
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የኢኮኖሚዋ መሰረት ግብርና ቢሆንም ቅሉ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚያስችሏትን በርካታ የልማት መርሃ ግብሮችን ቀርፃ እየሰራች ትገኛለች። በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሃገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ለመሰለፍ የሚያንደረድሯትን አስቻይ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ሥራዎችን በማከናወን ሥራ ተጠምዳ ቆይታለች።
ይህ ጉዞ ግን በርካታ ፈተናዎችም ገጥመውት እንደነበር ይታወቃል። የመሰረተ ልማት አለመሟላትና የመሳሰሉት፣ ኮቪድ፣ ዓለማቀፋዊና ሃገራዊ ግጭቶች እንደ ዓለምአቀፍና የሀገሮች ጫናዎች ጀመረችው የሽግግር ጉዞ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድረው ቆይተዋል። በዚህ የተነሳም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከማምረት አቅማቸው በታች ለማምረት ተገደው እንደነበር ይታወቃል።
መንግሥት ባለፉት ዓመታት ኢንዱሰትሪው ያጋጠሙትን ፈተናዎች መቋቋም ያስችላሉ ያላቸውን የአሰራር ስርዓቶች ተግባራዊ አድርጓል። በተለይ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ፖሊሲና የሕግ ማሕቀፎችን በማሻሻል፤ የዘርፉን ተዋናዮች ሊያነቃቃና የሀገሪቱን ምርቶች ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ሊያሰፉ የሚችሉ መርሃግብሮችን ነድፎ ተግባራዊ አድርጓል።
ከእነዚህም የልማት መርሃግብሮች መካከል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዋነኛው ነው። ንቅናቄው ላለፉት ሶስት ዓመታት ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሀገራዊ ሥርዓት በመዘርጋት አምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማነትና ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ እውን መሆን ሲተገብር ቆይቷል።
አምራች ዘርፉ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በመለየት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃዎችን ለማምጣት ሰርቷል፤ ችግሮቹም በየደረጃው ባለቤት ኖሯቸው እንዲፈቱ ጥረት ተደርጓል። ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ዘርፉ የበኩሉን አስተዎፅዖ እንዲያደርግ ማስቻል፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማሳደግ ምቹና አስቻይ ሁኔታዎች በመፍጠር አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀም በማሻሻል እና ምርታማነትን በማሳደግ የአምራች ኢንዱስትሪን ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ማረጋገጥን ታሳቢ በማድረግ ንቅናቄው እየተተገበረ ይገኛል።
እንደሀገር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲጎለብትና ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተቀናጅተውና ተናበው መስራት ይኖርባቸዋል። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ከፌደራል ተቋማት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉባቸው አምስት ክላስተሮች እንዲዋቀሩ ተደርገዋል። የእነዚህ ክላስተሮች መደረጃት ዋነኛ ዓላማም ሁሉም ድርሻውን ወስዶ በኃላፊነት እንዲሰራ ከማድረግ በዘለለ በየጊዜው ተገናኝተው ሥራዎችን እንዲከታተሉ፤ ችግሮች ተለይተው እንዲፈቱ በማድረግ ለዘርፉ ተዋናዮች ምቹ መደላደል መፍጠር ነው።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደው የአምስቱ ክላስተሮች የጋራ ውይይት መድረክም የዚሁ አካል ነበር። በመድረኩ የንቅናቄው የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በንቅናቄው የሁለት ዓመታት ጉዞ በርካታ አንኳር ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ተቋማዊ አደረጃጀት መፈጠር ዋነኛው ነው። በእነዚህ በፌደራል እንዲሁም በክልልና የከተማ አስተዳደሮች በየደረጃው መዋቅራዊ አደረጃጀት በመፍጠር ንቅናቄውን ተቋማዊ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።
ቅንጅትና ተናቦ የመሥራት ባሕልን በማሳደግ፤ በንቅናቄው የአጭር ዓመታት ጉዞ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማሻሻያውን ጨምሮ በርካታ ስትራቴጂዎችና የሕግ ማሕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ መሸጋገራቸውን አያና/ዶ/ር/ ያመለክታሉ። በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዓለም አቀፍዊነት በመጠበቅ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሀገር ውስጥ አምራቾችን በመደገፍ፣ የውጪ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ ሕብረተሰቡ የሀገሩን ምርት እንዲያውቅና እንዲሸምት በማድረግ ውጤታማ ሥራ መከናወናቸውን ይጠቁማሉ።
‹‹በንቅናቄው ከተመዘገቡ ውጤቶች መካከል የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ብድር አቅርቦት በአማካይ 40 በመቶ እድገት ሲኖረው፤ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎቹ ደግሞ በአማካይ ከ75 በመቶ በላይ እድገት ያሳየበት ሁኔታ ይጠቀሳል›› ይላሉ። ለአምራች ኢንዱስትሪው የቀረበ ግብዓትን በተመለከተ በ2016 በጀት ዓመት 10 ወራት ውስጥ 11 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ቶን የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ከቀደመው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በአንድ ነጥብ 77 ሚሊየን ቶን ብልጫ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ አያና (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶችና ምርምሮች ወደ ምርት የገቡ ምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአማካይ 23 በመቶ እድገት አሳይተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ለ490 ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ቆጣሪ፣ የመስመርና የትራንስፎርመር ችግራቸው እንዲፈታላቸው ተደርጓል። በተመሳሳይ በ2017 በጀት ዓመት በስምንት ወራት የቆጣሪ፣ የመስመርና የትራንስፎርመር ችግራቸው የተፈታላቸው ደግሞ በድምሩ 522 ናቸው።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት አራት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ 236ሺ 934 ቋሚ የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ ካለፈው ዓመትም በ6 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማሳየቱን አያና (ዶ/ር) በሪፖርቱ አመላክተዋል።
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አፈፃፀምን በተመለከተ ‹‹በ2014 በጀት ዓመት 94 የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ የተቻለ ሲሆን፣ በ2016 ደግሞ 220 መሳብ ተችሏል›› ሲሉ አብራርተዋል። ይህም በየዓመቱ በአማካይ 50 በመቶ እድገት እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ደግሞ በ2014 በጀት ዓመት 240፣ በ2016 ደግሞ 889 መሳብ መቻሉን አስታውቀዋል። ይህም በየዓመቱ በአማካይ ከእጥፍ በላይ እድገት ማሳየቱን ነው ያስረዱት።
ከተጀመረ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ለማሳደግ ሰፊ ርብርብ መደረጉንም አስተባባሪው ጠቅሰዋል። በዚህም በ2ዐ13 ከነበረበት 46 በመቶ በ2ዐ17 ግማሽ ዓመት ወደ 61 በመቶ መድረሱን ገልጸው፣ ከ2014 እስከ 2017 በጀት ግማሽ ዓመት በአማካይ በየዓመቱ አምስት ነጥብ አንድ በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩልም አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር የሚገቡትን ምርቶች በመተካት ለሀገር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግም ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስተባባሪው አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶች አንጻራዊ የምርት ብልጫ እና ተወዳዳሪነት እንዲኖራቸው አቅም በመፍጠር፣ ከውጪ የሚገቡ ስትራቴጂክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት፣ የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ለማጥበብ የሚያስችል ተግባራትም ተፈጽመዋል።
በዚህም በ2016 በጀት ዓመት ሁለት ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬን በተኪ ምርት ማዳን ተችሏል። በ2017 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ደግሞ ሁለት ነጥብ 78 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች ተመርተዋል። በአጠቃላይ በዘርፉ ስትራቴጂክ ሥራ ተኪ ምርቶችን ለይቶ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተካሄዱ ጅምር ጥረቶች አበረታች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ማየት እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት።
እንደ አስተባባሪው ገለፃ፤ ባለፉት ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና በጥራት የማምረት አቅም ለማጎልበትም የተቀናጀ ሥራ ተሰርቷል። ይህም በመሆኑ ሀገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶችም ሆኑ መዳረሻ ሀገራት መጠን እየጨመረ መጥቷል።
በ2017 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 95 ሺ 167 ነጥብ 40 ቶን የምርት መጠን መላክ ተችሏል። ይህም ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከቀረበው ጋር ሲነፃፀር የ26 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እድገት ተመዝግቦበታል። ከውጭ ምንዛሬ ግኝትን አንፃርም በአጠቃላይ 204 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ይህም ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ጋር ሲነፃፀር የ12 በመቶ ብልጫ አለው።
አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባሮች ዘርፉ በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት ከአራት ነጥብ ስምንት ከመቶ እድገት፣ ወደ 10ነጥብ አንድ በመቶ ማደጉን አስተባባሪው ይጠቅሳሉ። ይህም ዘርፉ በየዓመቱ በአማካይ 44 ነጥብ አራት በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ መምጣቱን እንደሚያመላክት አያና (ዶ/ር) ይገልፃሉ። አምራች ኢንዱስትሪው በ2014 እና በ2015 በጀት ዓመት ለኢኮኖሚው ያበረከተው አስተዋጽኦ ተመሣሣይ ቢሆንም፣ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸሙ ካለፉት ዓመታት አንፃር ሲታይ የአንድ ነጥብ አምስት በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ወደ ስድስት ነጥብ ስምንት በመቶ ማደጉን ይጠቁማሉ።
ይህን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከየትኛውም ጊዜ በላቀ በቅንጅትና በባለቤትነት በመስራታቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ከተገኘው ውጤት በላይ ማስመዝገብ የሚቻልበት እድል እንደነበርም ተናግረዋል።
በተለይም ደግም አንዳንድ አመራሮችና ተቋማት ላይ መንጠባጠብ መታየቱን አመልክተው፣ በመሆኑም ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ለምታደርገው ጉዞ መሳለጥ ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልም ይህን የሚያጠናክር ሀሳብ ነው የጠቀሱት። የአምራች ኢንዱስትሪው እድገት የሁሉም አካላት ድጋፍ ካልታከለበት ሊሳካ እንደማይቻል ተናግረው፣ ቅንጅቱ ሊጠናከር እንደሚገባ ይናገራሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ዘርፍን ለማሳደግ የተያዘው ሀገራዊ ግብ የሁሉም ተቋማት ድጋፍ ካልታከለበት ሊሳካ አይችልም። ንቅናቄው ከተጀመረበት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ለእነዚህ ሥራዎች መሳካት የክላስተር ኮሚቴዎች ሚና ከፍተኛ ነው።
የዘርፉ ባህሪ የሌሎችን ድጋፍና መናበብ እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ በንቅናቄው ከተለዩ ጉዳዩች መካከል የተቋማት የቅንጅት ክፍተት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። አምራች ዘርፉ ግብዓት፣ ፋይናንስ፣ መሠረተ ልማት፣ በአቅም ግንባታና በምርምር ካልተደገፈ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ካልመጡ የዘርፉ እድገት እውን አይሆንም ሲሉም አስገንዝበዋል። የግሉ ዘርፍ የሚደገፍበት ሥርዓትና ጠንካራ ግንኝነት ካልተፈጠረም እንደ ሀገር ተወዳዳሪ መሆን አዳጋች ነው ብለዋል።
“እነዚህ ሥራዎች ሁሉ በአንድ ተቋም ጥላ ስር ሊገኙ የሚችሉ አይደሉም፤ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃሉ” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዘላቂነት ካልተፈታና የሥራ እድል መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ አስተማማኝ ሰላም ማምጣት እንደማይቻልም አስታውቀዋል።
ለሠላም መናጋት ትልቁ ችግር ለዜጎች ዘላቂ የሥራ እድል መፍጠር አለመቻሉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ አምራች ዘርፍ የሥራ እድል ከሚፈጠርባቸው ዘርፎች መስኮች መካከል ዋነኛው መሆኑንም አመልከተዋል፤ የዘርፉ እድገት መጓተት በሥራ እጦት ለሚፈጠር የሰላም እጦት እንዲቀንስ የሚያደርግ እንደሆነም ያስገነዝባሉ።
ከግብርና ተነስተን ማኑፋክቸሪንግን ሳይነካ አገልግሎት ዘርፍ የማደግ ዝንባሌ እንደሚስተዋል አቶ መላኩ ጠቅሰው፤ በዚህም ጤናማ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደማይመጣ አመልክተዋል። በመሆኑም አምራች ዘርፉ እንዲያድግ ከተፈለገ ሁሉም ሚናውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው እስከ 2013 ዓ.ም የመጣንበት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብዙ ውጣ ውረድ የነበረበት እንደበረበት አስታውሰው፣ ኋላ ደግሞ ጦርነት፣ ኮቪድና ዓለም አቀፍ ጫናዎች ታክለውበት ዘርፉ ወደ ከፋ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶት እንደነበር አመልክተዋል።
የንቅናቄው መጀመር ዘርፍን ከነበረበት ድባቴ አስወጥቶ አዲስ ተስፋ እንዲታይና የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ተከፍተው ወደ ማምረት እንዲገቡ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲመጡ ለማድረግ ማስቻሉን ያብራራሉ። በዚህም በአጭር ጊዜያት ውስጥ 469 ሚሊዮን ዶላር ብድር በሊዝ ፋይናንስ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ማቅረብ መቻሉን ይጠቁማሉ።
ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ ንቅናቄው መጀመሩን ተከትሎ 116 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል። ሰባት ሺ 525 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ዘርፉን ተቀላቅለዋል። ሥራ አቁመው የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎችንም ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል። የማምረት አቅም አጠቃቀምንም ከ46 በመቶ ወደ 61 በመቶ ማድረስም ተችሏል።
ይህም በመሆኑ ሌላ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ሳይፈጠሩ ዘርፉ በአገራዊ ጥቅል ምርት ውስጥ ያለውን ድርሻ በእጥፍ ማሳደግ የሚቻልበት እድል መፈጠሩንም ነው የተናገሩት።
በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ትስስራቸውን ማጠናከርና ተናበው መስራት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። ሁሉም በተናጠል የተሰጠውንም የሥራ ድርሻ በኃላፊነት መስራት እንደሚጠበቅበት ያሳስባሉ።
‹‹በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ የማምጣቱ ሥራ ከሁላችንም የሚጠበቅ፤ በሁላችንም የሚወሰን ነው›› ያሉት አቶ መላኩ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካል የየራሱን የቤት ሥራ ወስዶ ኢትዮጵያን ለመሻገር ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ያመለክታሉ።
አሁን ያሉትን ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ጠንካራ ኢኮኖሚ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ይህም ለጠንካራ ሀገር፤ ለጠንካራ ዲሞክራሲ፤ እና ዘላቂነት ላለው ሰላም ዋስትና መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹ይህንን ሊያመጡ የሚችሉ ከዘርፋችን የሚጠበቁ ሥራዎችን መስራት ይጠበቅብናል›› ሲሉም አስገንዝበዋል።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም