“በዓባይ ግድብ ላይ ያልተሳካውን ተጽዕኖ በሶማሊያ በኩል ለመፈጸም እየተሞከረ ይመስለኛል” – አቶ ፈቂአሕመድ ነጋሽ የውሀ ሀብት አስተዳደር ባለሙያ

ግዙፍ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለስኬት የበቃ ነው- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ። ኢትዮጵያ ያለማንም አጋዥ የግድቡን ሥራ በማሳካት ብርታቷን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በጉልህ ማሳየት የቻለችበትም ተግባር ነው። ፈተናው ታልፎ ኢትዮጵያውያኑም ከግድቡ እየተገኘ ያለውን ትሩፋት መቋደስ ጀምረዋል። እኛም በዛሬው ወቅታዊ አምዳችን ላለፉት 35 ዓመታት በውሀ ላይ የሰሩትንና በሕዳሴ ግድቡ ጉልህ ሚና ያላቸውን የውሀ ሀብት አስተዳደር ባለሙያውን አቶ ፈቂአሕመድ ነጋሽን አነጋግረናል።

እርሳቸው፤ በአብዛኛው የሰሩት ወሰን ተሻጋሪ ውሀ ላይ ነው። በዚሁ በወሰን ተሻጋሪ ውሀ ላይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እስከ ዳይሬክተር ደረጃ ደርሰዋል። ቀጥሎም በናይል የትብብር መድረክ ‘በናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ’ ስር ካሉ ተቋማት አንዱ የሆነውን የምሥራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤትን በሥራ አስኪያጅነት መርተዋል። አሁን በውሀ ሀብት አስተዳደር ወሰን ተሻጋሪ ወንዞችና በውሃ ዲፕሎማሲ ላይ የግል አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ ቀርቶታል፤ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በጥናቱም፣ በማማከሩም ሆነ በድርድሩ ተሳታፊ እንደመሆንዎ መጠን የእስካሁን ሂደቱን እንዴት ያዩታል?

አቶ ፈቂአሕመድ፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገራችን ውስጥ በልማት ዘርፉ ከተወሰዱ ግዙፍ ውሳኔዎች የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል። ግድቡ ትልቅ የኃይል ማመንጫ ከመሆኑም በተጨማሪ በጣም ውስብስብ የሆነ ነው። ከኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ጋር በተያያዘ የሃይድሮ ሜካኒካልና ኤሌክትሮ ሜካኒካል የሚባሉት ሥራዎች በጣም ውስብስብ የሆኑ ናቸው። ግድቡ በጣም በረሃማ በሆነ ቦታ ላይ የተሰራና ብዙም ሕዝብ ያልሰፈረበት አካባቢ ያለ ነው። ግድቡ ወሰን ተሻጋሪ በሆነው በዓባይ ወንዝ ላይ የተሰራ ነው። የዓባይ ወንዝ ደግሞ በዓለማችን ላይ ካሉ ወንዞች በጣም ትልቅ ፍጥጫና ያለመግባባት ከሰፈነባቸው ወንዞች ውስጥ አንዱ ነውና እዛ ላይ መወሰኑ በራሱ ጉዳዩን የሚያገዝፈው ነው።

እንደሚታወቀው የእኛ ሕዝብ በአብዛኛው የሚተባበረው ጦርነት ላይ ነው። በትብብር ደረጃ ልማት ላይ ብዙ ልምድ አልነበረንም። እናም ሕዝብን አስተባብሮና አንድ አድርጎ ይህን ልማት ‘እጨርሳለሁ’ ብሎ መወሰንና ለሥራው መነሳት ትልቅ ውሳኔ ይመስለኛል። በወቅቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተገኘውም ምላሽም ትልቅ ነበር። ሕዝቡ ከጫፍ ጫፍ በዘር፣ በኃይማኖት፣ በጾታና በጎሳ ሳይለያይ ድጋፍ የሰጠው እጅ ለእጅ ተያይዞ ነው፡። በትብብርም ደረጃ ሲለካ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በእውቀትም ሆነ በሞራልና በጸሎት ጭምር ሕዝቡ ርብርብ አድርጓል። ከዚህ የተነሳ ፕሮጀክቱ ሕዝባዊ ፕሮጀክት ነው ብሎ መውስድ ይቻላል።

ግድቡ ሲጀመር ያልቃል ተብሎ የተወሰደው በሰባት ዓመት ውስጥ ነው። እንዲህ ዓይነት ውስብስብ ፕሮጀክቶች ከ40 እስከ 60 በመቶ በጊዜም በዋጋም ከእቅዳቸው በላይ ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃሉ። ስለሆነም የሕዳሴ ግድቡም ከ10 እስከ 11 ዓመት ድረስ ሊፈጅ እንደሚችል የሚጠበቅ ነበር፡። ከተጠበቀው አንድ ሁለት ዓመት ያህል የዘገየ ይመስለኛል። ይሁንና አሁንም ቢሆን በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ነው። ዋናው ነገር ደግሞ መጠናቀቁ ነው። ግድቡ ተጠናቆ ማየት መቻላችን ደስ የሚያሰኝ ነው፤ በቀጣይ ደግሞ ከግድቡ የሚጠበቅ ጥቅም ብቻ ሳይሆን የምንሻው ሌሎች ቀጣይ የሆኑና በርካታ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ነውና እነርሱም የሚጠበቁ ይሆናል። ሕዳሴ ሲጠናቀቅ ለእነዚያ ለምናስባቸው ግድቦች ፈር ቀዳጅ ይሆናል ብለን እናምናለን። ከዚህ አንጸር ሁሉም እንደየአቅሙና እንደየችሎታው መጠን የተረባረበበት ኢትዮጵያዊ የሆነ ፕሮጀክት ነው ማለት እንችላለን።

አዲስ ዘመን፡- ሀገራችን ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ድረስ የነበሩ የተለያዩ ተጽዕኖዎችን አስተናግዳ በብቃት ተወጥታቸዋለች፤ አሁን ላይ ያለፈቻቸውን ተጽዕኖዎች ሲያስታውሱ እውነት ኢትዮጵያ እነዚያን ተጽዕኖዎች መሸከም ትችል ነበር የሚል እምነት ነበርዎት?

አቶ ፈቂ አሕመድ፡- ፕሮጀክቱ መስከረም ወር 2003 ዓ.ም ለውሳኔ ፓርላማ በቀረበ ጊዜ አባላቱ በጣም በርካታ ጥያቄ መጠየቃቸውን አስታውሳለሁ። ከጠየቁት ጥያቄ ውስጥ አንደኛው ‘ግብጽ ዝም ትላለች ወይ?’ የሚል ይገኝበታል። በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሰጡት ምላሽ፣ ‘አይ! ዝም አትልም፤ ታስፈራራናለች’ ሲሉ መልሰዋል። አክለውም፤ “መፍትሔው ደግሞ አለመፍራት ነው” አሉ። አለመፍራት ሲባል ደግሞ ዝም ብሎ መቀመጥ ማለት ሳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄን ማድረግ ነው ሲሉ አብራሩ። ይህ በመሆኑ ወደ ፕሮጀክቱ ትግበራ የተገባበት ለሁሉም ነገር ዝግጁ በመሆን ነው።

ይሁንና አንዳንድ ጫናዎች ወደ ጽንፍ የገቡበት ሁኔታዎች ተስተውለዋል። ያልተጠበቁ ምላሾችንም ያገኘንባቸው ሁኔታዎች ነበሩ፡። ደግሞም ልንማርባቸው የምንችላቸው ስሕተቶችንም ሰርተናል። በተለይ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የነበረው ጫና በጣም ከባድ ነበር። ሀገራቱ በመጀመሪያ ሲገቡ ተለሳልሰውና ድምጻቸውን አጥፍተው ነው። ሲጠይቁን የነበረውም ‘እባካችሁ ስጋት አለንና መረጃ ስጡን፤’ እያሉ የተማጽኖ ያህል ነበር። እንዲያውም አዲስ አበባ በመጡ ጊዜ ግንቦት ወር በ2003 ዓ.ም ላይ በዚያን ጊዜ ሕዝባዊ ዲፕሎማሲ መጥቶ ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያን ለማሳሳት ብለው ‘የ1929ኙን ስምምነት ውድቅ እናደርጋለን’ እስከ ማለት ደርሰው ነበር። ነገር ግን የ1959ኙ ውድቅ እናደርጋለን አላሉም።

እኛ ደግሞ በወቅቱ ብዙ ነገር ቃል ገባንላቸው፤ እሱ ደግሞ ጥሩ ነው። ከሀገራት ጋር በጥርጣሬ እየተያዩ አብሮ መሥራት አደጋ ስላለው ያው በራችንን ከፍተንላቸው ነበር። ከዚያም ነገር ተጠቃሚ ነን፡። እስከ መጨረሻው ድረስ አሳትፈናቸዋል። ግድቡንም እንዲያውቁት አድርገናል። ምክንያቱም ጉዳት እንደሌለው ሲያውቁት ስለሚረዱ ግንዛቤው ይኑራቸዋል የሚል እምነት ነበረን። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ኢትዮጵያ ማድረግ ከሚጠበቅባት በላይ አልፋ መሔድ ችላለች ብዬ አምናለሁ።

ይህ መታየት ያለበት ከምን አኳያ ነው ከተባለ ግብጽ በ1960 ላይ የአስዋንን ግድብ ግንባታ ስትጀምር በወቅቱ ኢትዮጵያ ‘መረጃ ይሰጠኝ’ ብላ ጠይቃ ነበር። ፈቃደኛ አልነበሩም፤ ምላሻቸው ‘አንሰጥም’ የሚል ነበር። ቆየት ብለው እንደ ቶሽካ ዓይነት ፕሮጀክቶቻቸውን ሲጀምሩም በዚያን ጊዜም ኢትዮጵያ መረጃ ጠይቃለች፤ እነርሱ ግን አልሰጡም። እኛ በእነርሱ ልክ አልመለስንላቸውም።

የላይኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት ሁሉም በጣም ደጎች ናቸው ማለት ይቻላል። እነርሱ ተርበው የታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት እንዲበሉ፤ እነርሱ ተጠምተው የታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት እንዲጠጡ እንዲሁም እነርሱ ታርዘው የታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት እንዲመቻቸው የማያደርጉት ጥረት የለም። ኢትዮጵያም የዚያው አካል ትመስለኛለች። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በወቅቱ ግብጾች መረጃ አልሰጡኝምና ‘ዞር በሉ’ አላለችም፡ ይልቁኑ ኢትዮጵያ ስለግድቡ መረጃ ሰጠቻቸው፤ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች መጥተው ግድቡን ይዩ አሉ፤ እነርሱንም አስገብተን አብረን አየን። ተጨማሪ ባለሙያ አምጥተን ምርመራ ይደረግ አሉ። ያንንም አደረግን። ያለንን መረጃ በሙሉ ሰጠናቸው፤ ሚኒስትሮቻቸው፣ ፖለቲከኞቻቸው ሁሉ ሄደው ግድቡን አይተዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን በእነርሱ ዘንድ ይታይ የነበረው ለዓለም አቀፍ ጫና ሲያመቻቹን እንደነበር ነው። በየጊዜው እያንዳንዱ ነገር ላይ ‘ይህን ጉዳይ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቢሰሩ፣ ያኛውን ነገር የዓለም አቀፍ አማካሪዎች ቢመለከቱ’ እያሉ ቆዩና በኋላ ላይ ደግሞ ‘የዓለም ባንክ በጉዳዩ ቢገባ’ የሚል ጥያቄ አነሱ። እኛ በዚህ ጊዜ ሃሳባቸውን ውድቅ አደረግንባቸው። ከዚያ ደግሞ ትንሽ ቆዩና የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግሥት ሲሉ ዞረው በአሜሪካ መንግሥት መጡ። በወቅቱ እኛም የአሜሪካ መንግሥትንም ሆነ የዓለም ባንክን ማስገባት ያልነበረብን ቢሆንም፤ አስገብተናቸዋል።

ከገቡ በኋላም ያደረጉትን አስተውለናል። በመጨረሻም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የዓለም አቀፍ ሰላም ስጋት አድርገውት ለተባበሩት መንግሥታት የሰላም ጥበቃ ምክር ቤት የወሰዱበት ሁኔታ ነበር። ይህንን ሁሉ ግን ኢትዮጵያ በተረጋጋ ሁኔታ ስታይ ቆየች። በወቅቱም ብዙ ባለሙያዎች ያሉበት በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኤክስፐርቶች ፓናል በሚል ስያሜ ቡድን ተቋቋመው። ቡድኑ ሀገራችን ውስጥ አሉ የሚባሉ ወደ ሃያ ባለሙያዎች ያሉበት ስብሰብ ነው። ጉዳዩ ወደ አሜሪካ እስኪሔድ ድረስ ባለሙያዎቹ ናቸው መንግሥትንም እያማከሩ ያለምንም ክፍያ በራሳቸው መኪና፣ ነዳጅ፣ ስልክ እና ኢሜል እየተንቀሳቀሱ እየተደራደሩም ሆነ እያማከሩ ይዘው ተጉዘው የቆዩት። በኋላ ላይ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ቡድኑ እንዲበተን ተደረገ። በርግጥ የዚያ ቡድን አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ የነበረ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የመበተናችሁ ምክንያት ምንድን ነው? በዚያ ልትቀጥሉ አለመቻላችሁ ምን ተፈጥሮ ነው?

አቶ ፈቂ አሕመድ፡- ምክንያቱ በርግጥ ምን እንደሆነ በውል አይታወቅም፤ ምናልባት እንዲሁ መገመት ይቻል ካልሆነ በስተቀር። የባለሙያዎችን ተሳትፎ እናሰፋለን በሚልና በአዲስ መልክ ይዋቀራል በሚል የተበተነ ነው። በወቅቱ እኔ የቡድኑ ሰብሳቢ ነበርኩ። ከዚያም ሰብሳቢ ተቀየረ። ቀጥሎ ለስብሰባ የሚጠራ ሰው ጠፋ። በአሁኑ ወቅት አምስት ዓመት ሆኖታል። አንድ ሁለት ጊዜ ስብሰባ የተጠራን ቢሆንም ተሰረዘ። በሌላ ጊዜ እንዲሁ ለማቋቋም ሞክረው ነበር። ለምን እንደቀረ ግን አልታወቀም። ነገር ግን በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ብዙዎቹ ባለሙያዎች መደገፍና ማገዝ እንፈልጋለን ብለው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሳውቀው እንደነበር ይታወቃል። በተለይ በሚኒስትር ዴኤታው አማካይነት ይጠይቁ እንደነበር ራሳቸው ሚኒስትር ዴኤታው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ግን የቀረው እንደተበተነ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ታሳድር የነበረውን ተጽዕኖ በማቃለል ደረጃ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሚናውን ያለአድልዎ ተወጥቷል ብለውስ ያስባሉ?

አቶ ፈቂአሕመድ፡- የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ስንል ሶስት ቦታ መክፈል እንችላለን። አንደኛ የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት አሉ። እነርሱ ተጽዕኖውን ለመቀነስ ያደረጉት ርብርብ በጣም ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም የግድቡን ግንባታ የወሰዱት ፍትሃዊ ነው ብለው ነው። ይሉ የነበረውም ይህ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት ነው የሚል ነው። ምናልባትም ተፋሰሱ ውስጥ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን ያስፍናል የሚል እምነት አላቸው። የአፍሪካ ሀገራት በአብዛኛው ከተወሰኑ ሀገራት ውጭ ሁሌ ከኢትዮጵያ ጋር የሚጋጩ ሀገሮች እንዳሉ ይታወቃል። ከእነዚያ ውጭ በአብዛኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ጨምሮ የሰጡት ድጋፍ ነው።

ሌሎቹ ገለልተኛ የተባሉ ሀገራት ነበሩ። ለምሳሌ እኤአ እስከ 2020 ድረስ የአውሮፓ ኅብረትና በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ገለልተኛ ነበሩ። ከኢትዮጵያም ጋር መጋጨት አይፈልጉም። ከግብጽ ጋርም መጋጨት አይፈልጉም። ማንንም ማስቀየም አይፈልጉም። ተደራደሩ፤ ተስማሙ፤ ከማለት ውጭ ብዙ ጫና አልነበራቸውም። የኢስያ ሀገራትም ተመሳሳይ ዓይነት አቋም ነበራቸው። እነርሱን በገለልተኛነታቸው መውሰድ ይቻላል። አሜሪካም መጀመሪያ ላይ እንደዚያ ዓይነት አቋም ታሳይ ነበር። በኋላ ግን ግልጽ በሆነ መልኩ አሜሪካና የተወሰኑ የአረብ ሀገራት፣ የተወሰኑ ሀገራት ከአውሮፓም ከአፍሪካም መውሰድ እንችላለን ከግብጽ ጎን ቆመው ኢትዮጵያን እስከ ማስፈራራት እና ጫና እስከ መፍጠር፣ ብድር እስከ ማስከልከል መንቀሳቀስ እና ርዳታ እስከ መሰረዝ የሄዱበት ሁኔታ ነበር። ስለዚህ ሶስት ዓይነት ጫናዎች ነበሩ ማለቴ

ከዚህ የተነሳ ነው። በኢትዮጵያ በኩል ሁሉንም በአንድ መልክ የማየት ነገር ነበር። አሜሪካም ብትሆን ፍትሃዊና ሚዛናዊ የሆነ ሃሳብ ወይም አስተያየትና ድጋፍ ትሰጣለች ተብላ አትታሰብም። አረብ ሊግም ከግብጽ ጎን ቆሞ ሲከራከር ኢትዮጵያ ባስተዋለች ጊዜ፣ ‘ግድየለም አረብ ሊግ የተቋቋመው ለዚህ አይደለምና እኛው እርስ በእርሳችን ብንፈታው ይሻላልና ከዚህ ብትወጡ’ በማለት ሃሳብ ስታቀርብ ነበር። የአፍሪካ ሀገራት ግን ድጋፍ እንዲሰጡንና ከጎናችን እንዲቆሙ በፈለግን ጊዜ አፍሪካ ኅብረት እንዲሁም ኢጋድ ከጎናችን መቆም ችለዋል። ይዘው የተንቀሳቀሱትም ማስታረቅንና ብቸኛው አማራጭ ሰላም መፍጠር ነው በሚል ነው። የተለያዩ ጫናዎችን መቋቋም የቻልነው በዚህ መልኩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ እንደተለመደው ሰሞኑን ለጸጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድቡ ላይ የያዘችውን የተናጠል ፖሊሲ ሙሉ ለሙሉ እቃወማለሁ ብላለች፤ በርግጥ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያላማከረችው ሃሳብ አለ? የተናጠል ፖሊሲ የሚባለው ከየት የመጣ ነው? የሕዳሴ ግድቡ ተገንብቶ እየተጠናቀቀ ባለበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ማንሳት ምን ማለት ነው?

አቶ ፈቂአሕመድ፡- ያው የግብጽ ጥያቄ ሁሌም ቢሆን የሚጠበቅ ነው። ከዚህ በኋላም ግድቡ አልቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምርም ይቀጥላል። በእኛ በኩል ጥበብ የሚያስፈልገን ይመስለኛል።

ወደኋላ ተመልሰን አንድ ማየት የተገባን ጉዳይ አለ ብዬ አስባለሁ። ይህን ጉዳይ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ አንስቼዋለሁ። ግንቦት 20 ቀን እኤአ 2013 ላይ የዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች ፓናል አዲስ አበባ ላይ የመጨረሻውን ስብሰባ ሲካሔድ ነበር። እኛ በወቅቱ ‘ሪፖርቱ ይፈረማል፤ አይፈረምም’ የሚል ጭንቅ ላይ ነበር። ስብሰባው ተጀምሮ በ5ኛው ቀን ግብጾች ስብሰባውን ረግጠው ወጡ። ምንድን ነው ሲባል ‘የሕዳሴው ግድብ አቅጣጫውን ቀይሯል።’ አሉ። አቅጣጫ መቀየሩን ደግሞ ከዚያ በፊት ሔደው በተግባር አይተውታል። ተመልሰውም ያሉት ነገር አልነበረም። ነገር ግን ግንቦት ሃያ በዓል ግድቡ ዘንድ እየተከበረ ነበር። መንግሥትም በዓሉ እዚያ እንዲከበር ሲያደርግ የእነርሱን ስሜታዊነት ትኩረት ስላላደረገው እነርሱ ከአዲስ አበባ ስብሰባውን ረግጠው ወጡ። ካይሮ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለበት ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ አካሔዱ። ኤምባሲው ላይም ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። ካይሮ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተደበደቡ። የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሙርሲ፣ የግብጽ ጦር በከፍተኛ ተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዙ። ሚኒስትራቸው እኛ ሚኒስትር ዘንድ ደውለው ‘ንግግር አድርጉና የግብጽን ሕዝብ እምባ አረጋጉ’ አሉ። እኛ ደግሞ ‘የግብጽን ሕዝብ ማረጋጋት ያለበት የግብጽ ሚኒስትር ነው እንጂ የኢትዮጵያ አይደለም’ አልን። በብዙ ልፋትና በሱዳኖች ጥረት ግብጻውያኑ ወደ ስብሰባ ተመልሰው ሰነዱ ተፈርሞ እንዲወጣ ተደረገ።

የመጀመሪያ ጊዜ ተርባይንም ሲገባ እንዲሁ በግብጽ በኩል ተቃውሞ ነበር። ምክንያቱም ባለስልጣናቱ የሕዝብ ጫና አለባቸው። ይህ ዓይነት ነገር ላይ ጥንቃቄ ይሻል። እኛ ተርባይን ገባ ብለን ስናከብር እነርሱ ዘንድ የሚፈጠረው ጭንቀት ነው። የሆነ ነገር ሥራው ከፍ እያለ ሲመጣ እና መንግሥት ያንን ሲገልጽ “በቃ ድርድሩ ይቀጥል፤ እንዲህ እንዲሆን አንፈልግም’ የሚል ጫና ለመፍጠር ይጥራሉ። ስለዚህ እዚህ ላይ በእኛ በኩል ጥበብ የሚያስፈልገን ይመስለኛል። በርግጥ ሥራው የት እንደደረሰ መግለጽ ከሕዝብ ዘንድም ለድጋፍ የሚፈለግ ነው፤ ነገር ግን በጥንቃቄና እነርሱንም በማያስከፋ ድጋፍም በማይዳከምበት ሁኔታ ሚዛናዊ አድርጎ መሃል ላይ መሔድን ይጠይቃል።

ይሁንና አሁን ግድቡ ሞልቷል፤ ቀደም ሲል ሲሉ የነበረው ‘ግድቡ አንድ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሲይዝ ሁሉት ሚሊዮን የግብጽ አርሶ አደር ይፈናቀላል፤ አንዱ ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ ወደ አውሮፓ ይሰደዳል። ከቀረው ሕዝብ ደግሞ ግማሹ አሸባሪ ይሆናል’ ነበር። ይህን የማስፈራሪያ ካርድ ይሰማኛል ላሉት አካል ሁሉ ለመምዘዝ ሞክረው ነበር። ሌላው ያሉት ነገር የሕዳሴው ግድብ ሲሞላ የአስዋን ግድብ ወደ በረሃነት ይቀየራል የሚል የጉዳት መመዘኛም ነበራቸው።

በአሁኑ ወቅት የሕዳሴው ግድብ ሞልቷል ማለት ይቻላል። ነገር ግን አንድም የግብጽ አርሶ አደር አልተፈናቀለም። በመሆኑም ሌላ የሚያነሱት ነገር ስለሌላቸው ያላቸው አማራጭ ዝም ብሎ ለሙከራ ወደተባበሩት መንግሥታት መውሰድና ምናልባት ቅር ያላቸው ነገር ካለ ወደዚያ አቅጣጫ ለመሄድ ይሆናል እንጂ በአሁኑ ጊዜ ምንም ምክንያት የላቸውም።

አዲስ ዘመን፡- በአሁን ወቅት በሶማሊያ ውስጥ እያደረገች ያለውን የግብጽን እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል?

አቶ ፈቂአሕመድ፡- ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ቅሬታ አላት። የግብጽ ቅሬታ ላለፉት በርካታ ዓመታት ተፋሰሱ ውስጥ የነበራት የበላይነት መፋዘዙን ተከትሎ የመጣ ነው። ግብጽ ተፋሰሱ ውስጥ ምንም ነገር እንዳይሰራ የተፋሰሱ ሀገራት ሰላም ሳያገኙ እንዲኖሩ ያላደረገችው ጥረት የለም። የሕዳሴው ግድብ ድንገት ሲጀመር በፍጹም ያልጠበቀችው ነገር ሆነባት። ከዚያ በፊት ትናገር የነበሩትን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ አልቻለችም።

ከዚያ በፊት ግብጾች ይሉት የነበረው ለምሳሌ ፕሬዚዳንት ሙባረክ በሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ‘ኢትዮጵያ ዓባይ ላይ ግድብ ብትሰራ ግድበን እናፈርሰዋለን’ የሚል ነበር። ይህ ግድብ ሲጀመር ግን ፕሬዚዳንት ሙባረክ ቢሯቸው ውስጥ ነበሩ። ግን ምንም ርምጃ አልወሰዱም፤ ያልወሰዱት ለምንድን ነው ከተባለ የውሀ ላይ ግጭት ማንንም አያዋጣም። በተለይ ለታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ግጭት የመጨረሻው አደገኛ ነገር ነው። ምክንያቱም በሚፈጥሩት ችግር ራሳቸው ተመልሰው ሰለባ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው።

ምናልባት ግብጽ አሁን በግድቡ ምክንያት ወደግጭት ብትገባ ራሷ የግጭቱ ሰለባ እንደምትሆን ስለምታውቅ በሌላ አቅጣጫ ያንን አጀንዳ ይዛ በሱማሊያ በኩል የመጣች ይመስለኛል፡። በዚህ ጉዳይ በእኛ በኩል አሁንም የሚያስፈልገን ጥበብ ነው። እነርሱ በተፋሰሱ ውስጥ ‘እኛ ካቦ ነበርን’ ሲሉ ለረጅም ጊዜ ቆይተዋል፤ አሁን ያ ካቦነታቸው ቀርቷል። ‘አንድ ቀን ኢትዮጵያ ግድብ ሰርታ ዓባይን አቁማ ታጠፋናለች’ የሚል የቆየ ፍራቻ አላቸው። እሱ ፍራቻችን እውን ሆነ ብለው ስጋት ውስጥ ገብተዋል። ይህን ነገር መፍቻ ብቸኛው መንገድ ተፋሰሱ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ጉዳዩን መፍታት ነበረባቸው። ያንን ደግሞ እነርሱ የወሰዱት እንደ ድክመት ነው። ወደዛ መምጣት ስላልቻሉ ሌላ ሰበብ ሊፈጥሩ ይችላሉ። አሁንም በሱማሊያ በኩል መምጣታቸው ሌላ ሰበብ ፍለጋ ይመስለኛል። ይህን ጉዳይ መንግሥት በጥበብ ማለፍ አለበት የሚል አተያይ አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮያ ሕዝብ ይህንን ያልተገባ አካሄድ በመቀልበስ ህጋዊ ጥያቄውን እውን ለማድረግ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?

አቶፈቂ አሕመድ፡- በግድቡ ዙሪያ በቅድሚያ ማድረግ ያለብን ሀገራዊ አንድነትን መፍጠር ይመስለኛል። ሀገራዊ አንድነት መፍጠር ከተቻለ ግብጾች ሊያመጡት የሚችሉት ምንም ዓይነት ጫና አይኖርም። ሀገራዊ አንድነትን መፍጠር ካልቻልን ግን የመዳፈር ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። ዋናው ነገር በሀገር ደረጃ ሁሉም አካል መክሮ እንደ ሀገር የሚያዋጣንን አቅጣጫ መውሰድ ጥሩ ነው እላለሁ።

ግጭት ለማንም ቢሆን አዋጭ አይሆንም። ወደ ግጭት የመጣ ሁሉ አዋጭ አለመሆኑን አይቶ ይመለሳል። ያሸነፈ አካል እንኳን ራሱ የሚቆጥረው እንደተሸነፈ አድርጎ ነው። በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግጭት የሚበረታታ አይደለም፤ ሕይወት ያሳጣል፤ አካል ያጎድላል፤ ኢኮኖሚ ያጎሳቁላል፤ ሕዝብን ያፈናቅላል፤ ንብረት ይወድማል። በግጭት የሚበላሹ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ከዚህ የተነሳ ግጭት የሚያስከፍለው ነገር ስለሚበዛ ያንን በሰከነ ሁኔታ አይቶ ማለፉ የሚሻል ይመስለኛል።

ራሽያ ወደዩክሬን ስትገባ በ15 ቀናት ውስጥ አጠናቅቃለሁ በሚል ነበር። በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል ጊዜ እንዳስቆጠረ የአደባባይ ምሥጢር ከመሆኑም በላይ ምን ያህል የሰው ሕይወት እንደጠፋ እና ምን ያህል ንብረት እንደወደመ እንዲሁ የሚታወቅ ነው። ግጭት መጀመሩ እንጂ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመራ አይታወቅም። ስለሆነም በጥበብ መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የግብጽ ዘመናት ያስቆጠረና ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የማይሄድ፤ የውሀው ብቸኛ ተጠቃሚ እኔ እና እኔ ብቻ ነኝ የሚለውን መስመር የሳተ አካሄድ ለዘለቄታው ለመግራት፣ የተፋሰሱ ሀገራት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

አቶ ፈቂአሕመድ፡- የተፋሰሱ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ያሉት ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው። የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ስድስት ሀገራት ፈርመው አጽድቀውታል፤ ከዚያ የሀገር መሪዎች በቅርብ ጊዜ የመሰብሰብ እቅድ ያላቸው ይመስለኛል። ምናልባትም የሚሰበሰቡት በቀጣዩ ዓመት ጥቅምትና ኅዳር አካባቢ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ። የሚሰበሰቡት ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው። ከዚህ በኋላ የሚቋቋመው ኮሚሽን ነው። የኮሚሽኑ የበላይ አስተዳዳሪ የሚሆኑት የሀገር መሪዎች ናቸው። መሪዎቹ ተሰብስበው ውሳኔ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ማለት ነው። የሚሰጠውም ውሳኔ ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ተቋቁሞ ሥራ ይጀምር የሚል ነው።

ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ሥራ ሲጀምር ጥርስ ያለው ኮሚሽን የሚሆን ከሆነ በናይል ላይ ግዙፍ ግዙፍ የሆኑ ውሳኔዎችን መወሰን ይችላል። እንዲያ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ግብጽ የናይልን ግዙፍ የሆኑ ውሳኔዎች ከሚወሰኑበት መድረክ ላይ ትጠፋለች የሚል እምነት የለኝም። ከዚያ ቀድሞ ግን ኮሚሽኑ እንዳይቋቋም እስከ መጨረሻው ድረስ ግብጾች ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህ ይታወቃል፤ አሁንም ይህንኑ እያደረጉ ነው። ኮሚሽኑ ከተቋቋመም በኋላ ጥርስ እንዳይኖረው ማድረጋቸው አይቀርም፤ ጥረት ያድርጋሉ። የተፋሰሱ ሀገር መሪዎች ግን ጠንካራ ኮሚሽን ካቋቋሙና ውሳኔ እንዲሰጥ በቂ ኃይል ከሰጡት ወይም ደግሞ ሥልጣን ከሰጡት ግብጽ ወደዚያ ትመጣለች የሚል እምነት አለኝ።

ሌላኛው ነገር የግብጽን ፍራቻና ስጋት መረዳት አንዱ ነው። ግብጽ ዝናብ የላትም፤ የከርሰ ምድር ውሃ ቢኖራትም እንኳን አካባቢዋ በረሃ ነው። ሁሉም የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት እየተሳቀቁና እየፈሩ የሚኖሩት በጭንቀት ነው። የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት አካባቢ፤ የሆነ እንቅስቃሴ ሲኖር ሁሉም የሚያዩት በስጋት ነው። ስለሆነም ያንንም ስጋታቸውን መረዳት ነው፡። ከዚያ በኋላ መተማመን መፍጠር ከተቻለ ሀገራቱም ተረባርበው መሥራት ከቻሉ ስምምነቱ የውሃ መጠቀም ብቻ ሳይሆን የውሃ አስተዳደሩንም ጥበቃውንም ቁጥጥሩንም እንክብካቤውንም ስለሚይዝ ተጨማሪ ውሀ ተፋሰሱ ውስጥ መፍጠር ይቻላል የሚለውን ነገር በአግባቡ የዲፕሎማሲ ሥራ ከተሠራ ግብጽ የያዘችውን አቋም እያለሰለሰች ትሄዳለች የሚል እምነት አለኝ።

እነርሱም ደግሞ በውሀው ላይ የተለየ እምነት መጣል የለባቸውም። የግብጽ ኢኮኖሚ በጣም ጠንካራ ነው። ምናልባት ሔሮደተስ ግብጽ የናይል ስጦታ ነች ያለው በአራተኛ ክፍለ ዘመን ነው። ያኔ ግብጽ በናይል ላይ መቶ በመቶ የመኖር አለመኖር እጣ ፈንታዋ የተመሰረተው በዚሁ ወንዝ ላይ ነበር። አሁን ግን የግብጽ ግብርና በውሃ ላይ የተመሰረተው 15 በመቶ ነው። በውሃ ላይ የተመሰረተው የኃይል ማመንጫዋ ደግሞ ወደ አምስት በመቶ ነው። ስለዚህ ናይል ለግብጽ ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጽኦ በተለይ በግብርና ላይና በኃይል ማመንጫ አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዚህ ሁሉ የላይኞቹ ተፋሰሱ ሀገራት ከተባበሩ ግብጽ አመለካከቷን ትቀይራለች የሚል እምነት አለኝ። ግብጽ ሌላ አማራጭ የላትም፤ ከላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ጋር መስማማት አለባት።

አዲስ ዘመን፡- በእስካሁኑ ሂደት በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ እንደ ባለሙያ በጣም ደስ የተሰኙበት አሊያም ቅር የተሰኙበት ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ ፈቂአሕመድ፡- ግድቡ የሕዝብ ግድብ ነው። ይህ ግድብ ተጀምሮ ኢትዮጵያውያን ከላይ እስከ ታች ድረስ ሲረባረቡ ማየቱ በጣም ትልቅ ስኬት ነው የሚል እምነት አለኝ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየጾሙ የምግባቸው ወጪ ለግድቡ እንዲተላለፍላቸው አድርገዋል። ሁሉም ሠራተኛ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ከግድቡ አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎች ሲነሱ እንዲያውም ካላቸው ሀብት ለግድቡ ግንባታ 25 በመቶውን በመለገስ ጭምር ነው። ከዚያ በተረፈ ነፃ የጉልበት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆናቸው ጠይቀው ነበር። ሌላው ደግሞ አካባቢው ላይ ጸጉረ ልውጥ ሰው ሲያገኙ ይዘው ለጸጥታ ኃይሉ ይሰጣሉ። እነዚህ ሰዎች ከቦታቸው መነሳታቸው ተጽዕኖ የሚያርፍባቸው ሰዎች ሆነው ሳሉ ለግድቡ ያላቸው ቁርጠኝነት በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው።

እኔ ግድቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገራዊ አንድነት ይፈጥራል የሚል እምነት ነበረኝ። እሱን እድል ሙሉ ለሙሉ የተጠቀምንበት አይመስለኝም። ምናልባትም አንድ ያመለጠን እድል ቢኖር እርሱ ነው። ሀገራዊ አንድነት በግድቡ ዙሪያ መፍጠር አልቻልንም።፡ አሁንም እስከ መጨረሻ ድረስ ጥረት ማድረግ ያለብን ይመስለኛል። ምናልባት እድለኞች ከሆንን ተሳክቶልን እሱን እናሳካለን የሚል እምነት አለኝ። ግድቡ ትልቁ ግድብ እንጂ የመጨረሻው ግድብ አይደለም። የሕዳሴ ግድብ በተሳካ ሁኔታ በቅርቡ ይጠናቀቃል። እሱ ከተጠናቀቀ ደግሞ መንግሥት ተጨማሪ እንደዚህ ዓይነት ጠንካራ ጠንካራ ውሳኔዎችን ወስኖ ኢትዮጵያውያኑም ሁሉን ነገር ትተው ወደ ልማት ፊታቸውን ለማዞር እድል ይከፍታል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ፈቂአሕመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You