ሕዝቦች ተደራጅተው የራሳቸውን ችግር በጋራ የመፍታት አማራጭ በመያዝ የህብረት ሥራ ማህበራትን ከመሠረቱ በዓለም ደረጃ ከ100 በላይ ዓመታትን አስቆጥረዋል። በሀገራችን ምንም እንኳ እንደ ዘመኑ የአሰራር ሂደት የተለያየ ቢሆንም፤ የህብረት ሥራ ማህበር ከተጀመረ ስድስት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል።
የህብረት ሥራ ማህበራት እንደ ሀገር ረጅም ዓመታትን ቢያስቆጥሩም በገበያ ውስጥ ያላቸው ድርሻ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ እና ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ ይነገራል። ለዚህም ሕገወጥ ንግድ ማነቆ እንደሆነባቸው ይነሳል። በዚህ ምክንያት ገበያን ከማረጋጋት ረገድ ይበል የሚያስብል ሥራ መሥራት አልቻሉም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘመን በኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ መሐመድን አነጋግሯል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ምን ተሰራ? አዲስ ዓመትን ጨምሮ ለመጪዎቹ በዓላት በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ምን እየተከናወነ ነው? ከምርት አቅርቦት ጋር ተያይዞ በ2017 በጀት ዓመት ምን ታቅዷል? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የተገኙ ምላሾችን ይዞ ቀርቧል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡- የህብረት ሥራ ማህበራት የተቋቋሙበት ዓላማ ምንድን ነው?
አቶ አብዲ፡- የህብረት ስራ ማህበር በተለያየ መልኩ ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው ሰዎች በጋራ ችግራቸውን ለመፍታት የሚደራጁበት ተቋም ነው። የህብረት ሥራ ማህበር በ1884 ከእንግሊዝ ኢንዱስትሪ አብዮት ጋር ተያይዞ የተመሰረተ ነው። በወቅቱ አሁን በኢትዮጵያ ገበያ የሚታዩ በተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ላይ ባዕድ ነገር መቀላቀል እና ከሚዛን የመስረቅ ችግር ገጥሟቸው ነበር።
በዚህ ምክንያት ሸማቹ ማህበረሰብ ተደራጅቶ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጠኝ ዋጋ ለአባሉ ማቅረብን አላማ አድርጎ የተመሰረተ ነው። አሁን ላይ የህብረት ሥራ ማህበራት የሌሉበት ሀገር የለም። በሀገራችን የህብረት ሥራ ማህበር ከተጀመረ 60 ዓመት አስቆጥሯል።
የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ቴክኖሎጂዎች በማቅረብ ምርትና ምርታማነት የማሳደግ አላማ በመያዝ በንጉሱ ጊዜ ነው የተመሰረቱት። የሶሻሊስት ርዕዮትን ለማራመድ ደርግ የገጠር ገበሬ ማህበራትን በስፋት ይጠቀም ነበረ። የደርግ ሥርዓት ሲወድቅ ኢሕአዴግ ያሉትን ነገሮች አሻሽሎ የቀጠለበት ሁኔታ አለ።
አሁን በደረስንበት ሁኔታ ስናይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የህብረት ሥራ ማኅበር አስፈላጊነት በሀገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ለውጥ አለ። መንግሥትም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት የሰጠበት ሁኔታ አለ። በቁጥር ስንመለከት ከ110 ሺ በላይ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ይገኛሉ። ከአራት መቶ በላይ ዩኒየኖች አሉ። አምስት ደግሞ ሌላ የፌዴሬሽን ማህበራት ተደራጅተዋል።
26 ሚሊዮን የሚጠጉ ማህበራት ተደራጅተው ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውን እየፈቱ ይገኛሉ። የማህበራቱ ካፒታል ሲታይ 50 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ነው። የተፈጠረ የሥራ እድል ስንመለከት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ጊዜያዊ እና ቋሚ የሥራ እድል በህብረት ሥራ ማህበራት ተፈጥሯል።
የህብረት ሥራ ኮሚሽኑ በሶስት ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። የመጀመሪያው ግብርና ሲሆን በዚህም አምራችና ሸማችን የማስተሳሰር ሥራ ይሰራል። ሌላኛው ኢንዱስትሪ ነው። በዚህም የተለያዩ ምርቶች ከአርሶ አደሩ በመረከብ እሴት ጨምሮ ለገበያ ያቀርባሉ። ሶስተኛው የብድርና ቁጠባ ማህበራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። በገንዘብ እና ቁጠባ 23 ሺ የሚጠጉ ማህበራት ተሰማርተዋል።
የህብረት ሥራ ማህበራት በጣም በርካታ ናቸው። እደ ጥበብ ላይ፣ ቤቶች ላይ እና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩት በርካታ ህብረት ሥራ ማህበራት አሉ። እኛ ግን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተጽዕኖ አላቸው ብለን ባሰብናቸው ሶስቱ ላይ እንደ ህብረት ሥራ ኮሚሽን እንደግፋለን።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራባቸው ዘርፎች ምንድን ናቸው?
አቶ አብዲ፡- እንደ ፌዴራል ተቋም የኮሚሽኑ ትልልቆቹ የሥራ ኃላፊነቶች ከፖሊስ፣ ከአሰራር አንጻር፣ የሕግ ክፍተት ካለ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ ከዛም አልፎ የህብረት ሥራ ማህበራት የገበያ ችግር ሲያጋጥማቸው ገበያን በማፈላለግ ከውጭና ከሀገር ውስጥ ገበያ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ይሰራል። በአጠቃላይ ክፍተታቸውን በመለየት የአቅም ግንባታ ሥራ ይሰራል።
የማደራጀት ሥራን በተመለከተ በብዛት የሚፈጽሙት የክልል ህብረት ሥራ ኮሚሽኖች ናቸው። የእኛ ኃላፊነት የበለጠ የሚያተኩረው በቁጥጥር ሥራ ላይ ነው። ይህን መሠረት በማድረግ ባለፉት ዓመታት ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።
አዲስ ዘመን፡- በ2016 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ በሰራቸው ሥራዎች የተገኘው ውጤት እንዴት ይገለጻል?
አቶ አብዲ፡- ባለፉት ዓመታት በስፋት የተሰራው በማህበራት ቁጥር ላይ ነው። ሰዎች በመደራጀት የራሳቸውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው ችግሮች እንዲፈቱ ለማስቻል ትኩረት የተሰጠው ማህበራትን ማደራጀት ላይ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮሚሽኑ የሪፎርም ሥራዎችን ያስጀመረበት እና እስከታች ወዳለው መዋቅር ንቅናቄዎችን ያስጀመረበት ዓመት ነው። ኮሚሽኑ ይህን ዓላማ አድርጎ የተነሳው አንዳንድ የህብረት ሥራ ማህበራት ፣ እንደአዋጭ ቁጠባ ማህበር፣ ኦሮሚያ የቡና ህብረት ሥራ ማህበራት እና ሌሎች ማህበራት ትልቅ እድገት እያስመዘቡ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም፤ በተቃራኒው ደግሞ ምንም ለውጥ ያላመጡ ማህበራት አሉ።
ይህን ታሳቢ በማድረግ የህብረት ሥራ ማህበራት በቁጥር በርካታ ናቸው። የሪፎርም ሥራው የተጀመረው እንዴት ተጽዕኖ ፈጣሪ እናደርጋቸው? በሚል ነው። ስለዚህ በ2016 ዓ.ም የተነሳነው በቁጥር ትንሽ፣ በተጽዕኖ ትልቅ ማህበራትን መፍጠር ዓላማ አድርገን ነው።
እንደ ሀገር ከሚፈጠሩ ለውጦች ጋር ተወዳዳሪ የሆኑ የህብረት ሥራ ማህበራት እስካሁን በተለመደው አሰራር ተጉዘን መፍጠር አንችልም። ስለዚህ ምንድን ነው ያለባቸው ተግዳሮቶች የሚለውን ለየን።
ያለባቸው አንደኛው ተግዳሮት፣ የህብረት ሥራ ማህበራት፤ በሙያዊ እውቀት የታገዙ አይደሉም። የህብረት ሥራ ንግድ ነው፣ ንግድ ደግሞ መመራት ያለበት በእውቀት ነው። በሕዝብ የተመረጡ የህብረት ሥራ ቦርድ አባላት፤ ተምረው የትምህርት ማስረጃ ቢኖራቸውም፤ እውቀት የሌላቸው ወይም ያልተማሩ ናቸው። የህብረት ሥራ ማህበራት የሚወዳደሩት ከግል ባለሀብት ጋር ነው። ስለዚህ የህብረት ሥራ ማህበራት በተማሩ ቦርዶች እና ሥራ አስኪያጆች መመራት አለባቸው በሚል፣ አሰራራቸው እና አደረጃጀታቸው መለወጥ አለበት የሚል አቅጣጫ አስቀመጥን።
በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የህብረት ሠራ ማህበራትን የማያሰሩ ሕጎች አሉ። እነዚህ መሻሻል አለባቸው ብለን ነው የወሰድነው። በሰሩት ሥራ ጥራታቸው እየተገመገመ የምስክር ወረቀት መስጠት እንደሚገባም በአቅጣጫው ተመላክቷል።
ደህንነታቸው መጠበቅ አለበት የሚል አቅጣጫም ተቀምጧል። ህብረት ሥራ ማህበራት ብዙ ሀብት ፈጥረዋል። ዜጎች ከህብረት ሥራ ማህበራት ጀርባ መንግሥት አለ ብለው ነው ሀብታቸውን በህብረት ሥራ ማህበራት ላይ የሚያስቀምጡት። ስለዚህ ይሄ ሥርዓት በጠንካራ ሕግ መጠበቅ አለበት። ሌላኛው ወደ ሪፎርም የተገባው የህብረት ሥራ ማህበራት የገንዘብ አቅርቦት ሥርዓታቸውን የማሻሻል አቅጣጫ ተይዞ ነው።
ከለውጥ ሥራዎቹ ጋር ተያይዞ ባለፈው በጀት ዓመት የተጀመሩት ሰፋፊ የንቅናቄ ሥራዎች ናቸው። እኛ ለግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም እንደመሆናችን፤ ንቅናቄውን የጀመርነው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ ነው። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለህብረት ሥራ ማህበራት ለውጥ ያስፈልጋቸዋል የሚለው አጀንዳ እንዲያዝ በማድረግም ጭምር ነው።
በለውጡም የተቀመጡት አራት ሥራዎች ናቸው። የመጀመሪያው የመረጃ ማጥራት ሥራ ነው። ቁጥራቸው የተገለጹ ማህበራት ሁሉም አሉ?፣ እነማን ናቸው? ሥራቸውስ ምንድን ነው? የሚለውን የማጥራት ሥራ ነው።
ሁለተኛው፣ የህብረት ሥራ ማህበራትን በደረጃ መለየት ነው። አንዳንዱ ማህበራት በንጉሱ ጊዜ የተደራጀ እና ለስም የተቀመጡ ናቸው። እነዚህን የሕብረት ሥራ ማህበራት በቁጥር መለየት፣ በደረጃ መለየት እና መጣመር ያለባቸውን ህብረት ሥራ ማህበራት ማጣመር ነው።
በዚህ መሠረት ምንም እቅስቃሴያቸው ደካማ የሆኑትን፣ የካፒታል መጠናቸው እና የአባላት ቁጥራቸው ዝቅተኛ የሆኑትን ማህበራት ተመሳሳይ በአንድ ወረዳ ውስጥ ስድስት የሚሆኑ ካሉ በፍላጎታቸው መሠረት ካፒታላቸውን፣ አመራራቸውን ሰብሰብ በማድረግ በቁጥር ትንሽ፤ በተጽዕኖ ደግሞ ትልቅ ማህበራት መፍጠር ነው።
አዋጭ አንድ መሠረታዊ ማህበር ነች፤ ትልቅ ሀብትና አባል መፍጠር ችላለች። ስለዚህ ሌሎች ማህበራትም ወደዚህ እንዲመጡ ይፈለጋል። በተመሳሳይ ሌሎች ማህበራትም አሉ፤ በአንድ ክልል የሁሉንም አባል ችግር ፈትተው፤ አጠቃላይ ሁሉንም ሥራ መሥራት የሚችሉ ናቸው። ከባለሀብቶች ጋር የመወዳደር አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ሆነ።
አሁን ላይ ያሉ አንዳንድ የህብረት ሥራ ማህበራት በገበያ ላይ ባለው አቅም ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ቦታ እየያዘ ያለው ደላላው ነው። በዚህ የተነሳ ዋጋ የሚወስንላቸው ደላላው ነው። ስለዚህ በምርታቸው ተወዳዳሪ የሆኑ ማህበራት ለመፍጠር አንደኛው ማዋሀድ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ መሰረዝ ያሉባቸው ካሉ መሰረዝ ነው። ሶስተኛው የአባላት ቁጥራቸው በጣም በዝቶ ለማስተዳደር የሚከብዱ ካሉ መክፈል ነው። እነዚህ ሶስቱ ተግባራዊ የሚደረጉት በፍላጎት መሠረት ነው። አራተኛው እነዚህን ደረጃዎች ከሄድን በኋላ የምስክር ወረቀት መስጠት ነው።
እነዚህ እንቅስቃሴዎች ለማስጀመር በበጀት ዓመቱ ከፌዴራል፣ ከክልል የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች፣ የህብረት ሥራ አመራሮች ፣ ማህበራት ባሉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሰርተዋል። ሥራውን ከፌዴራል ጀምርን እስከ ክልል ለማድረስ በክልል ፕሬዚዳንቶች እንዲመራ ተደርጓል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርቷል።
አማራ ክልል አሁን የደህንነት ስጋት አለበት። ነገር ግን አመራሩ ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማሳየት፤ በፕሬዚዳንቱ የሚመራ ኮሚቴ አቋቁሞ፤ የለውጡ እንቅስቃሴ እስከ ወረዳ ድረስ ወዳለው መዋቅር ደርሷል። በተመሳሳይ በማዕከላዊ እና ኦሮሚያ ክልሎች የንቅናቄ ሥራው ተሰርቷል። ሌላው የፓርላማ አባላት በወከሉት አካባቢ ለቁጥጥር ሥራ ሲሄዱ ሥራዎች በትክክል እየተሰሩ መሆኑን ክትትል እንዲያደርጉ ተደርጓል።
በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ሶስት ተዋንያን አሉ። አንደኛው የግሉ ባለሀብት፣ ሁለተኛው መንግሥት ነው። በሶስተኛነት በሁለቱ መሃል የሚገባው የህብረት ሥራ ማህበር ነው። የጅማ ቦርጩማ ያለው ሶስት እግር ነው። ሁለት እግሩ ብቻውን ሊቆም አይችልም። እንደሀገርም የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያው ችግር ሊቀረፍ የሚችለው፤ ህብረት ሥራ ማህበር በመሃል ገብቶ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግር መፍታት ሲችል ነው።
በኢኮኖሚ ውስጥ ዜጎች ተደራጅተው ተዋንያን እንዲሆኑ፣ እንደመንግሥት አጀንዳ እንዲሆን፤ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። በርካታ ክልሎች ሪፎርሙን ተቀብለው እስከወረዳ ድረስ አድርሰውታል።
አዲስ ዘመን፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ተጠናቋል?
አቶ አብዲ፡- አላለቀም፤ አቅጣጫ የተቀመጠው ሪፎርሙ በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ ነው። በእኛ በኩል ማዘግየት አንፈልግም፤ አምስት ዓመት ሳይሞላም ሊጠናቀቅ ይችላል። ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልልን ብንወስድ፤ የሪፎርም ሥራው ተጀምሮ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከአባላት ቁጥር አንጻር ከአንድ ሚሊዮን በላይ አዳዲስ አባላት የህብረት ሥራ ማህበራትን ተቀላቅለዋል። ቁጠባና ካፒታል በስፋት ማፍራት ተችሏል።
ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተያይዞ የማህበራትን ሀብት አላግባብ ሲጠቀሙ የነበሩ ከ100 በላይ፤ የቦርድ አመራሮች፣ ሥራ አስኪያጆች እና ሌሎች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ አካላት አስተዳደራዊ እና የሕግ ርምጃ ተወስዶባቸዋል።
የባከነ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ ተመልሷል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ተወስዶ ያልተመለሰ 10 ቢሊዮን የማዳበሪያ ብር ተመልሷል። አሁንም ኦሮሚያን ብቻ ወስደን፤ ከዚህ በፊት ኦዲት የሚደረጉ ህብረት ሥራ ማህበራት 45 በመቶ ብቻ ነበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ 80 በመቶ ማድረስ ተችሏል።
በአማራ ክልልም በተመሳሳይ የኦዲትና የፍተሻ ሥራዎች የጨመሩበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ይህ ንቅናቄ በርካቶችን እያንቀሳቀሰ ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ ይህን ማድረግ ተችሏል። ለህብረት ሥራ ማህበራት ዋንኛ ነገር ታማኝነት ነው። አንድ ሰው የሚደራጀው ለመጠቀም ነው። ታማኝነት ኖሮ በግልጸኝነት እና በተጠያቂነት ከተሰራ አባላቱ ውጤታማ ይሆናሉ።
ችግር ያለበት አመራር ካለ ደግሞ ይወርዳል። ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ አዲስ ይመረጣል ማለት ነው። ስለዚህ በብዙ ማህበራት ውስጥ ተጠያቂነት እየመጣ ነው።
ሪፎርሙ በስፋት ተግባራዊ ከሆነባቸው የከተማ አስተዳደሮች አንዱ አዲስ አበባ ነው። ሪፎርም እየተደረገ ያለው በሁለት መልኩ ነው። አንደኛው የማህበራት አደረጃጀት ማሻሻል ሲሆን፤ ሌላኛው ከመንግሥት በኩል ድጋፍ የሚያደርገው አካል ወይም ተጠሪ የሚሆነው መሥሪያ ቤት ለውጥ ተደርጓል።
ከዚህ በፊት ማህበሩ ተጠሪ የሆነው ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ለአዲስ አበባ ከንቲባ ተጠሪ እንዲሆን ተደርጓል። ሌላው እስከ ክፍለ ከተማ ያለውን አደረጃጀት ፈተና አዘጋጅቶ አወዳድሮ የተሻሉ አመራሮች እንዲመጡ የሚያስችል ሥራ ተሰርቷል።
ከህብረት ሥራ ማህበራት ደንቦች ጋር ተያይዞ የተጀመረ ሥራ አለ። ህብረት ሥራ ማህበራት ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደረጓቸውን አዋጆች ማሻሻል ነው። የህብረት ሥራ አዋጅ የሆነው 985 አለ። እሱን ተከትለው ሊወጡ የሚገባቸው ደንቦች ለረጅም ጊዜ አልወጣም። አሁን ላይ ረቂቁ አልቆ ወደ ግብርና ሚኒስቴር ለመላክ ደርሷል።
ሌላው 985 አዋጅ ከወጣ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል። አሁን ከወቅታዊ ለውጦች ጋር አብሮ የሚሄድ ስላልሆነ መለስተኛ ማሻሻያም ቢሆንም ሊደረግለት እንደሚገባ ታሳቢ ተደርጓል። ለምሳሌ የህብረት ሥራ ማህበራት የራሳቸው ባንክ የላቸውም፤ ብድር የሚወስዱት ከግልና ከመንግሥት ባንኮች ነው።
እነዚህ ባንኮች ደግሞ ህብረት ሥራ ማህበራት በሚፈልጉበት ሰዓት ብደር አይሰጧቸውም። ብድር የሚሰጡት የራሳቸው ደንበኞች ከወሰዱ በኋላ ነው። ስንዴ በሚሰበሰብበት ሰዓት ህብረት ሥራ ማህበራት ገንዘብ ቢያስፈልጋቸው ብድር አያገኙም። ስለዚህ አዋጁ በሚሻሻልበት ወቅት የህብረት ሥራ ማህበራት የራሳቸው የገንዘብ ተቋም ወይም የግብርና ባንክ ሊኖር ይገባል ። ለዚህም መመሪያዎች እየተዘጋጁ ነው።
ስለዚህ የሚፈለገው ነገር ህብረት ሥራ ማህበራት ያለውን አውድ አውቀው በድጎማ የሚሰሩት መቆም አለበት። ድጎማ ሲባል፤ ህብረት ሥራ ማህበራት ዱቄትና ዘይት ሲያቀርቡ የሚደጎሙት በመንግሥት ነው። እንደዚህ ዓይነት ህብረት ሥራ ማህበራት በአሁን ጊዜ አያስፈልጉም። ማህበራት አቅማቸውን አሳድገው ሁሉንም ዓይነት የፍጆታ እቃ በራሳቸው አቅም አሟልተው ለሸማቹ ሆነ፤ ለሌላው ሕዝብ አማራጭ ሆነው መቅረብ አለባቸው።
አሁን ያሉት ማህበራት በዛ ልክ አልሆኑም፤ ለዚህ ደግሞ የተማረ እውቀትና ክህሎት ያለው እና ኃላፊነት ተሰጥቶት የሚሰራ፤ ካልሰራ የሚጠየቅ አስተዳደር ያስፈልጋል። በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ በመሆን ለሸማቹም፣ ለሌላውም ዜጋ አማራጭ ሆኖ መቅረብ አለባቸው እንጂ በድጎማ መቀጠል የለባቸውም ብለን እየሰራን ነው።
ለዚህ ደግሞ እውቀት እና ክህሎት ያለው፤ ኃላፊነት ተሰጥቶት የሚሰራ ካልሰራ የሚጠየቅ አስተዳደር መኖር አለበት። ህብረት ሥራ ንግድም ጭምር ነውና በድጎማ መቀጠል የለበትም ብለን በስፋት እየተወያየን ነው። ለ60 ዓመታት የቆየ አስተሳሰብ ስለሆነ በቀላሉ አይሰበርም፤ በዚህ ዙሪያ ስልጠና እና የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠ ነው።
ለ2017 በጀት ዓመት እነዚህ ደንቦች በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ በማድረግ መሬት ላይ ማውረድ ነው። አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ሥራው ውጤታማ መሆን ይቻላል። ነባር ሥራዎች እየሰራን ወደ ትልቅ ሥራዎች እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፡- በህብረት ሥራ ማህበራት እስካሁን በተሰሩ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ምን ውጤት ተገኘ?
አቶ አብዲ፡– አቅርቦት ላይ ኮሚሽኑ ሶስት እቅዶች ነድፎ ይሰራል። አንደኛ በገጠር ያሉ አምራች ማህበራት እና በከተማ ያሉ ሸማች ማህበራት እንዲተሳሰሩ ማድረግ ነው። ሁለተኛው፣ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አምራቾች ምርታቸውን እንዲያሳዩ እና ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረግ ሲሆን፣ ሶስተኛው ማህበራት በእሁድ ገበያዎች አማካኝነት ምርታቸውን ያቀርባሉ።
አሁን ላይ እሁድ ገበያ ላይ የሚያቀርቡ ማህበራት መንግሥት ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል የምርት ጥራታቸውም እየተሻሻለ ነው። ሌላው ደግሞ ለበዓላት ምርት ማቅረብ ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ናቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በ2017 ዓመት ለሚከበሩ በዓላት በሁሉም ክልሎች ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ጠቅለል አድርጌ ሳቀርብ 56 ሺህ 700 ኩንታል ጤፍ፣21 ሺህ 250 ኩንታል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ከ2 ሺህ 200 ኩንታል በላይ ፣ 20 ሺህ ዶሮ፣ እንቁላል ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ፣ ከ143 ኩንታል በላይ ቅቤ፤ የበቆሎ ዱቄት ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ፣ ዘይት ሁለት ሚሊዮን 361 ሺህ 500 ሊትር ፣ ከ10 ሺህ 600 በላይ በሬ፣ በግ እና ፍየል እና ሌሎች ምርቶች ለበዓል ቀርቧል።
ሕዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በዓላትን በሰላም እንዲያሳልፍ ህብረት ሥራ ማህበራት አማራጭ ሆነው ቀርበዋል። በግብይት ሂደት ጤፍ ትንሽ የተወደደበት ሁኔታ አለ። ለዚህ ከግብርና እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ይሰራል።
የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር፣ ከዶላር መጨመር ጋር ተያይዞ ያጋጠመው የእቃዎች መወደድ እና የማምረቻ ዋጋ የእነዚህ እቃዎች ዋጋ ገበያ ላይ ጨምሯል። መፍትሔው አቅርቦትና ፍላጎትን ማጣጣም ነው። ለዚህ በሁሉም ደረጃ ይኬዳል፤ የህብረት ሥራ ማህበራትም በተቻለ አቅም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይጥራሉ።
ለበዓላት በሁሉም ክልል ካሉ አምራች ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በዝርዝር በማውራት፤ በከተማ ከሚገኙ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመሆን የግብርና ምርቶችን በስፋት እንዲያቀርቡ በየዓመቱ የሚሰራ ሥራ ነው። የህብረት ሥራ ማህበራት ኃላፊነት ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ይወጣሉ። በዚህም ከሚያገኙት ትርፍ ለማህበራዊ ጉዳይ አምስት በመቶ ይሰጣሉ።
አሁን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለን ድርሻ ከአራት በመቶ ያልበለጠ ነው። የበለጠውን ድርሻ እየወሰደ ያለው የግሉ ሴክተር ነው። ስለዚህ የእኛ ሪፎርም ህብረት ሥራ ማህበራት በገበያ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ማሳደግና ተወዳዳሪነታቸውን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ከፍ ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በ2017 በጀት ዓመት ገበያን ለማረጋጋት ምን ዓይነት እቅድ ተይዟል?
አቶ አብዲ፡- በአጠቃላይ ቅድም እንዳልኩት ሪፎርም ውስጥ ነው ያለነው። በዚህ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉት ብዙ ማነቆች ናቸው። ከውጭና ከውስጥ ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት እንደሀገር ሰፊ የኑሮ ውድነት ነው ያለው። ይህን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እኛም በአቅማችን የቻልነውን ያህል እንሰራለን።
ለዚህ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ፤ አንደኛው ሕገወጥ ንግድ ነው። ሕገወጥ ንግድ የህብረት ሥራ ማህበራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። የህብረት ሥራ ማህበራት ምርት የሚሰበስቡት ከአባላቶቻቸው ነው። ለምሳሌ አንድ ኩንታል ጤፍ ህብረት ሥራ ማህበራት ሰባት ሺህ ብር ከሆነ የሚገዙት፤ ሕገ ወጥ ደላላዎች ይመጡና 10 ሺህ ያደርጉታል።
አባሉ ደግሞ እዚህ 10 ሺህ ብር ለሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላላዎች እየሸጠ፣ ለአባሉ በሰባት ሺህ ብር ሊሸጥ አይችልም። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ ገበያ መቅረት አለበት፤ ይሄን የሚያደርጉት ህብረት ሥራ ማህበራትን ከገበያ ለማስወጣት ነው። ነጋዴው ከወጣ በኋላ ብቻውን ገበያውን ተቆጣጥሮ የፈለገውን ያህል ብር ጨምሮ ለመሸጥ ነው።
እነዚህን ሕገወጦች ለማስቆም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሆነን በመሥራት ሥርዓት እንዲይዙ ማድረግ አለብን። አምራቹም ያመረተበትን ዋጋ በአግባቡ አግኝቶ፤ ህብረት ሥራዎችም ምርቶቹን ለማስጫን እና ለማውረድ ያወጣውን ወጪ ታሳቢ አድርጎ ተመጣጣኝ ትርፍ አግኝቶ ሲሸጥ ፍትሃዊ የሆነ ነገር ይኖራል። አሁን ያለው የገበያ ምህዳር ፍትሃዊ አይደለም። የህብረት ሥራ ማህበራትን ከገበያ የሚያስወጣ ነው። በዚህ ምክንያት በገበያው ተወዳዳሪ እና በቂ ምርት መያዝ አልቻሉም፤ ሕገወጥ ነጋዴዎች ወስደው ይሰበስቡና፣ አርቲፊሻል የሆነ እጥረት እንዲያጋጥም ያደርጉና ጠፋ ሲባል፤ በውድ ዋጋ እያወጡ ነው የሚሸጡት።
የህብረት ሥራ ማህበራት ብቻ ችግር ስላልሆነ በጋራ ማስተካከል ይጠይቃል። ምርት እየተመረተ ነው፤ ያለው ነገርም በቂ ነው። ነገር ግን ፍትሃዊ የሆነ የገበያ ሁኔታ የለም። ይሄ የህብረት ሥራ ማህበራት በጣም እየጎዳ ነው ያለው።
ቡና ላይም የሚያጋጥመው ሕገወጥ ንግድ ከፍተኛ ነው። በዶላር የሚሸጠው በዝቅተኛ ዋጋ ነው። በዚህ ምክንያት ነጋዴው ዶላሩን ስለሚፈልግ ህብረት ሥራ ማህበራት ቡና ገዝተው ለውጭ ገበያ ማቅረብ አልቻሉም። ከዚህ በውድ ዋጋ ቡና ይገዛና፤ ለውጭ ገበያ ያቀርባል። ቡናውን በሸጠው ዶላር ሌሎች ሸቀጦችን ከውጭ ገዝቶ ያመጣና እዚህ በመሸጥ ያካክሳል።
የህብረት ሥራ ማህበራት ይህን ማድረግ አይችሉም። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ህብረት ሥራ ማህበራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋል። ያም ሆኖ ባላቸው አቅም ገበያን ለማረጋጋት ሰፊ ጥረት እያደረጉ ነው። ፍትሃዊ ገበያ ካለ እንደማንኛውም ሀገር ህብረት ሥራ ማህበራት ያላቸው የተወዳዳሪነት አቅም እያደገ ይሄዳል።
ስለዚህ ሕገወጥ ንግድ እና ደላላ ሥርዓት መያዝ አለባቸው። የከተማ መስተዳደሮች፣ ደንብ አስከባሪዎች፣ ንግድ ቢሮ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሆነን መሥራት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል ከእናንተ በኩል ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አብዲ፡– በእኛ በኩል የሚሰሩ ሥራዎች አሉ። አንደኛው አባላት ምርታቸውን ለማህበራቱ እንዲያደርሱ ማድረግ ነው። በዛ ውስጥ የአመራር ችግር ያለባቸው ካሉ፤ በለውጥ ሥራው እያጠራን ነው። አባላት በቂ ምርት እንዲያመርቱ እና ያመረቱትን ምርት ለገበያ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው።
ከ98 በመቶ በላይ አርሶ አደሮች የህብረት ሥራ ማህበር አባል ናቸው። በቂ ምርት እንዲያመርቱ መንግሥት ማዳበሪያ፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እና ምርጥ ዘር በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ ነው።
ገበያን የሚያረጋጋው አጠቃላይ ባለው የገበያ ሁኔታ እንጂ፤ የህብረት ሥራ ማህበራት ብቻ ገበያን አያረጋጉም። ያላቸውም ድርሻ አራት በመቶ ብቻ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ገበያን ሊያረጋጋ አይችልም። የመጀመሪያ ግዴታቸው የአባላቱን ጥያቄ መመለስ ነው። አሁን ያለው የግንዛቤ ችግር የሁሉንም ሸማች ችግር ህብረት ሥራ የሚፈታው ተደርጎ ነው የሚታሰበው። በዚህም ሁኔታ ማህበራቱ ገበያን ለማረጋጋት እየጣሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከምርት እጥረት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በምን መልኩ ሊፈታ ታቅዷል?
አቶ አብዲ፡- ከምርት እጥረት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት የግብርና ሥርዓቱ መዘመን አለበት። ህብረት ሥራ ይህን አይፈታም። 120 ሚሊዮን ሕዝብ ተይዞ በተለመደ መልኩ መሥራት አይቻልም። ይህን መንግሥት ተረድቶ የተለያዩ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ ሌማት ትሩፋት፣ ግብርናን የማዘመን ሥራዎች ተጀምረዋል። መፍትሔው በቴክኖሎጂ ተደግፎ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አብዲ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም