ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ማነቆዎችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እያከናወነች ያለችው ተግባር ለእዚህ በአብነት ሊጠቀስ ይችላል።በንቅናቄው የሚመለከታቸው በርካታ ተቋማት አብረው የሚሠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይህም በተለይ ከመሠረተ ልማት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እያስቻለ መሆኑ በመንግሥት በኩልም በተደጋጋሚ ተጠቁሟል።
ንቅናቄው ለዓመታት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን መፍታት በማስቻሉም የኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅም አጠቃቀም መሻሻል ማሳየት ጀምሯል።ተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እየተሠራ ነው።
ኢንዱስትሪው ከዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት ጋር እንዲሠራም ይጠበቃል።በኢትዮጵያም በ2005 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ጥምረት /ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ሊንኬጅ/ ተመሥርቶ እየሠራ ይገኛል።ሰሞኑን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ያደረጉት ውይይት መድረክም የዚሁ አካል ነው።
ውይይቱ በዋናነት በመንግሥት በባለድርሻ አካላት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሶስትዮሽ ግንኙነት ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፣ ለሶስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑም ተገልጿል።
በውይይቱ ላይም ሀገሪቱ በተለይ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ እና ውጤቶችን ወደ ድል በመቀየር በኢንዱስትሪው ልማት የተሻለ ግብይት የሚፈጠርበት አቅጣጫ ተጠቁሟል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ጥምረቱ እየለማ ያለው የሰው ኃይል እና የምርምር ውጤት የኢንዱስትሪው ዘርፍ አመርቂ ውጤቶችን እያሳየ መሆኑ እንዲሁም መንግሥት ፖሊሲ በመቅረጽ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ ኢንስቲትዩቱ በተለይ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጥምረት በመሥራት በተማሪዎች ሥልጠና ፕሮግራም (ኢንተርን ሺፕ) እንዲሁም በመምህራን ዝግጁነት (ኤክስተርን ሺፕ) በተጨማሪም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።በዋናነት ግን ከውጭ ሀገር የሚመጡ የቴክስታይል ግብዓቶችን በማስቀረት በሀገር ውስጥ የሚመረቱበትን ሁኔታ በመፍጠር ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ጥምረቱ ከአስር ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ጠቅሰው፣ በተፈለገው ልክ እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነም አስታውቀዋል።ለዚህም ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ቀለም ትምህርት ላይ ማተኮራቸው፣ ቴክኖሎጂን ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
በተቋማት ምርት እና ትርፍ ላይ ብቻ በማተኮር ኢንዱስትሪው በሚፈልጋቸው እንደ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ባሉት ጉዳዮች ላይ እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውም ሌላው ዋና ምክንያት መሆኑን አመልክተው፣ በመንግሥት በኩልም ይሄን ክፍተት በመመልከት ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት በኩል ውስንነት እንዳለ ፕሮፌሰር ታምራት አስገንዝበዋል፡፡
ይሄን ታሳቢ በማድረግ በ2023 የዩኒቨርሲቲ ጥምረት የሕግ ድጋፍ እንዲያገኝ በአዋጅ መውጣቱን ጠቅሰው፣ ከዚያን ጊዜ አንስቶም በየጊዜው እየተገመገመ በሚኒስትሮች እና በሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የሚመሩ ትልልቅ ፎረሞች መመሥረታቸውንም ገልጸዋል።የዩኒቨርሲቲዎች ይህን ሥራ ወደ ተግባር በመቀየር ደረጃ እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የውይይት መድረኩም የዚህ አንድ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።በቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ጥምረቱ የመንግሥት አካላት እና ሌሎች ባለድርሻዎች በተገኙበት ሰፋ ያለ የፓናል ውይይት በማዘጋጀት እየተነቃቃ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ይበልጥ ለማነቃቃት የድርሻውን እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡
ለፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ ‹‹በመጪዎቹ ጊዜያት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምን ታስቦላቸዋል?›› የሚል ጥያቄ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፤ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ባለፉት አስርት ዓመታት በዕድገት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ አዳዲስ እና ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አምጥቶ በመጠቀም ረገድ ግን ደካማ መሆኑን አስታውቀዋል።እንደ ሀገር ዲጅታላይዜሽንን በማስፋፋት እና ሌሎች የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ቢቀጥል በዘርፉ እምርታ ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ዩኒቨርሲቲዎች እና አምራች ተቋማት በሚፈለገው ልክ በጥምረት አለመሥራታቸው በኢንዱስትሪ ልማቱ ላይ የራሱን እክል ፈጥሯል።የኢንዱስትሪ ሠራተኞች የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ናቸው።የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጉዳዩ አትኩሮት በመስጠት ከአምራች ተቋማት ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩበት ሁኔታ ቢመቻች ጥቅሙ ከፍተኛ ይሆናል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ከማምረት ባለፈ በቴክኖሎጂ እና በሥልጠና በሌሎችም የእውቀት ማበልጸጊያ ዘርፎች ሠራተኞቻቸውን በክህሎት ማብቃት ቢችሉ ኢንዱስትሪው ላይ መነቃቃት ሊፈጠር እንደሚችል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።ይህም እንደ አምራች የሚነሱ የጥራትም ሆነ የብቃት ጥያቄዎችን በማስቀረት ሀገሪቱ በዘርፉ በጥራትም፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ጭምር ተወዳዳሪ እንድትሆን ያድርጋታል ሲሉ ገልጸዋል።
በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው አንጋፋ ስም ያለው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ ሲያብራሩም የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ላለፉት ስልሳ ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን በተለይም የጋርመንት እና የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ላቅ ያለ አበርክቶ እንደነበረውም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ በ1963 ዓ.ም ሲቋቋም በዲፕሎማ መርሀ ግብር አንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ብቻ ይዞ ነው።አሁን ስምንት የመጀመሪያ ዲግሪና /አንደር ግራጁየትድ/ ፕሮግራሞች እንዲሁም አስራ ሰባት ማስተርስ እና ሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች አሉት።ይህም በሙያው የተካኑ ሠራተኞችን ከማፍራት አኳያ ኢንስቲትዩቱ ያለው ድርሻ ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ተቋሙ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል በማቅረብ፣ ከፎርማን ጀምሮ እስከ ሥራ አስኪያጅ ድረስ ባለው ደረጃ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በማብቃት ለኢንዱስትሪው እድገት ሚናውን የተወጣ እና እየተወጣ ያለ ኢንስቲትዩት ነው፣ በፖሊሲ ደረጃም ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኢንስቲትዩቶች እና የማክሮ ባለሙያዎች እንዲሁም በዳይሬክተርነት ደረጃ ካሉ ኃላፊዎች ጋር የሥራ ጥምረቶችን በመፍጠር ሚናውን በማጠናከር ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ጋርመንት ሴክተር የሚባለውን እንደዚሁም በቆዳና የቆዳ ምርት ማዕከል በሚል የሚታወቀውን በማቋቋም እና ለእነሱም አስፈላጊውን ድጋፍ እና የምርት ሂደትን የሚያቀላጥፍ የሰው ኃይል በማቅረብ እየሠራ ነው።
የቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች 37 በመቶ የሚሆኑት በዘርፉ የራሳቸውን የሥራ እድል በመፍጠር ከራሳቸው አልፈው በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ታምራት ጠቁመዋል።የኢንስቲትዩቱ ምሩቃን ሥራ ፈጣሪዎች እስከ 300 እና 400 የሚደርሱ ሰዎችን ቀጥረው የሚያሠሩበት ሁኔታ እንዳለም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በቴክስታይል ኢንዱስትሪው ላይ ስላመጣው ለውጥ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳሉትም፤ ‹የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመደገፍ፣ ሃሳቡን በማራመድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲሠራ ቆይቷል።በኢትዮጵያ የተሠራ /ሜድኢን ኢትዮጵያ/ እና ሜድኢን ኤአይቴክስ በሚል ኤግዚብሽኖችን፣ ባዛሮችን በኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ ውስጥ በማዘጋጀት ሰዎች ምርቱን እንዲጠቀሙ ከማድረግ ጀምሮ ተሠርቷል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ ተመራቂ ተማሪዎቹን ጭምር የንቅናቄው ተሳታፊ በማድረግ በእውቀታቸው የድርሻቸውን እንዲያበርክቱ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።ምሩቃኑ ተጠቃሚዎች የኢትዮጵያን ምርት እንዲገዙ በማድረግ፣ የሀገሪቱን ምርቶች ለውጭ ገበያ ከማስተዋወቅ ከፍ ሲልም ዘወትር የሀገሪቱን ምቹ አልባሳት በማምረት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው በሚል አቋም ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ የራሱን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቴክስታይል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለው የቆየ ስም አመርቂ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።በተቀመጡ የለውጥ አቅጣጫዎች ተጨባጭ ለውጥ ሊመጣ የሚችልባቸው ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃግማ (ዶ/ር) ስለውይይቱና ስለሚመሩት ተቋም ሀገራዊ ፋይዳ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሁለት ተጠሪ ተቋማት አሉት።አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሲሆን ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የሚባለው ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለመካከለኛ እና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ በማድረግ፣ አቅጣጫ በማስቀመጥ ይሠራል፤ አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ደግሞ ከዚህ በፊት ስድስት በሚሆኑ የተለያዩ ኢንስቲትዩቶች ማለትም በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በምግብ እና መጠጥ፣ በካይዘን፣ በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ፣ በኮንስትራክሽን እና ኬሚካል ተዋቅሮ ይሠራ ነበር።ከሶስት ዓመት በፊት ደግሞ እነዚህን ወደ አንድ በማምጣት የመንግሥት አስፈጻሚ አካል በመሆን አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በሚል ተደራጅቶ በ504/2014 ደንብ ቁጥር ተግባርና ኃላፊነቱ ተለይቶ ወደሥራ ገብቷል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ኃላፊነት አምራች ዘርፉን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን መሥራት መሆኑን ገልጸው፣ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፤ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፖሊሲ ሃሳቦችን በማቅረብ ለዘርፉ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
የአስር ዓመት እቅድ ወጥቶለት እየተተገበረ በሚገኘው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ላይ ተሳታፊ በመሆን በጦርነት እና በኮረና እንዲሁም በመሰል ሁኔታዎች የተቀዛቀዘውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በማነቃቃት ብርቱ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ንቅናቄው ውጤቶች እያስመዘገበ መሆኑን አቶ ሚልኬሳ ጠቅሰው፣ ኤክስፖርት ቀደሞ ከነበረው የጨመረበትን፣ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ የተደረገ ግንዛቤ ማስጨበጥ ጥሬ ውጤት ያስገኘበትን ሁኔታም ለእዚህ በአብነት ጠቅሰዋል።
አምራች ዘርፉ በተኪ ምርት በስምንት ወራት ውስጥ ከሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶች መመረታቸውን ጠቅሰው፣ ከሶስት እና ከአራት ዓመት በፊት የአጠቃላይ አምራች ኢንዱስትሪዎቻችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ከነበረበት 48 በመቶ ከሶስት ዓመት ወዲህ በተደረገ ሥራ ወደ 60 ነጥብ በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ከውጪ ሲገቡ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት ጫማዎችን በሀገር ቤት በማምረት ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት እስከ መላክ መደረሱን አስታውቀው፣ ምግቦች፣ ቦርሳና የቆዳ ውጤቶችን በራስ ለራስ ማምረት ላይ በትኩረት በመሠራቱ ለውጥ እንደመጣም ገልጸዋል።
ከጨርቃ ጨርቅ ምርት ጋር በተያያዘም ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው፡ በማደራጀት፣ በማምረት፣ እንደዚሁም ከውጭ ሲገቡ የነበሩ እንደ ክር ያሉ ግብዓቶችን በሀገር ማምረትን ጨምሮ እንደ አግዋ ባሉ ክልከላዎች ኤክስፖርት እንዳይቆም፣ ሠራተኛ እንዳይበተን ቀድሞ ያልነበረን የገበያ አማራጭ በማምጣት ሰፊ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ልማቱን በቅርብ የመከታተል፣ የክህሎት እንዲሁም የአቅም ግንባታ /በሥራ ላይ ሥልጠና/ ሥራ መሥራት፣ በማምረት ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ማመንጨት፣ የመብራት እና የውሃ ችግሮች ሲፈጠሩ እልባት መስጠት፣ ከኢምባሲዎች ጋር በመገናኘት የውጭ ገበያዎችን ማመቻቸትና የመሳሰሉትን እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የቀድሞ የኢንስቲትዩቱ ምሩቃን የራሳቸውን ምርትና የሥራ ፈጠራ ለእይታ አቅርበው በመድረኩ ተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል።ምሩቃኑ አልባሳትን በማምረት፣ ዲዛይን በማድረግ፣ በመሸጥ እና የሠራ እድል በመፍጠር የተማሩትን ወደ ተግባር የለወጡበትን እውነታ አሳይተዋል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም