
ስለ ቅርጻ ቅርጽ ባትረዳ ኖሮ ዓለም ወና በሆነች ነበር። ውበት የራቃት፣ ግሳንግስ የተከመረባት አስቀያሚና ባዶ ሆና በታየችን ነበር። ቅርጽ አልባ የሆነ ነገር ሁሉ ለዓይን ብቻ ሳይሆን ለውስጥም ይቀፋልና ዛሬም ሆነ ጥንቱን ዓለም ለቅርጽና ቅርጻ ቅርጽ ያላት አመለካከት፣ በሁሉም ቦታ ላይ መሠረታዊ ጉዳይ እንዲሆን አድርጓታል። እንኳንስ የሰው ልጅ የሠራውንና ተፈጥሮን ስናደንቅ እንኳን የመጀመሪያውን የስበት ኃይል በዓይንና ልባችን ውስጥ የሚረጩት ቅርጾች ናቸው። በዘመናይ ዓለም ስር ቢሆን እንኳ በፋሽን ዲዛይኑ፤ በአልባሳትና ጌጣጌጦቻችን፣ በቤተ አሠራርና ቁሳቁሶቻችን፣ አልፎም ቅንጦት ላይ ሲደርስ በምግቦች ላይ ሳይቀር እንመለከተዋለን። ከጸጉር አቆራረጥ እስከ አሠራር ቅርጾች አሉ። ራሱ የሰውነት ቅርጽ የሚባል ነገር ሁሉ አለ። ቅሉ አብዛኛዎቹ ከስነ ውበታዊ ማርኪነት ጋር የተያያዙ እንጂ የርዕሰ ጉዳያችንን ያህል ላቅ ያለ ጽንሰ ሀሳብ ያላቸው አይደሉም። ከተፈጥሮ ውስጥ ስለዚህ መግነጢሳዊ ኃይል በመረዳት፣ ቅርጾችን ወደ ረቂቅ ምስጢራት ሳይቀር በማመሳጠር ኢትዮጵያ ከቀዳማዊዎችና አሸናፊዎቹ ተርታ ነበረች። አሁን የት አለች? እንጃ! ይህን ራሷም አታውቀውም።
ፍለጋውን ለእያንዳንዳችን እንተውና ከዚህ ጥበብ ጋር ግን ጥቂት እንመሳጠር። ጉዳዩን ከምንጩ ስር ለመቅዳት ያህል ‹ጥበብ› ስንል ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ አሊያም ዕደ ጥበብ የሚሉት ሁሉ እንደልጅ ልንመለከታቸው እንችላለን። ዳሩ ግን ‹ኪነ ጥበብ› እና ‹ሥነ ጥበብ› አባባላችን ዘልማዳዊ ሆኖ እንጂ ሥነ ጥበብ ሁለቱንም ሊያጠቃልል የሚችል ትክክለኛው ስያሜ ነበር። ይሁንና የዛሬው መንገዳችን ከዕደ ጥበብ ጋር እንደመሆኑ እዚሁ ላይ እናተኩር። ዕደ ጥበብ የተዋቡ እጆች ውጤቶች ናቸው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግዙፍ ኢኮኖሚ ከሚያንቀሳቅሱ ዘርፎች አንደኛው ቢሆንም፤ በእኛ ሀገር ውስጥ ግን እንደ ዘንባባ በቅለው እንደ ችፍርግ ቀጭጨው፣ በአጽማቸው ከቀሩ ዘርፎች ግንባር ቀደሙ ነው። ምናልባት አሁን አሁን ጥቂት መነቃቃቶች እንዳሉም።
ዕደ ጥበብ በጉያው ከታቀፋቸው ነገሮች ውስጥ አንደኛው የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ነው። ቅርጻ ቅርጽ ማኅበረሰባዊ የአኗኗርና የባህል፣ የሃይማኖት መሠረት ያላቸው፤ ፍልስፍና፣ ዕውቀትና ጥበብን አጣምረው የያዙ ናቸው። የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ግን ‹ዕደ ጥበብ› እንበለው እንጂ በዚህ ብቻ የምንገድበው አይደለም። ምክንያቱም ከስዕል ጥበብ አንስቶ ከሌሎች በርካታ ነገሮች ጋርም ትስስር ያለው ነውና። ከእጅ ሥራዎች ባሻገር በስዕል ጥበብ ውስጥ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው። ከዋናው ዓላማው ጎን ለጎን ሥነ ውበታዊ ፍልስፍናን የሚከተልም ነው። “ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል” ነውና ለውበት የሚሰጠው ቦታም ከፍተኛ ነው።
የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ለኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የመጣ ሳይሆን፣ ከሺህ ዓመታት በፊትም የብዙ ማኅበረሰባችን እንጀራ እና የጥንት የሀገራችን ጠቢባን የዕውቀትና የጥበብ ብርሃን የሚለኩሱበት አትሮኖሳቸው ነበር። ሁሉም ዕደ ጥበብ ቢሆኑም፤ እይታና አመለካከቱ ግን በሁለት የሚከፈል ነው። ምክንያቱም፤ ከቤት ውስጥ የመገልገያ ቁሳቁስ እስከ ግዙፍ የሐውልትና ቅርጻ ቅርጽ ጥበቦችን ያካተተ ነውና። ከታች እንደ አናጢና ሸክላ ሠሪ ያሉት በቀደመው ማኅበረሰባችን ውስጥ ቦታ የማይሰጣቸውና የተናቁ ጥበበኞች ነበሩ። እንደ ጌጣ ጌጥና የጦር ዕቃዎችን ሲሠሩ የነበሩ አብዛኛዎቹም እኚሁ የተናቁት ናቸው። ይሁንና ከፍ ብሎ ደግሞ፤ ዛሬ ላይ መላው ዓለም፣ እኛም የምንደነቅባቸውና በቅርስነት የተያዙ የእጅ ገጸ በረከቶችም አሉን።
‹ቅርጻ ቅርጽ› ከሚሉ ሁለት ቃላት ውስጥ አስቀድመን ‹ቅርጽ› የምትለዋን ነጥለን ደግሞ እንያት። ምክንያቱም ስለ ቅርጻ ቅርጽ ለማውራት መጀመሪያ ቅርጽ ሊኖር የግድ ነውና። ቅርጽ እንደየ ዓይነቱ ክብ (ሙሉ ክበብ፣ ግማሽና ሩብ ክበብ እንደጨረቃ) ሞላላ፣ ዝግዛግ፣ ሰያፍ፣ ቀጥታ መስመር፣ አግድም፣ መስቀለኛ፣ ከሦስት ማዕዘን ጀምሮ ያሉ ማዕዘናትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። አንዳንዴ ፊደላትም አሉበት ለምሳሌ እንደ “ቶ” እና “ሐ” ያሉት። ታዲያ በኢትዮጵያዊያን ጠቢባን ዘንድ እንኳንስ ቅርጾቹና አንዲት ነጥብ እንኳን የራሷ ትርጓሜ አላት። ቅርጾች አንድን መልዕክት ወይንም ሚስጢር የሚያመለክቱ ውክል ናቸው። አገልግሎታቸውም ምልክትነት ነው። ቅርጾች አገልግሎት ላይ ይውሉባቸው ከነበሩ መካከል አንደኛው የጠልሰም ስዕሎች ናቸው። ከመድኃኒትነት አንስቶ ለበርካታ ጉዳዮች በሚውለው በዚህ የጠልሰም ስዕል ውስጥ ከቃላትና ቀለማት ጋር ምልክቶችን እናገኛለን። በውስጡ ከያዘው ነገር አንጻርም በመልዕክት ሳይሆን ከምስጢራት ውስጥ እንመድበዋለን። በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ መስቀል፣ በእስልምናው ደግሞ የኮከብና ጨረቃ ቅርጾች መሠረታዊና ምስጢራዊና መለኮታዊ ምልክቶችን የያዙ ቅርጾች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ጥንታዊ ስዕሎች ውስጥ በብዛት የሰዎች ፊት የሚሳለው በክብ ቅርጽ ሆኖ እናገኘዋለን። አሳሳሉ ለተመልካች የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው። ዓይኖቻቸው ጎላ ጎላ ብለው ጭንቅላታቸው ደግሞ አነስ ተደርገው የሚሳሉበት የራሱ ምክንያትም ስላለው ነው።
በጥንታዊ የቤት አሠራሮች፣ በጥንታዊ ቁሳቁሶች፣ በታሪካዊ ሐውልቶቻችን እንዲሁም በጥንታዊ ቤተ መንግሥቶቻችንና ግንቦች ላይ የምንመለከታቸው ቅርጾች፤ እያንዳንዳቸው ትርጓሜ ያላቸው ምስጢራት ናቸው። ኢትዮጵያዊነትና ቅርጾች እጅግ ውስብስብና ለመግለጥ በማይቻል ደረጃ መንፈሳዊ ትስስር ያላቸውም ጭምር ናቸው። የቅርጾቹ መጠን፣ ርዝመት፣ ቁመት፣ ስፋት…የሚቀመጥበት መንገድም በልኬትና ትርጉም ባለው መልኩ ነው። ከስዕሎች እስከ ግዙፍ ግንባታዎች ድረስ አንድን ነገር የሚሠሩበት ልኬት ወይም ወደ ተግባር የሚለውጡበት ፕሮፖርሽን የሚያሰሉት ረቀቅ ባለ መንገድ ነው። ዳሩ የስዕል ጥበብ ስላላቸው መሳል ብቻ ሳይሆን፤ ሰዓሊ ሊሆኑ የሚችሉበት ረቂቃዊ ምስጢርም ነበራቸው። በብዙ ነገሮች ከምናባዊ ጥበብ በተጨማሪ ገሀዳዊ ዕውቀትን የመጠቀም ክህሎት ነበራቸው።
ለምሳሌ፤ በትንሹ የአንድን ሰው ስዕል ለመሳል እንኳን የሚጠቀሙበት ስልት አላቸው። የዚያን ሰው መልክና ገጽታ ለማምጣት ከጭንቅላት አንገትና ትከሻ፣ ከእጅ እግር፣ ከወገብ፣ ጉልበት እስከ ተረከዝ…ልኬት አለው። ዳቪንቼ ዓለምን ሁሉ ስታስደንቅ የምትኖረውን ሞናሊዛን የሳለበት መንገድም ከዚሁ ቀመር የተያያዘ ነው። የሚገርመው ነገር ደግሞ፤ የጥንት ኢትዮጵያውያን በተለይ ሰውነቱ ላይ ጉዳት የደረሰበትን ሰው በሚያክሙበት ወቅት ስዕልን ይጠቀሙ ነበር። የቱ ጋር ስንት አጥንቶች፣ ምኑ ጋር ደምስር፣ በየትኛው ቱቦና መገጣጠሚያ…እንዳለ ስለ ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎቻችን ያወቁት ቀዶ ጥገና አድርገው ሳይሆን፤ በነበራቸው ዕውቀት ተመራምረው በደረሱበትና ባስቀመጡት ስዕላዊ መግለጫ ነው። እናም እያንዳንዱን ውስጣዊ አካላችንን የደም ዝውውሩን ሳይቀር ከነ ቅርጽና መጠኑ ቁጭ ቁጭ ያደርጉታል። ስብራትና ውልቃት፣ እንዲሁም እብጠት የመሳሰሉትን በመዳፎቻቸው ዳሰው፣ በጣት ነክተው ይደርሱበታል። የታካሚውን ጉዳት ብቻ ሳይሆን የጉዳቱን መንስኤ ሳይቀር ያውቁታል። ዛሬ ላይ ራጅና አልትራሳውንድ የምንላቸውን ነገሮችን የእኛ አባቶች በስዕል እያስቀመጡ ተፈጥሮን በተፈጥሯዊ መንገድ ሲያክሙበት ነበር።
በቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ካላቸውና ሊነጠሉ ከማይችሉ ወሳኝ ነገሮች መካከል ቀለማት አንደኛዎቹ ናቸው። ዓለም ስለ ቅርጻ ቅርጽ፣ ስለ ውበትና ስለ ቀለማት መጠበብ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ክብ፣ አራትና ሦስት ማዕዘናት ወሳኝ የመነሻ ቅርጾች እንደተደረጉ ሁሉ፤ ሰማያዊ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትም በየትኛውም የጥበብ ሥራዎች ውስጥ መሠረታዊያን ናቸው። እንደ ግብአት እምነበረድ፣ ነሐስ፣ ብረታ ብረት፣ አፈር(ጭቃ)፣ ድንጋይ እና ሌሎችም አገልግሎት ላይ ይውላሉ። ሀገራችንም ከሽመና አንስቶ በየትኛውም የቅርጽ ንድፍ ውስጥ ከሥነ ውበት በገዘፈ መልኩ ሁሉንም የተራቀቀችበት ነበረች። ሁሉም ነገሮች ምክንያታዊ ወይንም ምስጢራዊ መገለጫዎች የነበሯቸው ናቸው።
ቅርጾች ከምልክትነትና ውበት ባለፈ ከሰው ልጆች ጋር ሥነ ልቦናዊ መስተጋብር አላቸው። በቀደመውም ሆነ በአሁኑ ዓለም ውስጥ ለቅርጾች የሚሰጠው ቦታ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ከጥንት ጀምሮ አሁንም ድረስ በቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ግንባር ቀደም ተብለው ከሚጠቀሱት ግሪክ፣ ጀርመን፣ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓን እና ቻይና የመጀመሪያዎቹ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጥ እኛም ነበረን፤ ችግሩ ግን አሁን የለንም። ታዲያ ዓለማችን ከተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርጾች ጋር በጥበብ፣ በሥነ-ውበትና በፍልስፍና ዛሬም ድረስ ሽርብትን እያለች ማጌጧን አላቆመችም። ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትና የኢኮኖሚ ምጥቀት እያስመዘገቡ ካሉ መዳረሻዎች ቅርጻ ቅርጾች ከዋናዎቹ አንዱ ነው። በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ክበቦች ውስጥ አገልግሎትና ጠቀሜታቸው ይህ ነው ተብሎ ብቻ የሚገለጽ አልሆነም። በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎትና ጠቀሜታቸው ረቂቅ ምስጢራትን እስከመያዝ የደረሱ እንደነበሩ ሁሉ፣ ከላይ የጠቀስናቸውን ሀገራቶችን ጨምሮ በሌሎችም ሀገራት ውስጥ ለልዩ ልዩ ግብሮች ያውሏቸዋል። ምስጢራዊ ኃይላቸውን የተረዱና ዛሬም ይጠቀሙባቸዋል።
በአንድ ወቅት የቀድሞው የአርሰናል እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ የነበሩት አርሰን ቬንገር ጃፓንን ይጎበኟታል። ባዩትና በሰሙት ነገር ከመደነቅ አልፈው ውስጣቸውን ቀይሮት ነበርና ከጉብኝቱ በኋላ ወደ እንግሊዝ ሲመለሱ አንድ ነገር አደረጉ። የእግር ኳስ አሠልጣኝ የነበሩት ሰው ከጉብኝቱ መልስ የኪነ ህንጻ ጠበብትም ጭምር ሆኑ። እናም አራት ማዕዘን የነበረውን የአርሰናል ስታዲየም፣ የተጫዋቾች መልበሻና መታጠቢያ ክፍሎችን ሁሉ ፈርሰው ዳግም በክብ ቅርጽ እንዲሠሩ አስደረጉ። ነገሩን ወደ ቡድኑ አመራር ይዘው ሲቀርቡ፣ የክብ ቅርጽን ውበት በመግለጽ ብቻ ሳይሆን፤ ከሰው ልጆች ሥነ ልቦና እና ሥነ መለኮታዊ መስተጋብር ጋር ያለውን ልዩ ምስጢር በመረዳትና በማስረዳት ነበርና ሁሉም ፈርሶ ዳግም እንዲሠራ ተደረገ። የቀለም ቅቡም እንዲሁ በአዲሱ ፍልስፍና ውስጥ ተመሳጠረ። በክብ ቅርጽ መሠራቱና ሌላ ዓይነት መቀባቱ ለአርሰናል አዲስ መንፈስ የሚያጎናጸፍና ለአዲስ ስኬት የሚያዘጋጅ በረከት ተደርጎ የተቆጠረ ለውጥ ነበር።
“ጥበብ ቤቷን በ 7 አምድ ላይ ሠራች” እንዲል ጠቢቡ የጥንት ታሪካዊ ቅርሶችና ቅርጻ ቅርጾቻችን በሚያስገርም መልኩ ቅርጾቻቸው በቁጥሮች ቀመር ተስልተው የተሠሩ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ፊደላቶቻችን እንኳን ቅርጾቻቸው ተፈጥሯዊ ውክልናና ተምሳሌትነት እንዲኖራቸው ተደርገው የተቀረጹ ናቸው። የአክሱም ሐውልትን ቅርጽ የተመለከትነው እንደሆን ከአናቱ ላይ ካለው የግማሽ ክበብ ቅርጽ አንስቶ፣ በእያንዳንዱ የድንጋይ ክፍል ላይ በቁጥርና ፊደላት ተሰልቶ የተቀመጠበትን ምስጢራዊ ኮድ እንዳለው ሲገባን፣ ከሐውልቱ በበለጥ ሐውልቱ በያዘው ነገር እንደነቃለን። ጠቢባን አባቶቻችን ከነበራቸው የዕውቀትና ጥበብ ምጥቀት የተነሳ ቅርጾችን በመጠቀም ተአምር የሚመስሉ ነገሮችን ሁሉ ሲሠሩባቸው ነበር። የስልጣኔና የታላቅነታችን መነሻ የነበረውም ተፈጥሮን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ እየሄዱባቸው የነበሩ መሰል ስሌታዊ ፈለጋቸው ነበር።
ዛሬ ላይ ከምንመለከታቸውና ከምንከውናቸው የቅርጻ ቅርጽ ጥበቦች መካከል አንዱ ስለሆነው የሐውልት ሥራ ጥቂት እንበል። ሐውልቶችም በዓይነትና በመጠን ልዩ ልዩ ናቸውና ስለ መታሰቢያ የሐውልት ማለታችን ነው። እንደ አክሱም ያሉትም የመታሰቢያ ሐውልቶች ቢሆኑም፤ በምትኩ ዛሬ ላይ ልናነሳቸው የምንችለው በየአደባባዩና መሰል ስፍራዎች የምንመለከታቸውን ሐውልቶችን ነው። ለጀግና ሰማዕታት፣ ለሀገር ባለውለታዎች፣ ለጠቢባን…በአጠቃላይ አብዛኛውን ጊዜ በሕይወት ለሌሉና ዝነኛ ለሆኑ ባለውለታዎቻችን የምናቆማቸው ናቸው። ለዚህ ቅርጻ ቅርጾች መሠረታውያን ቢሆኑም፤ ሐውልት ግን ከቅርጻ ቅርጽ ከፍ ያለ ጥበብ የሚጠይቅና በመጠኑም የሚገዝፍ ነው። በቅርጻ ቅርጽ ውስጥ የቀራጺው በፈጠራ የመራቀቅ ነጻነትና ስልጣን ሲኖረው፤ በሐውልት ሥራዎች ውስጥ ግን የተገደበ ነው። ምክንያቱም በሐውልቱ ላይ የሚቆመው ሰው ታሪክና ማንነቱ በግልጽና ሁሉም ተመልካች በቀላሉ ሊረዳው በሚችለው መልክ መቀመጥ ይኖርበታል። ቢያንስ ‹ማነው?› እና ‹ምንስ ሠራ?› የሚሉ ነገሮች ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ ማስቀመጥን ይጠይቃል።
ይሁንና አክሱም፣ ላሊበላ…እያልን የምንጠራቸው በወጥ ድንጋይ በተጠበቡባት ኢትዮጵያ፣ ቀለም ሳይሆን የእህል ዘሮችን ተጠቅመው ስዕል ሲስሉ በነበሩባት ሀገራችን፤ ሐውልቶችን የምናሠራው ውጭ ሀገር ነው። በየአደባባዮቻችን የምንመለከታቸው አብዛኛዎቹ ሐውልቶችም የተሠሩት በእኛ እጆች አይደለም። አሁን አሁን እጆቻችን ጥቂት መነካካት ቢጀምሩም፤ ተሠሩ ተብለው በድፍረት የሚቆሙ ሥራዎቻችን አስቂኝ እየሆኑ ነው። ‹የእገሌ ሐውልት› ተብሎ ምስሉ ግን ምኑም እገሌን አይመስል። ብዙ ቀራጺያን የሚያቀርቡትን ሥራዎቻቸውን የተመለከትን እንደሆነ ገና ዘርፉ ላይ መሥራት እንዳለብን የሚያሳዩ ናቸው። ጥበብ ያለሙከራ አትመጣምና ሙከራዎች መልካምና ልናበረታታም የሚገባ ነው፤ ግን ራሳችንን እየሸወድን በዚህ መልክ ከቀጠልን ይህን ታላቅ ጥበብ መግደላችን ነው። ትልቁ መፍትሔ፤ በየደረጃው መማር፣ መሠልጠን አለብን። ለዘርፉ መንግሥት ምን ያህል እየሠራ ነው? በሀገር ውስጥ ተቋማትን ከማደራጀት ጀምሮ፣ የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት ብቁና የኢትዮጵያን ጥበብ የሚመጥኑ ባለሙያዎችን የማውጣት ኃላፊነት አለበት። ቀራጺዎቻችን ጥንትን መርምሮ ለዛሬያችን የሚመጥን ለመሥራት በበለጠ መትጋት ግድ ይላቸዋል።
የቀደመው ዘመን የቅጻ ቅርጽ ዕውቀትና ጥበብ ችግሩ ምን ነበር? ካልን ትልቁ ችግር በቤተ ክርስቲያንና ገዳማት ውስጥ ታጥሮ መቅረቱ ነበር። ከእነዚህ ስፍራዎች ተነስተው ወደ ቤተ መንግሥት መግባት የቻሉ ቢኖሩም፤ ከነበሩት አንጻር በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የነበረውን ዕውቀትና ጥበብ ለትውልድ ከማስተላለፍ አንጻር ከክፍተት የገዘፈ ገደል ተፈጥሯል። ሌላው ቀርቶ ቤተ መንግሥት አካባቢ የደረሱትን እንኳን የሚያውቅና የሚረዳ አዲስ ትውልድ ካለመኖሩ የተነሳ ታሪካዊ ቅርስ ብቻ ሆነው ቀርተዋል። የሠሩት እንጂ የሠራነው የለምና የሠሩትን እንደ ታቦት ስናነግሥ ብቻ መኖራችን በዚያ የትውልድ ሽግግር ውስጥ የዕውቀትና ጥበብ ቅብብሎሽ ባለማድረጋችን ነው። የአሠራር ንድፎችን(ማንዋል) የያዙ በርካታ የብራና መጻሕፍት አሁንም ቢኖሩንም፤ ምኑንም ለመረዳት ባለመቻላችን “መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም” ዓይን እያቁለጨለጩ መፋጠጥ ብቻ ነው። ግዙፍ የዕውቀትና የጥበብ ፍልስፍና ያላት ሀገር እንዳለችን በኩራትና በድፍረት እናወራለን፤ ፍልስፍናው ምን እንደሚል ግን የምናውቀው አንዳችም ነገር የለንም።
‹ቅርጻ ቅርጽ› ሁለት ቃላት ስለሆነ ‹ቅርጽ› ከምትለዋ ከአንዲት ቃል የሚገዝፍ መስሎ እንዳይታየን፤ ግዙፍ ባህረ ሀሳብ ያላትና የምትተልቀው ቅርጽ ናትና። ዳር ዳሩን በነካካናቸው ሀሳቦች ውስጥ እስካሁን በምናውቃቸውና ስለ ቅርጾች በተረዳነው ልክ ብቻም እንዳንገድበው። ምድርም ሆነች ሰማይ ያለ ቅርጽ አልተዋቀሩም፤ የሰው ልጅም የተፈጠረው ከቅርጽ ጋር ነው፤ መሬትና ፕላኔቶች፣ ጨረቃና ፀሐይ ሁሉም የራሳቸውን ቅርጽ ይዘው የቆሙበት ራሱን የቻለ ግዙፍ ምክንያት አለው። ምንም ነገር ያለቅርጽ አይሠራም ደግሞም አይቆምም። መሬት አሁን ያላትን ቅርጽ ይዛ መቀጠል ባትችል እኛ ሰዎችም ምድር ላይ የመኖራችን ህልውና ያከትማል። እናም ስለ ቅርጾች ማወቅና መከወን መቻል ዓለምን የመቆጣጠሪያ ቁልፍ አገኘን እንደማለት ነው። ቅርጾችን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ማመሳጠሩንም እንድረስበት። ጥበብን ከጲላጦስ ሳይሆን ከአባቶች እናድርግና።
በሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም