ትውልድ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ይላበስ ዘንድ ሰውነት በምግብ እንደሚገነባው ሁሉ አዕምሮም በእውቀት መገንባት ይኖርበታል። ንባብ ደግሞ እውቀት የሚሸመትበት ትልቁ ገበያ ነው። መፅሀፍት የሰዎችን አመለካከት በመቅረፁ በኩል ያላቸው ሚና ወደር የለሽ ነው። አንባቢ ትውልድ አብዝቶ ነገሮችን ያሰላል፣ ያነበቡ አእምሮዎች ሚዛናዊ ናቸው። ነገሮችን በቀናነት ይመለከታሉ፣ ጉዳዮችን በማስተዋል ይታዘባሉ። ጠቢባን ጥበብ ያወረሰቻቸው ጸጋ በብዕራቸው ከትበው ለሌሎች ያወርሳሉ።
ለዚህም ነው የንባብ ክህሎት በብዙዎች ይሰርፅ ዘንድ የንባብን ጠቀሜታ ተደጋግሞ የሚነገረው። በእርግጥም መፅሀፍት የተሰበረ አዕምሮን ይጠግናሉ። የተዛነፈ አመለካከትን ያቀናሉ። የተቡ ብዕሮች የማህበረሰብን ምግባር በማነፅ ድንቅ እሴትን ያስቀጥላሉ። መፅሀፍት ባህልን በማስተዋወቅ አገራዊ ገፅታን ይገነባሉ። ወቅቱ አንባቢያን ወደ መፅሀፍት መፅሀፍትም ወደ ተደራሲው ይበልጥ የሚቀርቡበት ነውና እኛም ንባብ ላይ ትኩረት አደረግን።
አንድ እድሜው ገና አራት ያልዘለለው ህፃን መድረክ ላይ የተረት መፅሀፍ ይዞ በተለያየ ቅላፄ ለመርሀ ግብሩ ታዳሚ በሚመስጥ መልኩ ያነባል። የልጁ ኮልታፋ አንደበትና ድንቅ የሆነው የንባብ ክህሎት መድረኩ ላይ የሚሰማውን ድምፅ በሁሉም ተወዳጅ አድርጎታል። መድረኩ ላይ የተሰቀለው ትልቅ ባነር “ሰኔ 30 የንባብ ቀን”ተብሎ በተፃፈ ፅሁፍ በጉልህ ይታያል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ያሰናዳው የንባብ ቀን መርሀ ግብር በዚህ ጣፋጭ በሆነ ህፃን ንባብ መክፈቻውን አድርጓል።
ብዙዎች ክረምትን ከንባብ ጋር ያገናኙታል። መነሻ ምክንያታቸው ደግሞ ትምህርት ቤት የሚዘጋበትና አብዛኛው አንባቢ የሆነ ማህበረሰብ ከመደበኛ ስራው ገሸሽ ብሎ በእረፍት የሚከርምበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የእረፍት ጊዜውን በንባብ እንዲያሳልፈው ከማለም ጋር የተያያዘ መሆኑ ይነገራል። የክረምት ወቅት ብዙዎች ንባብ ላይ ትኩረት የሚያደርጉበት ወቅት ነው። ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በተገኘው መረጃ መሰረትም፤ ሰኔን ተከትሎ የሚመጡት የክረምት ወራት ከሌላው ጊዜ በተለየ አንባቢና መፅሀፍ የሚበዙበት ነው።
በዚህ ወቅት የብዙ የአገራችን ደራሲያን ለአንባቢያን መጻህፍት የሚያቀርቡበትና በአንፃራዊነትም ጥሩ ሽያጭ የሚካሄድበት ወር ነው። ለዚህ ልዩ ልዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በተለይ ወቅቱ ከትምህርት ገበታው ለሚለየው ተማሪና አንዳንድ ተቋማት ተዘግተው የእረፍት ወቅት በመሆኑ ነው።
ተማሪው የእረፍት ጊዜውን አልባሌ ቦታ ከመዋል ተጠብቆ ለወደፊት ህይወቱ መልካም ተሞክሮን በመቅሰምና እራሱን በእውቀት ማነፅ የሚያስችለውን የንባብ ፍቅሩን ለማሳደግ የሚረዳውን ልማድ ማዳበሩ መልካም ነው።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሰኔ 30 የንባብ ቀን እንዲሆን የወሰነበት ዋነኛ ምክንያት አንዱም ይሄው ነው። ትምህርት ቤቶች ትምህርት ጨርሰው የሚዘጉበት ወቅት በመሆኑ ተማሪው ትምህርት ከተዘጋ በኋላ የት ይውላል በሚል ማህበሩ ለዚህ ሰፊ ድርሻ ያለው የማህበረሰብ ክፍል ትኩረት መስጠትና ጊዜው በማንበብ እንዲያሳልፍ በማለም መሆኑን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ በመድረኩ ላይ ተናግረው ነበር። በተመሳሳይም ብዙ ተቋማት ክረምቱን ተከትሎ ይዘጋሉ። በዚህም በእረፍት የሚቆየው ማህበረሰብ የእረፍት ጊዜው በንባብ እንዲያሳልፍ ግንዛቤ ለመፍጠር ይረዳል።
በየዓመቱ ሰኔ 30 የሚከበረው የንባብ ቀን ዘንድሮ 4 ኪሎ በሚገኘው አብርሆት ቤተ መፅሀፍ ‹‹አንባቢዎች መሪዎች ናቸው›› በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ነበር። በደራሲያን ማህበር በተዘጋጀው በዚሁ ዓመታዊ የንባብ ቀን መርሀ ግብር ላይ የስነ ፅሁፍ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ ጋዜጠኞችና ልዩ ልዩ እንግዶች የታደሙበት ሲሆን ንባብን በተመለከተ ልዩ ልዩ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል። ደራሲያንና ከመፅሀፍት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ተሞክሮዋቸውን በዚሁ መርሀ ግብር ላይ አጋርተዋል።
የንባብ ቀን እንዲከበር የተወጠነበት ዋንኛ ምክንያት ትውልዱ የንባብ ጠቀሜታን የተረዳና አንብቦ አገርን የሚጠቅም፣ ምክንያታዊነትን እንዲላበስና እያንዳንዱን ጉዳዮች በሚዛናዊነት እንዲመለከት ለማነፅ መሆኑ ተገልፃል። አሁን ላይ በተለያዩ አካላት ተደጋግሞ እንደሚነገረው የንባብ ልምድ እንደ አገር እጅጉን እንደተዳከመና በዚህም ምክንያት አልባነት እንደተንሰራፋ ነው።
በሰለጠነው ዓለም ሰዎች በተለያዩ መጓጓዣዎችን ሁሉ ሲጠቀሙ በእጃቸው ላይ የሚነበብ ነገር ይዘው መመልከት የተለመደ ነው። ወደ እኛ ማህበረሰብ ስንመለስ ደግሞ በእጃቸው መፅሀፍ ይዘው የሚዞሩና በትንሹም ቢሆን የማንበብ ልምድ አዳብረው አዘውትረው ሲያነቡ የምናገኛቸው እጅግ በጣም ውስን ሰዎች ናቸው። እንደውም እንዚህን ሰዎች በሌሎች የተለየ ተፈላሳፊና በራሳቸው ዓለም የመነኑ ልዩ ፍጡራን አድርጎ የመመልከቱ ልምድ አለ። ይህ እጅግ የተሳሳተ እሳቤ ደግሞ የንባብ ልምድ እንዳይኖረንና አንባቢ ማህበረሰብ እንዳንፈጥር አድርጎናል። በዚህም እንደ አገር የሚገባንን ዘርፈ ብዙ በጎነት ርቆን በማንበብ የሚታደሉት ብሩህ ነገር ተደብቆብን ቆይቷል።
በ1960ዎቹና 1970ዎቹ የነበረው በአንፃራዊነት የንባብ ልምድ ነበር በተባለው ትወልድ ተቀጣጥሎ የነበረውና በመላ አገሪቱ በትንሹም ቢሆን ይሰራባቸው የነበሩ የንባብ ክህሎት ማዳበሪያ፣ የንባብ ማዕከላትና ቤተ መፅሀፍት ዛሬ ላይ የአንባቢ እጥረት እንደገጠማቸው በተለያየ መድረኮች ይነሳል። በእርግጥ የንባብ ጥቅምና ለማህበራዊ ለውጥ ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ብንረዳ እንኳን የነበሩት ቤተመፅሀፍት አዳዲስ ተጨምሮም በአንባቢያን በተጨናነቁ ነበር።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር በመሆን በማህበረሰቡ ዘንድ የንባብ ክህሎት እንዲዳብርና አንባቢ ማህበረሰብ እንዲገፈጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል። የዚህ የንባብ ቀን መከበር ምክንያትም ዋነኛ ግቡ ማንበብን ማበረታታትና ከንባብ የሚገኘውን ጥቅም ማስረዳት ሲሆን በዚህም ንባብን ባህል ያደረገ ህብረተሰብ መፍጠር አልሟል።
አሁን ላይ በአገራችን በተለያየ መልኩ የሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች መነሻቸው ትውልዱ ከንባብ በመራቁና ነገሮችን በተለያየ መልኩ ከማየት ይልቅ በስሜት በመነዳቱ፤ ከእውቀት የራቀና ምንያታዊ ትውልድ ባለመሆኑ እንደሆነ ትችት ይሰነዘርበታል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ንባብን ልምድ ማድረግና የሰዎች አመለካከትና አስተሳሰብ በጎ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ በተወያዮች በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የነበረ ዋንኛ ጉዳይ ነው።
በተለይም ባለፉት ጊዜያት ወጣቱ የማንበብ ልምዱን እጅግ መቀነሱና በጉዳዮች ላይ የመወያየት ልምዱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የገለፁት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ፣ ትውልዱ እንዲያነብ እንዲሁም ምክንያታዊና ሞጋች እንዳይሆን ስላልተፈለገ ከመፅሃፍት ሊርቅ እንደቻለ ተናግረዋል። ይህ ፈጽሞ ትክክል እንዳልነበረና አገሪቱን በእጅጉ እንደጎዳት በመጠቆምም ለዚህ መፍትሄው የንባብ ልምድ እንዲዳብር መስራትና ታዳጊዎች ለመጻሀፍት ፍቅር እንዲኖራቸው መስራት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
‹‹አድርግ ሲባል ለምን የማይል ትውልድ ተፈጥሯል፤ ይህ የሆነው ትውልዱ ወደመፅሀፍ ስላልተመራና በማንበብ የሚገኘው ትሩፋት ስላልተቋደሰ ነው›› የሚሉት አቶ አበረ፣ መጽሀፍት ሰዎችን በድጋሚ መስራት የሚችሉ መሆናቸውን አፅኖት ሰጥተው ገልፀዋል። በአገራችን ትልልቅ የሚባሉ ደራሲያን ከቀለም ትምህርቱ ባሻገር በንባብ የላቀ ልምድ ስለነበራቸው ከእነሱ ብዙ ጥበብና የፅሁፍ ችሎታን መቅሰም እንደተቻለም በማስታወስ፣ የደራሲ ሀዲስ አለማየሁ፣ አቤ ጉበኛ፣ ፃውሎስ ኞኞ፣ ሀይለመለኮት መዋእል፣ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያና የመሳሰሉ ትልልቅ ደራሲያን በማንሳት በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፉ በንባብ የጠለቀ እውቀትን መሸመት እንደሚቻል ማስረጃዎች እንደሚሆኑ ስራዎቻቸውን ለታዳሚው በመጥቀስ አብራርተዋል።
ስርዓተ ትምህርቱ አንባቢ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና ስላለው መጠናትና መስተካከል የሚኖርበት መሆኑም በመድረኩ ተነስቷል። የትምህርት ስርዓቱ አብዛኛው ወጣት በትምህርት ላይ እንደመኖሩ በማንበብ እራሱንና አገሩን በትክክለኛ መንገድ እንዲጠቅምና ጠንካራ የሆነ ማህበረሰብ ለመመስረት እንዲረዳ ተደርጎ መዋቀር እንደሚኖርበትም በርካቶች አስተያየት ሰጥተውበታል። ነገር ግን አሁን እየተተገበረ ያለው የትምህርት ስርዓት ይህንን አላማ ለማሳካት በሚያስችል መልኩ መተግበር እንደሚገባው ተነስቷል።
በመድረኩ ላይ ተጋብዘው ‹‹የንባብ ክህሎትን ለማሳደግና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት ዶክተር መንግስቱ ታደሰ በንባብ ክህሎትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ስራ መስራታቸውና በተለይም ህፃናትን ከንባብ ልምድ ጋር ለማገናኘት ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በዚህም በንባብ ክህሎት ትልቅ የሆነ ክፍተት መኖሩን አስረድተዋል።
የንባብ ልማድ በአገር ደረጃ ከጊዜ ወደጊዜ እጅግ እያቆለቆለ መሆኑን ያስረዱት የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር መንግስቱ፤ እንደ ማህበረሰብ የንባብ ልማዳችን ያልዳበረና ወደፊት በዚህ ዘርፍ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን ጠቁመዋል። ንባብ ጠንካራ ማህበረሰብን ለመገንባት እንደሚያስችልም አክለዋል። ለዚህ ብዙ ምንያቶች ሊነሱ እንደሚችሉ ያስረዱት ዶክተር መንግስቱ፣ ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ ለንባብ ክህሎትና ልምድ ጠቃሚ ጉዳዮች በደንብ ትኩረት እንዳልተሰጣቸው አብራርተዋል።
የትምህርት ስርዓቱ በአገራዊ ልማዳዊ እውቀት አለመቃኘቱ የንባብ ባህል ለመዳከሙ ዋነኛ መሰናክል እንደሆነ በመጠቆም ተሞክሯቸውን ያጋሩት ዶክተር መንግስቱ፣ የመምህራን አሰለጣጠንና ስርዓተ ትምህርቱ ሲዘጋጅ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደነበሩበት አንስተዋል። ትምህርት ቤቶች ላይም ሰፊ ችግር መኖሩን በመጠቆም፣ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የደረሱ ተማሪዎች እንኳን የማንበብ ክህሎት ስለሌላቸው የተሰጣቸውን ተግባር ለመረዳት እንደሚቸገሩ ከልምዳቸው በመነሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የንባብ ክህሎት ማለማመጃ የሆኑት ትምህርት ቤቶች እና የትምህርት ስርዓቱ ለንባብ ክህሎት ትኩረት እንዲሰጡና አንባቢ ማህበረሰብ መፍጠር ላይ እንዲሰሩ የመርሀ ግብሩ ታዳሚዎች በተሞክሮ ልውውጣቸው ወቅት ደጋግመው ያነሱት ነጥብ ነበር። በእርግጥም የንባብ ክህሎት መዳበርና አንባቢ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር ወሳኝ ነውና ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት መስራት እንደሚገባ ይታመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2014