ኢትዮጵያ በመንግስት የዘመን አቆጣጥር ደረጃ የምትቀበለው ከዓለም ሀገራት የተለየ የዘመን አቆጣጥር አላት። ይህንንም የራሷ መለያ አድርጋ 13 የፀጋ ወራት በሚል ስትጠቀም ኖራለች። የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር መሰረት፣ ስሌት እና ከሌሎች የዓለም ሀገራት የተለየበትን ምክንያት በተመለከተ የባህረ ሃሳብ ባለሙያ ከሆኑት መምህር ሔኖክ ያሬድ ፈንታ ጋር የዝግጅት ክፍላችን ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡– በቅድሚያ ስለኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ይንገሩን?
መምህር ሔኖክ፡– ኢትዮጵያ ከተወሰነ ዓመታት ወዲህ እንደራሷ መለያ አድርጋ ከምትጠቀማቸው፣ አንዱ ምድረቀደምት የሚለው ስያሜ ነው። ምድረ ቀደምት ከሚያሰኛት አንዱ ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠሯ ነው። ይሄም ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረ ነው። ከ60 ዓመታት በላይ የቱሪዝም ማስታወቂያ የነበረው 13 የፀጋ ወራት ተብሎ የሚታወቀውም አንዱ መለያችን ሆኖ ቆይቷል።
በእርግጥ ጥንታዊያን ይሄን የ13 ወር አውድ ይጠቀሙ ነበር፤ በግዜ ሂደት ትተውታል። በአሁን ግዜ በሀገር፣ በመንግስት እና በቤተክርስትያን ደረጃ 13 ወር በማለት ኢትዮጵያ ትለያለች። ግብፅ በመንግስት ደረጃ ባይጠቀሙም የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ግን 13 ወር በማለት ትጠቀማለች።
13 ወራት ስንል አንዳቸው 30 ቀናት ያሉት 12 ወራት አሉት፤ የመጨረሻው ደግሞ አምስት ወይም ስድስት ቀን አለች። ለዚህ ነው እንግዲህ ይችን ንውስ ወር ልዩ የሚያደርጋት እና ጳጉሜን ብለን የምንጠራት። ስለዚህ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ብለን ስናስብ መነሻ የሆኑ የተለያዩ አቆጣጠሮችን ጭምር በማሰብ ነው።
በዓለም ዙሪያ መደበኛው ካሌንደር እኛም ጋር በተጓዳኝ ያለው የጊርጎሪያን አቆጣጠር ነው። በልማት የአውሮፓውያን አቆጣጠር ተብሎ የሚታወቀው፤ በዓለም ሁሉም የራሱ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር ቢኖረውም በመደበኛነት የጊርጎሪያን ዘመን አቆጣጠር ይጠቀማሉ።
የጊርጎሪያን የዘመን አቆጣጠር ለመጠቀም መሰረት የሚያደርገው አቆጣጠሩ እራሱ ከቤተክርስትያን አቆጣጠር ጋር የተያያዘ ነው። ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር ተያይዞ ነው የሚቆጥረው። ልክ ለዓለም ሁሉ ጊርጎሪያን መሰረት እንደሆነው፤ ለኢትዮጵያም የዘመን አቆጣጠር መሰረት የሆነዉ የቤተክርስትያን አቆጣጠር ነው።
ስለዚህ አሁን የምንቀበለው አዲሱ ዓመት 2017 ዓ.ም ብለን እንጠቅሳለን። 2017 ስንል ከጌታችን ልደት ተነስተን የምንቆጥረው፤ ከመስከረም አንድ ጀምሮ የምናወሳው መንገድ ነው። ይህ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ የምንቆጥርበትም መንገድ አለ። ይህ ደግሞ ዓመተ ዓለም ተብሎ የሚታወቅ ነው።
ዓመተ ዓለም ማለት ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን 5500 ዓመት ላይ 2017 ስንደምር 7517 ዓመተ ዓለም፤ በኢትዮጵያ አነጋገር ስምንተኛው ሺህ ማለት ነው። ስምንተኛው ሺህ የገባው አንድ ሺህ 501 ዓ.ም ላይ ነው ። አሁን ስምንተኛው ሺህ ከገባ 517 ዓመት ላይ እንገኛለን።
ስለዚህ የዓመተ ዓለም አቆጣጠር አለን፤ የዓ.ም አቆጣጠርም አለን። ይሄ በፀሀይ ላይ የተመሰረተው አቆጣጠራችን ነው። የቀኑን ብርሃን የቀን ቁጥር ብለን እንደምንቆጥረው ሁሉ፤ የማታው ደግሞ የራሱ የሆነ ቁጥር አለው። የማታው አቆጣጠር ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን የሚያገናኝ ጭምር ነው። በተለይ ቤተ እስራኤሎች፣ አይሁድም በጨረቃ ነው የሚቆጥሩት፤ የሙስሊም ወንድሞችም በሂጅራ ሲቆጥሩ ጨረቃ ነው የሚጠቀሙት።
ስለዚህ በጨረቃ አቆጣጠር ደግሞ ተመሳሳይነት አለ። ፀሀይ፣ ጨረቃ እና ከዋክበት የተፈጠሩት ለብርሃንነት ነው። ስለዚህ የጨረቃ አቆጣጠርም አለ። የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ስንል የፀሀዩን ብቻ እናነሳና 2017 እንላለን። ሌላው በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ውስጥ ከጨረቃ ጋር የተያያዙ በዓላትን የምንለይበት የጨረቃና የፀሀይ ጥምር አቆጣጠር አለ። ይሄ ‹‹ዩኒሶላር›› የምንለው ነው።
አምና 2016 ዓ.ም ፋሲካ ሚያዚያ፣ 27 ነው የዋለው። በጨረቃ ምክንያት ዘንድሮ 2017 ሚዚያ 12 ነው የሚውለው። መስከረም አንድ ቀን በፀሀይ
አቆጣጠር 2017 ዓ.ም ገብቷል። በፀሀይና በጨረቃ ጥምር አቆጣጠር 2025 ዓ.ም ገብቷል። ስለዚህ ሁለት ምሶሶዎች አሉ ማለት ነው።
ቤተክርስትያን ደረጃ ሁለቱንም አቆጣጠር እንጠቀማለን። በሕዝብ አቆጣጠር ግን መስከረም አንድ እንቁጣጣሽ ብለን አዲስ ዘመንን 2017 ብሎ ተቀብሏል። በተክርስትያን መሰረት ሆና ይሄንኑ መስከረም አንድ ስትቀበል ስም አላት፤ ቅዱስ ዮሐንስ ብላ ትጠራዋለች።
እያንዳድኑን ዓመት ደግሞ በቤተክርስትያን ደረጃ በወንጌላውያን ስም ትሰይመዋላች። አሁን በሸኘነው 2016 ዮሐንስ አበቃ፤ በዚህም የአራት ዓመት ዙር አብቅቷል። አሁን አዲስ አራት ዓመት ነው ምንጀምረው። መደበኛውንም አቆጣጠር ያስገኘው የቤተክርስትያኑ አቆጣጠር ነው ብለን መግለጽ እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡– በጨረቃና በፀሀይ ጥምር አቆጣጠር 2025 መሆኑን ገልጸዋልና፤ ይሄኛው አቆጣጠር በሕዝብ በዙም አይታወቅም። እንዴት ነው ስሌቱ?
መምህር ሔኖክ፡– መሰረቱ ኦሪት ዘፍጥረት ላይ፤ መጀመሪያ እግዚያብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ብሎ፤ ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃን ሆነ። በአራተኛው ቀን ብርሃናትን ለያቸው። ትልቁ ብርሃን ፀሀይ ቀንን እንዲገዛ፤ ትንሹ ጨረቃ ከከዋክብት ጋር ምሽትን እንዲያስተዳድር አደረገ። እነዚህን ፀሀይ፣ ጨረቃ እና ከዋክበት ለአራት ነገር ነው የተፈጠሩት።
አራቱ ነገሮች ምንድናቸው፤ ምልክቶች አለ፤ ምልክቶች ሲል በዓሎች፣ ጾሞች እና ለአራቱ ወቅቶች፤ በእኛ ክረምት፣ መጸው፣ በጋ እና በልግ የሚባለው ነው። በፀሀይ ዓመት ላይ የተመሰረተው አቆጣጠር እነዚህን አራቱን ወቅቶች ያፈራርቃል። ሌላኛው ደግሞ ለእለታት አለ፤ አንድ ሳምንት ሰባት ቀን፣ አንድ ወር 30 ቀን፣ አንድ ዓመት 365 ቀን በፀሀይ፣ በጨረቃ 354 ቀን ነው። የጨረቃ ኡደት አጭር ነው ከፀሀይ በ11 ቀን ልዩነት አላት።
መሬት ፀሀይ ዞራ የምትፈጽምበት 365 ቀን ከስድስት ሰዓት ነው። ስለዚህ ይህ ስድስት ሰዓት በአራት ዓመት አንዴ ጳጉሜ ስድስት ቀን እንዲሆን ታደርጋለች፤ አራት ጊዜ ስድስት 24 ሰዓት ሆና።
ሙስሊሞች ጨረቃን አይተው ጾም ይይዛሉ። እኛም ኦርቶዶክሶች ጨረቃን አይተን ጾም እንይዛለን። የአይሁዶችን እንደዚሁ ነው። ፋሲካና የዓብይ ጾም የሚቀያየረው ከጨረቃ ጋር ተያይዞ ስለሚቆጠር ነው። ስለዚህ ይህን ለማወቅ የጨረቃና የፀሀይ ጥምር አቆጣጠር አለ። 2017 ዓ.ም ላይ ስምንት የምንደምርበት የጨረቃዋን ኡደት አምጥተን ነው።
ጨረቃ መጀመሪያ ጭረት ነች፣ ከዛን ማጭድ፣ እሩብ እየሆነች፣ አጋማሽ ……እየሆነች መጨረሻ ላይ ሙሉ ትሆናለች። ከዛ ደግሞ እየጎደለች ትሄዳች። ስምንትን የምንደምረው የጨረቃዋን ኡድት መሰረት አድርገን ነው። ስምንት ቋሚ ቁጥር ናት። ስምንት ሁልግዜ በየዓመቱ ትደመራለች ምክንቱም የጨረቃን ስሌት ስለምታመጣ። 2017 ብቻውን አያመጣም።
የሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ላይ “ቀንንና ወርን ዘመንን፣ ዓመትን በጥንቃቄ ትጠብቃላቹ” ይላል። ምክንያቱም ጨረቃን አይተን ነዋ። ጨረቃ ኡደቷ 29 ነጥብ አምስት ነው። 29 ነጥብ አምስት ሲባዛ በአስራ ሁለት ወራት 354 ይመጣል። ስለዚህ መስከረም አንድ ላይ 2017 እና 2025 ዓ.ም ገብቷል፤ 7517 ዓመተ ዓለም ገብቷል እንላለን።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌሎች የዘመን አቆጣጠር የተለየበት ምክንያት ምንድ ነው?
መምህር ሔኖክ፡– ማንም ሕብረተሰብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር አለው። መደበኛ የሆነው አቆጣጠር የመጣው የክርስቶስን ልደት ተከትሎ ነው። አውሮፓውያኑ መነሻ የሚደርጉት እና እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው አቆጣጠራቸው ከሮም ከተማ ጋር ተያይዞ ነው። ሮም ከተመሰረተችበት ዓመት አንድ ብለው ነው የሚጀምሩት።
ጌታችን ሲወለድ ሮም በተመሰረተች 753 ዓመት ላይ ነው። ዲዮናሲዮስ ኤግስጊዮስ የሚባል እስክንድርያ በመሄድ በ532 ዓ.ም አምኖ ዶሚኒ (ኤ. ዲ) ወይም የጌታ ዓመት በማለት አቆጣጠሩ ከጌታ ልደት ጋር ተያይዞ እንዲነሳ አደረገ። በተለይ የፋሲካ ቀን አወጣጥን ተከትሎ የእስክንድሪያ ጳጳሳት ናቸው የሚያወጡት። ከእነሱ ነው ያጠናው።
በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እነ አባ ዲሜጥሮስ የተከሉት ቱፊት ቀጥሎ፤ እሱ ሄዶ ያንን ሲያጠና፤ ‹‹የሶላርን ››እና ‹‹የዩኒሶላርን›› አቆጣጠር ነው ያሳዩት። እሱ በሄደበት ወቅት በፀሀይ 524 ነው። በጨረቃ እና በፀሀይ ጥምር አቆጣጠር ደግሞ 532 ዓመት ነው። እሱ ግን ስምንት የሚደመርባት አቆጣጠር ያዘና በዛው ቀጠለ።
ከዛን ለዓለምም አስተዋወቀው፤ ሌሎች ዓለማት ‹‹ዩኒሶላሩን››፤ ‹‹ሶላር›› አድርገው ነው የቀጠሉት። እኛ ግን ሁለቱንም ጎን ለጎን አድርገን ነው የቀጠልነው። ልዩነቱ የመጣው ለዚያ ነው።
ከዛ ደግሞ የወር አመዳደባችን ይለያል፤ የዓመት መነሻችንም ይለያያል። የእነሱ ድሮ መጋቢት ላይ ነበር፣ አሁን ጥር ላይ ነው። የወራቱን ስያሜ በነገስታቱ ስም፣ ነው ያደረጉት፤ በእነ አውግስቶስ፣ በጁለሴ፤ አድርገው ከፋፈሉት፤ በተረፈ በቁጥር ስም ነው የነበረው። ‹‹ሴፕቴምበር›› ሲል ሰባት ነው፤ ‹‹ኦክቶበር›› ሲል ስምንት ….ነው። የወሩን መደብ 31፣ 28 አድርገው በመቁጠር አነስተኛ ወሯን እንድትቀር አደረጓት።
በጥንት በተለያዩ ሕብረተሰብ ውስጥ የ13 ወር አቆጣጠር አለ። ኢትዮጵያውያን ጥንታዊነቱን ይዘን ነው የቀጠልነው። ስለዚህ እኛ አንድ ወር 30 ቀን እና 12 ሲባዛ በ30 ቀናት 360 ሲደመር አምስት ቀን ከሩብ ብለን ይዘናል። እነሱ ግን በታትነውታል አንዱ ይሄ ነው ልዩነታችን።
እነሱ ሁልግዜ ጥር አንድ ቀን አዲሱ ዓመት ነው ይላሉ፤ እኛ ደግሞ መስከረም ላይ ነው አዲስ ዓመት የምንለው። ይሄ ደግሞ ልዩ ገጽታ ነው። ከክረምቱ በኋላ፤ ብራ የሚሆንበት፣ አበቦች የሚፈኩበት እና ግልጽ ያለ የጠራ ሰማይ የሚታይበት ስለሆነ የተለየ ያደርገዋል። ለጊርጎሪያን ካሌንደር መነሻው ጁሊያን ካሌንደር ነው።
በዓመተ ዓለም አቆጣጠር እኛ 7517 ዓመተ ዓለም ስንል በእነሱ 4400 እንደዛ አካባቢ ነው። አንግሊካል ደግሞ 4004 ዓመተ ዓለም ነው። 4004 ላይ 2024 ብንደምር ለእነሱ 6028 ዓመተ ዓለም ነው። እነሱ ሰባተኛው ሺህ ላይ ናቸው። እኛ ደግሞ 7517 ዓመተ ዓለም ላይ ነን። እኛ ደግሞ ስምንተኛው ሺህ ላይ ነን ያለነው።
አዲስ ዘመን፡–ኢትዮጵያውያን የፀሀይን አቆጣጠር እና፣ የጨረቃንና የፀሀይን ጥምር አቆጣጠር ይዘን ነው የቀጠል ነው። ከዚህ በፊት የነበረው የቀን አቆጣጠር ስሌቱ ብቻ ነበር ወይስ ወቅቱኑ በማከለ መልኩ ነው ስሌቱ የተስተካከለው?
መምህር ሔኖክ፡– የወቅት ጉዳይ አደለም፤ ወቅቶች እራሳቸውን የቻሉ ናቸው። የሚገኙትም በፀሀይ ነው። በጨረቃ ካሌንደር ውስጥ ወቅት የለም። ለምሳሌ ሙስሊሞች ረመዳንን ጾመው ነው ኢድ አል ፈጥርን የሚያከብሩት፣ በ33 ዓመት ኡደት ውስጥ 12ቱም ወር ይደርሰዋል። ምክንያቱም ጨረቃዋ በጋውም ላይ፣ ፀደይ ላይም ይሄዳል መጸው ላይ ይሄዳል፣ በክረምትም እንደዛው ይሄዳል።
አሁን ፋሲካ ከመጋቢት 26 በታች አይወርድም ከሚያዚያ 30 በላይ አይወጣም፤ ወቅቱ ደግሞ ጸደይ ነው አይለቅም። የፀሀይና ጨረቃ አቆጣጠር በሕዝብ አቆጣጠር ውስጥ የለም። ወደ ሃይማኖታዊ አቆጣጠር ስንገባ በእስልምናም በክርስትና እና በአይሁድ ሃይማኖቱን ተከትለው የሚመጡ በዓላት አሉ። ስለዚህ የፀሀይና ጨረቃ አቆጣጠር የምናስበው ከቤተክርስትያን አቆጣጠር ጋር ነው።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ስሌቱ እንዴት ነው?
መምህር ሔኖክ፡– አንደኛው ከጥንተ ፍጥረት፤ ኢትዮጵያ ክርስትናን ከመቀበሏ በፊት የንጉስ ሰለሞንን
ግኑኝነት፣ ቀዳማዊ ምኒሊክን ተከትሎ የአይሁድ እምነት አለ። እምነቱ ካለ ደግሞ የዘመን አቆጣጠሩ እና በዓል አከባበር አለ።
ስለዚህ አንደኛው የዘመን አቆጣጠር የሚነሳው ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ ነው። የፍጥረት የዘመን አቆጣጠር የምንለው ከክርስቶስ ልደት በፊት 5501 ብሎ የሚነሳው ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት ካለው ዘመን ይነሳል። ሁለተኛው ከክርስቶስ ልደት ዘመን ወዲህ ያለው ብለን የምንቆጥረው ነው።
የፈረንጆቹ የቀን አቆጣጠር የሚጀምረው ጥር የመጀመሪያው ወር ብሎ ይጀምርና ታህሳስ ላይ ይጠናቀቃል። የኢትዮጵያ ደግሞ መስከረም አንድ ብሎ ይጀምርና ጳጉሜ ላይ ያልቃል። ሌላው በየአራት ዓመቱ ሰግር የምንለው ጭማሪ አንድ ቀን አለች።
ስሌቱ ከጥንተ ፍጥረት ይነሳል፣ ከክርስቶስ ልደት ጀምሮ ይነሳል። እያንዳንዱ ወር 30 ቀናት አሉት። ከዛን የወሩ ስያሜ ደግሞ ከእርሻ ጋር የተያያዘ ነው። ጳጉሜ ደግሞ 360 አብቅቶ ሌላኛውን 360 ለመረከብ እንደ አረካካቢ አድርገን ማየት እንችላለን። ሌላው አቆጣጠር ደግሞ የሃይማኖታዊ በዓላትን ለመለየት የምንጠቀምበት ነው። ስሌቱ የተመሰረተው በፀይና በጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከሌሎች ዓለማት የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ልዩነቱ ምንድነው?
መምህር ሔኖክ፡-መሬት በራሷ ዛቢያ ስትዞር አንድ ቀንን ታስገኛላች። በፀሀይ ዛቢያ ስትዞር 365 ቀን ከስድስት ሰዓት ነው። እስከ 16 መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ምዕራቡ ሆነ ሁላችንም በዚሁ ሁኔታ ነበር ስንቆጥር የቆነው። ንጉስ ጊርጎር በተነሱበት ዓመት ሊቃውንቱ ተሰብስበው፤ መሬት ፀሀይን ምትዞርበት 365 ቀን ከስድስት ሰዓት ነው የሚለውን መረመሩ። 365 ቀን 5 ሰዓት ከ48 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ነው በሚለው ተማመኑ ።
ያለአግባብ ቀን ተጨምሯል በማለት የጁሊያን ካሌንደር እንከልሰው በማለት ከለሱት። ለቤተክርስትያን አቆጣጠር መሰረት የሆነው በ325 ዓ.ም ኒቂያ ላይ የተደረገው ጉባኤ ነው። ሊቃዉንቱ ከ325 እስከ 1582 ያሉት ዓመታት ላይ ያለአግባብ ተጨምሯል ያሉት 11 ደቂቃ ሲሰበሰብ 10 ቀን ወጣው።
ያለአግባብ ነው 10 ቀን የተጨመረው፤ ምን እናድርግ አሉ ። ከዛን ጥቅምት 4 በማግስቱ ጥቅምት 5 መሆን ሲገባው 10 ቀን ጨመሩና ጥቅምት 15 ብለው መቁጠር ጀመሩ። ይህን ውሳኔ ምስራቆቹ አልተቀበሉትም፤ ምዕራቦቹ ተቀበሉት። መስከረም አንድ 2017 በጁሊያን ካሌንደር ነሐሴ 29 ነው። በጊርጎሪያን ካሌንደር መስከረም 11 ነው።
አዲስ ዘመን፡– ጳጉሜ አንዳንድ ግዜ ሰባት ቀን ትሆናለች የሚባል ነገር አለና፤ መቼ ነው የምትሆነው?
መምህር ሔኖክ፡– ጳጉሜ ሰባት ቀን ሆና አታውቅም። ምንድነው ጨረቃ ምድርን የምትዞርበት 354 ብቻ አይደለም ትርፍራፊ ሰዓት አላት ልክ ፀሀይ እንዳላት ሁሉ፤ እሱን ሰብስበው በ600 ዓመት አንድ ግዜ ጳጉሜ ሰባት ትሆናለች ይላሉ። ይሄ ደግሞ ስላልተመዘገበ አይሆንም። የፋሲካ ሰንጠረዥ አለ፤ በዚህ ላይ ጳጉሜ ከጥንት ጀምሮ አምስት እና ስድስት ብቻ ነው።
ለቀን አቆጣጠሩ የራሱ የሆነ ኡደት አለ። የሰባት ቀን፣ የ30 ቀን፣ የ365 ቀን፣ የአራት ዓመት፣ የዘጠኝ ዓመት፣ 28 ዓመት፣ የ76 ዓመት ኡደት ሲሆን ትልቁ ቀመር ደግሞ 532 ዓመት ወስጥ ነው የሚመላለሰው። ስድስተኛዋ ቀን ጳጉሜ መሪያ ትባላለች የምታዘዋውር ማለት ነው። ዓመቱ በዋለበት ቀን ተመልሶ እንዳይውል የም ታደርግ ናት።
በ532 የሚዘዋወረው የዘመን ኡደት ውስጥ ጳጉሜ አምስት፣ አምስት፣ አምስት፣ ስድስት ነው የሚሆነው። ሰባት የሚል ሰንጠረዥ ውስጥ የለም። ጳጉሜን ስድስት እራሷን ችላ ቀን አይደለችም። ከ365 ቀን የምትተርፈው ስድስት ሰዓት ተደምራ ነው በአራት ዓመት አንዴ ስድስት የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡–ጳጉሜ ስድስት ሲሆን ገና ታህሳስ 28 ነው የሚከበረው። ይሄ ከምን የመጣ ነው?
መምህር ሔኖክ፡–ጳጉሜ 5 እና የጌታ ልደት አንድ አይነት ናቸው። በቤተክርስትያን ስርዓት ጳጉሜ 5 ልደት ናቸው። ስለዚህ ሁልግዜ ጳጉሜ አምስትና ልደት ተመሳሳይ ቀን ነው የሚውሉት። 2016 ጳጉሜ 5 ማክሰኞ ነው የዋለው። ታህሳስ 29፣ 2017 ማክሰኞ ነው የሚውለው። አንድ ዓመት 52 ሳምንት ከአንድ ቀን ነው።
ስለዚህ ከ52 ውስጥ የሌለችው ልዩዋ ቀን ጌታ የተወለደባት ቀን ናት። ጳጉሜ ስድስት ሲሆን በ28 የሚውለው ከጳጉሜ አምስት ጋር ለማናበብ ነው። ለሎች ቱፊቶች ቢኖርቱም ዋና ቱውፊቱ ይሄ ነው። የፈረንጆቹ ታህሳስ 25 አይለቅም ምክንያቱም የእነሱ ጭማሪዋ ቀን እንደኛ በዓመቱ መጨረሻ ስላልሆነች።
አዲስ ዘመን፡– የዘመን አቆጣጠሩን ስንረከብ የጳጉሜ ቀናት እንደ ኢትዮጵያ በዓመት መጨረሻ ላይ ነው። ወይስ እንደፈረንጆቹ በእያንዳንዱ ወር ላይ ተደምሮ እና ተቀንሶ ነው?
መምህር ሔኖክ፡– አንድ ወር 30 ቀን አንድ ዓመት 12 ወር የሚለው ብሂል ጥንታዊ ነው። አንድ ወር 30 ቀን ማለት ከዚሁ ከአፍሪካ የበቀለ ነው። ከጥንት ከግብጻውያን ጋር እና እኛም ጋር ከአባይ ወንዝ ጋር ተከትሎ የመጣ ነው። ለሌላው የቀን አቆጣጠርም መነሻ የሆነው።
አዲስ ዘመን፡– ጳጉሜ አምስት ወይም ስድስት ቀን ናት፤ እንዴት 13 ወር ሊባል ቻለ?
መምህር ሔኖክ፡– ጳጉሜ ማለት የግሪክ ቃል ነው። የፀሀይ ኡደት 365 ቀን ነው። አንድ ወር በ30 ቀን መስከረም ጀምሮ ነሐሴ ላይ ያበቃል። የጨረቃ ደግሞ ነሐሴ 24 ያበቃል። ነሀሴ 25 በጨረቃ ስሌት መስከረም ወር ነው። ለፀሀይ ግን አምስት ቀን ትርፍ አላት።
ስለዚህ 13ኛዋን ተውሳክ፤ በመጨረሻ የግሪኩ ቃል ተስማማቸው ተውሳክ አሏት።ለነገሩ ንኡስ ወር ነው የምትባለው፤ በተጨማሪም ፍራንክ ስለሌላት ተጠዋሪቷ ባልቴትም ትባላለች። ሌሎቹን ወራት እንደ ቦላሌ ሱሪ ወስደን እሷ እንደቁምጣ ማየት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– እያንዳንዱ ዓመት ከአራቱ ወንጌላውያን በአንዱ ይመሰላልና ይሄስ ከምን የመጣ ነው?
መምህር ሔኖክ፡– የቤተክርስትያን ቱውፊት ስንመለከት ዓመተ ምህረት ከክርስቶስ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ስለዚህ የክርስቶስን ታሪክ የጻፉ፣ የምስራቹን የተናገሩት አራቱ ወንጌላውያን ናቸው። የማቴዎስ ወንጌል፣ የማርቆስ ወንጌል፣ የሉቃስ እና የዮሐንስ ወንጌል ብለን አራቱ ወንጌል አለ።
አንዱም እኮ የሚለየን እሱ ቱውፊት ነው። ወንጌላውያን በተመለከተ በምስራቅም፣ በምዕራብም ያሉ ክርስትያኖች የሚያከብሩባቸው ቀን አላቸው። ነገር እያንዳንዱን ዓመት በእነሱ አይሰየሙም። ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ፣ ዘመነ ዮሐንስ ብሎ በየአራት ዓመቱ ይመላለሳል። የጳጉሜን ቀናትንም ያስተሳስራል፤ ከዮሐንስ እስከ ማርቆስ አምስት ቀን ሆኖ፣ ሉቃስ ስድስት ቀን ይሆናል። ይህን ደግሞ የአዘቦት ዓመትና የሰግር ዓመት እንላለን።
አዲስ ዘመን፡– ዓመቱ በየትኛው ወንጌላዊ እንደሚውል ለማወቅ፤ በምን መልኩ ነው የሚሰላው?
መምህር ሔኖክ፡– የአዲስ ኪዳን መጽሃፍ ሲከፈት በመጀመሪያ የማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ ወንጌሎች፤ ከአንድ እስከ አራት ባለው ቅድመ ተከተል ናቸው። ዓመተ ዓለም ሲደመር ዓመተ ምህረት ሲካፈል ለአራት ተብሎ፤ ቀሪው አንድ ከሆነ ማቴዎስ፣ ሁለት ከሆነ ማርቆስ፣ ሶስት ከሆነ ሉቃስ ሲሆን ምንም ቀሪ ከሌለው ዮሐንስ ይሆናል።
ዘንድሮ አዲስ አንድ ዓመት ብቻ ሳይሆን አዲስ የአራት ዓመት እና አዲስ የ28 ዓመት ኡደት የምንጀምርበት ልዩ ዓመት ነው። ቱውፊቱ ቢታወቅ የመንግስት ተቋማት ሆነ የሃይማኖት ተቋማት በእቅድ አወጣጥ ላይ ተግባራዊ ሊያደርጉት ይችላሉ። ምድረ ቀደምት እንላለን፤ ነገር ግን ለኢትዮጵያ የግዜ አቆጣጠር ምን ያህል ጥልቅ እውቀት አለን የሚለው ጥያቄ ይፈጥራል።
አሁን ክረምት ሲያልፍ ብዙዎቹ ከአደይ አበባ ጋር ስለሚያያዝ ፀደይ ይላሉ። ፀደይ ግን መጋቢት ላይ ነው። ክረምት ቀጥሎ የሚመጣው መጸው ነው። ይህም አበባ ማለት ነው። ክረምት ላይ ሆነን ‹‹ሰመር›› ወይም ‹‹ሰመር ኮርስ›› ይባላል። ሰመር ማለት በጋ ማለት ስለዚህ ለአውሮፓውያን እንጂ ለኢትዮጵያ አይደለም። ለእኛ ክረምት ነው እንግሊዘኛውን ቃል እንጠቀም ከተባለም ‹‹ዊንተር›› ነው።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ጠብቀው ያቆዩት እነማናቸው?
መምህር ሔኖክ፡– የዘመን አቆጣጠሩ ሀገራዊም ነው። ክርስትና ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ ከዓለም ከአይሁድ እና ከሌሎችም የተቀበልነው ልዩ ልዩ ሀሳቦች ስላሉ እከሌ ነው ማለት አንችልም። ነገር ግን በየዘመኑ ያስተማሩ ሊቃውንት አሉ። ስለዚህ የጥንት ሕብረተሰብ ነው። ክርስቲያናዊ፣ አይሁዳዊ እና እስላማዊ ሀሳቦች ደግሞ ከተመሰረቱበት አውድ ጋር ተያይዞ ይገለጣሉ።
የዘመን አቆጣጠሩ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገችው ቤተክርስትያን ናት። በቤተክርስትያን ባህረ ሃሳብ እንደ አንድ ሙያ ነው የሚሰጠው። ለቤተክርስትያን የዘመን አቆጣጠር መነሻው ብርሰቱ ደረጃ ቅዱስ ያሬድ ነው። በፊት ግን ከመጀመሪያ ዘመን ጀምረው ያሉ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቅርስ እየተቀበሉ እያስማሙ ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በዋናነት በሃይማኖት ሊቃውንት እና በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ሊቃውንት የተቀመረ ነው። በምስራቅም፣ በምዕራብም ያሉ። አውዲዮናሲዮስ፣ ዲሜጥሮስ ወደ እኛ ስንመጣ ደግሞ እንደነ እጨጌ አበሙ የመሳሰሉት አሉ።
ስለዚህ የኢትዮጰያ ሊቃውንት እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የኢትዮጵያን ዘመን አቆጣጠር አደራጀ። ከዛን ዓለም አቀፍ ከሆነው አቆጣጠር ጋር ተዛመደ።
አዲስ ዘመን፡– በዘመን አቆጣጠር ከኢትዮጵያ ጋር የሚመሳሰል ሀገር አለ?
መምህር ሔኖክ፡– ግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አንድ ነው። መስከረም አንድን ቲቶ አንድ ነው የሚሉት፣ ሕዳርን ሀቱር፤ ጳጉሜን አልናሲ ይላሉ። በመንግስት ካሌንደር ደረጃ ኢትዮጵያ ብቸኛ ናት። 13 ወር በማለት ግን የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ትመሳሰላለች።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ የሚገልጹት ሀሳብ ካለ?
መምህር ሔኖክ፡– ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል፣ ቁጥር፣ የራሷ ካሌንደር ያላት ብለን እናስተዋውቃለን። ነገር ግን በአግባቡ አናውቅም ፤በትምህርት ተቋማትም በአግባቡ አይገለጽም። አራቱን ወቅቶች እንኳን በቅጡ የማንገልጽ ነን። በደራሲዮች፤ በገጣሚዎች እና በዘፋኞች ፀደይን ለመስከረም የመስጠት ነገር አለ። ፀደይ በልግ ማለት ነው እንጂ ስፕሪንግ አይደለም። ቀጣይነት ያለውን የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር መጠበቅ ይገባል። ቀን ይሞሸራል ዓመት ይቀመራል። መልካም ዘመን እንዲሆንላቹ እመኛለው!
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም