ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦቷን በአስተማማኝ መንገድ ለመገንባት፤ ብሎም ለቀጠናው ሁነኛ የኃይል አማራጭ ለመሆን በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ መገንባት ከጀመረች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። የዓባይን ውሃ ጥቅም ላይ የማዋሉ ጉዳይ ምንም እንኳን ዘመናትን ያስቆጠረ ህልሟ ቢሆንም ቅሉ ውሃውን በብቸኝነት ሲጠቀሙበት የኖሩት ግብፅና ሱዳን በቅኝ ገዢያቸው እንግሊዝ ፊታውራሪነት ኢትዮጵያ በገዛ ውሃ ‹‹የበይ ተመልካች›› አድርገዋት ኖረዋል።
ኢትዮጵያ ግን ይህንን የቅኝ ግዛት ውላቸውን ‹‹አሻፈረኝ›› ብላ ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት በብዙ ውጣ ውረዶችም እያለፈችም ቢሆንም ልማቷን ቀጥላለች። ከዚሁ ጎን ለጎንም ትብብርንና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ማዕከል ያደረገ ስምምነት እንዲፈጠር የተፋሰሱን አገራት በማስተባበርም ሆነ በጋራ በመስራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች።
ሆኖም ግብፅና ሱዳን ‹‹የውሃ ታሪካዊ ባለቤትነት›› የሚሉትን በራስ ወዳድነት ላይ የተጠነሰሰውን ከንቱ ትርክት ይዘው የአረቡን ዓለም ብሎም ምዕራብውያኑን በማሳመንና በማሳደም የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ሲሉ ከሰማይ በታች ያለ አሻጥርና ተንኮል ከመስራት ለአንዲትም ቀን አልቦዘኑም። በተለይም የግብፅ መንግስት ጉዳዩ ከኢኮኖሚያዊ ይዘት በላይ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዲኖረውና የዓለም ኃያላን የኃይል አሰላለፍ እንዲታይበትም ይህንን እኩይ እንቅስቃሴ በማዛመት የሚስተካከለው አልተገኘም።
በቅርቡም የአውሮፓ ህብረት ግድቡን በሚመለከት ያወጣው ወደ አንድ ጎን የተንሻፈፈ መግለጫም የዚሁ የግብፅ እኩይ ዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት መሆኑ እሙን ነው። በዚህ ሚዛናዊነት በጎደለው የህብረቱ መግለጫ አንድምታና በቀጣይ ሊሠሩ በሚገባቸው ስራዎች ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር የሆኑትን ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራን አነጋግረናቸዋል እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የአውሮፓ ህብረት የዓባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ግብፅ በተደጋጋሚ የምታነሳውን የቅኝ ግዛት ‹‹ታሪካዊ የመጠቀም መብት›› ደግፎ በቅርቡ መግለጫ አውጥቷል። አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ይሄ ምንያህል ህጋዊ መሰረት አለው ብለው ያምናሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡- በዓለም አቀፍ ህጉ መሰረት ማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ ወንዝን የሚጋራ ወይም በተፋሰስ ውስጥ አገርና ህዝብ ከውሃው የመጠቀም መብት አለው። ውሃውን የሚያመነጨውም አካል ይሁን በተፋሰሱ ከግርጌ የሚገኙት አገራት ጨምሮ በውሃው የመጠቀም መብት አላቸው። እኛ ያለንበትን ሁኔታ ስናይ ግብፅም ሆነ ሱዳን ያን ያህል የውሃ አስተዋፅኦ ሳይኖራቸው ነው ሁለቱ አገራት በብቸኝነት ሲጠቀሙ የኖሩት። እነዚህ አገራት የተፋሰሱ አካል በመሆናቸው የመጠቀም መብት አላቸው ማለት ግን ታሪካዊ መብት መጠቀም ከሚሉት ጋር የተያያዘ አይደለም። እነሱ ታሪካዊ የመጠቀም መብት አለን የሚሉት የኢትዮጵያንና ሌሎች የተፋሰሱ አገራትን ያላካተተ፤ አግላይ የሆነ ስምምነት ይዘው ነው። በእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ስር በነበሩበት ጊዜ ውሃውን ግብፅና ሱዳን ብቻ የመጠቀም መብት የሰጠ፤ የሌሎቹን የመጠቀም መብት ከግምት ውስጥ ያላካተተ ስምምነትን ነው ታሪካዊ የውሃ መጠቀም መብት የሚሉት። ይሄ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ተፈፃሚ እናድርገው ማለት ፈፅሞ የማይቻልና እውን የሚሆንም አይደለም።
በመሰረቱ ይህ የቅኝ ግዛት ውል ሌሎቹን የተፋሰሱን አገራት ያገለለ በመሆኑም ነው የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ በ1999 ዓ.ም ተቋቁሞ በጋራ በተፈሰሱ ውስጥ ያሉ አገራት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩት። እነዚህ አገራት ይህንን ኢኒሼቲቭ በአንድ ላይ ሆነው በዘላቂነት ውሃውን ለመጠቀም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያቋቋሙት ሲሆን በዚህ መድረክ የኢትዮጵያ ሚና ትልቅ እንደነበር የሚታወቅ ነው። እንደሚታወሰው ደግሞ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ግብፅ ያንን ያረጀ ያፈጀ የቀኝ ግዛት ውል እንዲቀበሉት ጥረት አድርጋ አልተሳካላትም። ይሁንና ኢትዮጵያ በኢንሼቲቭ ያቀረበችው ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሮችን ለመፍታት የአባይ ተፋሰስ ኮሚሽንን በማቋቋም አባይን የማልማት ጉዳይ የሁሉም ስምምነት የታከለበት ጉዳይ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል።
በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት መሰል ስምምነቶች በኤዢያ ኔኮንግ በሚባል ወንዝ ላይ ኮሚሽን ተቋቁሞ ቻይና፣ ካምቦዲያና ሌሎችም አገራት ተስማምተው በጋራ እያለሙና እየተጠቀሙ ነው ያሉት። ኢኒሼቲቩ አባይም ላይ ተመሳሳይ ስምምነት ተፈፅሞ በዘላቂነት ለመጠቀም ነበር ሃሳቡ። የዚያ ኢንሼቲቭ ዋና ውጤቱ ደግሞ የትብብር ማዕቀፉ ነው። በአሁኑ ሰዓት አራት አገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ፈርመው በምክር ቤታቸው አፅድቀው የህግ አካል አድርገውታል፤ ኬኒያና ደቡብ ሱዳን ደግሞ ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል። በእርግጥ ደቡብ ሱዳኖች መንግስት ወደ ምክር ቤታቸው ከመሩት ቆይቷል። ስለሆነም ሁለቱ አገራት ካፀደቁት ይሄ የተፋሰሱ ኮሚሽን መቋቋም ይችላል ማለት ነው።
የኮሚሽኑ እውን መሆን ማናቸውንም አባይን ለማልማት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በአገራት ስምምነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህንን ስምምነት ሱዳንና ግብፅ ማፅደቅ ቀርቶ ለመፈረምም አልፈለጉም። ምክንያቱም እ.ኤ.አ 1929 እና 1959 በብቸኝነት ለመጠቀም የተስማሙበትን ስምምነት እንድንቀበል ስለሚፈልጉ ነው። ይሄ ደግሞ ቀልድ እንጂ ፈፅሞ የሚሆን ነገር አይደለም። ምክንያቱም እኛንም ሆነ ሌሎቹን የተፋሰሱ አገራት ጨርሶ ያገለለ በመሆኑ ነው። ይህንን ስምምነት ተቀበሉ ብሎ የአውሮፓ ህብረትም ሆነ ሌላ አካል ሊያስገድደን አይችልም። ከ86 በመቶ በላይ ውሃ እያመነጨን ተጠቃሚ አትሆኑም የሚል አስተሳሰብ የእጅ አዙር ቀኝ ለመግዛት የሚደረግ ጫና ነው። ይሄ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም።
እስከዛሬም በሚደረጉ ድርድሮች መስማማት ካልቻልንባቸው ጉዳዮች አንዱ ይሄ ነው። በመሰረቱ እኛ ብቻ እንጠቀም፤ እናንተ መንካት አትችሉም የሚባለው ነገር ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም። የውሃ ባለቤት ሆነን ሳለ ከዚህ ቀደም እነሱ የፈረሙትን ስምምነት ተቀበሉ ማለት ስድብ ነው። በእነሱ ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ወስደው ችግራችሁን በራሳችሁ ፍቱ ብሎ ወደ አፍሪካ ህብረት እንደተማራ ይታወሳል። ይህንን ደግሞ ማድረግ አልተቻለም። አሁንም ግብፅና ሱዳን ከስምምነት ላይ እንዳይደረስ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ የሚታወቅ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ግጭት ምክንያት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጫና እየጠነከረ ሲመጣ ግብፅ ያንን ተገን በማድረግ ሁኔታዎችን እንደማስረጃ እያቀረበች ‹‹የውሃ ፍላጎት የደህንነት ጉዳይ ነው፤ ችግር ውስጥ ገብተናል፤ ኢትዮጵያ ግድቡን ከመሙላት መቆጠብ አለባት›› የሚል አቤቱታዎቿን ስታቀርብ ነው የቆየችው።
በመሆኑ የሰሞኑ የአውሮፓ ህብረቱ መግለጫ ግብፅ የምዕራቡን አለም ቀልብ እንደያዘ አንድ ኃይል ደግሞ ጫና እንዲደረግ ከምታደርገው ጥረት አንድ አካል ነው ብዬ ነው የማስበው። ይሄ ግን በማንኛውም መመዘኛ መፈፀም የሚችል ጉዳይ አይደለም። የአውሮፓ ህብረትም ሆነ ሌላ አካል በመኖርና ባለመኖር እጣፈንታችን ላይ የመወሰን መብት የለውም። ግብፆች የሚሉትን ታሪካዊ ውሃ የመጠቀምና አግላይ የሆነ ስምምነት ተቀበሉ ማለት በፍፁም አይችሉም። ማለትም የሚችሉት ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ አንድ ፅንፍ የያዘ አቋም በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደመግባት ነው የሚቆጠረው።
አዲስ ዘመን፡- የአውሮፓ ህብረትም ሆነ ሌሎች የምዕራቡ አገራት ግብፅን በመደገፍ የራሳቸውን ጥቅም የማስጠበቅ ዓላማቸው ምን ያህል ይሳካል ብለው ያምናሉ ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– እንዳልሽው የአውሮፓ ህብረትም እና ሌሎች የምዕራቡ አገራት ዋና አላማቸው የራሳቸውን ጥቅም ማስጠበቅ በመሆኑ ነው ግብፅን የሚደግፉት። አሁን ደግሞ የራሺያ የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ በምዕራብ አገራት ኢኮኖሚ በተለይ በምግብ እህል ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል። አውሮፓም ሆነ አፍሪካ በእነዚህ አገራት ምርት ላይ ጥገኛ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ስለዚህ በአንድ በኩልም ያንን ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም የሚሄዱበት መንገድ ነው ብለን ለመውሰድ እንችላለን። በዚህም አለ በዚያ የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። ከዚያ ባለፈ ሶስቱ አገራት ተመካክረው ውሳኔ መስጠት ያለባቸው ጉዳይ ነው። በግድቡም ሆነ በውሃ አጠቃቀም ላይ የአውሮፓ ህብረት በፍፁም ጣልቃ ሊገባ አይችልም። ጉዳዩም ስላልሆነ የመወሰንና አቅጣጫ የመስጠት መብት የለውም።
የአውሮፓ ህብረት በአገር ውስጥ ጉዳይ ግብፅን ወግኖ እኛ ላይ ጫና ለማሳደር የሚደረገው ጥረት በምንም መልኩ ሊሳካ አይችልም። እንደሚታወቀው መጪው ክረምት እንደመሆኑ የውሃ እጥረት ስለማይኖር በግብፅ በኩል የሚደረጉትን የሃሰት ትርክቶች ፉርሽ ነው የሚሆኑት። በኢትዮጵያ በኩል ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ሲገለፅ እንደነበረው የግብፅን ህዝብ በውሃ ጥም የመጉዳት አላማ የለም። እነሱ እንዲጠሙና እንዲራቡ ማድረግ ፍላጎታችን አይደለም። እውነታው ግን እዚያ ደረጃ የሚደርስ አይደለም፤ በቂ የሆነ የዝናብ ውሃ አለ፤ ግድቡም እየተሞላ ያለው የሶስት አገራት መሪዎች በተስማሙበት ማዕቀፍ መሰረት ነው። ዘንድሮም የሚካሄደው ሙሌት በጊዜ ሰሌዳው መሰረት የሚደረግ እንጂ የተለየ አዲስ ነገር የለም።
እርግጥ የግብፅ ዋነኛ ስጋት የውሃ እጥረት ያጋጥመኛል ከሚል መነሻ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ከዚያ ይልቅም ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ኃይል በመሸጥ ኢኮኖሚዋን ታሳድጋለች፤ ህዝቦቿንም ከድህነት ታወጣና በቀጠናው የበላይ ትሆንብናለች ከሚል ስጋት የመነጨ ነው። የዚህ ግድብ ኃይል ማመንጨት ደግሞ አረቦችንም ጨምሮ ሌሎች በኢኮኖሚ ያደጉ አገራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚበረታታ ነው። በተጨማሪም ከግብፅ ጋር ስታነፃፅሪው የተሻለ በቀላሉ ሊለማ የሚችል መሬት አላት። በርካታ አገራትን የምታዋስን አማካኝ ቦታ ላይ መሆንዋ ኃይል ማመንጨት ከቻለች ለእነዚህ አገራት
መሸጥ የምትችልበት እድሏ ሰፊ ነው። ይህም ደግሞ አገራቱ ኢትዮጵያ ላይ ትብብርን መሰረት ያደረገ የኃይል ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የራሱ አስተዋፅኦ አለው። ይህም ማለት በማመነጨው ኃይል ምክንያት ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላምና በትብብር የምትኖርበትን እድል ይፈጥርላታል።
የዚህ ግድብ ኃይል ማመንጨት የውጭ ምንዛሬ ክምችታችንን ከማሳደግ በተጨማሪ ከአገራት ጋር በሰላም ለመኖርና በአወንታዊ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም ማለት በድምሩ በቀጠና ውስጥ የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍ እያለ እንዲመጣ ያደርጋል። ኢትዮጵያ በፊትም ቢሆን ማንንም ለመጉዳት ተነስታ አታውቅም፤ አብረን እንልማ ነው ያለችው፤ ይህንን ደግሞ ማንም አያደርገውም። የኢትዮጵያን አብረን እንስራ የሚለውን ጥያቄ በእነሱ ያለመቀበል ምክንያት ነው የተናጠል ስራ እየሰራች ያለችው። ኢትዮጵያ በጋራ መስራት ተምሳሌት መሆን ነበር አላማ የነበራት። ግብፅ ግን የኢትዮጵያ በቀጠናው ጎልቶ መታየትና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆንን ስለማትሻ በአካባቢው የራሷን ህልውን ብቻ እያስቀጠለች መኖር ነው የምትፈልገው።
የእኛ ጠንክረን መስራት ደግሞ ያንን የግብፅን ፍላጎት ይቀለብሰዋል። በአገራት መካከል ያለው ግንኙነት ጥቅምን መሰረት ያደረገ ስለሆነ አረቦችም ቢሆኑ የተሻለ ነገር ካገኙ ወደእኛ የማይመጡበት ምክንያት የለም። ይህንን ደግሞ ግብፆቹም ስለሚያውቁ ነው የሚሰሩት። በአካባቢው ያሉ አገራት ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ካዞሩ የእነሱ የገቢ ምንጭ ይቀንሳል፤ የኢትዮጵያ የማደግ እድሏን ያጎላዋል። በአጠቃላይ ዋናው የግብፅ ዓላማ የውሃ መቀነስና ድርቅ ይከሰታል ከሚል ስጋት የመነጨ ሳይሆን የቀጠናው የኃይል ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ ያደላል ከሚል ፍራቻ የተፈጠረ እንጂ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ለመሆን የምትመጣበትን መንገድ ማቋረጥና ማደናቀፍ ነው ዋናው ፍላጎታቸው።
ኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህ ቀደምም በቀኝ ግዛት ያልተገዛች አገር ከመሆንዋ ጋር ተያይዞ ነፃነትን የማረጋገጥ ልበ ሙሉነትና ኩራት ላይ በመመስረት ጠንክራ የምትወጣ ከሆነ ለማንም የማታጎበድድ ጠንካራ አገር ሆኖ ስለምትወጣ አሁን ያለው የጂኦ-ፖለቲካ አስተሳሰብ ደግሞ ይህንን የማይደግፍ ስላልሆነ፤ ሁሉም ኃያል አገር የበላይ ሆኖ ለመቀጠል፤ ሌላው ደግሞ አሽከር እንዲሆን ይፈለጋል። ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን ፈፅሞ የማትቀበል አገር መሆንዋን ያውቃሉ፤ የዚህ ግድብ መገደብ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ተጨማሪ ኩራት ሆኗት ቀና የሚያደርጋት ሌሎችንም ድሃ አገራት ታነሳሳብናለች ብለው ይሰጋሉ። ይህ ደግሞ ስለማይፈለግ ግድቡን እውን እንዳይሆንና የአገራችን እንቅስቃሴ የማዳከም አላማ ነው ያለው። አሁን ደግሞ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ይህንን የግብፅ አቋም በግልፅ ማንፀባረቅ ደረጃ ላይ ደርሷል።
አዲስ ዘመን፡- የሶስተኛው ዙሩ ውሃ ሙሌት ከኢትዮጵያ ባሻገር ለተፋሰሱ አገራት የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– በመሰረቱ ግብፅና ሱዳን አባይ አለምአቀፋዊ መልክ እንዲኖረው በማድረግ ከአረቦች ጋር ያላቸውን የኃይል አሰላለፍ በማስጠበቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመቀጠል ነው የዘወትር ጥረታቸው። በተለይ ግብፅ የምዕራብ ዓለሙን ቀልብ ለመያዝ ስትል የተለያዩ ሴራዎችን እንደምትሰራ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል በምዕራቡና በአረቡ ዓለም መካከል እንደድልድይ በመሆኑ የእነሱ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆና ነው የኖረችው። በተለይ በእስራኤልና በአረብ አገራት መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ያላት ሚና ትልቅ ስለሆነ ምዕራባውያኑ የግብፅን ጥቅም እንዲከበር ነው የሚፈልጉት። ስለሆነም ሁልጊዜ የጫና በትራቸውን የሚያዞሩት ኢትዮጵያ ላይ ነው። አሁን ያለንበት ውስጣዊ ችግር ደግሞ ከእነሱ የበለጠ እኛን ተጋላጭ አድርጎናል።
የግድቡ መሰራትም ሆነ የውሃ ሙሌት መከናወኑ ጉዳት እንደማያደርስባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተለይ በየአመቱ በሚካሄደው የውሃ ሙሌት የተመጣጠነ ውሃ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ግን እነሱ ጥያቄያቸው ውሃ ከማግኘትና ካለማግኘት ጋር የተያያዘ አይደለም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ በቀጠናው ተፅዕኖ ፈጣሪነታችን ኢትዮጵያ ትቀማናለች የሚል ከባድ ፍራቻ ስላለባቸው ነው። ግብፆች በአረቡም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ያላቸው ተሰሚነት እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ለመልማት የምታደርገውን ጥረት ማደናቀፍ ነው የሚፈልጉት።
ይህንን ካደረጉ ደግሞ ኢትዮጵያ ሃይል በማመንጨት የጎረቤት አገራትን የኃይል ፍላጎት በማሟላት በቀጠናው ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍ እንደሚልና እነሱን የሚፈልግ ላይኖር እንደሚችል ያውቁታል። በነገራችን ላይ በአካባቢው ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ መቀጠል የህልውና ጉዳይ ነው። ምዕራባውያኑም ቢሆኑ ግንኙነት መፍጠር የሚፈልጉት ለእነሱ ከሚያጎበድድ ጋር ነው። እውነታው ግን አንዱ ብቻውን ሁሉም ነገር በበላይነት በመቆጣጠር ሳይሆን ሁሉም በትብብር፤ ሰጥቶ በመቀበል በጋራ መስራት ሲቻል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን በመጠቀም ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ትንኮሳ የግድቡን ግንባታ በተለይ የውሃ ሙሌቱን የማደናቀፍ አንዱ ሴራ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ አኳያ ሊሰራ ይገባል የሚሉት ነገር ምንድን ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡- ግብፅም ሆነች ሱዳን ግድቡ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ ግንባታውን ለማደናቀፍ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። በውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትም ሆነ ቀጥታ ትንኮሳ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ከግድቡ ላይ እንዲነሳ ግንባታው እንዲስተጓጎል በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል። በሌላ በኩል ግን እነሱ እኛ ላይ ትንኮሳ ባደረጉ ቁጥር የየራሳቸው ውስጣዊ የፖለቲካ ችግር ሲቀሰቀስ ይታያል። አሁንም በሁለቱም አገራት ውስጥ ከፍተኛ የሚባል የፖለቲካ ተቋውሞ በመንግስታቱ ላይ እየቀረባባቸው ይገኛል። ሰሞኑን እንኳን ብታዩ የግብፅም ሆነ ሱዳን አደባባዮች ከፍተኛ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎችን እያስተናገዱ ነው ያሉት። ህዝባዊ ተቋውሞ እየበረታባቸው ነው ያሉት።
አንቺ እንዳነሳሽው ሱዳን በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳ እያካሄደች ነው ያለችው። ይሁንና የዚህ ትንኮሳ አላማ የሱዳን ህዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ለዚህ ደግሞ እንደሚታወሰው የሱዳን ህዝብ ከአንድም ሁለት ጊዜ የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ትንኮሳ በመቃወም ‹‹ኢትዮጵያኖች ወንድሞቻችን ናቸው፤ ከኢትዮጵያ በሰላም መኖር ነው የምንፈልገው›› ብለው ሰልፍ ወጥተዋል። በመሰረቱ ሁልጊዜ ኢትዮጵያንና ግድቡን ምክንያት አድርጎ ግጭት መፍጠር የሱዳንም ሆነ የግብፅ መንግስታት ያለባቸውን ውስጣዊ ተቋውሞ አጀንዳ ለማስቀየር የሚጠቀሙበት ዘዴም ነው። ይሁንና እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ህዝባዊ ተቋሞው እየጨመረባቸው ነው የመጣው። ሱዳን ላይ ሰሞኑን የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ህዝቡ ከቤቱ ወጥቶ በከፍተኛ ደረጃ ተቋሞውን እየገለፀ ነው።
በአልቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ መንግስት ተደጋጋሚ ትንኮሳ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይ ይህ ሰው የግብፅ ተላላኪ እንደመሆኑ ወደ ፕሬዚዳንትነት ከመምጣቱም በፊት አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት እንድትፈጥር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ነበር። እንደሚታወቀው በአልቡርሃን የሚመራው የሱዳን መከላከያ ወደ ኢትዮጵያ መሬት ግዛታቸውን በማስፋፋት እኛ ላይ ወረራ አካሂዷል። ይህ ብቻ ሳይሆን በወረሩት መሬት ላይ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት በመገንባት ለመሬት ባለቤትነታቸው ማረጋገጫ የሚሆን ማስረጃ አበጅተዋል። ይህም ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ማሳመኛ ነው የሚሆናቸው። በአጠቃላይ እነሱ የሚከተሉት የብልጥት አካሄድ ነው።
በመሰረቱ የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ሱዳን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት እንደአጋጣሚ በመጠቀም ነው የግዛት ማስፋፋት ዓላማዋን ማከናወን የቀጠለችው። ኢትዮጵያ ደግሞ እስካሁን ድረስ ይሄ ጉዳይ በሁለቱ አገራት መካከል በንግግር መፈታት አለበት የሚል መንግስታዊ አቋም ነው እያራመደች ያለችው። በተቃራኒው የሱዳን መንግስት በወረረው የኢትዮጵያ መሬት ላይ ድልድይና የመሳሰሉትን መሰረተ ልማቶች እየገነባ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ወደፊት ድርድር ሲካሄድ ‹‹የእኛ መሬት ነው›› ለማለት ጥሩ ማስረጃ እንዲሆናቸው ነው።
ከዚያ ባሻገር በግብፅ ረዳትነት አካባቢው የብጥብጥ ቀጠና እንዲሆን በማድረግ የግድቡን ግንባታ ማስተጓጓል እኩይ የሆነ አላማቸውን እውን ለማድረግ እየሰሩ ነው። ሌሎች ታጣቂ ሃይሎችንም ጭምር በመደገፍ፤ በማሰልጠንና ትጥቅ ጭምር በመስጠት ኢትዮጵያን በማወክ ለግድቡ በመንግስት ትኩረት እንዲያጣ የማድረግ፤ ብሎም ከፕሮጀክቱ የሚመጣውን ትሩፋት እንዳንጠቀምበት ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው። ስለዚህ ይሄ የሱዳን ፀብ አጫሪነት እንቅስቃሴ የድንበር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሰላም እንዳይጠናቀቅ የትልቁ ሴራ አካል ነው። ለዚህ ደግሞ ሁለቱም አገራት አቋማቸውን በተለያየ አጋጣሚ አሳይተዋል።
የቀኝ ግዛት ስምምነታቸውን ለማስጠበቅና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ አለምአቀፍ ጫና የመፍጠር ስራ ውስጥ የሚካተት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ይህ አላማቸው እንዳይሳካላቸው የሚቻለውን ጥረት እያደረገ ነው። እርግጥ የሶስትዮሽ ድርድሩ ከተካሄደ አንድ ዓመት አልፎታል፤ የመጨረሻው ስብሰባው በኮንጎ ኪንሻሳ ነበር የተካሄደው፤ በወቅቱ የኮንጎ ፕሬዚዳንት እውነታውን በመረዳታቸው የአባይ መገደብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው አገራት የኃይል አውታር በመሆንና የተረጋጋ ቀጠና እንዲኖር ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የተናገሩት። እንዳውም ከህዳሴው የሚገኘው ኃይል ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና አንድ ግብዓት እንደሚሆን አስረግጠው ተናግረዋል።
ግብፅና ሱዳን በጋራ የመጠቀምና የመልማት ሃሳብን ለመቀበል እንደተለመደው ሳይቀበሉት ቀርተዋል። በተለይ የግብፅ መንግስት የሱዳን መንግስትን ተላላኪ በማድረግ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋና የሚሰራውንም ስራ ለማኮላሸት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ነው የምረዳው። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት። በተጨማሪም የሱዳንን ተንኳሽ ድርጊት ዝም ብሎ ከመመልከት ይልቅ ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ በመስጠት ልክ እነሱ እንደሚያደርጉት ሁሉ መሬታችን ላይ መሰረተ ልማት ግንባታ በአፋጣኝ ማከናወን ይገባናል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ካይሮ ላይ በሚካሄደው የአፍሪካ ክላይሜት ሞቭሊቲ ኢንሺቲብ አለምአቀፍ ጉባኤ የግብፅ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ነጥብ ለማስቆጠር እያደረገ ያለውን ዝግጅት እንዴት ያዩታል? በኢትዮጵያ በኩልስ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– የአፍሪካ ህብረት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመሆንና የአየር ንብረት ለውጥ ያተኮረ ስራ በአፍሪካ የሚሰራ ድርጅት ነው። ይህ ኢኒሼቲቭ ከዚህ ቀደም ኮፐንሃገን ዴንማርክ ሲካሄድ እንደነበረው ትልልቅ አለምአቀፍ ኮንፍረንሶች የተስተካከለ አፍሪካ ውስጥ በተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ማጠናቀቂያ ግብፅ ውስጥ ይካሄዳል። የዚህ ኮንፍረንስ ዋና አላማ ከዚህ ቀደም ብዙ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣውን ተጽዕኖ በሚመለከት ጥናቶች ተካሂደው ተተችተዋል። የእነዚህ ጥናቶች ውጤትና ምክረ ሃሳብ ቀጣይ አቅጣጫን የሚጠቆምበት ጉባኤ ነው የሚሆነው።
ግብፆች ይህችን አጋጣሚ በመጠቀም የህዳሴ ግድቡ በቀጠናው የአየር ንብረት ለውጥ የሚኖረውን አሉታዊ ሚና የሃሰት ትርክት በማዘጋጀት ላይ ናቸው። በዚህ ግድብ ምክንያት ግብፅ ምንያህል አደጋ ውስጥ እንደሆነች፤ ድርቅ ህዝቧን አደጋ ውስጥ የከተተባት መሆንዋን፤ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግድብ የውሃ እጥረት እንዲከሰት ስለማድረጉ፤ በኢኮኖሚው የተጎዳውን ህዝብ የበለጠ ችግር ውስጥ የሚከት ስራ እየሰራች ነው። ኢትዮጵያ አሳሪ የሆነ ስምምነት ላለመፈፀም በእምቢተኝነትና በአሻፈረኝነት መንፈስ ግብፃውያንና ሱዳናዊያንን የሚጎዳ ስራ እየሰራች ነው የሚል ክስ እያዘጋጀች ነው ያለችው።
በዚህ ጉባኤ ላይ ይህንን ሃሰተኛ ትርክቷን በደንብ በማጠናከር እንዲሁም በዩክሬንና ራሺያ ጦርነት ምክንያት የምግብ እህልና የነዳጅ ዋጋ ንረት ያመጣውን ተፅዕኖ ጨምረውበት ያው እንደለመዱት የተጋነነ፤ ስር መሰረት የሌለው ክስ የሚያቀርቡበት ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት እዲቀጭጭ ስራ ለመስራት እየተዘጋጁ ነው ያሉት። የአውሮፓ ህብረት መግለጫ እስከማውጣት የደረሱበት የዚሁ ሴራ አንድ አካል ነው።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ከተያዘው የእሳት ማጥፋት ዘመቻ ያለፈ ስራ መስራት አለበት። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ብዙ ምክረሃሳብ ሰጥተናል። እነሱ እንደሚያደርጉት በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ መሰራት አለበት ሲባል ከርመናል። መንግስት፤ መንግስታዊ ያልሆኑ፤ ኢትዮጵያን የሚወዱ ሰዎች በአንድ ላይ ሆነው የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ በተለይም የአባይ ውሃ ጥቅም ላይ እንዲውል መስራት አለባቸው ይባላል።
እውነቱን ለመናገር ግን እስካሁን ጠብ ያለ ነገር አላየሁም። ጥናትና መረጃን መሰረት ያደረጉ ስራዎችም እምብዛም እየተሰሩ አይደለም። በዘርፉ ያሉ ምሁራንም ምክክርና ጥናት በማድረግ በጋራ ሲሰሩ አላየንም። አሁንም ቢሆን አልፎ ቦግ እልም ከሚል ስራ ባለፈ ተመጋጋቢ የሆነ የግብፅን እንቅስቃሴ የሚመጥን ስራ እየሰራን አይደለም። በመሆኑም በመንግስት አስተባባሪነት ዘላቂና የአገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ስራ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2014