በጊዜው አዋጅ 101/86ን የቀየረው አዋጅ 568/2000 የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት ሲወጣ ተካፋይ ነበር።624 የህንጻ አዋጅ ዛሬም የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ አይደለም ቢልም እንዲወጣ ሲጥሩ ከነበሩት አካል ጉዳተኞች መካከል አንዱ ነው። አንቀጽ 34 ላይ ከሀ እስከ ሸ እንዴት ደረጃ እንደሚሰራ አራትና ከዛ በላይ ፎቅ ያላቸው ህንፃዎች አሳንሰር (ሊፍት) ማስገባት እንዳለባቸው እየዘረዘረ ያስረዳል።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ልዩ ስሙ ጉለሌ የተሰኘው አካባቢ በ1960 ዓ.ም የተወለደው ዮሴፍ በራሱ ላይ የሚደርሱ እንቅፋቶችን ለሰው አያካፍልም። ገፍትሮና ሰብሮ በመግባት ራሱ ይቀርፋቸዋል እንጂ። ‹‹ብዙ አካል ጉዳተኞች ወደ ማህበሩ የሚመጡት ችግር ሲደርስባቸው ነው። ሆኖም አካል ጉዳተኛው የሕብረተሰብ ክፍል በመጀመሪያ ለራሱ ራሱ ነው መቆም ያለበት›› ይላል።
እንደ እሱ በተለይ ቤተሰቦች አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን ደብቀው ከሆነ መጀመሪያ የተደበቀበትን በር ሰብሮ መውጣት ያለበት ራሱ አካል ጉዳተኛው ነው። ለምሳሌ መሥሪያ ቤት ላይ ችግር ገጥሞት ከሆነ ድረሱልኝ የሚል እርዳታ ከመጠየቅ ችግሩን ለመቅረፍ መታገል እንዳለበት ይመክራል። የተማረ ወንድም እንዲሁም ጥሩ ደረጃ የደረሰች እህት ካሉት አካል ጉዳተኛው ተዘግቶበት ከሆነ ሰብሮ የሚወጣበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው ያስገነዝባል፤ በአካል ጉዳተኛ ሕይወት ውስጥ ብዙ የተዘጉ በሮች መሥራት፤ መማር እየቻሉ አትችሉም የተባሉ ሙያቸውን በላቀ ሁኔታ ማስቀመጥ እየቻሉ እድሉን የተነፈጉ አሉ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ይህንን ችግር ሰብረው በትግላቸው ነፃ የወጡ ብዙ የአካል ጉዳተኞች እንዳሉም ራሱን ዋቢ አድርጎ ይናገራል።
ወቅቱ 1984 ዓ.ም ነው። ያኔ እሱ የአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ጨምሮ በሌሎች ሚዲያዎች አማተር ፀሐፊና በፍካት ወጣት ደራሲያን አማተር ደራሲ ነበር። ምድር ጦር አንድ ሪፖርተር ለመቅጠር ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ያወጣል። በማስታወቂያው የተጠራው የ12ኛ ክፍል ትምህርትን ያጠናቀቀ ነበር። ይሄን ጊዜ ዮሴፍ 12ኛ ክፍልን አጠናቅቆ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ትምህርቱን ጀምሯል። እናም በመስኩ ከፍተኛ ልምድና ችሎታ አላቸው ከተባሉና ከሚታወቁ ጸሐፍት ጋር በመወዳደር ማስታወቂያውን ከጽሑፍ ጀምሮ እስከ ቃል ፈተና ድረስ አለፈ።
በተለይ ስክሪብት አፃፃፍ ላይ የተሻለ ልምድ ስለነበረው ጥሩ ውጤት አምጥቶ በአንደኝነት ውድድሩን ያሸንፋል። ስሙም ይለጠፋል። ግን ወደ ቅጥር ሂደት ሲገባ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች መካከል አንዱ የእግር ጉዳተኛ መሆኑን ገና ሲመለከተው ደስተኛ አልሆነም። እንዴት ሊሰራ ነው ? በሚል ዓይነት የመግፋት ዕይታ ፊቱን ጭፍግግ አድርጎ ነበር የተቀበለው። በዚህ ብቻ ሳይበቃ የቅጥር ሂደቱን ፈፅሞ ሥራውን እንዲሰራ በብርቱ ከሚፈልጉ ኃላፊዎች ጋር ተሟግቶ ሥራውን እንዳይቀጠር አደረገው። እሱ እያለም ተጠባባቂውን ጠርተው ቀጠሩ።
ሆኖም እልኸኛው ዮሴፍ ይሄን ኃላፊ በዋዛ አላለፈውም። ቅሬታውን በዛው በምድር ጦር ደረጃ ላሉ የበላይ ኃላፊዎች ለማቅረብ መመላለሱን ተያያዘው። በግንባር ሳይበቃውም በስልክ ሁሉ ኃላፊዎቹን ለማግኘት ጣረ። በኋላ ያ ኃላፊ ልንቀጥረው አንፈልግም በማለት ጊቢው ውስጥ እንዳይገባ ስላስከለከለው ሊሳካለት አልቻለም። አዋጅ 101/86 የአካል ጉዳተኞች ሕግ የወጣው ያኔ ነበርና ይሄንኑ ሕግ በመጥቀስ በእግሩ ጉዳት ምክንያት ከሥራ ቅጥር የመገፋት ቅሬታውን በማቅረብ ሲቪል ሰርቪስ ሄዶ ከሰሰው። ተሟግቶም አሸነፈ። ሆኖም የሕግ ባለሙያው በበቀል አጉል ቦታ ሊልኩህ ስለሚችሉ ይቅርብህ ብለው የመከሩትን ምክር ሰምቶ ሥራ መቀጠሩን ተወው።
በቃ ዮሴፍ አሳዛኝና በአካል ጉዳተኝነቴ ገጠመኝ የሚለው ይሄን ብቻ ነው። ሌሎቹን የተገፋባቸውን በሮች በሙሉ ገፍትሮ ሰብሮ ገብቶ ነው ዛሬ ላይ መድረስ የቻለው። የመኖሪያ ቤት ያገኘበት ገፍትሮ ለመግባቱ ማሳያ ነው። ኪራይ ቤቶች መኖሪያ ቤት እንዲሰጠው ሲያመለክት ቁጥሩ 50ኛ ነበር። ሆኖም በሥራ አውሮፓ ሄዶ ቆይቶ ሲመለስ ዕድሉን ያገኙት በሺዎች ሲቆጠሩ ለእሱም ሆነ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች አልተሰጠም። ከመጣም በኋላ ብዙ ቆይቶም ሊሰጠው አልቻለም።
ኪራይ ቤቶች በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርብና ሀሳብ አስተያየታችሁን መስጠት የምትፈልጉ ሲባል ዮሴፍ በስብሰባው ታደመ። ከቤት ፈላጊዎች መካከል 50ኛው ቁጥር ላይ መመዝገቡን ከነማስረጃው አቀረበ። ታዲያ ለምን ሳይሰጠው እንደቀረም ጠየቀ። መስሪያ ቤቱም ሁኔታው ስህተት መሆኑን በማመን አሁን እየኖረበት ያለውንና ለአካል ጉዳቱ የሚያመቸውን ቤት ሰጠው። እሱ ካገኘ በኋላ በርካታ አካል ጉዳተኞች ከኪራይ ቤቶች በተመጣጣኝ ክፍያ የመኖሪያ ቤት መብት ተጠቃሚ እንዲሆኑም አስቻለ። መብት የሚከበረውና ተጠቃሚነት የሚገኘው በመጮህና በትግል መሆኑንም አስመሰከረ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2014