ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት አገር ናት። አገሪቱ የአምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለዘርፉ እድገት አዎንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች አሏት።
ይህን አቅም በመጠቀምና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውናለች። ለአብነትም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተግዳሮቶች በሚል ተለይተው የነበሩትን የመሬት፣ የመሰረተ ልማት፣ የቢሮክራሲ ችግሮችን የሚቀርፉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል። በዚህም ባለሀብቶች ማሸነሪዎቻቸውን ብቻ ገጥመው ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ዘርፉ አሁንም ተግዳሮቶች ይስተዋሉበታል። እነዚህ የዘርፉ ችግሮች፤ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና በአጠቃላይ የሕዝቡን የተቀናጀ ጥረት እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ተጠቁሟል። ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው ውጤቶች ቢመዘገቡም፤ ከችግሮቹ ስፋት አንፃር መፍትሄዎቹ የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኙ አልቻሉም።
በ2014 በጀት ዓመት አገሪቱ ከዚሁ ዘርፍ ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ ማግኘቷን ትናንት የኢንዱስትሩ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል መግለጻቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል። በበጀት አመቱ አስር ወራት ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ረገድ ደግሞ ማሳካት የቻለችው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።
ዘርፉ ጥሬ ዕቃ፣ በሰው ኃይል፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች ተተብትቧል። በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት ከአቅማቸው በታች እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎችም ያሳያሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ የማኑፋክቸሪን ኢንዱስትሪው የአቅሙን 50 በመቶ ያህል እንኳ እያመረተ እንዳልሆነ ገልፀው፤ የዘርፉን አቅም ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት የስድስት ነጥብ ስምንት በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ፣ አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድም ተይዟል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የሚኒስቴሩን የ10 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በርካታ መሰናክሎች እንዳሉበትና የአገሪቱ አቅምና የገበያ ፍላጎትም ከተመዘገበው አፈፃፀም በላይ እንደሆነ አስረድተዋል። ‹‹ከ10 ዓመቱ የአገራችን ብሔራዊ የልማት እቅድ ውስጥ ለአምራች ዘርፉ የተቀመጡት ግቦች በጥረት ሊሳኩ የሚችሉ ቢሆኑም፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸውን እየተጠቀሙ እንዳልሆነ በጥናት ማረጋገጥ ተችሏል›› ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው የ‹‹ስለ ኢትዮጵያ›› መድረክ አካል የሆነውና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያተኮረው የውይይት መርሃ ግብር በድሬዳዋ ከተማ ሲካሄድ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድሎችንና የመንግሥትን ትኩረት በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አገሪቱ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ግዙፍ አቅም እንዳላት ጠቅሰዋል፤ ዘርፉ በርካታ ችግሮች እንዳሉበትም አመልክተው፣ መፍትሄው የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ይፈልጋል ብለዋል።
በዚሁ መድረክ የተገኙት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የአጠቃቀም ፍትሃዊነት መጓደል፣ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት፣ የሥራ ባህል ደካማነት እንዲሁም ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር የዘርፉ ባለሀብቶች ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ በኢትዮጵያ የአምራች ዘርፉ በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት ያደረጉት ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ‹‹የታዳጊ አገራት የአምራች ዘርፎች በሙሉ አቅማቸው እንደማይሰሩ ይታወቃል። የዘርፉን አቅም የመጠቀም ደረጃ ግን በየአገራቱ የተለያየ ነው። ›› ያሉት ዶክተር ዳዊት፣ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎችም እያመረቱ ያሉት ከአቅማቸው በታች መሆኑን እሳቸውም ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ዳዊት ገለፃ፣ ከውጫዊ ምክንያቶች አንዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው። አብዛኞቹ የማምረቻ ዘርፎች ከ25 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን ጥሬ እቃዎቻቸውን የሚያገኙት ከውጭ አገራት ነው። አምራቾቹ ይህን ከውጭ የሚገባ ጥሬ እቃ በበቂ መጠን ለማግኘት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እጥረት ስላለባቸው የምርት ግብዓቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ እንዳያገኙና በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ያደርጋቸዋል።
ሌላው ውጫዊ ምክንያት ደግሞ ከውጭ የሚገቡ የምርት ግብዓቶች አቅርቦት አስተማማኝ አለመሆን ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ክስተቶች ግብዓቶቹ በበቂ ሁኔታ እንዳይገኙ አድርገዋል። የበርካታ ጥሬ እቃዎች ምንጮች የሆኑት ሩስያ እና ዩክሬይን ወደ ጦርነት መግባታቸው ግብዓቶቹ በበቂ መጠን እንዳይገኙ በማድረጉ በኢትዮጵያ አምራች ዘርፍ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
የገበያ እድል እጦት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት የሆነ ሌላው ምክንያት ነው። ከዚህ ቀደም አምራቾች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ልከው ከሚያገኙት ገቢ መካከል የተወሰነውን የውጭ ምንዛሬ፣ ለሚያስልጋቸው ጥሬ እቃ መግዣ ያውሉታል። ኢትዮጵያ የአጎዋ (AGOA) ተጠቃሚነት እድልን ማጣቷን ተከትሎ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ያመርቱ የነበሩ የጨርቃ ጨርቅ ውጤት አምራቾች ምርቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አልቻሉም። አማራጭ የገበያ እድሎችን በመፈለግና የምጣኔ ሀብት ዲፕሎማሲ ስራዎችን በማከናወን ረገድ የነበረው አፈፃፀም በቂ ባለመሆኑ በአምራች ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጠር አድርጓል።
ዶክተር ዳዊት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት የሆኑ ውስጣዊ ችግሮች እንዳሉም ያስረዳሉ። አንዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት ነው። ለአብነት ያህል የግንባታ እቃ የሚያመርቱ አምራቾች በኃይል እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ከማያመርቱ አምራቾች መካከል ይጠቀሳሉ። እንደ ሕንድ ያሉ አገራት የድንጋይ ከሰል ሀብታቸውን አጋዥ አድርገው በመጠቀማቸው ለማምረት አለመቸገራቸውን በምሳሌነት በመጥቀስም ‹‹ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ የድንጋይ ከሰል አማራጮችን ማጤንና መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል›› ይላሉ።
ሌላው ውስጣዊ ምክንያት የአገር ውስጥ ገበያ በቂ አለመሆን ነው። ለአንዳንድ ምርቶች በቂ የአገር ውስጥ የገበያ አማራጭ አለመኖር ኢንዱስትሪዎቹ በአቅማቸው ልክ እንዳያመርቱ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል። የብድር አቅርቦትም ሌለው የዘርፉ ችግር ነው። አምራቾች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው የምርት ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ አሟልቶ ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ ይቸገራሉ። ስለሆነም አምራቾቹ ብድር በፍጥነትና በአነስተኛ ወለድ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ያግዛቸዋል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ዳዊት ገለጻ፤ ለአምራች ዘርፉ የአቅም ውስንነት ሚና ያለው ሌላው ምክንያት የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ነው። ኢትዮጵያ ብዙ የሰው ኃይል ቢኖራትም፣ አምራች ዘርፉ በትክክል የሚፈልገውና በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ግን አነስተኛ ነው። ይህም የኢንዱስትሪዎቹን የማምረቻ ወጪ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ሲሆን አምራቾቹ በሙሉ አቅማቸውና በከፍተኛ መጠን ማምረት አይችሉም።
በአገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግርም የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በአቅማቸው ልክ እንዳያመርቱ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። እነዚህ ችግሮች ተገማች የሆነ የአገር ውስጥ ገበያ እንዳይኖር በማድረጋቸው አምራቾች በሙሉ መተማመን እንዳያመርቱና ለገበያ እንዳያቀርቡ አድርጓቸዋል ሲሉ ዶክተር ዳዊት ያመለክታሉ።
የጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ የኃይል አቅርቦት እጥረትና የውጭ ምንዛሬ ችግር የአምራች ኢንዱስትሪው ዋነኛ ተግዳሮቶች ሆነው መቆየታቸውን በመግለጽ የዶክተር ዳዊትን ሀሳብ የሚያጠናክር ሃሳብ ይሰነዝራሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የፀጥታ ችግሮች የዘርፉ ተጨማሪ ፈተናዎች እንደሆኑም ያመለክታሉ።
‹‹የኃይል አቅርቦት ጉዳይ እጅግ መሰረታዊ ችግር ነው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦት ችግሩን በመፍታት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ። ‹‹አንዳንዶቹ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ከ35 እስከ 40 በመቶ በሚሆነው አቅማቸው ብቻ ነው። የኃይል እጥረቱ አምራቾቹ ማሽኖቻቸውን ብቻም ሳይሆን የሰው ኃይላቸውንም በበቂ መጠን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል። የኃይል አቅርቦት ችግሩ መፍትሄ ካገኘ አምራቾች በአቅማቸው ልክ ማምረት ይችላሉ›› ሲሉ ይገልጻሉ።
‹‹ፖሊሲ ብቻውን ችግር አይፈታም›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ ጥሩ ፖሊሲዎች ብቃት ባለው የመሰረተ ልማት አቅርቦት ካልታገዙ ዋጋ ስለማይኖራቸው የላቀ ትኩረት የሚፈልጉት የመሰረተ ልማት ችግሮችን መፍታት እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹አምራቾች ለማምረት በሚያስፈልጋቸውና ምርቶቻቸውን ሸጠው በሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ መጠን መካከል ያለው የትርፍ ልዩነት መታወቅ አለበት። አንዳንድ አገራት ፋብሪካዎቻቸውን ወደ ሌሎች አገራት ልከው ጥሬ እቃዎች ከአገራቸው ወደ ፋብሪካዎቹ በመውሰድ አገራቱን የጥሬ እቃዎቻቸው ገበያ ያደርጓቸዋል። ›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ‹አንዳንድ አምራቾች አንዳንድ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ የሚያስገቡት የምርቶቹ ከውጭ መግባት በእርግጥ አስገዳጅ ሆኖ ነው?› የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል›› ይላሉ። አምራቾችን ከአገር ውስጥ ግብዓት አቅራቢዎች ጋር ማስተሳሰርና የምርት ግብዓቶችን ከአገር ውስጥ መጠቀም እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ዶክተር ዳዊት ለአምራች ዘርፉ ችግሮች በመፍትሄነት ከሚጠቅሷቸው ሃሳቦች መካከል የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ማጠናከር አንዱ ነው። በኢኮኖሚው ዘርፍ የዲፕሎማሲ አቅምን በማሳደግ አማራጭ የገበያ እድሎችን ማስፋት ይገባል። የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በመፈራረም ለውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ይላሉ።
አማራጭ ኃይልን በመጠቀም ለኢንዱስትሪዎች ያልተቆራረጠ ኃይል ማቅረብ እንደሚገባም ያመለክታሉ። የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላትን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን እንዲያሰለጥኑ በማድረግ የማምረቻ ወጪን መቀነስ እንደሚያስፈልግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ጥረት ማድረግም እንደሚገባ፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ብድር በፍጥነትና በዝቅተኛ ወለድ የሚቀርብበትን አሰራር ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባሉ። እነዚህን ተግባራት በረጅም ጊዜ የመፍትሄ አማራጭነት በመጠቀም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ ይገባል ሲሉ ይገልፃሉ።
በአሁኑ ወቅት የአምራች ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሎ ታምኖባቸው በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ ነው። የአገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የስራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው።
የኢንዱትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ንቅናቄው የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ የወጪ ንግድን ለመጨመርና ገቢ ምርቶችን ለመተካት ለሚደረገው ጥረት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ተናግረዋል። ንቅናቄው ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱ ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማስቻሉ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ማምረት አቁመው ከነበሩ ፋብሪካዎች መካከል በንቅናቄው ትግበራ 118 የሚሆኑት ወደ ስራ መመለሳቸውን አስታውቀዋል። ‹‹ችግርን እንደመውጫ መንገድና መፍትሄ መፈለጊያ በመጠቀም የአምራቹን ዘርፍ ማነቆዎች መፍታት ያስፈልጋል›› ሲሉም ሚኒስትሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፣ ዘመቻው ምን ለውጥ እንዳስገኘ በየጊዜው ክትትል እያደረጉ መገምገም ያስፈልጋል ይላሉ። የዘርፉ ችግሮች መዋቅራዊ የሆኑ መፍትሄዎችን የሚፈልጉ መሆናቸውን በማመልከትም፣ ከአጭር ጊዜ ይልቅ ዘላቂ ለውጥ ለሚያመጡ የመፍትሄ አማራጮች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2014