ዘመን እየተቀየረ ነው። የዘመን መቀየር በግለሰቦችም ሆነ በሀገር ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት መነሻ ይሆናል የሚል ተስፋ አለ። ይህንን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት በፖለቲካው ላይ ስላሉ ጉዳዮች እና ስለቀጣይ ተስፋዎች፤ አዲስ ዓመት በተመለከተ ከሰላም ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከአቶ ደስታ ዲንቃ ጋር ቆይታ አድርገናል። አቶ ደስታ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ እናት ፓርቲያቸው ሲሆን፤ በፓርቲያቸው የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ፀሐፊ ናቸው። ኦፌኮ ያለበት የአንድነት መድረክ ዋና ፀሐፊ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ሰብሳቢ ናቸው። ቆይታችንን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- በመጪው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲረጋገጥ ምን መሠራት አለበት?
አቶ ደስታ፡- በትክክል በኢትዮጵያ ሠላም እንዲሰፍን ዋናው እና ቁልፉ ነገር፤ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ማስቻል ነው። በቀጣይ ዓመት ሕግ እንዲከበር ከተሠራ ሰላም የማይኖርበት ምክንያት የለም። ሕግ መከበር አለበት ሲባል፤ በተወሰነ ሰው ብቻ አይደለም። ከተራ ዜጎች ጀምሮ የመንግሥት ቁልፍ ሰዎች እና የመንግሥት ቁንጮዎችን ጨምሮ ሁሉም ከህግ በታች መሆን አለባቸው።
ሕግ ሲባል ደግሞ በዜጎች እና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ፤ በመንግሥት እና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ፤ በመንግሥት ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ ሕገ መንግሥታዊ እና ሌሎች ሕጎች ማክበር ማለት ነው። በሀገሪቱ የሚኖሩ ግንኙነቶች በሙሉ በሕግ እና በሕግ አግባብ መሆን አለባቸው። ሕግ እና ሕገመንግሥቱ መከበር አለበት። ሁሉም ለሕግ በሚገዛበት ጊዜ መብት እና ግዴታውን በአግባቡ ያውቃል፤ በደንብ ይከበራል። ሁሉም ሕግን ተከትሎ ግዴታውን ይወጣል፤ ሕግን ተከትሎ መብቱን ይጠይቃል። ስለዚህ ለአንድ ሀገር ብልፅግና፣ ሰላም እና መረጋጋት፤ ለግንኙነቶች ሰላማዊ መሆን ቁልፉ ነገር ሁሉም አካላት ከሕግ በታች መሆን አለባቸው የሚል እምነት አለኝ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላም ፈላጊ መሆን፤ መከባበር እና በመካከላቸው የሚደረጉ ውድድሮች በንግግር ላይ የተመሠረቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የሰብአዊ መብቶችን ማክበር እና ለማስከበር መስራት፤ መብትን እና ግዴታን አውቆ በዛ ማዕቀፍ ውስጥ መንቀሳቀስ ሰላምን እና ብልፅግና ለማረጋገጥ መሠረት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ሰላም በተወሰነ ወገን ሥራ ብቻ መምጣት ይችላል? መንግሥት ከሕዝብ የወጣ እና ሕዝብን የሚመስል ነው። ሕዝብስ ግዴታ የለበትም?
አቶ ደስታ፡- በእርግጥ መንግሥት ከሕዝብ የወጣ ነው። መንግሥት ሕዝብን ይሰማል ይባላል። እኔ በዚህ አልስማማም። በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ መንግሥትን ይመስላል። ማለት አይቻልም። እያየን ያለነው ሕዝብ መንግሥት የሚለውን ይከተላል። ይህ መንግሥትን መስማት እና መከተል ከታሪካችን የመጣ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ንጉስ ቀዳማይ ኃይለስላሴ ከእግዚአብሔር የተላኩ ነኝ ሲሉ ሕዝቡ አምኖ ሲያከብራቸው ኖሯል።
ነገር ግን የሕዝቡ ንቃተ ሕሊና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየዳበረ ሲመጣ፤ ልክ በሌላው ዓለም ጥያቄ እንደቀረበው ሁሉ በኢትዮጵያም ንጉስ ሰው እንደመሆኑ የሌሎችን መብት ባከበረ እና ሁለንተናዊ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ መንቀሳቀስ አለበት የሚለው ሳይንሳዊ ፅንሰ ሃሳብ እየተስፋፋ እና እየታወቀ ሲመጣ ዜጎች ስለመብት እና ግዴታቸው በደንብ ሲያውቁ፤ በሌሎች ሀገሮች እንደሆነው ሁሉ ንጉስ ከእግዚአብሔር የተላከ ሳይሆን ሰው ነው ብለው ሰዎች መንግሥትን ወይም ንጉስን መጠየቅ ጀመሩ።
ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገሮች እንደዚሁ የተለመደ ነው። የሰዎች ንቃተ ህሊና ከዘመን ጋር ተያይዞ በሚያድግበት ጊዜ ዜጎች የማያውቋቸው ነገሮች እየቀነሱ ሲመጡ እና ግንዛቤያቸው ሲያድግ ጥያቄ ያነሳሉ። መንግሥታት የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች እንደየዘመናቱ እንደየጊዜው ጥያቄዎቹን የሚመጥኑ መልሶችን መስጠት ካልቻሉ አመፅ ይነሳል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በተመሳሳይ መልኩ ጠይቋል። ለጥያቄው መልስ ካገኘ የመረበሽ ባህሪ ያለው አይመስለኝም።
መንግሥታት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ሲያቅታቸው ሕዝብ ጫካ በመግባት ወይም ሕዝባዊ አመፅ እየተደረገ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ነገር ግን መንግሥታት ዘመንን የዋጁ መልሶች እየተሰጡ ሲሆን፤ የመንግሥት መቀያየር በጉልበት ወይም በሕዝብ አመፅ አይሆንም ነበር። ስለዚህ ከመንግሥት የሚጠበቀው ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ጊዜውን የዋጁ ምላሾችን መስጠት ነው። የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው። ለምሳሌ አሁን ዜጎች የሚጠይቁት መንግሥት ከራሱ ጀምሮ ሕግን ያክብር፤ ሰብአዊ መብትን ያስከብር፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበርም ማስከበርም አለበት የሚል ነው።
ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባማረ መልኩ በሕገ መንግሥቱ ተቀምጠዋል። የመንግሥት ስልጣን የሚያዘው በሕዝብ ነፃ ፍትሐዊ እና ተአማኒነት ባለው ምርጫ መሆን አለበት ይላል። ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን አዋጅ ሕግም ሆነ መመሪያ እንዲሁም የየትኛውም የመንግሥት ኃላፊ ውሳኔ ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ መንግሥት በሕግ እና በሕገመንግሥት በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት ውስጥ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ይህ በጣም ትልቅ እና ሰፊ ነገር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን ዜጎች፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቡድኖች ያላገኙትን መብታቸውን እና ለጥያቄያቸው መልስ ማግኘት ባለመቻላቸው ሕግን በራስ ማስፈፀም የሚለውን የሕግ ፅንሰ ሃሳብ እየተገበሩ ቆይተዋል።
ራሳቸው የሚፈልጉትን መብታቸውን በጉልበት ወደ ማስጠበቅ አዝማሚያ መሔድ በሌላውም ዓለም ያጋጥማል። የሕዝብ አመፅም ሆነ ጠመንጃ ይዞ ጫካ መግባት የዚሁ አካል ነው። ሕግን አክብሮ ማስከበር ዋናው የሰላም ምሰሶ ነው። በኢትዮጵያ ያለው ልማድ በተለያዩ ዘመናት ቢቀያየሩም መንግሥታት ራሳቸው ከሕግ በላይ ሆነው ዜጎች ብቻ ሕጉን እንዲያከብሩ ያደርጋሉ። ይሔ ልማድ መቅረት አለበት። በሕዝብ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው እንደውም ከ90 በመቶ በላይ ለሕግ ተገዢ ነው። ራሱን ለማሳደግ እና ኑሮውን ለማሻሻል የሚባዝን ነው። ነገር ግን ከሕብረተሰቡ ውስጥ የተወሰኑ ቡድኖች የሕግን አለመከበር የሚቃወሙ ሰዎች አሉ።
የመንግሥትን ሕግ አለማስከበር በተመለከተ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎች የነቁ ፣ ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የሚያስቡ ሕገወጥነትን መሸከም የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ ያነሳሉ። የሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ ጥያቄው ከእነርሱ አልፎ ወደ ወጣቱ እና ወደ ተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚሔድበት ጊዜ ወደ ግጭት ወደ አለመግባባት እና በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል ያለው ግንኙነት የተበላሸ ይሆናል። ይህ ደግሞ ለጦርነት እና ለግጭት ይዳርጋል።
ዜጎች በአንድ ሀገር ውስጥ ኑሯቸውን በሚገፉበት ጊዜ የሚጠበቁባቸውን ሕጋዊ እና ሕገመንግስታዊ መብቶችን እና ግዴታዎቻቸውንም ማወቅ አለባቸው። እንቅስቃሴያቸውም በሕግ ውስጥ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአብዛኛው ለሕግ ተገዢ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንዶች እንደውም መብታቸውንም ስለማያውቁ ከመብታቸው ቀንሰው በስፋት ለመንግሥት የመገዛት አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ስለዚህ ችግሩ ከሕዝብ አይደለም።
በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሲቃኝ በሃይማኖቶች እና በወጣቶች፣ በብሔር ስም በየአካባቢው የሚካሄዱ የቡድን እንቅስቃሴዎች ከኋላቸው ግፊት አላቸው። ዝም ብለው ተሰብስበው የመነሳት ጉዳይ ብቻ አይደሉም። የፖለቲካ ፍላጎት እና ጥቅምን ማዕከል ያደረጉ ናቸው። እነዚህ በሕዝብ ስም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው እንጂ፤ የሚጠቅሙት ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የተወሰኑ ጥቅም ማግኛ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን ብቻ ነው።
በኢህአዴግ ጊዜ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ተጠቅሟል ማለት አይቻልም። አሁን ላይ ወደ ኦሮሚያ ተረኛ ናቸው የሚባል ነገር አለ። ነገር ግን የኦሮሞ ሕዝብ እጅግ የሥቃይ ኑሮ እየገፋ ነው። ለምሳሌ ሰሞኑን ሰላሌ አካባቢ ለአምስት እና ለስድስት ዓመታት ሲፈራረቅባቸው የነበረውን ጫና እና ጭቆና መሸከም አቃተን እያሉ ነው። በዚህ እኛም እየተሳቀቅን ነው። መንገደኛውም ከከተማ ወደ ገጠር፤ ከገጠር ወደ ከተማ ለመንቀሳቀስ ችግር እያጋጠማቸው ነው። ይህ ሁሉ የአጭር ጊዜ ፍላጎት ያመጣው ውጤት ነው። ዛሬ የምናገኘው ጥቅም ዘላቂ እንዳልሆነ፤ ዛሬ የሚፈፀም ግፍ እና በደል፤ ነገ በእኛም ሆነ በልጆቻችን ላይ ችግር እንደሚያስከትል የመገንዘብ ፍላጎታችን በጣም የተወሰነ በመሆኑ ይኸው በየዘመናቱ በግጭት ውስጥ እና በጦርነት ውስጥ እንኖራለን።
አዲስ ዘመን፡- ሕግ መከበር አለበት የሚለው ያስማማል፤ ነገር ግን ለግጭቶች መነሻቸው ምንድን ነው? ድህነት በራሱ የግጭት መነሻ አይሆንም?
አቶ ደስታ፡- መንግስት ጥሩ እና የተመቸ ከሆነ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። በየቦታው በምርምር የታገዘ ሥራ ይሠራል። ሕግ ቢኖር ሁሉም በሚወደው የሥራ መስክ ይሠማራ እና ውጤታማ መሆን ይቻላል። ድህነት ይቀንሳል። ለምሳሌ የእግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን የሚፈልግ ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ስኬታማ ይሆናል። የምርምር ዝንባሌ ያለውም ተመራማሪ ይሆናል። ነፃነት ካለ ዜጎች በነፃነት እያሰቡ፣ በነፃነት እየሠሩ እና እየተቃወሙ፤ በነፃነት እየጠየቁ በዘርፋቸው ውጤታማ
ይሆናሉ ማለት ነው። ነጋዴዎችም ያለምንም ወሰን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ሥራቸውን ማስፋፋት ቢችሉ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። ይህ ሁሉ የተመቻቸ መንግሥታዊ አስተዳደር እና መንግሥታዊ አሠራር ይፈልጋል።
ሁልጊዜ ሰዎች ሰላም ሲነሳ ወደ መንግሥት ወቀሳ የሚያዘነብሉት ለዚህ ነው። የአሁኑ ሰላም የአሁኑ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥታትን ያለፉትን ጨምሮ የሚመለከት ጉዳይ ነው። የተለያየ ሙያ ያላቸው እና ለቴክኖሎጂ እና ለፈጠራ መንስኤ የሆኑትን ባለሙያዎች ቀደም ሲልም ከመንግሥት ጀምሮ ሲፈረጅ ቆይቷል። አንዱን ሸማኔ፣ አንዱን ቀጥቃጭ ሌላውን ፋቂ በማለት ስናናንቅ ኖረናል። ይህ አሁንም ይታያል። ስለዚህ መነሻው መንግሥት ነው። ድህነቱ ከተነሳ ወደ መንግሥትም የሚሔዱ ሰዎች ዕውቀት ኖሯቸው፤ ከህብረተሰቡ የተሻሉ ሆነው ሕብረተሰቡን ለመጥቀም እና ሀገሪቷን ለመለወጥ ሳይሆን የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ነው።
አሁን በተወሰነ መልኩ የተማሩ እና አቅም ያላቸው ሰዎች ወደ ፖለቲካ ሲገቡ እየታየ ነው። ለምሳሌ ኢህአዴግ ሲመለምል የነበረው በትምህርታቸው የወደቁትን ብቻ ነበር። እነርሱ ደግሞ የራሳቸውን ኑሮ ለማሸነፍ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም የማያስቡ በመሆናቸው መንግሥት እንደላካቸው ይንቀሳቀሳሉ። ራሳቸውን ሆነው ማሰብ አይችሉም። የሌላ ሰውን ሃሳብ እየደገፉ ይኖራሉ። በተቃራኒው ብዙ አቅም ያላቸው ጨዋ ሰዎች ራሳቸውን መንግሥት መዋቅር ውስጥ አስገብተው ከሚያሰቃዩ ቤት መቀመጥን መርጠዋል። ወይም ደግሞ ከሀገር ተሰደው ይኖራሉ።
ሁልጊዜም ከሀገር እና ከሕዝብ ጥቅም አንፃር ሳይሆን ከመንግሥታቱ ፍላጎት አንጻር የማኖር ፍላጎት አለ። መንግሥታት ዜጎች ከዘመናዊነት ይልቅ በራሳቸው በተለካ እሳቤ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ይፈልጋሉ። የተማሩ፣ የነቁ እና የበቁ ሳይሆኑ ለመታዘዝ ምቹ የሆኑት ብቻ እየቀጠሉ ይሔዳሉ ማለት ነው። የመንግሥትን ጥቅም ለማስጠበቅ የቻለ ይቀጥላል። ያልቻለ ይቀራል። ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ሥራ ለመሥራትም ቢሆን አስቸጋሪ ነው። ከመንግሥት እና ከካድሬ አቋም የተለየ ሃሳብ ከተያዘ በግብር ስም ወይም በሌላ መንገድ ሥራው ይደናቀፋል። ነገር ግን የተለየ ለውጥ የሚመጣው በነፃነት ሲታሰብ ነው።
ሁሉም ሰው በነፃነት ሲያስብ ለውጥ ይመጣል። ነገር ግን ሁለት በመቶ ወይም አምስት በመቶ የሆኑ ሰዎች ብቻ የ120 ሚሊዮን ሕዝብን ጭንቅላት እኔ ወደ ፈለግኩት ብቻ ሃሳብ እወስዳለሁ ከተባለ ለውጥ አይመጣም። ዘመኑ የሚፈልገው ዴሞክራሲ፤ ሕዝቡ የሚፈልገው ነፃነት እስካልተገኘ ድረስ ለውጥን ማየት በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ድህነቱን ማሸነፍ ያልቻለ በቀላሉ ወደ መንግሥት ይገባል። በጣም ትልቁ በሽታችን ድህነት ሲሆን፤ የድህነታችን ምንጭ ደግሞ መንግሥቶቻችን ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ነገር ግን ለድህነታችንም ሆነ ሰላም ለማጣታችን መንስኤው ከቀጣናው እና ከውጪ ተፅዕኖ ጋርስ የተያያዘ አይደለም?
አቶ ደስታ፡- ቤቱን በትክክል ማስተካከል አቅቶት ጎረቤትን መክሰስ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም አንድ መንግሥት ጉብዝና እና ጥንካሬ ከሌለው ከሌላ ጋር እየተወዳደረ አቅም ሲያጡ ጎረቤቶቼ እንዲህ ስላደረጉኝ ነው የሚለው ተቀባይነት የለውም። ሁልጊዜም ቢሆን፤ ሌሎች ሀገሮች የእኛን ሀገር ለመብለጥ የተለያዩ መንገዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። በሃይማኖት ወይም በሪዮት ዓለም (በአይዶሎጂ) ሊመጡ ይችላሉ። ነገር ግን አንድ ቤት ሊፀና የሚችለው በቤቱ ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት ሲኖር ነው። የዜጎች በነፃነት የመኖር እና የማሰብ እንዲሁም የመሥራት ሁኔታ በጣም ወሳኝ ነው። በተገደበ ሁኔታ ውስጥ መኖር በራሱ ለሌሎች በር ይከፍታል።
እኔ ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ በነፃነት አልኖርኩም። ተገድቤያለሁ። የመንግሥትን መዋቅር በያዘ ሁለት በመቶ ሰው እሳቤ እና ፍላጎት ብቻ እንድናስብ ከተደረግን ነፃነት የለንም ማለት ነው። ነገር ግን በተፈጥሮ የሰው ልጅ ይመራመራል። ቁጭ ብሎም ሆነ እየተራመደ ያስባል። ሃሳቦች እየገፉት ከተገደበ ችግር ይፈጠራል። አንድ መንግሥት ለሕዝቡ ነፃነት ሰጥቶ እንደ ሕዝቡ ፍላጎት የሚያስተዳድር ከሆነ ከውጪ የሚመጡትን ጫናዎች መቋቋም ይችላል። ስለዚህ የውጪ ጫና በተከፈተ በር ከገባ ጥፋቱ የመንግሥት ነው። አሁን የውጪ ጫና ብቻ ሳይሆን ባለሀብትም በራሱ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። ስለዚህ በነፃነት እየመሩ ያሉ ሀገራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያሾሩናል። ለዚህ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለውም።
ውስጥን አይቶ ፈትሾ ራስን ከማስተካከል ይልቅ ችግሮችን ወደ ውጭ ማላከክ ደግሞ ውጤት አያመጣም። እኔ ለምን መቋቋም አልቻልኩም የሚለውን በደንብ ማየት ይሻላል። የኢትዮጵያ መንግሥታት ክፍተትን ውጫዊ ማድረግ አንዱ ልማዳቸው ነው። ሕዝቡ ጥያቄ ሲያነሳ ይሔ የውጪ ተላላኪ ነው ብሎ የመፈረጅ ሁኔታ አለ። ነፃነት በማጣታችን በጫና ሥር ስላለን የውጪ ሰዎች በዕምነት እና በፖለቲካ አመለካከት ቢያምሱን አያስገርምም። እንደውም ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ ባለሀብቶችም እያመሱን ናቸው። ይህ በየትኛውም ዓለም የተለመደ ነው። አሜሪካ ራሺያን ራሺያ አሜሪካንን ትሰልላለች። አንዱ ሌላውን ከመሰለል አልፎ ሌሎች ነገሮች እንዲፈፀሙ ሁሉ ይሠራል። ይሄ በየትኛውም ሀገር ላይ ያለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ፈቅዶ ለግጭት አንደኛው መፍትሔ ይሆናል በማለት አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ምክክር እየተካሄደ ነው። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ደስታ፡- መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍፁም ነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ አለበት። ባላቸው በሕገመንግሥቱ በተቀመጠላቸው መብት ተጠቅመው ፕሮግራማቸውን ማስተላለፍ ቢችሉ ይህ ወደ ሌላ የማየት ነገር አይኖርም። ስለዚህ ከመንግሥት የሚጠበቀው ትልቅ እና የአንበሳ ድርሻ ነው። መንግሥት የሚጠበቅበትን ባለማድረጉ አሁን ጫካ ገብተው ከሕግ በላይ የመሆን እና የመዋጋት ፍላጎት ቢኖር እንኳ የሚያራርቁ ሥራዎችን ከመሥራት ይልቅ የሚያቀራርቡ ሥራዎችን መሥራት አለብን። ከሀገራዊ ምክክሩ አንፃር አሁን እዚህ እና እዛ ያለው ግጭት ሀገራዊ ምክክሩን እየሸፈነው ነው። የሚፋለሙ ወገኖች እርስ በእርስ እየተገዳደሉ ነው።
በመንግሥት እና በእነዚህ ተፋላሚ ወገኖች መካከል እውነተኛ ንግግር መኖር አለበት። ልክ ትግራይ አካባቢ እንደነበረው ጦርነት የሚቆምበት ሁኔታ መፈጠር መቻል አለበት። ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሰጥቶ የመቀበል ድርድር መደረግ እና ወደ ውይይት መገባት አለበት። ጦርነት እየተካሔደ ምክክር ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው። ከዛ በፊት ድርድር መካሔድ ይኖርበታል። ስለዚህ በመንግሥት እና በተዋጊ ኃይሎች መካከል ጦርነትን ማስቆም የሚችል ድርድር መደረግ አለበት።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌሎች ተቋማት የሲቪክ ማህበራት ሚዲያው ነፃ እና ገለልተኛ በመሆን፤ በማሸማገል ሂደት ውስጥ የራሳቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል። ያጠፋውን አንተ አጥፍተሃል ማለት ካልተቻለ በመጣንበት መንገድ እንቀጥላለን። ይህ ማለት መፍትሔ አይገኝም ማለት ነው።
መንግሥትም ኃይል ስላለኝ ሁልጊዜ አሸንፋለሁ ማለት አይችልም። በጦርነት እየወደመ ያለው ንብረት እና እየጠፋ ያለው ሀብት ለብዙዎች የሥራ ዕድል ይፈጥር ነበር። ጦርነት ገንዘባችንን እየበላ ነው። ለመሳሪያ መግዣ፣ ለወታደር ደመወዝ እና የመረጃ ሰራተኛ ለመቅጠር እንዲሁም ለሌሎችም ከጦርነት ጋር ለተያያዙ ወጪዎች ተዳርገናል። አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ አገልግሎት አሰጣጥ ትንሽ የተስተካከለ ይመስላል እንጂ፤ በተለያዩ ክልሎች ግብር ለመክፈል እንኳ ብዙ ፈተና አለ። በየክልሉ በተለይ በኦሮሚያ ግብር ለመክፈል ሲኬድ የሚሊሻ፣ የሠራዊት፣ የቀይ መስቀል፣ የአደጋ ስጋት እና ሌሎችም ክፍያዎችን ይጠየቃል። ዜጎችን የማስጨነቅ ሁኔታ እየታየ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን የባህር በር ጉዳይ እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ እንደ አንድ የፖለቲካ ሰው የሚሉት ካለ?
አቶ ታደሰ፡- ከላይ እንደገለፅኩት ቤትን ከፍቶ ሌባ ቢመጣ ምንም ማድረግ አይቻልም። በኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች አሉ። መንግሥታት ደግሞ በእኩዮቻቸው ላይ ጫና የማድረግ ዝንባሌ አለባቸው። ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ወደብ አልባ ሆናለች። ይህም በኢኮኖሚዋ ላይ ጫና ፈጥሯል። ስለዚህ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካን መያዝ ወሳኝ ነው። ምሥራቅ አፍሪካ ላይ በመቀመጧ የባህር በር ጉዳይ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
የባህር በር ለማግኘት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሌ ላንድ ጋር ስምምነት ፈጥሮ ነበር፡፤ እርሱ ደግሞ ሌላ ችግርን ወልዷል። በዚህ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰፊ ውይይት አካሂደው ነበር። የባህር በር በመርህ ደረጃ ይደገፋል፤ ነገር ግን ሊመጡ የሚችሉት ችግሮች ትኩረት ሊደረግባቸውና ቀላል ዋጋ የሚያስከፍለውን ዘዴ መከተል አለብን የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብ ሰንዝረዋል። በዛ ላይ እኔም እስማማለሁ።
የባህር በር ያስፈልጋል፤ ነገር ግን በምን መልኩ እናግኘው የሚለውን በኪራይ ነው ወይስ በሌላ የሚለው መታወቅ አለበት። የሶማሌ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገውን ስምምነት በመቃወም ያ ተቃውሞ ዲፕሎማሲውንም እያካለለ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ግብፅ በዓባይ ጉዳይ አኩርፋለች። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ከሶማሌ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት እያየን ነው። ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል ምንም ጥያቄ የለውም። ነገር ግን ወደብ ለማግኘት ስንሰራ ውጤታማ እና ብቃትን እንዲሁም አግባብነትን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት። እርሱን ለማግኘት የውስጣችን ጉዳይ ወሳኝ ነው። ውስጥ ሰላም ካለ ጉልበት እና ጥንካሬ ይኖራል።
አሁን በግብፅ እየተደረገ ያለው ወዴት እንደሚሔድ አይታወቅም። እኛ በከፈትነው በር ሁሉም እንዳይገባ ለውስጣችን ሰላም ቅድሚያ መስጠት አለብን። የመንግሥት ባለስልጣን የሚያስከፍላቸው ዋጋ ቢኖርም ከሀገር ጥቅም አንፃር ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት አለባቸው። አወንታዊ ውጤት በሚያስገኝ አኳኋን መፍታት ያስፈልጋል።በተለይ ከሶማሊያ ጋር ተያይዞ የቅርብ ክትትል እና ዝግጅት ማድረግ ይጠይቃል። ይህ ማለት ቀጥታ ጦርነት ውስጥ እንገባለን ማለት ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲው ላይ ትልቅ ሥራ በመሥራት ለሕዝባችን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ ደስታ፡- እኔም እጅግ አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም